ልባችሁ በመንፈሳዊ ሀብት ላይ ያተኮረ ይሁን
“ሀብታችሁ ባለበት ልባችሁም በዚያ ይሆናል።” —ሉቃስ 12:34
1, 2. (ሀ) ይሖዋ ከሰጠን መንፈሳዊ ሀብቶች መካከል ሦስቱ ምንድን ናቸው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ የይሖዋን ያህል ባለጸጋ የለም። (1 ዜና 29:11, 12) ይሖዋ ለጋስ አባት እንደመሆኑ መጠን ብዙ መንፈሳዊ ሀብት ሰጥቶናል። ይሖዋ ከሰጠን መንፈሳዊ ሀብቶች መካከል (1) የአምላክ መንግሥት፣ (2) ሕይወት አድን የሆነው አገልግሎታችን እንዲሁም (3) በቃሉ ውስጥ የሚገኙት ውድ እውነቶች ይገኙበታል፤ ይሖዋ እነዚህን ውድ ሀብቶች ስለሰጠን በጣም አመስጋኞች ነን! ይሁንና ካልተጠነቀቅን ለእነዚህ ውድ ሀብቶች ያለንን አድናቆት ልናጣና እንደ ተራ ነገር ልንመለከታቸው እንችላለን። እነዚህን ውድ ሀብቶች ከፍ አድርገን መመልከታችንን ልንቀጥል የምንችለው በሚገባ ስንጠቀምባቸውና ለእነሱ ያለን ፍቅር እያደገ እንዲሄድ የማያቋርጥ ጥረት ስናደርግ ነው። ኢየሱስ “ሀብታችሁ ባለበት ልባችሁም በዚያ ይሆናል” በማለት ተናግሯል።—ሉቃስ 12:34
2 ለአምላክ መንግሥት፣ ለአገልግሎታችንም ሆነ ለእውነት ፍቅርና አድናቆት ማዳበር እንዲሁም ፍቅራችንና አድናቆታችን ሳይከስም እንዲቆይ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ይህን ስንመረምር፣ በግለሰብ ደረጃ ለእነዚህ መንፈሳዊ ሀብቶች ያለህን ፍቅር ማሳደግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ አሰላስል።
እንደ ውድ ዕንቁ የሆነው የአምላክ መንግሥት
3. ኢየሱስ በምሳሌው ውስጥ የጠቀሰው ነጋዴ ያንን ውድ ዕንቁ ለማግኘት ሲል ምን ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኗል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
3 ማቴዎስ 13:45, 46ን አንብብ። ኢየሱስ ዕንቁ ስለሚፈልግ አንድ ነጋዴ የሚገልጽ ምሳሌ ተናግሮ ነበር። ይህ ነጋዴ ለብዙ ዓመታት በመቶ የሚቆጠሩ ዕንቁዎችን ገዝቶና ሸጦ መሆን አለበት። ይሁን እንጂ አሁን ያገኘው ዕንቁ በጣም ውብ ከመሆኑ የተነሳ ገና ሲያየው እጅግ ተደሰተ። ይህን ውድ ዕንቁ ለመግዛት ሲል ያለውን ሁሉ ለመሸጥ ፈቃደኛ ሆኗል። ይህ ነጋዴ ዕንቁውን ምን ያህል ከፍ አድርጎ እንደተመለከተው መገመት ትችላለህ።
4. ነጋዴው ዕንቁውን የወደደውን ያህል እኛም የአምላክን መንግሥት የምንወድ ከሆነ ምን ለማድረግ እንነሳሳለን?
4 እኛስ ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው እውነት በጣም ውድ በሆነው ዕንቁ ሊመሰል ይችላል። ነጋዴው ያንን ዕንቁ የወደደውን ያህል እኛም የአምላክን መንግሥት የምንወድ ከሆነ የመንግሥቱ ተገዢዎች ለመሆን ስንል ማንኛውንም ነገር ለመተው ፈቃደኛ እንሆናለን። (ማርቆስ 10:28-30ን አንብብ።) በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ ሁለት ሰዎችን እንመልከት።
5. ዘኬዎስ ለአምላክ መንግሥት ሲል ምን ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኗል?
