ዘላለማዊነትን በማሰብ አካሄድን ከአምላክ ጋር ማድረግ
“እኛም በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም እንሄዳለን።”—ሚክያስ 4:5
1. ይሖዋ “የዘላለም ንጉሥ” ተብሎ ሊጠራ የሚችለው ለምንድን ነው?
ይሖዋ አምላክ መጀመሪያ የለውም። ከዘላለም ጀምሮ የነበረ በመሆኑ ‘በዘመናት የሸመገለ’ ተብሎ መጠራቱ የተገባ ነው። (ዳንኤል 7:9, 13) ወደፊትም ይሖዋ ለዘላለም ይኖራል። “የዘላለም ንጉሥ” እሱ ብቻ ነው። (ራእይ 10:6፤ 15:3 NW) እንዲሁም በዓይኖቹ ፊት ሺህ ዓመት “እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን፣ እንደ ሌሊትም ትጋት” ነው።—መዝሙር 90:4
2. (ሀ) አምላክ ለታዛዥ የሰው ልጆች ያለው ዓላማ ምንድን ነው? (ለ) ተስፋዎቻችንና እቅዶቻችን በምን ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ አለብን?
2 ሕይወትን የሰጠው አካል ዘላለማዊ ስለሆነ ለመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ጥንድ ማለትም ለአዳምና ለሔዋን በገነት ውስጥ ማለቂያ የሌለው ሕይወት ሊሰጣቸው ይችል ነበር። ይሁን እንጂ አዳም ባለመታዘዙ ምክንያት ለዘላለም የመኖር መብቱን ከማጣቱም በላይ ለዘሮቹ ኃጢአትንና ሞትን አስተላልፏል። (ሮሜ 5:12) ሆኖም የአዳም ማመፅ የአምላክን የመጀመሪያ ዓላማ አላጨናገፈውም። ታዛዥ የሰው ልጆች ለዘላለም እንዲኖሩ የይሖዋ ፈቃድ ነው፤ ይህንንም ዓላማውን ደግሞ ያለምንም ጥርጥር ዳር ያደርሰዋል። (ኢሳይያስ 55:11) ስለዚህ ተስፋዎቻችንንና ዕቅዶቻችንን ዘላለማዊነትን በአእምሮ ይዞ ይሖዋን በማገልገል ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ ምንኛ የተገባ ነው። በአእምሯችን “የይሖዋን ቀን” አቅርበን መመልከት የምንፈልግ ቢሆንም ግባችን ከአምላክ ጋር ለዘላለም መጓዝ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።—2 ጴጥሮስ 3:12
ይሖዋ በወሰነው ጊዜ እርምጃ ይወስዳል
3. ይሖዋ ዓላማዎቹን የሚፈጽምበት ‘የተወሰነ ዘመን’ እንዳለው እንዴት እናውቃለን?
3 አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር ያደረግን እንደመሆናችን መጠን የአምላክን ፈቃድ የመፈጸም ከፍተኛ ጉጉት አለን። ይሖዋ ልክ በወሰነው ጊዜ ያሰበውን ነገር በመፈጸም ረገድ ተወዳዳሪ የማይገኝለት አምላክ ነው፤ ዓላማዎቹን በወሰነው ጊዜ እንደሚፈጽም ቅንጣት ታክል አንጠራጠርም። ለምሳሌ ያህል “የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር . . . ልጁን ላከ።” (ገላትያ 4:4) ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ የተመለከታቸው ትንቢታዊ ነገሮች የሚፈጸሙበት ‘የተወሰነ ዘመን’ እንዳለ ተነግሮታል። (ራእይ 1:1–3) ‘ሙታን ፍርድ የሚያገኙበት የተወሰነ ዘመን’ አለ። (ራእይ 11:18) ሐዋርያው ጳውሎስ ከዛሬ 1,900 ዓመታት በፊት አምላክ ‘በዓለም ላይ በጽድቅ ለመፍረድ ቀን እንደቀጠረ’ በመንፈስ ተገፋፍቶ ተናግሯል።—ሥራ 17:31
4. ይሖዋ ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ለማጥፋት እንደሚፈልግ እንዴት እናውቃለን?
