ወጣቶች—ዲያብሎስን ተቋቋሙ
“የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች መቋቋም እንድትችሉ ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ ልበሱ።”—ኤፌ. 6:11
1, 2. (ሀ) ወጣት ክርስቲያኖች ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር በሚያደርጉት ውጊያ እንዲያሸንፉ የረዳቸው ምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ምስል ተመልከት።) (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቲያኖችን ሕይወት በጨበጣ ውጊያ ላይ ካሉ ወታደሮች ሁኔታ ጋር አመሳስሎታል። እርግጥ ነው፣ ይህ ሲባል ቃል በቃል እንዋጋለን ማለት አይደለም፤ ውጊያው መንፈሳዊ ነው። ያም ቢሆን ጠላቶቻችን በእውን ያሉ አካላት ናቸው። ሰይጣንና አጋንንቱ የረጅም ጊዜ ተሞክሮ ያካበቱ ተዋጊዎች ናቸው። በመሆኑም በውጊያው ለማሸነፍ ጨርሶ ተስፋ የሌለን ይመስል ይሆናል። በተለይ ደግሞ ወጣት ክርስቲያኖች በቀላሉ የሚሸነፉ መስለው ሊታዩ ይችላሉ። ታዲያ ወጣቶች ከሰው በላይ አቅም ካላቸው ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር በሚደረግ ውጊያ አሸናፊ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? እንደ እውነቱ ከሆነ ወጣቶች በውጊያው ማሸነፍ ይችላሉ፤ ደግሞም እያሸነፉ ነው! እንዲያሸንፉ የረዳቸው ምንድን ነው? ‘ከጌታ ኃይል’ ማግኘታቸው ነው። ከዚህም ሌላ ለጦርነት ታጥቀዋል። ጥሩ ሥልጠና እንዳገኙ ወታደሮች ሁሉ እነዚህ ወጣቶችም “ሙሉ የጦር ትጥቅ [ለብሰዋል]።”—ኤፌሶን 6:10-12ን አንብብ።
2 ጳውሎስ ይህን ምሳሌ የተናገረው የሮም ወታደሮች የሚለብሱትን የጦር ትጥቅ በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። (ሥራ 28:16) በዚህ ርዕስ ላይ ይህን ግሩም ምሳሌ እንመረምራለን። በተጨማሪም አንዳንድ ወጣቶች እያንዳንዱን ትጥቅ ከመልበስ ጋር በተያያዘ ያጋጠማቸውን ተፈታታኝ ሁኔታ እንዲሁም ይህን ማድረጋቸው ያስገኘላቸውን ጥቅም በተመለከተ የሰጡትን ሐሳብ እንመለከታለን።
‘የእውነት ቀበቶ’
3, 4. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውነት የሮም ወታደሮች ከሚታጠቁት ቀበቶ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
3 ኤፌሶን 6:14ን አንብብ። የሮም ወታደሮች የሚታጠቁት ቀበቶ ትናንሽ ጠፍጣፋ ብረቶች የሚደረጉበት ሲሆን ይህም ወታደሩ ወገቡ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት ይከላከላል። በተጨማሪም ቀበቶው ወታደሩ ከላይ የሚለብሰውን ከባድ ጥሩር ይደግፍለታል። አንዳንዶቹ ቀበቶዎች፣ ሰይፍና ጩቤ ለማስቀመጥ የሚያስችሉ ጠንካራ ማንጠልጠያዎችም አሏቸው። ወታደሩ ቀበቶውን በሚገባ ከታጠቀ በልበ ሙሉነት ለውጊያ መሰለፍ ይችላል።
4 በተመሳሳይም ከአምላክ ቃል የምንማራቸው እውነቶች የሐሰት ትምህርቶች ከሚያስከትሉት መንፈሳዊ ጉዳት ይጠብቁናል። (ዮሐ. 8:31, 32፤ 1 ዮሐ. 4:1) በተጨማሪም ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ይበልጥ ፍቅር ባዳበርን መጠን ‘ጥሩራችንን’ መሸከም ይኸውም በአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች መመራት የበለጠ ቀላል ይሆንልናል። (መዝ. 111:7, 8፤ 1 ዮሐ. 5:3) ከዚህም ሌላ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት እውነቶች ግልጽ ሲሆኑልን፣ ተቃዋሚዎች በእውነት ላይ ለሚሰነዝሩት ጥቃት በልበ ሙሉነት መከላከያ ማቅረብ እንችላለን።—1 ጴጥ. 3:15
5. እውነት መናገር ያለብን ለምንድን ነው?
