ጥናት 15
የአድማጮችህን ልብ መንካት
1–4. አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ለልብ ከፍተኛ ቦታ የምንሰጠው ለምንድን ነው?
1 ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹን የሰበከላቸው ሰዎች ‘የልባቸው ዓይን እንዲበራ’ ወደ ይሖዋ መጸለዩን አላቋረጠም ነበር። (ኤፌ. 1:16–18) ጳውሎስ የጸለየው አእምሮአቸው ሳይሆን ልባቸው እንዲበራ ነበር። እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ውጤታማ አስተማሪዎችና ተናጋሪዎች ለመሆን ከፈለግን ይህን ጉዳይ መረዳት ያስፈልገናል።
2 የታላቁ የልብ መዛኝ ታማኝ አገልጋዮች የተናገሩትን የይሖዋ መንፈስ በጳውሎስ በኩል ይገልጥ ነበር። (ምሳሌ 21:2) ለምሳሌ ያህል ንጉሥ ዳዊት በእርጅናው ዘመን ለንግሥናው ወራሽ የሚከተለውን ጥሩ ምክር ሰጥቶ ነበር። “ልጄ ሰሎሞን ሆይ፣ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፣ የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃልና የአባትህን አምላክ እወቅ፤ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው፤ ብትፈልገው ታገኘዋለህ፤ ብትተወው ግን ለዘላለም ይጥልሃል።” (1 ዜና 28:9) ፈጣሪን የሚያስደስተው ከልብ የቀረበ እውነተኛ አምልኮ ነው።
3 ታላቁ ዳዊት ኢየሱስ ክርስቶስም የሚከተለውን በመናገር ተመሳሳይ የሆነ የጥበብ ምክር ሰጥቷል:- “በፍጹም ልብህ፣ በፍጹምም ነፍስህ፣ በፍጹምም አሳብህ፣ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ።” (ማር. 12:28–30) አምላክን በማስደሰት ረገድ በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር በዚያ ፍጡር ልብ ውስጥ ያለው ነገር ነው። ይህን ስንገነዘብ በምሳሌ 4:23 ላይ የሚገኘው ቃል የጠለቀ ትርጉም እንዳለው እንረዳለን። “ልብህን ከሁሉ በላይ አብልጠህ ጠብቅ፤ ምክንያቱም ልብ የሕይወት ምንጭ ነው።” የ1980 ትርጉም
4 ይህ የእያንዳንዱን አድማጭ ልብ የመንካት ጉዳይ የአምላክን መንግሥት ምሥራች የሚሰብኩትንና የሚያስተምሩትን ሁሉ ሊያሳስብ የሚገባ ጉዳይ ነው። ክርስቲያን ወላጅ ልጁን ሲያስተምር፤ እንዲሁም ምሥራቹን ለሚሰሙ ሰዎች የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚመራ አገልጋይ የሚያስተምራቸውን ሰዎች ልብ እንዴት እንደሚነካ በጥብቅ ማሰብ ይኖርበታል። መድረክ ላይ ወጥተው የሚያስተምሩ ወንድሞች በሙሉ ስለዚህ ጉዳይ ማሰብ ይገባቸዋል። በእነዚህ ሁኔታዎች ሁሉ ውድ የሆነውን የእውነት መልእክት ወደ ሌሎች አእምሮ ለማስተላለፍ እንጥራለን። ይሁን እንጂ ማድረግ የሚኖርብን ከዚህ የበለጠ ነገር አለ። የሰዎችን ልብ ለመንካት እንፈልጋለን። ‘ልባቸውን ለታላቁ ሰማያዊ አባት እንዲሰጡ’ ለመገፋፋት እንፈልጋለን። — ምሳሌ 23:26
5, 6. በሌሎች ሰዎች አእምሮ ውስጥ እውቀት ከማስተላለፍ የበለጠ ነገር ማድረግ የሚገባን ለምንድን ነው?