4 ይሖዋ ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ ስሙ እየተነቀፈ በመሆኑ ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ወደ ፍጻሜው ያመጣዋል። ክፉዎች ለምልመዋል። (መዝሙር 92:7) በንግግራቸውም ሆነ በድርጊታቸው አምላክን ይሰድቡታል፤ እንዲሁም አገልጋዮቹ ሲሰደቡና ሲሰደዱ መመልከት ክፉኛ ያንገበግበዋል። (ዘካርያስ 2:8) ይሖዋ ጠቅላላውን የሰይጣን ድርጅት በቅርቡ ለማጥፋት መወሰኑ ምንም አያስደንቅም! አምላክ ይህ የሚሆንበትን ትክክለኛ ጊዜ የወሰነ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መፈጸማቸው ደግሞ ‘በፍጻሜ ዘመን’ ውስጥ እንደምንኖር በግልጽ ያሳያሉ። (ዳንኤል 12:4) እሱን የሚወዱትን ሁሉ ለመባረክ በቅርቡ እርምጃ ይወስዳል።
5. ሎጥና ዕንባቆም በዙሪያቸው ስላለው ሁኔታ እንዴት ተሰምቷቸው ነበር?
5 ጥንት የነበሩ የይሖዋ አገልጋዮች ክፋት የሚያከትምበትን ጊዜ ለማየት ይናፍቁ ነበር። ጻድቁ ሎጥ ‘በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ ተጨንቆ ነበር።’ (2 ጴጥሮስ 2:7) በዙሪያው በነበረው ሁኔታ በማዘኑ ነቢዩ ዕንባቆም እንዲህ ሲል አቤቱታ አቅርቧል:- “አቤቱ፣ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ስለ ግፍ ወደ አንተ እጮኻለሁ፣ አንተም አታድንም። በደልንስ ስለ ምን አሳየኸኝ? ጠማምነትንስ ስለ ምን ትመለከታለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ ነው፤ ጠብና ክርክር ይነሣሉ።”—ዕንባቆም 1:2, 3
6. ይሖዋ ለዕንባቆም ጸሎት ምን ምላሽ ሰጠ? ከዚህስ ምን ልንማር እንችላለን?
6 ይሖዋ በከፊል በሚከተሉት ቃላት ለዕንባቆም መልስ ሰጠ:- “ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፣ ወደ ፍጻሜው ይቸኩላል፣ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም።” (ዕንባቆም 2:3) በዚህ መንገድ አምላክ ‘የወሰነው ጊዜ’ ሲደርስ እርምጃ እንደሚወስድ ግልጽ አድርጓል። ጊዜው የዘገየ ቢመስልም ይሖዋ ያለአንዳች ጥርጥር ዓላማውን ይፈጽማል!—2 ጴጥሮስ 3:9
በማይቀዘቅዝ ቅንዓት ማገልገል
7. ኢየሱስ የይሖዋ ቀን የሚመጣበትን ትክክለኛ ጊዜ ባያውቅም አገልግሎቱን የቀጠለው እንዴት ነበር?
7 አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር በማድረግ በቅንዓት ለመመላለስ ይሖዋ ነገሮችን የሚያከናውንበትን ትክክለኛ ጊዜ የግድ ማወቅ ያስፈልገናልን? የለም አያስፈልገንም። አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከቱ። ኢየሱስ በሰማይ የሆነው የአምላክ ፈቃድ በምድርም የሚሆንበትን ጊዜ የማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ነበረው። እንዲያውም ክርስቶስ ተከታዮቹ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ኢየሱስ ይህ ጥያቄ መልስ እንደሚያገኝ ቢያውቅም ነገሮች የሚከናወኑበትን ትክክለኛ ጊዜ ግን አያውቅም ነበር። የዚህን የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ አስመልክቶ በተናገረው ታላቅ ትንቢቱ ላይ እንዲህ ብሏል:- “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም።” (ማቴዎስ 24:36) ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክን ዓላማዎች በማስፈጸም ረገድ አቢይ ሚና የሚጫወት እንደ መሆኑ መጠን በሰማያዊ አባቱ ጠላቶች ላይ በሚወሰደው የቅጣት እርምጃ ቀጥተኛ ተሳትፎ ይኖረዋል። ሆኖም ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አምላክ መቼ እርምጃ እንደሚወስድ እንኳን አያውቅም ነበር። ታዲያ ይህ ለይሖዋ አገልግሎት የነበረውን ቅንዓት ቀንሶበታልን? በፍጹም! ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን በቅንዓት ሲያጸዳ ተመልክተው “ደቀ መዛሙርቱም:- የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ አሰቡ።” (ዮሐንስ 2:17፤ መዝሙር 69:9) ኢየሱስ በምድር ላይ እንዲያከናውን የተሰጠውን ሥራ በመፈጸም ራሱን ሙሉ በሙሉ ከማስጠመዱም በላይ ሥራውን ያከናወነው በማይቀዘቅዝ ቅንዓት ነበር። በተጨማሪም አምላክን ያገለገለው ዘላለማዊነትን በአእምሮው በመያዝ ነው።
8, 9. ደቀ መዛሙርቱ መንግሥቱ ስለሚመለስበት ጊዜ ሲጠይቁ ምን ምላሽ አገኙ? እንዴትስ ተሰማቸው?