5 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንደ ቀበቶ በሚገባ ከታጠቅን፣ ከዚህ እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር እንዲሁም በማንኛውም ጊዜ እውነት ለመናገር እንነሳሳለን። ለመሆኑ መዋሸት የሌለብን ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው በጣም ውጤታማ መሣሪያዎች አንዱ ውሸት ነው። ውሸት፣ ለተናጋሪውም ሆነ የተነገረውን ለሚያምነው ሰው ጎጂ ነው። (ዮሐ. 8:44) ስለዚህ ፍጽምና የሚጎድለን ሰዎች ብንሆንም እንኳ በተቻለን መጠን ውሸት ላለመናገር እንጠነቀቃለን። (ኤፌ. 4:25) በእርግጥ ይህን ማድረግ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። የአሥራ ስምንት ዓመቷ አቢጋኤል እንዲህ ብላለች፦ “እውነት መናገር ሁልጊዜ ጠቃሚ ላይመስል ይችላል፤ በተለይ ደግሞ መዋሸት ከአንድ ችግር ለማምለጥ የሚያስችል በሚሆንበት ጊዜ እውነቱን መናገር ከባድ ይሆናል።” ታዲያ ምንጊዜም ቢሆን እውነቱን ለመናገር የሚያነሳሳት ምንድን ነው? “እውነቱን ስናገር በይሖዋ ፊት ንጹሕ ሕሊና ይኖረኛል። ወላጆቼና ጓደኞቼም ሊተማመኑብኝ እንደሚችሉ ያውቃሉ” ብላለች። የ23 ዓመት ወጣት የሆነችው ቪክቶሪያ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “እውነቱን ስንናገርና ለምናምንባቸው ነገሮች ጥብቅና ስንቆም ሌሎች ሊያስቸግሩን ይችላሉ። ሆኖም የምናገኘው ጥቅም ምንጊዜም የላቀ ነው፦ በራስ የመተማመን ስሜታችን ይጨምራል፤ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንቀርባለን እንዲሁም የሚወዱንን ሰዎች አክብሮት እናተርፋለን።” በእርግጥም ምንጊዜም ‘ወገባችንን በእውነት ቀበቶ መታጠቃችን’ የሚክስ ነው።
‘የጽድቅ ጥሩር’
6, 7. ጽድቅ ከጥሩር ጋር የተመሳሰለው ለምንድን ነው?
6 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የሮም ወታደሮች ከሚጠቀሙባቸው የጥሩር ዓይነቶች መካከል፣ አንዱ በሌላው ላይ በተነባበሩ ጠፍጣፋ ብረቶች የተሠራ ጥሩር ይገኝበታል። እነዚህ ብረቶች ከወገብ በላይ ያለውን ሰውነት ለመሸፈን በሚያስችል መልኩ ጎበጥ ተደርገው ከተሠሩ በኋላ በዘለበቶችና በቀለበቶች አማካኝነት በጠፍር ይታሰሩ ነበር። ለወታደሩ ትከሻም እንዲሁ በጠፍጣፋ ብረቶች የተሠራ መከላከያ የሚዘጋጅ ሲሆን ይሄም በቆዳ ይያያዛል። ወታደሩ እንዲህ ዓይነቱን ጥሩር ማድረጉ እንቅስቃሴውን በተወሰነ መጠን ይገድብበታል፤ ከዚህም ሌላ ጥሩሩ ቦታውን እንዳልለቀቀ ሁልጊዜ ማረጋገጥ ይኖርበታል። ይሁን እንጂ ጥሩር ማድረጉ፣ ጠላቱ በሰይፍ አሊያም በፍላጻ ተጠቅሞ ልቡን ወይም ሌሎች የሰውነቱን ክፍሎች እንዳይወጋ ለመከላከል ይረዳዋል።
7 ወታደሮቹ የሚለብሱት ጥሩር፣ ምሳሌያዊውን ልባችንን ከጉዳት ከሚጠብቁት የይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ሊመሳሰል ይችላል። (ምሳሌ 4:23) አንድ ወታደር ከብረት የተሠራ ጥሩሩን አውልቆ መናኛ በሆነ ንጥረ ነገር የተሠራ ጥሩር እንደማያደርግ የታወቀ ነው፤ በተመሳሳይ እኛም ትክክል የሆነውን ነገር በተመለከተ የይሖዋን መሥፈርቶች ትተን በራሳችን መሥፈርቶች ለመመራት ፈጽሞ አንፈልግም። የሰው ልጆች፣ ልባችንን ለመጠበቅ የሚያስችል የማመዛዘን ችሎታ ጨርሶ የለንም። (ምሳሌ 3:5, 6) በመሆኑም ይሖዋ የሰጠንን ‘የብረት ጥሩር’ ልባችንን በሚገባ በሚከልል መንገድ መታጠቃችንን አዘውትረን ማረጋገጥ ይኖርብናል።
8. የይሖዋን መሥፈርቶች መከተል ይክሳል የምንለው ለምንድን ነው?
