ምዕራፍ 76
ከአንድ ፈሪሳዊ ጋር ተመገበ
ኢየሱስ ግብዝ የሆኑትን ፈሪሳውያን አወገዘ
ኢየሱስ በይሁዳ እያለ አንድ ፈሪሳዊ ያቀረበለትን የምሳ ግብዣ ተቀበለ። (ሉቃስ 11:37, 38) ፈሪሳውያን ምግብ ከመብላታቸው በፊት እጃቸውን እስከ ክርናቸው ድረስ የመታጠብ ልማድ አላቸው። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላደረገም። (ማቴዎስ 15:1, 2) እርግጥ አንድ ሰው እጁን ያን ያህል መታጠቡ የአምላክን ሕግ እንዲጥስ አያደርገውም፤ ያም ቢሆን አምላክ በዚህ መንገድ እንዲታጠብ አይጠብቅበትም።
ፈሪሳዊው ኢየሱስ ይህን ወግ ባለመጠበቁ ተገረመ። ኢየሱስም ስሜቱ ስለገባው እንዲህ አለ፦ “እናንተ ፈሪሳውያን ጽዋውንና ሳህኑን ከውጭ በኩል ታጸዳላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በስግብግብነትና በክፋት የተሞላ ነው። እናንተ ማስተዋል የጎደላችሁ! የውስጡንስ የሠራው የውጭውን የሠራው አይደለም?”—ሉቃስ 11:39, 40
ኢየሱስ ያወገዘው ምግብ ከመብላት በፊት መታጠብን ሳይሆን ሃይማኖታዊ ግብዝነትን ነው። ወጉን ተከትለው እጃቸውን የሚታጠቡት ፈሪሳውያንም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ልባቸውን ከክፋት አላጠሩም። በመሆኑም ኢየሱስ “በልባችሁ ውስጥ ያሉትን ነገሮች ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፤ ያን ጊዜ በሁሉም ነገር ንጹሕ ትሆናላችሁ” ሲል መከራቸው። (ሉቃስ 11:41) ይህ ምንኛ እውነት ነው! አንድ ሰው ስጦታ የሚሰጠው በፍቅር ተነሳስቶ ከልቡ እንጂ ጻድቅ በመምሰል ሌሎችን ለማስደመም ሲል መሆን የለበትም።
እርግጥ እነዚህ ሰዎች አይሰጡም ማለት አይደለም። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ከኮሰረት፣ ከጤና አዳምና ከሌሎች አትክልቶች ሁሉ አሥራት ትሰጣላችሁ፤ ነገር ግን የአምላክን ፍትሕና እሱን መውደድን ችላ ትላላችሁ። እርግጥ አሥራት የመስጠት ግዴታ አለባችሁ፤ ሆኖም ሌሎቹን ነገሮች ችላ ማለት አልነበረባችሁም።” (ሉቃስ 11:42) የአምላክ ሕግ፣ ሕዝቡ ከምርታቸው አሥራት (አንድ አሥረኛ) እንዲሰጡ ያዛል። (ዘዳግም 14:22) ይህም ምግብን ለማጣፈጥ ከሚያገለግሉት እንደ ኮሰረትና ጤና አዳም ያሉ ቅመሞች አሥራት መስጠትን ያጠቃልላል። ፈሪሳውያን የእነዚህን ቅመሞች አሥራት እንኳ ምንም ሳያዛንፉ ይሰጣሉ፤ ሆኖም ፍትሕን እንደ ማድረግና ልክን አውቆ ከአምላክ ጋር እንደ መሄድ ካሉት በሕጉ ውስጥ የሚገኙ ይበልጥ አስፈላጊ ነገሮች ጋር በተያያዘስ ምን ያደርጋሉ?—ሚክያስ 6:8