8 ይህ ነገር በክርስቶስ ደቀ መዛሙርትም ላይ ታይቷል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ከጥቂት ጊዜ በፊት አግኝቷቸው ነበር። ታሪኩ እንዲህ ይላል:- “እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ:- ጌታ ሆይ፣ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን? ብለው ጠየቁት።” ልክ እንደ ጌታቸው እነርሱም የመንግሥቱን መምጣት ይናፍቁ ነበር። ይሁንና ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ:- “አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።”—ሥራ 1:6–8
9 ደቀ መዛሙርቱ በዚህ መልስ ተስፋ እንደቆረጡ የሚያሳይ ምንም ነገር አናገኝም። ከዚህ ይልቅ የስብከቱን ሥራ በቅንዓት በማከናወን ተጠምደው ነበር። በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታቸው አጥለቀለቋት። (ሥራ 5:28) እንዲሁም በ30 ዓመታት ውስጥ የስብከት እንቅስቃሴያቸው እጅግ ከመስፋፋቱ የተነሣ ጳውሎስ፣ ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ” ተሰብኳል ብሎ ለመናገር ችሎ ነበር። (ቆላስይስ 1:23) ደቀ መዛሙርቱ በተሳሳተ መንገድ እንደጠበቁት መንግሥት ‘ለእስራኤል ባይመለስም’ እንዲሁም በእነሱ የሕይወት ዘመን መንግሥቱ በሰማይ ባይቋቋምም ዘላለማዊነትን በአእምሮአቸው በመያዝ ይሖዋን በቅንዓት ማገልገላቸውን ቀጥለዋል።
ውስጣዊ ግፊታችንን መመርመር
10. አምላክ የሰይጣንን ሥርዓት የሚያጠፋበትን ጊዜ አለማወቃችን ምን ለማረጋገጥ ያስችለናል?
10 በዚህ ዘመን የሚገኙ የይሖዋ አገልጋዮችም የዚህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ማየት ይናፍቃሉ። ይሁን እንጂ ከሁሉ በላይ የሚያሳስበን ነገር የእኛ ከጥፋት ድኖ አምላክ ወዳዘጋጀው አዲስ ዓለም መግባት አይደለም። የይሖዋ ስም ተቀድሶና ሉዓላዊነቱ ተረጋግጦ ማየት እንፈልጋለን። በዚህ ምክንያት አምላክ የሰይጣንን ሥርዓት ለማጥፋት የቀጠረውን ‘ቀን ወይም ሰዓት’ ስላልነገረን ልንደሰት እንችላለን። ይህ ሁኔታ አካሄዳችንን ለዘላለም ከአምላክ ጋር ለማድረግ የቆረጥነው በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረቱ የአጭር ጊዜ ግቦች ስላሉን ሳይሆን አምላክን ስለምንወደው እንደሆነ ለማረጋገጥ ያስችለናል።
11, 12. የኢዮብ ንጹሕ አቋም ጠባቂነት ፈተና የደረሰበት በምን መንገድ ነበር? ይህ ፈተና እኛንም ጭምር የሚነካውስ እንዴት ነው?
