ምዕራፍ 16
ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ምን ነገሮችን አከናውኗል?
ብዙ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ሲያስቡ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው በእናቱ እቅፍ ያለ ሕፃን፣ ጥበበኛ ነቢይ ወይም ተሰቅሎ ሊሞት እያጣጣረ ያለ ሰው ነው። በምድር ላይ ስላሳለፈው ሕይወት ስንመረምር ግን ስለ እሱ ብዙ ነገሮችን እንማራለን። በዚህ ምዕራፍ ላይ፣ ኢየሱስ ያከናወናቸውን አንዳንድ አስፈላጊ ነገሮችና እነዚህ ነገሮች በአንተ ሕይወት ላይ ምን ለውጥ እንደሚያመጡ እንመለከታለን።
1. የኢየሱስ ዋነኛ ሥራ ምን ነበር?
የኢየሱስ ዋነኛ ሥራ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ” ነበር። (ሉቃስ 4:43ን አንብብ።) አምላክ የሰው ልጆችን ችግሮች በሙሉ የሚያስወግድ መንግሥት ወይም መስተዳድር እንደሚያቋቁም የሚገልጸውን ምሥራች ይሰብክ ነበር።a ኢየሱስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል ይህን አስደሳች መልእክት ለሰዎች ሰብኳል።—ማቴዎስ 9:35
2. ኢየሱስ ተአምር ይፈጽም የነበረው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክ በኢየሱስ አማካኝነት ስለፈጸማቸው በርካታ ተአምራት፣ ድንቅ ነገሮችና ምልክቶች’ ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 2:22) ኢየሱስ ከአምላክ ባገኘው ኃይል የአየሩን ሁኔታ መቆጣጠር፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መመገብ፣ የታመሙትን መፈወስ አልፎ ተርፎም የሞቱትን ማስነሳት ችሏል። (ማቴዎስ 8:23-27፤ 14:15-21፤ ማርቆስ 6:56፤ ሉቃስ 7:11-17) እነዚህ ተአምራት ኢየሱስ በአምላክ የተላከ መሆኑን ግልጽ አድርገዋል። በተጨማሪም ይሖዋ ችግሮቻችንን ሁሉ ለመፍታት የሚያስችል ኃይል እንዳለው አሳይተዋል።
3. ከኢየሱስ ሕይወት ምን እንማራለን?
ኢየሱስ በሁሉም ሁኔታዎች ሥር ይሖዋን ታዟል። (ዮሐንስ 8:29ን አንብብ።) ተቃውሞ ቢያጋጥመውም በታማኝነት እስከ ሞት ድረስ አባቱ ያዘዘውን ነገር ፈጽሟል። የሰው ልጆች አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም እንኳ አምላክን በታማኝነት ማገልገል እንደሚችሉ አሳይቷል። በዚህ መንገድ ‘የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድንከተል አርዓያ ትቶልናል።’—1 ጴጥሮስ 2:21
ጠለቅ ያለ ጥናት
ኢየሱስ ስላከናወነው የስብከት ሥራና ስለፈጸማቸው ተአምራት እንመለከታለን።
4. ኢየሱስ ምሥራቹን ሰብኳል
ኢየሱስ በተቻለው መጠን ለብዙ ሰዎች ምሥራቹን ለመስበክ ሲል በአቧራማ መንገዶች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዟል። ሉቃስ 8:1ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ኢየሱስ ይሰብክ የነበረው እሱን ለመስማት ለሚመጡ ሰዎች ብቻ ነበር?
ኢየሱስ ሰዎችን ለማግኘት ሲል ምን አድርጓል?
አምላክ መሲሑ ለሰዎች ምሥራች እንደሚሰብክ አስቀድሞ ተናግሯል። ኢሳይያስ 61:1, 2ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ኢየሱስ ይህ ትንቢት እንዲፈጸም ያደረገው እንዴት ነው?
በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች ይህን ምሥራች መስማት የሚያስፈልጋቸው ይመስልሃል?
5. ኢየሱስ በጣም አስፈላጊ ትምህርቶችን አስተምሯል
ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች ከመስበክ በተጨማሪ ሌሎች አስፈላጊ ትምህርቶችንም አስተምሯል። በስፋት በሚታወቀው የተራራ ስብከቱ ላይ ያስተማራቸውን አንዳንድ ትምህርቶች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ማቴዎስ 6:14, 34ን እንዲሁም 7:12ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ኢየሱስ ምን ጠቃሚ ምክሮች ሰጥቷል?