5 ዘኬዎስ የቀረጥ ሰብሳቢዎች አለቃ የነበረ ሲሆን ሰዎችን በመበዝበዝ ብዙ ሀብት አካብቶ ነበር። (ሉቃስ 19:1-9) ይሁንና ይህ ኃጢአተኛ ሰው ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ሲሰብክ ሰማ፤ በዚህ ጊዜ የሰማው ነገር ያለውን ውድ ዋጋ ስለተገነዘበ አፋጣኝ እርምጃ ወሰደ። እንዲህ ብሏል፦ “ጌታ ሆይ፣ ካለኝ ሀብት ግማሹን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ከሰው የቀማሁትንም ሁሉ አራት እጥፍ እመልሳለሁ።” ዘኬዎስ ተገቢ ባልሆነ መንገድ የሰበሰበውን ገንዘብ የመለሰ ከመሆኑም ሌላ ለቁሳዊ ነገሮች ያለውን አመለካከት ለማስተካከል ፈቃደኛ ሆኗል።
6. ሮዝ የአምላክ መንግሥት ተገዢ ለመሆን ስትል ምን ለውጥ አደረገች? ይህን ለውጥ ለማድረግ ያነሳሳትስ ምንድን ነው?
6 ሮዝa የተባለች አንዲት ሴት ከጥቂት ዓመታት በፊት የመንግሥቱን መልእክት በሰማችበት ወቅት ሌዝቢያን (የሴት ፍቅረኛ ያላት) ነበረች። እንዲያውም ለግብረ ሰዶማውያን መብት የሚሟገት አንድ ድርጅት ፕሬዚዳንት ነበረች። ይሁንና ሮዝ መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው እውነት ያለውን ውድ ዋጋ ተገነዘበች። ሆኖም በሕይወቷ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋት ነበር። (1 ቆሮ. 6:9, 10) በድርጅቱ ውስጥ ያላትን ቦታ የለቀቀች ከመሆኑም ሌላ ከሴት ፍቅረኛዋ ጋር የነበራትን ግንኙነት አቋረጠች። ሮዝ በ2009 የተጠመቀች ሲሆን በቀጣዩ ዓመት የዘወትር አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። ለይሖዋና ለመንግሥቱ ያላት ፍቅር ከየትኛውም ሥጋዊ ምኞት የበለጠ ኃይል ስለነበረው እንዲህ ያለ ትልቅ ለውጥ ማድረግ ችላለች።—ማር. 12:29, 30
7. ለአምላክ መንግሥት ያለን ፍቅር እንዳይጠፋ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
7 አብዛኞቻችን የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ለመሆን ስንል በሕይወታችን ውስጥ ትላልቅ ለውጦችን አድርገናል። (ሮም 12:2) ይሁንና ይህ ብቻውን በቂ አይደለም። ለአምላክ መንግሥት ያለን ፍቅር እንዳይጠፋ ከፈለግን እንደ ፍቅረ ንዋይና ተገቢ ያልሆነ የፆታ ፍላጎት ያሉ ነገሮች እንዳይቆጣጠሩን ምንጊዜም ንቁዎች መሆን ይኖርብናል። (ምሳሌ 4:23፤ ማቴ. 5:27-29) ይሖዋ፣ ለአምላክ መንግሥት ያለን ፍቅር እንዳይቀዘቅዝ የሚረዳ ሌላ ውድ ሀብትም ሰጥቶናል።
ሕይወት አድን የሆነው አገልግሎታችን
8. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎታችንን ‘በሸክላ ዕቃ ውስጥ ያለ ውድ ሀብት’ በማለት የገለጸው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ አገልግሎቱን እንደ ውድ ሀብት አድርጎ እንደሚመለከት ያሳየው እንዴት ነው?