11 በተጨማሪም ንጹሕ አቋማችንን መጠበቃችን ዲያብሎስ ቅን የነበረው ኢዮብ ብሎም እንደ እሱ ያሉ የሰው ልጆች አምላክን የሚያገለግሉት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ነው በማለት ያቀረበው ክስ ሐሰት መሆኑን ለማረጋገጥ ይረዳል። ይሖዋ አገልጋዩ ኢዮብ እንከን የሌለው፣ ቅንና አምላክን የሚፈራ መሆኑን ከተናገረ በኋላ ሰይጣን በክፋት እንዲህ አለ:- “በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን? እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን ሁሉ አላጠርህለትምን? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፣ ከብቱም በምድር ላይ በዝቶአል። ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።” (ኢዮብ 1:8–11) ኢዮብ በፈተና ሥር ንጹህ አቋሙን እንደጠበቀ መቀጠሉ ይህ ተንኮል ያዘለ ክስ ሐሰት መሆኑን አረጋግጧል።
12 እኛም በተመሳሳይ ንጹህ አቋማችንን ጠብቀን የምንመላለስ ከሆነ ሰይጣን፣ ሽልማት እንደምናገኝ እርግጠኞች ስለሆንን ብቻ አምላክን እንደምናገለግል በማድረግ የሚያነሳው ማንኛውም ክስ ሐሰት መሆኑን ለማረጋገጥ እንችላለን። አምላክ በክፉዎች ላይ የቅጣት እርምጃ የሚወስድበትን ትክክለኛ ጊዜ አለማወቃችን በእርግጥ ይሖዋን የምንወድና በመንገዱም ለዘላለም ለመመላለስ የምንፈልግ መሆናችንን ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ ይሰጠናል። ለአምላክ ታማኞች እንደሆንንና እሱ ነገሮችን በሚያከናውንበት መንገድ ላይ እምነት እንዳለን ያሳያል። ከዚህም በላይ ቀኑንና ሰዓቱን አለማወቃችን በሌሊት እንደሚመጣ ሌባ መጨረሻው በማንኛውም ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል ስለምንገነዘብ ትጉና በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን ለመቀጠል ይረዳናል። (ማቴዎስ 24:42–44) ዕለት ዕለት አካሄዳችንን ከይሖዋ ጋር በማድረግ ልቡን ደስ እናሰኛለን፤ እንዲሁም እየሰደበው ላለው ለዲያብሎስ መልስ እንሰጣለን።—ምሳሌ 27:11
ዕቅዳችሁ ዘላለማዊ ይሁን!
13. መጽሐፍ ቅዱስ ለወደፊቱ ጊዜ እቅድ ማውጣትን በተመለከተ ምን ይላል?
13 አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር ያደረጉ ሰዎች ለወደፊቱ ጊዜ ምክንያታዊ ዕቅዶችን ማውጣት ጥበብ እንደሆነ ይገነዘባሉ። የዕድሜ መግፋት የሚያስከትላቸውን ችግሮችና የአቅም ገደቦች ከግምት ውስጥ በማስገባት ብዙ ሰዎች ለኋለኛ የሕይወት ዘመናቸው የሚሆናቸውን ገንዘብ ለማጠራቀም የወጣትነት ጉልበታቸውን በጥሩ ሁኔታ ለመጠቀም ይጥራሉ። ታዲያ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው የእኛ የወደፊቱ መንፈሳዊ ሁኔታስ? ምሳሌ 21:5 እንዲህ ይላል:- “የትጉህ አሳብ ወደ ጥጋብ ይደርሳል ችኩል ሰው ሁሉ ግን ለመጉደል ይቸኩላል።” ዘላለማዊነትን በአእምሮ በመያዝ ማቀድ በእርግጥ ጠቃሚ ነው። የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ መቼ እንደሚመጣ በትክክል ስለማናውቅ ወደፊት ስለሚያስፈልጉን ነገሮች በጥቂቱ ማሰብ ይኖርብናል። ሆኖም ሚዛናዊ በመሆን በሕይወታችን ውስጥ ለመለኮታዊ ነገሮች አንደኛ ቦታ እንስጥ። እምነት የሌላቸው ሰዎች ትኩረትን የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ላይ ማድረግ አርቆ አለማሰብ እንደሆነ አድርገው ሊደመድሙ ይችላሉ። በእርግጥ አርቆ አለማሰብ ነውን?