5 አእምሮንና ልብን መለየት። ጥሩ ብቃት ያለው የምሥራቹ አስተማሪ ወደ አድማጮቹ አእምሮ እውቀት ማስተላለፍ ይችላል። ተማሪው ራሱ ብዙም ሳይቆይ የተማራቸውን ነገሮች ለመድገምና ለማብራራት ይችላል። በሚገባ ስለተረዳው በአእምሮው ውስጥ ተቀርጿል ማለት ነው። ይሁን እንጂ በተማረው ነገር ምን ያደርግበታል? የሚል ጥያቄ ይነሣል። ፍላጎቱ እውቀት ለማግኘት ብቻ ነው ወይስ ያገኘው እውቀት ለድርጊት የሚያነሳሳው ነው?
6 የልብ ጉዳይ የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፤ ምክንያቱም ልብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከግፊትና ለድርጊት ከመነሳሳት ጋር ይዛመዳል። እውነተኛ የአምላክ አገልጋይ የሆነ ሰው በመንፈስ አነሣሽነት የጻፈ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንዳለው “አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ አኖራለሁ” ይላል። (መዝ. 119:11 የ1980 ትርጉም ) አንድ ሰው ስለ አምላክ ዓላማ የሚገልጹ አስደናቂ እውቀቶችን ወደ አእምሮው ሊያስገባ ይችላል። በጣም ግሩም ከሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ብዙዎቹን በሚገባ ሊረዳ ይችላል። ሆኖም እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶችና እውቀቶች ወደ ልቡ አስገብቶ በሕይወቱ ውስጥ በሥራ ላያውላቸው ይችላል። አጽናኙን የአምላክ ቃል እውነት የሰሙ ሰዎች ብዙ ናቸው። የሰሙትን በሥራ ላይ የማዋል ወይም ለሌሎች የማሰማት ጉዳይ ሲመጣ ግን ይህን ለመሰለው ነፍስ አድን ሥራ የሚያነሳሳ ልብ ይጎድላቸዋል።
7, 8. በልብና በአእምሮ መካከል ያለውን ልዩነት አስረዳ።
7 አእምሮ የግድ መረጃዎችን ተቀብሎ ማብላላት ይኖርበታል። የሐሳብ መፍለቂያና የእውቀት ማገናዘቢያ ማዕከል አእምሮ ነው። የተለያዩ መረጃዎችን አሰባስቦ በምክንያታዊ አስተሳሰብ አንድ ዓይነት ውሳኔ ላይ ይደርሳል። አእምሮ አስደናቂ በሆነ መንገድ ከልብ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ዝምድና እንዳለው ቅዱሳን ጽሑፎች ያመለክታሉ። ልብ ከፍቅርና ከፍላጎት ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ ስላለው በጣም አስፈላጊ የሆነ የሥራ ድርሻ አለው። ልብ ለመላው የሕይወት አካሄድ የሚሰጠው አመራር ለተመልካቾች ሁሉ ግልጽ ሆኖ ይታያል። ግለሰቡ ከውስጡ ምን ዓይነት ሰው መሆኑ እያደር ይገለጣል። ይሖዋ ግን ሁልጊዜም ቢሆን ‘በሰው ልብ ውስጥ ያለውን’ ያውቃል። — 1 ጴጥ. 3:3, 4
8 ልብ ከምክንያታዊ አስተሳሰብ ይልቅ ለስሜት ወይም ለፍላጎት የሚያደላ ግፊት በመስጠት አእምሮ የደረሰበትን መደምደሚያ ሊጥስ የሚችልበት ጊዜ አለ። አንድ ሰው በይሖዋ ዓይን ትክክል የሆነውን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ይህን ያወቀውን የመከተል ፍላጎት በልቡ ውስጥ ሊኖረው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልብ ‘እቅድ እንደሚያወጣ’ የሚናገረው ይህን የመሰለ ከተለያዩ አማራጭ መንገዶች አንዱን የመከተል ችሎታ ስላለው ነው። (ምሳሌ 19:21፤ 16:9) ሰዎች አስገዳጅ የሆነ ምክንያት ወይም ሁኔታ ካላጋጠማቸው በስተቀር ልባቸውን የሚማርከውን ነገር ያደርጋሉ። በተለይ ይህ ነገር እውነት የሚሆነው ሥነ ምግባርን በሚመለከቱና መንፈሳዊ በሆኑ ጉዳዮች ረገድ ነው። — ማቴ. 5:28
9, 10. የአንድን ተማሪ ልብ ለመንካት የሚረዳን ነገር ምንድን ነው?