8 አንዳንድ ጊዜ የይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ከባድ እንደሆኑ ወይም ነፃነትህን እንደሚገድቡት ይሰማሃል? የ21 ዓመት ወጣት የሆነው ዳንኤል እንዲህ ብሏል፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ለመመራት ጥረት ስለማደርግ አስተማሪዎቼና አብረውኝ የሚማሩ ልጆች ያሾፉብኝ ነበር። በዚህም የተነሳ በራሴ መተማመን አቅቶኝና በጭንቀት ተውጬ ነበር።” ይህን ስሜት ለማሸነፍ የረዳው ምንድን ነው? ዳንኤል እንዲህ ብሏል፦ “በይሖዋ መሥፈርቶች መመራት ያለውን ጥቅም ውሎ አድሮ ተመልክቻለሁ። አብረውኝ ከሚማሩት ልጆች አንዳንዶቹ ዕፅ መውሰድ ጀመሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ ትምህርታቸውን አቋረጡ። ሕይወታቸው ምን ያህል እንደተመሰቃቀለ ማየት አሳዛኝ ነበር። በእርግጥም ይሖዋ ጥበቃ ያደርግልናል።” የ15 ዓመቷ ማድሰን “የይሖዋን መሥፈርቶች በጥብቅ መከተልና እኩዮቼ አስደሳች እንደሆነ የሚያስቡትን ነገር አለማድረግ ትግል ይጠይቅብኛል” ብላለች። ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን ታደርጋለች? እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋን ስም እንደተሸከምኩ እንዲሁም የሚያጋጥመኝ ፈተና ከሰይጣን የሚሰነዘር ጥቃት እንደሆነ ለማስታወስ እጥራለሁ። በትግሉ ሳሸንፍ ስለ ራሴ ጥሩ ስሜት ይሰማኛል።”
‘የሰላምን ምሥራች መጫማት’
9-11. (ሀ) ክርስቲያኖች ምሳሌያዊውን ጫማ ማድረጋቸው ምን ያመለክታል? (ለ) ምሥራቹን መስበክ ይበልጥ ቀላል እንዲሆንልን የትኞቹን ዘዴዎች መጠቀም እንችላለን?
