ምዕራፍ 74
ስለ እንግዳ ተቀባይነትና ስለ ጸሎት የተሰጠ ትምህርት
ኢየሱስ ማርታና ማርያም ቤት ሄደ
በጸሎት መጽናት አስፈላጊ ነው
በደብረ ዘይት ተራራ ምሥራቃዊ ክፍል ከኢየሩሳሌም ሦስት ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ የምትገኝ ቢታንያ የምትባል መንደር አለች። (ዮሐንስ 11:18) ኢየሱስ ወደዚች መንደር የሄደ ሲሆን በዚያም ማርታና ማርያም የተባሉ ሁለት እህትማማቾች ቤት ገባ። እነሱም ሆኑ ወንድማቸው አልዓዛር የኢየሱስ ወዳጆች ናቸው፤ በመሆኑም ጥሩ አቀባበል አደረጉለት።
በእርግጥም መሲሑን በእንግድነት መቀበል ትልቅ ክብር ነው! ማርታ ኢየሱስን ጥሩ አድርጋ ለማስተናገድ ጓጉታለች፤ በመሆኑም ትልቅ ግብዣ ማዘጋጀት ጀመረች። ማርታ ሥራዋን ስታከናውን እህቷ ማርያም ኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጣ እያዳመጠችው ነው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ማርታ፣ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፣ እህቴ ሥራውን ሁሉ ለእኔ ጥላ ስትቀመጥ ምንም ግድ አይሰጥህም? መጥታ እንድታግዘኝ ንገራት እንጂ” አለችው።—ሉቃስ 10:40
ኢየሱስ ግን ማርያምን ከመውቀስ ይልቅ ማርታ ምግብ ለማቅረብ ከልክ በላይ በመጨነቋ እንዲህ ሲል መከራት፦ “ማርታ፣ ማርታ፣ ስለ ብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ፤ ደግሞም ትጠበቢያለሽ። ይሁንና የሚያስፈልገው ጥቂት ወይም አንድ ነገር ብቻ ነው። ማርያም በበኩሏ ጥሩ የሆነውን ድርሻ መርጣለች፤ ይህም ከእሷ አይወሰድም።” (ሉቃስ 10:41, 42) ኢየሱስ ብዙ ዓይነት ምግብ በመሥራት ረጅም ጊዜ ማጥፋት አስፈላጊ እንዳልሆነ ገልጿል። ቀለል ያለ ምግብ ማዘጋጀት በቂ ነው።
ማርታ ይህን ያደረገችው መልካም አስባ እንደሆነ የታወቀ ነው። ኢየሱስን ጥሩ አድርጋ ማስተናገድ ፈልጋለች። ሆኖም ስለምታቀርበው ምግብ ከመጠን በላይ በመጨነቋ፣ ከአምላክ ልጅ ግሩም ትምህርት የማግኘት አጋጣሚ እያመለጣት ነው! ኢየሱስ፣ ማርያም ጥሩ ምርጫ እንዳደረገች ጎላ አድርጎ ገልጿል፤ ይህ ምርጫዋ ዘለቄታዊ ጥቅም የሚያስገኝላት ከመሆኑም ሌላ ሁላችንም ልናስታውሰው የሚገባ ጥሩ ትምህርት ይሰጠናል።
በሌላ ወቅት ደግሞ ኢየሱስ አስፈላጊ የሆነ ትምህርት ሰጠ። አንድ ደቀ መዝሙር “ጌታ ሆይ፣ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት እንዳስተማራቸው ሁሉ አንተም እንዴት እንደምንጸልይ አስተምረን” ብሎ ጠየቀው። (ሉቃስ 11:1) ኢየሱስ ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በፊት በተራራው ስብከቱ ላይ ደቀ መዛሙርቱን እንዴት እንደሚጸልዩ አስተምሯቸው ነበር። (ማቴዎስ 6:9-13) ሆኖም ይህ ደቀ መዝሙር ያን ጊዜ በቦታው አልነበረ ይሆናል፤ ስለዚህ ኢየሱስ ዋና ዋና ነጥቦቹን ደገማቸው። ከዚያም በጸሎት የመጽናትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ተናገረ።
“ከእናንተ መካከል አንዱ፣ አንድ ወዳጅ አለው እንበል፤ በእኩለ ሌሊትም ወደ እሱ ሄዶ እንዲህ አለው፦ ‘ወዳጄ ሆይ፣ እባክህ ሦስት ዳቦ አበድረኝ፤ አንድ ወዳጄ ከመንገድ መጥቶብኝ የማቀርብለት ምንም ነገር አጣሁ።’ ወዳጁ ግን ከውስጥ ሆኖ ‘ባክህ አታስቸግረኝ። በሩ ተቆልፏል፤ ልጆቼም አብረውኝ ተኝተዋል። አሁን ተነስቼ ምንም ነገር ልሰጥህ አልችልም’ ይለዋል። እላችኋለሁ፣ ወዳጁ ስለሆነ ተነስቶ ባይሰጠው እንኳ ስለ ውትወታው ሲል ተነስቶ የፈለገውን ሁሉ ይሰጠዋል።”—ሉቃስ 11:5-8
ኢየሱስ፣ በታሪኩ ላይ ከተገለጸው ልመናን ሰምቶ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነ ግለሰብ ጋር ይሖዋን ማመሳሰሉ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ደግነት ለማድረግ ፈቃደኛ ያልነበረ አንድ ወዳጅ በተደጋጋሚ ጊዜ ልመና ሲቀርብለት ጥሩ ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ታማኝ አገልጋዮቹ ለሚያቀርቡለት ልባዊ ልመና ምንጊዜም ምላሽ እንደሚሰጥ መግለጹ ነው! ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “እላችኋለሁ፣ ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታሰልሱ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል። ምክንያቱም የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋል፤ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል፤ የሚያንኳኳም ሁሉ ይከፈትለታል።”—ሉቃስ 11:9, 10
ከዚያም ኢየሱስ ነጥቡን ይበልጥ ለማጉላት ሲል ፍጹም ያልሆኑ አባቶችን እንደ ምሳሌ ጠቀሰ፦ “ከመካከላችሁ ልጁ ዓሣ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ የሚሰጥ አባት ይኖራል? ወይስ እንቁላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋል? ታዲያ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባትማ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸው!” (ሉቃስ 11:11-13) አባታችን እኛን ለመስማትና የሚያስፈልገንን ለማሟላት ፈቃደኛ መሆኑን የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ማረጋገጫ ነው!