ኢየሱስ ቀጥሎም እንዲህ አለ፦ “እናንተ ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ምክንያቱም በምኩራብ ከፊት መቀመጥ፣ በገበያ ቦታ ደግሞ ሰዎች እጅ እንዲነሷችሁ ትፈልጋላችሁ። ሰዎች ሳያውቁ በላዩ ላይ የሚሄዱበትን የተሰወረ መቃብር ስለምትመስሉ ወዮላችሁ!” (ሉቃስ 11:43, 44) በእርግጥም ሰዎች እንዲህ ያሉ መቃብሮችን ሳያውቁ ሊነኩና በሕጉ መሠረት ሊረክሱ ይችላሉ። ኢየሱስ ይህን ያለው የፈሪሳውያን ርኩሰት በግልጽ የሚታይ አለመሆኑን ለማጉላት ነው።—ማቴዎስ 23:27
የአምላክን ሕግ በሚገባ የሚያውቅ አንድ ሰው “መምህር፣ እንዲህ ስትል እኮ እኛንም መስደብህ ነው” ሲል ቅሬታ አሰማ። ይሁንና እነዚህ ሰዎች ሕዝቡን መርዳት እንዳልቻሉ ሊገነዘቡ ይገባል። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የሕጉ አዋቂዎችም ወዮላችሁ! ምክንያቱም ለመሸከም የሚከብድ ሸክም በሰው ላይ ትጭናላችሁ፤ እናንተ ራሳችሁ ግን ሸክሙን በጣታችሁ እንኳ አትነኩትም። አባቶቻችሁ የገደሏቸውን ነቢያት መቃብሮች ስለምትሠሩ ወዮላችሁ!”—ሉቃስ 11:45-47
ኢየሱስ የጠቀሰው ሸክም፣ በቃል የሚተላለፈውን ወግና ፈሪሳውያን ለሕጉ የሰጡትን ትርጓሜ የሚያመለክት ነው። እነዚህ ሰዎች የሕዝቡን ሕይወት ከማቅለል ይልቅ እንደ ከባድ ሸክም የሆኑትን ሕጎች ሕዝቡ የግድ መጠበቅ እንዳለበት ያስተምራሉ። አባቶቻቸው ከአቤል ዘመን ጀምሮ የአምላክን ነቢያት ገድለዋል። እነሱ ደግሞ ለነቢያት መቃብር በመሥራት የሚያከብሯቸው ለመምሰል ይሞክራሉ፤ ሆኖም በዝንባሌያቸውም ሆነ በድርጊታቸው የአባቶቻቸውን ፈለግ እየተከተሉ ነው። ከሁሉ የላቀውን የአምላክ ነቢይ እንኳ ለመግደል ተነስተዋል። ኢየሱስ፣ ይህ ትውልድ በአምላክ ፊት ተጠያቂ እንደሆነ ገለጸ። ኢየሱስ የተናገረው ነገር ከ38 ዓመታት ገደማ በኋላ ይኸውም በ70 ዓ.ም. ተፈጽሟል።
ኢየሱስ ንግግሩን ሲቀጥል እንዲህ አለ፦ “እናንተ የሕጉ አዋቂዎች ወዮላችሁ! ምክንያቱም የእውቀትን ቁልፍ ነጥቃችሁ ወስዳችኋል። እናንተ ራሳችሁ አልገባችሁም፤ ለመግባት የሚሞክሩትንም ትከለክላላችሁ።” (ሉቃስ 11:52) የአምላክን ቃል ለሕዝቡ የማብራራት ኃላፊነት ያለባቸው እነዚህ ሰዎች ሕዝቡ ቃሉን ማወቅና መረዳት የሚችልበትን አጋጣሚ እንዲያጣ አድርገውታል።
ፈሪሳውያንና ጸሐፍት ምን ተሰማቸው? ኢየሱስ ወጥቶ ሲሄድ ክፉኛ ይቃወሙትና የጥያቄ መዓት ያዥጎደጉዱበት ጀመር። ጥያቄ የሚያቀርቡለት ሊማሩ ፈልገው አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስን ለማስያዝ የሚያስችላቸው ነገር እንዲናገር ለማድረግ እየሞከሩ ነው።