ምዕራፍ 46
የኢየሱስን ልብስ በመንካቷ ተፈወሰች
ማቴዎስ 9:18-22 ማርቆስ 5:21-34 ሉቃስ 8:40-48
አንዲት ሴት የኢየሱስን ልብስ በመንካቷ ተፈወሰች
ኢየሱስ ከዲካፖሊስ እንደተመለሰ የሚገልጽ ወሬ በገሊላ ባሕር ሰሜናዊ ምዕራብ ዳርቻ አካባቢ በሚኖሩ አይሁዳውያን ዘንድ ተዳረሰ። ኢየሱስ በቅርቡ ማዕበል በተነሳ ወቅት ነፋሱንና ውኃውን ጸጥ ማሰኘቱን ብዙዎች ሰምተው ይሆናል፤ አንዳንዶች ደግሞ አጋንንት ያደሩባቸውን ሰዎች መፈወሱን አውቀው ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ኢየሱስን ለመቀበል በባሕሩ አቅራቢያ ምናልባትም ቅፍርናሆም አካባቢ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ተሰበሰበ። (ማርቆስ 5:21) ኢየሱስ ከጀልባው ሲወርድ ሕዝቡ በከፍተኛ ጉጉት እየጠበቀው ነው።
ኢየሱስን በጉጉት ከሚጠብቁት ሰዎች አንዱ ኢያኢሮስ የተባለ የምኩራብ አለቃ ነው፤ ኢያኢሮስ በቅፍርናሆም ያለው ምኩራብ አለቃ ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ እግር ላይ ወድቆ “ትንሿ ልጄ በጠና ታምማለች። እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር፣ እባክህ መጥተህ እጅህን ጫንባት” በማለት ደጋግሞ ተማጸነው። (ማርቆስ 5:23) ኢያኢሮስ፣ 12 ዓመት የሆናትንና የሚወዳትን አንዲት ልጁን እንዲረዳለት ላቀረበው ልብ የሚነካ ልመና ኢየሱስ ምን ምላሽ ይሰጥ ይሆን?—ሉቃስ 8:42
ኢየሱስ ወደ ኢያኢሮስ ቤት እየሄደ ሳለ ስሜት የሚነካ ሌላ ሁኔታ አጋጠመው። አብረውት ከሚሄዱት ሰዎች ብዙዎቹ ኢየሱስ ሌላ ተአምር ሲፈጽም ያዩ እንደሆነ እያሰቡ ሊሆን ይችላል። በሕዝቡ መሃል ያለች አንዲት ሴት ግን የምታስበው ስላለባት ከባድ የጤና ችግር ነው።
ይህች አይሁዳዊት ለ12 ዓመታት ያህል ደም ሲፈስሳት ቆይቷል። እርዳታ ለማግኘት ወደተለያዩ ሐኪሞች የሄደች ሲሆን ያዘዙላትን ሕክምና ለመከታተል ያላትን ጥሪት ሁሉ ጨርሳለች። ይሁንና መፍትሔ አላገኘችም። እንዲያውም “ሕመሙ ባሰባት።”—ማርቆስ 5:26
ሕመሟ በጣም እንዳዳከማት ግልጽ ነው፤ ከዚህም ሌላ በሽታዋ የሚያሳፍር እንደሆነ መገመት አያቅትም። ስለ እንዲህ ዓይነቱ ሕመም በግልጽ አይወራም። ከዚህም በላይ በሙሴ ሕግ መሠረት ደም የሚፈስሳት ሴት ርኩስ ትሆናለች። ደም የነካውን ልብሷን ወይም እሷን የነካ ሰው ደግሞ መታጠብ ይኖርበታል፤ እስከ ማታ ድረስም ርኩስ ሆኖ ይቆያል።—ዘሌዋውያን 15:25-27
ይህች ሴት “ስለ ኢየሱስ የተወራውን” ስለሰማች ፈልጋ አገኘችው። ርኩስ እንደሆነች ተደርጋ ስለምትታይ የማንንም ትኩረት ሳትስብ በሕዝቡ መካከል ቀስ ብላ በማለፍ ወደ ኢየሱስ ሄደች፤ “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ” ብላ አስባለች። በእርግጥም የልብሱን ዘርፍ ስትነካ፣ ይፈስሳት የነበረው ደም ወዲያውኑ ሲቆም ታወቃት! ‘ያሠቃያት ከነበረው ሕመም ተፈወሰች።’—ማርቆስ 5:27-29
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “የነካኝ ማን ነው?” አለ። ሴትየዋ ይህን ስትሰማ ምን የተሰማት ይመስልሃል? ጴጥሮስ “መምህር፣ ሕዝቡ ከቦህ እየተጋፋህ ነው የሚሄደው” የሚል እርማት አዘል ሐሳብ ሰነዘረ። ለመሆኑ ኢየሱስ “የነካኝ ማን ነው?” ብሎ የጠየቀው ለምንድን ነው? “ኃይል ከእኔ እንደወጣ ስለታወቀኝ አንድ ሰው ነክቶኛል” በማለት ምክንያቱን ገለጸ። (ሉቃስ 8:45, 46) በእርግጥም ሴትየዋ ስትፈወስ ከኢየሱስ ኃይል ወጥቷል።
ሴትየዋ ሳይታወቅባት መሄድ እንዳልቻለች በተረዳች ጊዜ በፍርሃት እየተንቀጠቀጠች መጥታ በኢየሱስ ፊት ተደፋች። ከዚያም ስለ ሕመሟና እንዴት እንደተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት ተናገረች። ኢየሱስም “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ፤ ከሚያሠቃይ ሕመምሽም ተፈወሽ” በማለት በደግነት አጽናናት።—ማርቆስ 5:34
አምላክ ምድርን እንዲገዛ የመረጠው ንጉሥ፣ አፍቃሪና ሩኅሩኅ መሆኑን ከዚህ በግልጽ ማየት ይቻላል፤ ኢየሱስ ለሰዎች የሚያስብ ከመሆኑም ሌላ እነሱን ለመርዳት የሚያስችል ኃይል አለው!