9 ኤፌሶን 6:15ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ። አንድ የሮም ወታደር ጫማውን ካላደረገ ወደ ጦር ሜዳ ለመዝመት ዝግጁ አይደለም። ወታደሩ የሚያደርገው ክፍት ጫማ የሚሠራው ሦስት የቆዳ ንጣፎችን በማነባበር ነው። የጫማው አሠራር ምቹና ጠንካራ እንዲሆን ያደርገዋል።
10 የሮም ወታደሮች ይህን ጫማ የሚያደርጉት ለጦርነት ዝግጁ ለመሆን ነው፤ ክርስቲያኖች ግን ምሳሌያዊውን ጫማ ማድረጋቸው የሰላምን መልእክት ለማድረስ መዘጋጀታቸውን ያመለክታል። (ኢሳ. 52:7፤ ሮም 10:15) እርግጥ ነው፣ አጋጣሚውን በምናገኝበት ጊዜ ምሥራቹን መናገር ድፍረት ይጠይቃል። የ20 ዓመቱ ቦ እንዲህ ብሏል፦ “አብረውኝ ለሚማሩ ልጆች መስበክ ያስፈራኝ ነበር። የምፈራው ምሥራቹን መናገር ስለሚያሳፍረኝ ነበር። መለስ ብዬ ሳስበው ግን ምኑ እንዳሳፈረኝ አይገባኝም። አሁን ለእኩዮቼ መመሥከር ያስደስተኛል።”
11 በርካታ ወጣቶች ምሥራቹን ለመናገር በሚገባ መዘጋጀታቸው መስበክ ይበልጥ ቀላል እንዲሆንላቸው እንደሚያደርግ ይናገራሉ። ታዲያ በሚገባ መዘጋጀት የምትችሉት እንዴት ነው? የ16 ዓመቷ ጁልያ እንዲህ ብላለች፦ “የትምህርት ቤት ቦርሳዬ ውስጥ ጽሑፎችን እይዛለሁ፤ በተጨማሪም የክፍሌ ልጆች አመለካከታቸውንና የሚያምኑባቸውን ነገሮች ሲናገሩ አዳምጣቸዋለሁ። ይህም ምን እንደሚያስፈልጋቸው ለመረዳት ያስችለኛል። በሚገባ ከተዘጋጀሁ ለእነሱ የሚጠቅማቸውን ሐሳብ ላካፍላቸው እችላለሁ።” የ23 ዓመቷ ማኬንዚ ደግሞ እንደሚከተለው በማለት ተናግራለች፦ “አሳቢና ጥሩ አዳማጭ ከሆንን እኩዮቻችን የሚያሳስባቸውን ነገር ማወቅ እንችላለን። ለወጣቶች ተብለው የተዘጋጁ ርዕሶችን በሙሉ ለማንበብ ጥረት አደርጋለሁ። ይህን ማድረጌ ከመጽሐፍ ቅዱስ ወይም ከjw.org ላይ ለእኩዮቼ ጠቃሚ ሐሳብ ለማካፈል ያስችለኛል።” እነዚህ ወጣቶች ከሰጡት አስተያየት መረዳት እንደሚቻለው ለመስበክ በሚገባ ከተዘጋጃችሁ፣ “ጫማችሁን” በሚገባ እንደተጫማችሁ ይቆጠራል።
“ትልቅ የእምነት ጋሻ”
12, 13. ሰይጣን ከሚያስወነጭፋቸው ‘የሚንበለበሉ ፍላጻዎች’ መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
12 ኤፌሶን 6:16ን አንብብ። የሮም ወታደሮች የሚይዙት ‘ትልቅ ጋሻ’ አራት ማዕዘን ቅርፅ ያለው ሲሆን ከትከሻ እስከ ጉልበት ያለውን የሰውነት ክፍል ይሸፍን ነበር። የወታደሩ ጋሻ በሰይፍ፣ በጦርና በፍላጻ የሚሰነዘርበትን ጥቃት ለመመከት ያስችለዋል።
13 ሰይጣን ከሚያስወነጭፋቸው ‘የሚንበለበሉ ፍላጻዎች’ መካከል ስለ ይሖዋ የሚነገሩ ውሸቶች ይገኙበታል፤ ሰይጣን ይሖዋ እንደማይወዳችሁና ማንም ስለ እናንተ ግድ እንደሌለው ሊያሳምናችሁ ይፈልጋል። የአሥራ ዘጠኝ ዓመቷን ኢዳን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ኢዳ ዋጋ ቢስ እንደሆነች ይሰማታል። “ይሖዋ እንደማይቀርበኝና ወዳጄ መሆን እንደማይፈልግ ብዙ ጊዜ ይሰማኛል” ብላለች። ኢዳ፣ ሰይጣን የሚሰነዝረውን ይህን ጥቃት የምትቋቋመው እንዴት ነው? እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “ስብሰባዎች እምነቴን በጣም ያጠናክሩልኛል። ማንም ሰው እኔ የምሰጠውን ሐሳብ መስማት እንደማይፈልግ ስለማስብ በስብሰባዎች ላይ ምንም መልስ አልመልስም ነበር። አሁን ግን ለስብሰባዎች እዘጋጃለሁ፤ እንዲሁም ሁለት ወይም ሦስት መልስ ለመስጠት እሞክራለሁ። ይህን ማድረግ ከባድ ቢሆንም መልስ ስመልስ በጣም ደስ ይለኛል። ወንድሞችና እህቶችም በጣም ያበረታቱኛል። ሁልጊዜ ከስብሰባ ስመለስ፣ ይሖዋ እንደሚወደኝ ይሰማኛል።”
14. የኢዳ ተሞክሮ የትኛውን እውነት ያስገነዝበናል?