እነዚህ ምክሮች በዛሬው ጊዜም ጠቃሚ ይመስሉሃል?
6. ኢየሱስ ብዙ ተአምራት ፈጽሟል
ይሖዋ ለኢየሱስ ኃይል በመስጠት ብዙ ተአምራት እንዲፈጽም አስችሎታል። አንድ ምሳሌ ለማየት ማርቆስ 5:25-34ን አንብቡ ወይም ቪዲዮውን ተመልከቱ። ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
በቪዲዮው ላይ የታየችው ሴት ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበረች?
ከዚህ ተአምር ጋር በተያያዘ አንተን የሚያስገርምህ ምንድን ነው?
ዮሐንስ 5:36ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ስለ እሱ ምን ‘ይመሠክራሉ’?
ይህን ታውቅ ነበር?
ስለ ኢየሱስ የምናውቀውን አብዛኛውን መረጃ ያገኘነው ወንጌሎች ተብለው ከሚጠሩት አራቱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ማለትም ከማቴዎስ፣ ከማርቆስ፣ ከሉቃስና ከዮሐንስ ወንጌሎች ነው። እያንዳንዱ የወንጌል ጸሐፊ ኢየሱስን በተመለከተ የተለያየ ዝርዝር መረጃ አስፍሯል። እነዚህ ዝርዝር መረጃዎች አንድ ላይ ተዳምረው ስለ ኢየሱስ ሕይወት ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንድናገኝ ያስችሉናል።
ማቴዎስ
የመጀመሪያውን ወንጌል የጻፈው እሱ ነው። ይህ የወንጌል ዘገባ ኢየሱስ ስለተለያዩ ነገሮች በተለይ ደግሞ ስለ አምላክ መንግሥት ባስተማራቸው ትምህርቶች ላይ ያተኩራል።
ማርቆስ
ከወንጌል ዘገባዎች መካከል አጭሩን የጻፈው እሱ ነው። የማርቆስ ወንጌል በርካታ አስደናቂ ክንውኖችን አጠር አጠር አድርጎ ይዘግባል።
ሉቃስ
በተለይ ስለ ጸሎት አስፈላጊነትና ኢየሱስ ለሴቶች ስላሳየው ደግነት ዘግቧል።
ዮሐንስ
ኢየሱስ ከቅርብ ወዳጆቹና ከሌሎች ሰዎች ጋር ያደረጋቸውን በርካታ ውይይቶች የጻፈ ሲሆን የእሱ ዘገባ ኢየሱስ ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ለማወቅ ይረዳናል።
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ኢየሱስ ነቢይ ነው፤ ከሌሎች ነቢያት የተለየ ነገር የለውም።”
አንተስ ምን ይመስልሃል?
ማጠቃለያ
ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ሰብኳል፤ ብዙ ተአምራትን ፈጽሟል፤ እንዲሁም በማንኛውም ሁኔታ ሥር ይሖዋን ታዟል።
ክለሳ
ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ዋነኛ ሥራው ምን ነበር?
ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ምን ያረጋግጣሉ?
ኢየሱስ የትኞቹን ጠቃሚ ትምህርቶች አስተምሯል?
ምርምር አድርግ
ኢየሱስ በዋነኝነት ያስተማረው ስለ የትኛው ጉዳይ ነው?
“የአምላክ መንግሥት—ኢየሱስ ትልቅ ቦታ የሰጠው ለምንድን ነው?” (መጠበቂያ ግንብ ጥቅምት 1, 2014)
ኢየሱስ ተአምራቱን በእርግጥ ፈጽሟል ብለን እንድናምን የሚያደርጉን ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?
ኢየሱስ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ሕይወት በመምራት ረገድ የተወው ምሳሌ በአንድ ሰው ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል?
በጊዜ ቅደም ተከተል የተቀመጡትን የኢየሱስ አገልግሎት ዋና ዋና ገጽታዎች ተመልከት።
“የኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት አበይት ክንውኖች” (አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ተጨማሪ መረጃ ሀ7)
a ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጽ ዝርዝር ማብራሪያ ከምዕራፍ 31-33 ላይ ይገኛል።