9 ልብን መንካት። ታዲያ አንድ ክርስቲያን አስተማሪ የሰዎችን ልብ የሚነካው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ አድማጮች የተማሩትን ነገር በአድናቆት እንዲያሰላስሉ በማበረታታት ነው። የኢየሱስ ሥጋዊ እናት ስለነበረችው ስለ ማርያም “ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር” እንደተባለ አስታውስ። (ሉቃስ 2:51) በአእምሮዋ ማስታወስዋ ባይቀርም ታሪኩ “በአእምሮዋ ታስታውስ ነበር” እንዳላለ ልብ በል። የፍቅርና የስሜት ግፊት መቀመጫ በሆነው በልብዋ ውስጥ ስላስቀመጠችው የኋላ ኋላ የታመነች ክርስቲያን ለመሆን ችላለች። ዛሬም ተማሪዎች እውነትን ወደ ልባቸው እንዲያስገቡ ለማድረግ በቂ ጊዜ ወስደህ ቁልፍ የሆኑ ነጥቦችን አጥጋቢ በሆነ መንገድ አብራራ። በአንድ ጊዜ ከመጠን ያለፈ ብዙ ትምህርት ለመሸፈን አትሞክር።
10 የሚጠናው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በተማሪው ልብ ውስጥ ሥር በመስደድ ላይ መሆኑን ለማወቅ ጥያቄዎች በጣም ይረዳሉ። አዳዲስ እውነቶችን ከተወያየህ በኋላ “አሁን ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማሃል? አንተስ የምታምነው ይህንን ነውን?” ብለህ ለመጠየቅ ትፈልግ ይሆናል። እንደነዚህ ያሉትን ጥያቄዎች የተማሪ ንግግር በምትሰጥበት ጊዜ ተለማመድ። አንድን ሰው በይሖዋ አገልግሎት ዕድገት እንዲያሳይ ልንረዳው የምንችለው በልቡ ውስጥ ያለውን ለማወቅ ከቻልን ብቻ ነው።
11. አንድ ተማሪ ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አጥብቀን ማስገንዘብ የምንችለው እንዴት ነው?
11 የአምላክ ቃል በተማሪዎቹ ልብ ውስጥ እንዲቀረጽ ከተፈለገ የተማሩትን ከይሖዋ ጋር ካላቸው ዝምድና ጋር እያገናዘቡ እንዲያስቡ መረዳት ይኖርባቸዋል። ይህንን ችሎታ ለማዳበር ደግሞ ከአገልግሎት ትምህርት ቤት የተሻለ አጋጣሚ አይገኝም። የምታስተምራቸው ሰዎች ይሖዋን ስለሚወዱና እርሱም ስለሚወደን በሙሉ ልባቸው በእርሱ እንዲታመኑ አበረታታቸው። ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚማሩት ነገር ሁሉ ‘በጣም ርህሩህና መሐሪ’ ከሆነው ፈጣሪ ከይሖዋ የተገኘ መሆኑን ተስማሚ በሆኑ ጥያቄዎች አማካኝነት ማስገንዘብ ትችላለህ። (ያዕ. 5:11) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምትመራ ከሆነ በየሳምንቱ አብራችሁ በምታጠኑአቸው እውነቶች አማካኝነት የተገለጹትን የይሖዋ ፍቅርና ጥበብ ጎላ አድርገህ ግለጽ። ተማሪዎቹ የተማሩት ነገር ሕይወታቸውን እንዴት እንደነካና ወደፊትም እንዴት እንደሚነካ እንዲገነዘቡ አበረታታቸው። ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ጥሩ ትውውቅ እንዲኖራቸው እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ደጋግማችሁ ከልሱ። ማንኛውንም ውሳኔ ከማድረጋቸው በፊት የሰማያዊ አባታቸው ፈቃድ ምን እንደሆነ የማረጋገጥ ልማድ እንዲያዳብሩ እርዳቸው። ሕይወታችንና ያለን ነገር ሁሉ የአምላክ ንብረት መሆኑን እንዲገነዘቡ ቀስ በቀስ ትረዳቸዋለህ። “እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና።” በልባችንና በአእምሮአችን ውስጥ ቀዳሚውን ሥፍራ መያዝ የሚገባው የእርሱ አምልኮና አገልግሎት መሆኑን አስገንዝባቸው። — ሥራ 17:25
12–14. ተማሪዎች ስለ ልብ ግፊት መማር የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? አንድ ሰው የልብ ግፊቱን ሊመረምር የሚችለው እንዴት ነው?