14, 15. (ሀ) ለወደፊቱ ጊዜ እቅድ ማውጣትን በተመለከተ ኢየሱስ ምን ምሳሌ ተናግሯል? (ለ) በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ባለ ጠጋ አርቆ አስተዋይነት የጎደለው ለምን ነበር?
14 ኢየሱስ ይህን ሁኔታ ጥሩ አድርጎ የሚያስረዳ አንድ ምሳሌ ተናግሯል። እንዲህ አለ:- “አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያም ሆነችለት። እርሱም:- ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ። እንዲህ አደርጋለሁ፤ ጐተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፣ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤ ነፍሴንም:- አንቺ ነፍሴ፣ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፣ ብዪ፣ ጠጪ፣ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ። እግዚአብሔር ግን:- አንተ ሰነፍ፣ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? አለው። ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፣ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው።”—ሉቃስ 12:16–21
15 ኢየሱስ ባለ ጠጋ የነበረው ሰው ወደፊት ምንም ዓይነት ቁሳዊ ችግር እንዳያሰጋው በማሰብ ጠንክሮ መሥራቱን መቃወሙ ነበርን? ቅዱሳን ጽሑፎች ጠንክሮ መሥራትን ስለሚያበረታቱ መቃወሙ አልነበረም። (2 ተሰሎንቄ 3:10) የሀብታሙ ሰው ስህተት “በእግዚአብሔር ዘንድ ባለ ጠጋ” ለመሆን የሚያስፈልገውን ነገር አለማድረጉ ነበር። ቁሳዊ ሀብቱን ለብዙ ዓመታት ሊጠቀምበት ቢችልም እንኳ በመጨረሻ መሞቱ አይቀርም ነበር። ስለ ዘላለማዊነት የማያስብ አርቆ አስተዋይነት የጎደለው ሰው ነበር።
16. አስተማማኝ የወደፊት ጊዜ ለማግኘት በይሖዋ ላይ መታመን የምንችለው ለምንድን ነው?
16 ዘላለማዊነትን በአእምሮ በመያዝ አካሄድን ከአምላክ ጋር ማድረግ ተግባራዊና አርቆ አስተዋይነት ነው። ለወደፊቱ ጊዜ እቅድ ለማውጣት የሚያስችል ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው። ትምህርትን፣ ሥራንና የቤተሰብ ኃላፊነቶችን በተመለከተ ተግባራዊ እቅዶችን ማውጣቱ ጥበብ ቢሆንም ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን በፍጹም እንደማይተዋቸው ሁልጊዜ ማስታወስ አለብን። ንጉሥ ዳዊት “ጎለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 37:25) በተመሳሳይም ኢየሱስ አስቀድመው መንግሥቱን ለሚፈልጉና በይሖዋ የጽድቅ መንገዶች ለሚመላለሱ ሰዎች አምላክ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚያቀርብ ማረጋገጫ ሰጥቷል።—ማቴዎስ 6:33
17. መጨረሻው መቅረቡን እንዴት እናውቃለን?
17 አምላክን የምናገለግለው ዘላለማዊነትን በአእምሮአችን በመያዝ ቢሆንም የይሖዋን ቀን አቅርበን መመልከታችንን እንቀጥላለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መፈጸም ያ ቀን መቅረቡን በግልጽ ያሳያል። ይህ መቶ ዘመን በጦርነት፣ በበሽታ፣ በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በምግብ እጥረት፣ በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ በሚደርሰው ስደትና የአምላክ መንግሥት ምሥራች በዓለም ዙሪያ በመሰበኩ ተለይቶ የሚታወቅ ነው። እነዚህ ሁሉ የዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ገጽታዎች ናቸው። (ማቴዎስ 24:7–14፤ ሉቃስ 21:11) ዓለም ‘ራሳቸውን በሚወዱ፣ ገንዘብን በሚወዱ፣ ትምክህተኛ፣ ትዕቢተኛ፣ ተሳዳቢ በሆኑ፣ ለወላጆቻቸው በማይታዘዙ፣ በማያመሰግኑ፣ ቅድስና በሌላቸው፣ ፍቅር በሌላቸው፣ ዕርቅን በማይሰሙ፣ በሐሜተኞች፣ ራሳቸውን በማይገዙ፣ በጨካኞች፣ መልካም የሆነውን በማይወዱ፣ በከዳተኞች፣ በችኩሎች፣ በትዕቢት በተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን በሚወዱ’ ሰዎች የተሞላ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን በእነዚህ አስጨናቂ የመጨረሻ ቀናት ሕይወት አስቸጋሪ ይሆንብናል። የይሖዋ መንግሥት ክፋትን ሁሉ የሚያስወግድበትን ቀን ለማየት ምንኛ እንናፍቃለን! እስከዚያው ድረስ ግን ዘላለማዊነትን በአእምሮአችን በመያዝ አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔያችን ይሁን።
ፍጻሜ የሌለውን ሕይወት በአእምሮ በመያዝ ማገልገል
18, 19. ጥንት የነበሩ የታመኑ ሰዎች ዘላለማዊነትን በአእምሯቸው ይዘው አምላክን እንዳገለገሉ የሚያሳየው ምንድን ነው?
