ምዕራፍ 41
አምላክን የሚያስደስቱ ልጆች
በምድር ላይ ከሁሉም ልጆች ይበልጥ ይሖዋን በጣም ያስደሰተው ልጅ ማን ይመስልሃል?— የራሱ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ በሰማይ የሚኖረውን አባቱን ለማስደሰት ስላደረጋቸው ነገሮች እስቲ እንወያይ።
የኢየሱስ ቤተሰብ ይኖርበት የነበረው ቦታ ውብ የሆነው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ከሚገኝበት ከኢየሩሳሌም የሦስት ቀን መንገድ ያህል ይርቅ ነበር። ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን ‘የአባቴ ቤት’ በማለት ጠርቶታል። እሱና ቤተሰቡ ፋሲካን ለማክበር በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር።
ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ በነበረበት ጊዜ ቤተሰቡ በሙሉ የፋሲካን በዓል ካከበሩ በኋላ ወደ ቤታቸው ለመመለስ ጉዞ ጀመሩ። የኢየሱስ ቤተሰቦች ወደሚያድሩበት ቦታ ሲደርሱ ኢየሱስ ዘመዶቻቸው ጋርም ሆነ ጓደኞቻቸው ጋር እንደሌለ ተረዱ። ስለዚህ ማርያምና ዮሴፍ ወዲያውኑ ኢየሱስን ለመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ። ኢየሱስ የት የነበረ ይመስልሃል?—
ኢየሱስን ቤተ መቅደሱ ውስጥ አገኙት። እዚያ ያሉትን አስተማሪዎች እያዳመጣቸውና ጥያቄ እየጠየቃቸው ነበር። እነሱም ጥያቄ ሲያቀርቡለት ይመልስላቸው ነበር። አስተማሪዎቹ በሚሰጠው አስደናቂ መልስ ተገረሙ። አምላክ በልጁ የተደሰተው ለምን እንደሆነ አሁን ገባህ?—
ማርያምና ዮሴፍ ኢየሱስን ፈልገው ሲያገኙት በጣም ደስ እንዳላቸው ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ግን ምንም አልተጨነቀም ነበር። በቤተ መቅደሱ ውስጥ መሆን ጥሩ ነገር እንደሆነ ያውቅ ነበር። ስለዚህ “በአባቴ ቤት መሆን እንደሚገባኝ አታውቁም?” በማለት ጠየቃቸው። ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ የአምላክ ቤት እንደሆነ ያውቅ ስለነበር እዚያ መሆን ያስደስተው ነበር።
ከዚያ በኋላ ማርያምና ዮሴፍ 12 ዓመት የሆነውን ኢየሱስን ይዘውት ወደ ቤታቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። ኢየሱስ ለወላጆቹ ምን ዓይነት ጠባይ ያሳይ የነበረ ይመስልሃል?— መጽሐፍ ቅዱስ “እንደ ወትሮውም ይታዘዛቸው ነበር” በማለት ይነግረናል። ይህ ምን ማለት ይመስልሃል?— ይህ ማለት ኢየሱስ ለወላጆቹ ታዛዥ ነበር ማለት ነው። አዎ፣ ይህ ከጉድጓድ ውኃ እንደ መቅዳት ያሉ የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራት ሊጠይቅበት ቢችልም እንኳ ወላጆቹ ያዘዙትን ሁሉ ያደርግ ነበር ማለት ነው።—ሉቃስ 2:41-52
እስቲ አስበው:- ኢየሱስ ፍጹም የነበረ ቢሆንም እንኳን ፍጹም ላልሆኑ ወላጆቹ ይታዘዝ ነበር። ይህ አምላክን አስደስቶታል?— እንዳስደሰተው ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም የአምላክ ቃል ልጆችን “ለወላጆቻችሁ ታዘዙ” በማለት ይመክራቸዋል። (ኤፌሶን 6:1) አንተም ኢየሱስ እንዳደረገው ለወላጆችህ የምትታዘዝ ከሆነ አምላክን ታስደስተዋለህ።
አምላክን ልታስደስት የምትችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ስለ እሱ ለሌሎች መናገር ነው። አንዳንድ ሰዎች ይህ ልጆች ሊሠሩት የሚገባ ሥራ አይደለም ይሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሰዎች፣ ትንንሽ ወንዶች ልጆችን ስለ አምላክ እንዳይናገሩ ለመከልከል በሞከሩ ጊዜ ኢየሱስ ‘“አምላክ ከትንንሽ ልጆች አፍ ምስጋና ያዘጋጃል” የሚለውን ቃል በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ አላነበባችሁም?’ ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 21:16) ስለዚህ ከልብ ፍላጎቱ ካለን ሁላችንም ስለ ይሖዋም ሆነ እሱ እንዴት ያለ አስደናቂ አምላክ እንደሆነ ለሌሎች ልንነግራቸው እንችላለን። እንዲህ ካደረግን ደግሞ አምላክን እናስደስተዋለን።
ለሌሎች ሰዎች ስለ አምላክ ልንናገረው የምንችለውን ነገር የምንማረው ከየት ነው?— በቤታችን ከምናደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነው። ይሁን እንጂ የአምላክ ሕዝቦች ለማጥናት በሚሰበሰቡበት ቦታ ይበልጥ መማር እንችላለን። ነገር ግን የአምላክ ሕዝቦች እነማን መሆናቸውን ለይተን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?—
ሰዎቹ በስብሰባዎቻቸው ላይ የሚያደርጉት ምንድን ነው? የሚያስተምሩት ነገር በእርግጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል? መጽሐፍ ቅዱስን እያነበቡ ይወያዩበታል? አምላክን ማዳመጥ የምንችለው በዚህ መንገድ ነው፤ አይደለም እንዴ?— በመሆኑም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የአምላክ ቃል የሚነገርባቸው ቦታዎች መሆን አለባቸው፣ አይደል?— ነገር ግን ሰዎቹ መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው መሠረት መኖር እንደማያስፈልግህ የሚናገሩ ቢሆኑስ? እነዚህ ሰዎች የአምላክ ሕዝቦች ናቸው ልትል ትችላለህ?—