12 በአምላክ ዘንድ አስፈላጊ የሆነው ጉዳይ የምናደርገው ነገር ብቻ ሳይሆን ያንን ነገር እንድናደርግ የገፋፋን ምክንያት ጭምር መሆኑን በየጊዜው ጥቀስላቸው። ይሖዋ ፈቃዱን በማድረግ እንድንደሰት ይፈልጋል። የሰማዩ አባታችን በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸው አባት “ልጄ ሆይ፣ ንግግሬን አድምጥ ወደ ቃሌም ጆሮህን አዘንብል። ከዓይንህ አታርቃት፣ በልብህም ውስጥ ጠብቃት። ለሚያገኙአት ሕይወት፣ ለሥጋቸውም ሁሉ ፈውስ ነውና” በማለት ይጋብዘናል። — ምሳሌ 4:20–22
13 ስለዚህ የምታስተምራቸው ሰዎች አንዳንድ ነገሮችን እንዲያደርጉ የገፋፋቸው ዝንባሌ ምን እንደሆነ እንዲመረምሩና ራሳቸውንም እንደሚከተሉት ያሉትን ጥያቄዎች እንዲጠይቁ ሊበረታቱ ይችላሉ። ይህን ወይም ያን ለማድረግ የምፈልገው ለምንድን ነው? ይህን መንገድ እንድከተል የገፋፋኝ ነገር ምንድን ነው? አእምሮዬ ምን እንደሚል አውቃለሁ፣ ግን ልቤ ምን ይላል? የምፈልገው አምላክን ለማስደሰት ነው ወይስ የራሴን ፍላጎት ለማርካት? አስተሳሰቤ ቅንነት ያለው ነው ወይስ ራሴን በሐሰት አስተሳሰብ ለማታለል በመሞከር ላይ ነኝ?
14 በተጨማሪም የተዘናጉ ሰዎችን ስለሚያጋጥሙአቸው አደጋዎችና ሽንገላዎች ተማሪዎችን ማስጠንቀቅ ይቻላል። ለምሳሌ አንድ ሰው ልቡን በአንድ ዓይነት ግብ ላይ ያኖር ይሆናል። ይህ ግብ በራሱ ትክክለኛ የሆነ ግብ ቢሆንም ሰውዬው ለአምላክ የሚያቀርበውን አገልግሎት ወይም አምልኮ በአንድ ዓይነት መንገድ የሚያስተጓጉል ሊሆን ይችላል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የምሳሌ መጽሐፍ የሚከተለውን ቀጥተኛ ምክር ይሰጣል:- “በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሰነፍ ነው፤ በጥበብ የሚሄድ ግን ይድናል።” — ምሳሌ 28:26
15–17. የኢየሱስ አርዓያነትና ስለ ጸሎት የሚደረግ ውይይት ለልብ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?