18 አካሄዳችንን ከይሖዋ ጋር ስናደርግ አቤል፣ ሄኖክ፣ ኖኅ፣ አብርሃምና ሣራ ያሳዩትን እምነት እናስብ። ጳውሎስ እነሱን ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፣ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፤ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ።” (ዕብራውያን 11:13) እነዚህ የታመኑ ሰዎች “የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር [ለማግኘት] ይናፍቃሉ።” (ዕብራውያን 11:16) በአምላክ መሲሐዊ መንግሥት አገዛዝ ሥር ያለውን የተሻለ ቦታ ለማግኘት በእምነት ሲጠባበቁ ቆይተዋል። አምላክ በዚያ ቦታ ማለትም በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር በሚኖረው ምድራዊ ገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት በመስጠት እንደሚክሳቸው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።—ዕብራውያን 11:39, 40
19 ነቢዩ ሚክያስ የይሖዋ ሕዝቦች አምላክን ለዘላለም ለማምለክ ያደረጉትን ቁርጥ ውሳኔ ገልጿል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሕዝብም ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳል፣ እኛም በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም እንሄዳለን።” (ሚክያስ 4:5) ሚክያስ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል። ይህ ነቢይ በአዲሱ ዓለም ውስጥ በትንሣኤ ሲነሣ አካሄዱን ከአምላክ ጋር ማድረጉን ለዘላለም እንደሚቀጥል ምንም አያጠራጥርም። በዚህ የመጨረሻ ዘመን ውስጥ ለምንኖረው ለእኛ ይህ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!
20. ምን ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔያችን ሊሆን ይገባል?
20 ይሖዋ ለስሙ የምናሳየውን ፍቅር ያደንቃል። (ዕብራውያን 6:10) በዚህ ዲያብሎስ በሚቆጣጠረው ዓለም ውስጥ በእሱ ዘንድ ንጹህ አቋምን ጠብቆ መመላለስ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ያውቃል። ይሁን እንጂ “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።” (1 ዮሐንስ 2:17፤ 5:19) እንግዲያው በይሖዋ እርዳታ ከቀን ወደ ቀን የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት ለመቋቋም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። አስተሳሰባችንና የምንከተለው የሕይወት መንገድ አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ቃል በገባልን አስደናቂ በረከቶች ላይ ያተኮረ ይሁን። ዘላለማዊነትን በአእምሮአችን በመያዝ አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር ካደረግን እነዚህን በረከቶች ልናገኝ እንችላለን።—ይሁዳ 20, 21
[ምን ብለህ ትመልሳለህ?]
◻ አምላክ ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
◻ ይሖዋ ይህን ዓመፀኛ ዓለም ለማጥፋት እስከ አሁን እርምጃ ያልወሰደው ለምንድን ነው?
◻ አምላክ እርምጃ የሚወስድበትን ትክክለኛ ጊዜ አለማወቃችን ቅንዓታችንን ሊያቀዘቅዘው የማይገባው ለምንድን ነው?
◻ ዘላለማዊነትን በአእምሮ በመያዝ አካሄድን ከአምላክ ጋር ማድረግ ያሉት አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አካሄድን ከአምላክ ጋር ማድረግ እንደ ቀድሞዎቹ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እሱን በቅንዓት ማገልገልን ይጠይቃል