14 የኢዳ ተሞክሮ አንድ መሠረታዊ እውነት ያስገነዝበናል፦ ወታደሮቹ የሚይዙት ጋሻ ቁመቱና ስፋቱ የተወሰነ ነው፤ የእምነት ጋሻችን ግን መጠኑ ሊቀንስ ወይም ሊጨምር ይችላል። ይህ እኛ በምናደርገው ጥረት ላይ የተመካ ነው። (ማቴ. 14:31፤ 2 ተሰ. 1:3) በእርግጥም እምነታችንን ለመገንባት ጥረት ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው!
‘የመዳን የራስ ቁር’
15, 16. ተስፋ ከራስ ቁር ጋር የሚመሳሰለው በምን መንገድ ነው?
15 ኤፌሶን 6:17ን አንብብ። የሮም ወታደሮች የሚያደርጉት የራስ ቁር በውጊያ ወቅት በጭንቅላት፣ በአንገትና በፊት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ይከላከላል። አንዳንድ የራስ ቁሮች ማንጠልጠያ ስላላቸው ወታደሩ ቁሩን አውልቆ በእጁ ሊይዘው ይችላል።
16 የራስ ቁር የወታደሩን አንጎል ከጉዳት እንደሚጠብቅለት ሁሉ ‘የመዳን ተስፋችንም’ አእምሯችንን ማለትም የማሰብ ችሎታችንን ከጉዳት ይጠብቅልናል። (1 ተሰ. 5:8፤ ምሳሌ 3:21) ተስፋ፣ አምላክ በገባልን ቃል ላይ እንድናተኩርና ለሚደርሱብን ችግሮች ተገቢውን አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል። (መዝ. 27:1, 14፤ ሥራ 24:15) ይሁን እንጂ ‘የራስ ቁራችን’ ከአደጋ እንዲከላከልልን ከፈለግን አውልቀን በእጃችን ከመያዝ ይልቅ በጭንቅላታችን ላይ ልናጠልቀው ይገባል።
17, 18. (ሀ) ሰይጣን የራስ ቁራችንን እንድናወልቅ ሊያደርገን የሚሞክረው በምን መንገድ ነው? (ለ) በሰይጣን ማባበያዎች እንዳልተታለልን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
17 ሰይጣን የራስ ቁራችንን እንድናወልቅ ሊያደርገን የሚሞክረው በምን መንገድ ነው? ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ ምን እንዳደረገ እንመልከት። ኢየሱስ የሰውን ዘር የመግዛት ተስፋ እንዳለው ሰይጣን አውቆ መሆን አለበት። ሆኖም ኢየሱስ ይህ ተስፋ እንዲፈጸምለት፣ ይሖዋ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ መጠበቅ ይገባዋል። ከዚያ በፊት ደግሞ ተሠቃይቶ መሞት ነበረበት። ሰይጣን ግን የኢየሱስ ተስፋ ቶሎ እንዲፈጸም የሚያደርግ ግብዣ አቀረበ። ሰይጣን፣ ኢየሱስ አንድ ጊዜ ተደፍቶ ቢያመልከው የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ወዲያውኑ እንደሚሰጠው ነገረው። (ሉቃስ 4:5-7) ዛሬም በተመሳሳይ ይሖዋ በአዲሱ ዓለም ብዙ አስደናቂ ነገሮችን እንደሚሰጠን ቃል መግባቱን ሰይጣን ያውቃል። ሆኖም ይህ ተስፋ እስኪፈጸምልን መጠበቅ ያስፈልገናል፤ ያ ጊዜ እስኪደርስ ደግሞ የተለያዩ መከራዎች ያጋጥሙን ይሆናል። ሰይጣን ይህን ስለሚያውቅ በአሁኑ ጊዜ የተመቻቸ የሚባለውን ሕይወት እንድንመራ አጓጊ ግብዣዎች ያቀርብልናል። የምንፈልገውን ነገር ሁሉ አሁኑኑ ለማግኘት ጥረት እንድናደርግ ይፈልጋል። በመሆኑም በሕይወታችን ውስጥ ቁሳዊ ነገሮችን እንድናስቀድምና ለአምላክ መንግሥት ሁለተኛ ቦታ እንድንሰጥ ሊያደርገን ይሞክራል።—ማቴ. 6:31-33