ሌላም ልናስብበት የሚገባ ነገር አለ። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ሕዝቦች “ለስሙ የሚሆኑ ሰዎች” እንደሆኑ ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 15:14) የአምላክ ስም ደግሞ ይሖዋ ስለሆነ ሰዎቹ የሚያመልኩት ይሖዋን እንደሆነና እንዳልሆነ ልንጠይቃቸው እንችላለን። የሚያመልኩት ይሖዋን ካልሆነ እነዚህ የአምላክ ሕዝቦች እንዳልሆኑ እናውቃለን። በተጨማሪም የአምላክ ሕዝቦች ለሌሎች ስለ አምላክ መንግሥት ይናገራሉ። እንዲሁም ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር ትእዛዙን በመጠበቅ ያሳያሉ።—1 ዮሐንስ 5:3
እነዚህን ሁሉ ነገሮች የሚያደርጉ ሰዎች የምታውቅ ከሆነ አምላክን ለማምለክ ከእነሱ ጋር መሰብሰብ ይኖርብሃል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተህ በደንብ ማዳመጥ እንዲሁም ጥያቄዎች ሲቀርቡ መልስ መስጠት ይኖርብሃል። ኢየሱስ በአምላክ ቤት በነበረበት ጊዜ ያደረገው ይህንኑ ነው። አንተም እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ልክ እንደ ኢየሱስ አምላክን ማስደሰት ትችላለህ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አምላክን ያስደሰቱ ሌሎች ልጆች ታስታውሳለህ?— ጢሞቴዎስ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ነው። የጢሞቴዎስ አባት በይሖዋ አያምንም ነበር። እናቱ ኤውንቄና አያቱ ሎይድ ግን በይሖዋ ያምኑ ነበር። ጢሞቴዎስ እነሱን በማዳመጥ ስለ ይሖዋ ተማረ።
ጢሞቴዎስ አድጎ ወጣት በነበረበት ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ እሱ ወደሚኖርባት ከተማ መጥቶ ነበር። ጢሞቴዎስ ይሖዋን ለማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ጳውሎስ ተገነዘበ። ስለዚህ ጢሞቴዎስን ከእሱ ጋር ሆኖ አምላክን ይበልጥ እንዲያገለግል ጋበዘው። በሄዱበት ሁሉ ለሰዎች ስለ አምላክ መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ይናገሩ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 16:1-5፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:14, 15
ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አምላክን እንዳስደሰቱ የተጠቀሱት ልጆች ወንዶች ብቻ ናቸው?— በጭራሽ። አምላክን ስላስደሰተች አንዲት እስራኤላዊት ልጅ የሚገልጸውን ታሪክ እንመልከት። እሷ በኖረችበት ዘመን የሶርያ ሕዝብ የእስራኤል ሕዝብ ጠላቶች ነበሩ። አንድ ቀን ሶርያውያን ከእስራኤላውያን ጋር ከተዋጉ በኋላ ይህችን ልጅ ማርከው ወሰዷት። ከዚያም የሠራዊት አለቃ ወደሆነ ንዕማን ወደሚባል ሰው ቤት ተወሰደች። እዚያም የንዕማን ሚስት አገልጋይ ሆነች።
ንዕማን ደግሞ የሥጋ ደዌ በሽታ ይዞት ነበር። ማንም ሐኪም ሊፈውሰው አልቻለም። ይህች እስራኤላዊት ልጅ ግን የአምላክ ልዩ አገልጋይ የሆነ አንድ ነቢይ ንዕማንን ሊፈውሰው እንደሚችል ታምን ነበር። በእርግጥ፣ ንዕማንና ሚስቱ ይሖዋን አያመልኩም ነበር። ታዲያ ይህች ልጅ የምታውቀውን ነገር ልትነግራቸው ይገባል? አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?—
ልጅቷ ‘ንዕማን በእስራኤል ወደሚገኘው ነቢይ ቢሄድ ከሥጋ ደዌው ይፈወስ ነበር’ አለች። ንዕማን ልጅቷ ያለችውን ነገር ሰምቶ ወደ ይሖዋ ነቢይ ሄደ። ንዕማን ነቢዩ የነገረውን ነገር ሲያደርግ ተፈወሰ። ይህ ደግሞ ንዕማን እውነተኛውን አምላክ እንዲያመልክ አድርጎታል።—2 ነገሥት 5:1-15
አንተም እንደዚች ልጅ አንድ ሰው ስለ ይሖዋና እሱ ማድረግ ስለሚችለው ነገር እንዲማር መርዳት ትፈልጋለህ?— ልትረዳው የምትችል ሰው ይኖር ይሆን?— እርግጥ ነው፣ ልትረዳቸው የምትፈልጋቸው ሰዎች መጀመሪያ ላይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ላይሰማቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ስለሚያደርጋቸው ጥሩ ነገሮች ልትነግራቸው ትችላለህ። እነሱም ሊሰሙህ ይችላሉ። ይህ ደግሞ አምላክን እንደሚያስደስተው እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።
ልጆች አምላክን በማገልገል ደስታ እንዲያገኙ የሚያበረታቱ ተጨማሪ ሐሳቦች በሚከተሉት ጥቅሶች ላይ ይገኛሉ:- መዝሙር 122:1፤ 148:12, 13፤ መክብብ 12:1፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:12፤ ዕብራውያን 10:23-25