የአንባብያን ጥያቄዎች
ድንግል ማርያም ፍጹም አለመሆንዋ በኢየሱስ መፀነስ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ነበረውን?
በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ዘገባ ‘የኢየሱስን መወለድ’ አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች።” (ማቴዎስ 1:18) እውነት ነው፣ ከማርያም መፀነስ ጋር በተያያዘ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
ይሁን እንጂ ስለ ማርያምስ ምን ለማለት ይቻላል? የእሷ የእንቁላል ሕዋስ ለፅንሱ መፈጠር ያደረገው አስተዋጽኦ ነበር? አምላክ የማርያም ቅድመ አያቶች ለነበሩት ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ፣ ለይሁዳና ለንጉሥ ዳዊት ከገባው ቃል አኳያ የሚወለደው ልጅ እውነተኛ የልጅ ልጃቸው መሆን አለበት። (ዘፍጥረት 22:18፤ 26:24፤ 28:10-14፤ 49:10፤ 2 ሳሙኤል 7:16) አለዚያማ ከማርያም የሚወለደው ልጅ አምላክ የገባው የዚህ ቃል ኪዳን ሕጋዊ ወራሽ እንዴት መሆን ይችላል? ልጁ የማኅፀኗ ፍሬ መሆን ነበረበት።—ሉቃስ 3:23-34
የይሖዋ መልአክ ድንግል ልጃገረድ ለነበረችው ለማርያም ተገለጠና እንዲህ አላት:- “ማርያም ሆይ፣ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፣ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፣ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ።” (ሉቃስ 1:30, 31) ፅንስ እንዲፈጠር እንቁላሉ መዳበር አለበት። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ አምላክ የአንድያ ልጁን ሕይወት ከመንፈሳዊው ዓለም ወደ ምድር በማዘዋወር በማርያም ማኅፀን ውስጥ የነበረው እንቁላል እንዲዳብር አድርጓል።—ገላትያ 4:4
ፍጹም ካልሆነች ሴት በዚህ መንገድ የተፀነሰ ልጅ ፍጹም ሊሆንና ሰብዓዊ አካሉ ከኃጢአት ነጻ ሊሆን ይችላል? ፍጽምናና አለፍጽምና በሚዋሃዱበት ጊዜ የዘር ውርስ ሕግ የሚሠራው እንዴት ነው? የአምላክን ልጅ ፍጹም የሕይወት ኃይል ወደ ማርያም ማኅፀን በማዘዋወርና ፅንሱ እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ መንፈስ ቅዱስ የተጫወተው ሚና እንደነበር አስታውስ። ይህም በማርያም እንቁላል ውስጥ የነበረውን አለፍጽምና ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ ገና ከጅምሩ ፍጹም የሆነ በራሄያዊ ውርስ አስገኝቷል።
ያም ሆነ ይህ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በወቅቱ ያከናወነው ነገር የአምላክ ዓላማ ግቡን መምታቱን የሚያስተማምን እንደነበር እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። መልአኩ ገብርኤል ለማርያም እንዲህ ብሏት ነበር:- “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።” (ሉቃስ 1:35) አዎን፣ በማደግ ላይ የነበረው ሽል ምንም ዓይነት አለፍጽምና ወይም ጎጂ ተጽዕኖ እንዳያገኘው ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንደ ከለላ ሆኖለት ነበር።
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ፍጹም የሆነውን ሰብዓዊ ሕይወቱን ያገኘው ከሰማያዊ አባቱ እንጂ ከሌላ ከማንም ሰው አይደለም። ይሖዋ ‘ሥጋን አዘጋጀለት’፤ እናም ኢየሱስ ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ “ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ” ነበር።—ዕብራውያን 7:26፤ 10:5
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ”