ምዕራፍ 10
የኢየሱስ ቤተሰብ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ
የ12 ዓመቱ ኢየሱስ ለመምህራኑ ጥያቄ አቀረበ
ኢየሱስ ይሖዋን “አባቴ” ብሎ ጠራው
ጸደይ ደርሷል። በዚህ ወቅት ዮሴፍና ቤተሰቡ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ሆነው በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዛሉ። ወደዚያ የሚሄዱት ሕጉ በሚያዘው መሠረት ፋሲካን ለማክበር ነው። (ዘዳግም 16:16) ከናዝሬት ተነስቶ ኢየሩሳሌም ለመድረስ 120 ኪሎ ሜትር ገደማ መጓዝ ይጠይቃል። ይህ ወቅት እንቅስቃሴ የበዛበትና አስደሳች ነው። የ12 ዓመቱ ኢየሱስ በዓሉን እንዲሁም ወደ ቤተ መቅደሱ በድጋሚ የሚሄድበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቀ ነው።
ለኢየሱስና ለቤተሰቡ ፋሲካ የአንድ ቀን በዓል አይደለም። የፋሲካ ማግስት፣ ሰባት ቀን የሚወስደው ‘የቂጣ በዓል የሚከበርበት የመጀመሪያ ቀን’ ነው። (ማርቆስ 14:1) ይህ በዓል፣ የፋሲካ በዓል ክፍል እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። ቤተሰቡ ናዝሬት ከሚገኘው መኖሪያቸው ተነስተው የሚያደርጉት ጉዞ፣ ኢየሩሳሌም የሚቆዩባቸው ቀናት እና የመልስ ጉዞው በአጠቃላይ ሁለት ሳምንት ገደማ ይወስዳል። ሆኖም በዚህ ዓመት ከኢየሱስ ጋር የተያያዘ አንድ ሁኔታ በመከሰቱ ምክንያት ጉዞው ከዚህ የበለጠ ጊዜ ወስዶባቸዋል። ሁኔታው የታወቀው ከኢየሩሳሌም ተነስተው ጉዞ ከጀመሩ በኋላ ነው።
ዮሴፍና ማርያም፣ ኢየሱስ ወደ ሰሜን አብረዋቸው ከሚጓዙት ወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር መስሏቸዋል። ሆኖም ምሽት ላይ ሲያርፉ ኢየሱስን ሊያገኙት አልቻሉም። በመሆኑም አብረዋቸው በሚጓዙት ሰዎች መካከል ፈለጉት፤ እሱ ግን እዚያ የለም። ልጃቸው ሊገኝ አልቻለም! ስለዚህ ዮሴፍና ማርያም እሱን ለመፈለግ እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
ቀኑን ሙሉ ቢፈልጉትም ሊያገኙት አልቻሉም። በሁለተኛውም ቀን አልተገኘም። በመጨረሻም በሦስተኛው ቀን ልጃቸውን ቤተ መቅደሱ ውስጥ አገኙት። ከቤተ መቅደሱ በርካታ አዳራሾች በአንዱ ውስጥ በአይሁድ መምህራን መካከል ተቀምጧል። ኢየሱስ መምህራኑን እያዳመጠና እየጠየቃቸው ነው፤ እነሱም በመረዳት ችሎታው ተደንቀዋል።
ማርያም “ልጄ፣ ምነው እንዲህ አደረግከን? እኔና አባትህ እኮ በጣም ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” ስትል ጠየቀችው።—ሉቃስ 2:48
ኢየሱስ ግን የት ሊያገኙት እንደሚችሉ ባለማወቃቸው ተገረመ። “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መሆን እንደሚገባኝ አታውቁም?” አላቸው።—ሉቃስ 2:49
ኢየሱስ ከወላጆቹ ጋር ከተገናኘ በኋላ በናዝሬት ወደሚገኘው ቤታቸው አብሯቸው ተመለሰ፤ እንደ ወትሮውም ለወላጆቹ መገዛቱን ቀጠለ። በአካልና በጥበብ እያደገ ሄደ። ገና ልጅ ቢሆንም እንኳ በአምላክና በሰው ፊት ሞገስ አግኝቷል። በእርግጥም ኢየሱስ ከልጅነቱ ጀምሮ መንፈሳዊ ነገሮችን በመከታተል ብቻ ሳይሆን ለወላጆቹ አክብሮት በማሳየት ረገድም ጥሩ ምሳሌ ትቷል።