15 በመጨረሻም ፍጹም የሆነውን የኢየሱስን አርዓያነት ዘወትር ለተማሪዎቻችን ማሳሰብ ጥሩ ነው። ኢየሱስ ለሰማያዊ አባቱ ታማኝ ነበር። ‘ይሖዋ ከሌሎች ይልቅ እርሱን በደስታ ዘይት የቀባው ጽድቅን ስለወደደና ክፋትን ስለጠላ ነበር።’ (መዝ. 45:7) ይህን የመሰለ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ጠብቆ ለማቆየት የቻለው እንዴት ነው? አምላክን ለማወቅ ብቻ ሳይሆን አምላክን ለማስደሰት በማሰብ ያጠና ነበር። ዘወትር የአባቱን ፈቃድ ያስብ ነበር። ኢየሱስ አዘውትሮ አባቱን በጸሎት ያነጋግር ነበር። በሚያቀርባቸው ጸሎቶች አማካኝነት አምላክ ‘እንዲፈትነውና እንዲመረምረው፣ ኩላሊቱንና ልቡን እንዲፈትን’ ይጠይቅ ነበር። (መዝ. 26:2) በራሱ አስተሳሰብ ወይም በራሱ የልብ ዝንባሌ ብቻ አልተመካም። አስቀድሞ በትንቢት በተነገረው መሠረት የሚሞትበት ጊዜ ሲደርስ የወሰደው የጸሎት ውሳኔ “አባት ሆይ፣ . . . አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን” የሚል ነበር። — ማር. 14:36
16 ታዲያ ይህ ለተማሪዎቻችን ዘወትር ማሳሰብ የሚገባን ጥሩ አርዓያ አይደለምን? እነርሱም በሕይወታቸው በሙሉ አምላክ የሚወደውን ለመከተል የሚያስችላቸውን ጥበብ ልባዊ በሆነ ጸሎት እንዲጠይቁ ሊረዱ ይችላሉ። አንዳንዶቹን የኢየሱስ ጸሎቶች አንብብላቸው። ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ ልጅ እንደመሆኑ መጠን ወደ አምላክ ጸልዮአል። ደቀ መዛሙርቱ እንዴት እንደሚጸልዩ ባስተማረበት ጊዜም “አባታችን ሆይ” በሚሉት ቃላት ጀምሯል። (ማቴ. 6:9) ስለዚህ የሚጸልየው ሰው አባቱን ቀርቦ እንደሚያነጋግር ልጅ መሆን ይኖርበታል። ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና ምን ዓይነት መሆኑን ከሚያሳዩት ነገሮች ዋነኛው ጸሎት ሳይሆን አይቀርም። ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና አንድ ልጅ ከሚያከብረውና በሙሉ ልቡ ከሚወደው አባቱ ጋር ያለውን ዝምድና የሚመስል ሞቅ ያለ፣ የተቀራረበና መተማመን ያለበት ነውን? ወይስ ከጎረቤት ጋር ወይም ራቅ ካለ ወዳጅ ጋር ያለንን ዝምድና የመሰለ ተራ ትውውቅ ነው? ከምታነጋግራቸውና ከምታስጠናቸው ሰዎች ጋር ስለ ጸሎት ምን እንደሚሰማቸውና ስለ ምን ነገሮች እንደሚጸልዩ በመወያየት ልባቸውን ለመንካት ጥረት አድርግ። — ምሳሌ 15:8, 29
17 አምላክ ለልብ ይህን የመሰለ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጥ ከሆነ እኛም ቃሉን በምናስተምርበት ጊዜ ስለሚሰሙን ሰዎች ልብ በጥንቃቄ ማሰብ ይኖርብናል። የሕዝብ ንግግር ወይም የተማሪ ንግግር በምትሰጥበት ጊዜ ወይም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምትመራበት ጊዜ ዋነኛው ዓላማህ ብዙ ትምህርት ለመሸፈን መሆን የለበትም። አድማጮችህ ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ ለመርዳትና ቃሉ ልባቸው ውስጥ እንዲቀረጽ ለማድረግ በቂ ጊዜ ስጥ።