18 በርካታ ወጣት ክርስቲያኖች በዚህ ማባበያ አልተታለሉም፤ የ20 ዓመቷ ኪያና ከእነዚህ አንዷ ናት። “ችግሮቻችንን ሁሉ የሚፈታው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ አውቃለሁ” ብላለች። እንዲህ ያለ አስተማማኝ ተስፋ ያላት መሆኑ በአመለካከቷና በአኗኗሯ ላይ ምን ለውጥ አምጥቷል? “ምድር ገነት እንደምትሆን ያለኝ ተስፋ ለዓለማዊ ግቦች ተገቢ አመለካከት እንዲኖረኝ ረድቶኛል። ባሉኝ ተሰጥኦዎች ተጠቅሜ አንዳንድ ቁሳዊ ጥቅሞችን ለማግኘት ወይም በሥራው ዓለም የላቀ ቦታ ላይ ለመድረስ አልሞክርም። ጊዜዬንና ጉልበቴን የማውለው በመንፈሳዊ ግቦቼ ላይ ነው።”
‘የመንፈስ ሰይፍ’—የአምላክ ቃል
19, 20. የአምላክን ቃል ጥሩ አድርጎ የመጠቀም ችሎታ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
19 ጳውሎስ ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት የነበሩት የሮም ወታደሮች የሚይዙት ሰይፍ፣ ርዝመቱ 50 ሴንቲ ሜትር ገደማ ሲሆን ለጨበጣ ውጊያ የተዘጋጀ ነበር። የሮም ወታደሮች ጎበዝ ተዋጊዎች እንዲሆኑ የረዳቸው አንዱ ነገር በጦር መሣሪያዎቻቸው በየዕለቱ ልምምድ ማድረጋቸው ነው።
20 ጳውሎስ የአምላክን ቃል ከሰይፍ ጋር አመሳስሎታል፤ ይህን ሰይፍ ያገኘነው ከይሖዋ ነው። ይሁንና ለምናምንባቸው ነገሮች ጥብቅና ለመቆምም ሆነ አስተሳሰባችንን ለማስተካከል የአምላክን ቃል ጥሩ አድርገን የመጠቀም ችሎታ ልናዳብር ይገባል። (2 ቆሮ. 10:4, 5፤ 2 ጢሞ. 2:15) ታዲያ ችሎታችሁን ማሻሻል የምትችሉት እንዴት ነው? የ21 ዓመቱ ሴባስትያን እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ ከእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ አንድ ቁጥር መርጬ የመጻፍ ልማድ አለኝ። በዚህ መንገድ፣ የምወዳቸውን ጥቅሶች አንድ ላይ አሰባስባለሁ። ይህን ማድረጌ የይሖዋን አስተሳሰብ ይበልጥ ለመረዳት እንዳስቻለኝ ይሰማኛል።” ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዳንኤል ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ፣ በአገልግሎት ላይ ሰዎችን ለመርዳት የምጠቀምባቸውን ጥቅሶች ለማግኘት እሞክራለሁ። ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር እንዳለንና እነሱን ለመርዳት ልባዊ ጥረት እያደረግን እንደሆነ ሲመለከቱ መልእክቱን እንደሚቀበሉ አስተውያለሁ።”
21. ሰይጣንንና አጋንንቱን ከልክ በላይ መፍራት የማያስፈልገን ለምንድን ነው?
21 በዚህ ርዕስ ውስጥ ከተጠቀሱት ወጣቶች መመልከት እንደሚቻለው ሰይጣንን እና አጋንንቱን ከልክ በላይ መፍራት አያስፈልገንም። እነዚህ ጠላቶቻችን ኃያል ቢሆኑም የማይበገሩ ናቸው ማለት አይደለም። በዚያ ላይ ደግሞ ለዘላለም አይኖሩም። በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ሰይጣንና አጋንንቱ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ ማሳደር እንዳይችሉ ይደረጋሉ፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ ከናካቴው ይጠፋሉ። (ራእይ 20:1-3, 7-10) የጠላታችንን ማንነት፣ የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎችና ዓላማውን አውቀናል። በይሖዋ እርዳታ ደግሞ ይህን ጠላታችንን መቋቋም እንችላለን!