8 ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበክና የማስተማር ኃላፊነት እንደሰጠን አስታውስ። (ማቴ. 28:19, 20) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አገልግሎቱ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። የአዲሱን ቃል ኪዳን አገልግሎት ‘በሸክላ ዕቃ ውስጥ ካለ ውድ ሀብት’ ጋር አመሳስሎታል። (2 ቆሮ. 4:7፤ 1 ጢሞ. 1:12) ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን እንደ ሸክላ ዕቃ ነን፤ ሆኖም የምንሰብከው መልእክት ለራሳችንም ሆነ ለሚሰሙን ሰዎች የዘላለም ሕይወት ሊያስገኝ የሚችል ነው። ጳውሎስ፣ ይህን በመገንዘቡ “ምሥራቹን ለሌሎች አካፍል ዘንድ ለምሥራቹ ስል ሁሉን ነገር አደርጋለሁ” ሲል ተናግሯል። (1 ቆሮ. 9:23) ጳውሎስ፣ ለአገልግሎቱ ያለው ፍቅር ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በትጋት እንዲካፈል አነሳስቶታል። (ሮም 1:14, 15ን እና 2 ጢሞቴዎስ 4:2ን አንብብ።) በተጨማሪም የደረሰበትን ከባድ ስደት እንዲቋቋም አስችሎታል። (1 ተሰ. 2:2) እኛስ ለአገልግሎታችን እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
9. ለአገልግሎታችን ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
9 ጳውሎስ ሰዎችን ለማነጋገር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በሙሉ ለመጠቀም ንቁ በመሆን ለአገልግሎቱ ያለውን አድናቆት አሳይቷል። እኛም እንደ ሐዋርያትና የጥንት ክርስቲያኖች ሁሉ መደበኛ ባልሆነ መንገድ፣ በአደባባይ እንዲሁም ከቤት ወደ ቤት እንሰብካለን። (ሥራ 5:42፤ 20:20) በተጨማሪም ሁኔታችን በፈቀደልን መጠን ረዳት ወይም የዘወትር አቅኚ በመሆን አገልግሎታችንን ለማስፋት ጥረት እናደርጋለን። ከዚህም ሌላ አዲስ ቋንቋ እንማር አሊያም በአገራችን ውስጥ ወዳለ ሌላ ቦታ ወይም ወደ ሌላ አገር ተዛውረን እናገለግል ይሆናል።—ሥራ 16:9, 10
10. አይሪን ምሥራቹን ለመስበክ ያደረገችው ጥረት ምን በረከት አስገኝቶላታል?
10 በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረውን አይሪን የተባለች ያላገባች እህት እንደ ምሳሌ እንመልከት። አይሪን ሩሲያኛ ለሚናገሩ ከሌላ አገር የመጡ ሰዎች የመስበክ ልባዊ ፍላጎት ነበራት። በመሆኑም በ1993 በኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ በሚገኝ በሩሲያኛ ቋንቋ የሚመራ ቡድን ውስጥ ማገልገል ጀመረች፤ በዚህ ወቅት በቡድኑ ውስጥ የነበሩት አስፋፊዎች 20 ብቻ ነበሩ። አይሪን ለ20 ዓመታት ያህል የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎችን በትጋት ስትረዳ ቆይታለች። አይሪን “አሁንም ቢሆን ሩሲያኛ ቋንቋን አቀላጥፌ መናገር አልችልም” በማለት በሐቀኝነት ተናግራለች። ሆኖም ይሖዋ እሷም ሆነች እንደ እሷ ያሉ ሌሎች አስፋፊዎች ያሳዩትን ቅንዓት ባርኳል። በዛሬው ጊዜ ኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ በሩሲያኛ ቋንቋ የሚመሩ ስድስት ጉባኤዎች ይገኛሉ። አይሪን መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናቻቸው አሥራ አምስት ሰዎች ተጠምቀዋል። ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ቤቴላውያን፣ አቅኚዎች እንዲሁም ሽማግሌዎች ሆነው እያገለገሉ ነው። አይሪን “በሕይወቴ ውስጥ ሌሎች ግቦችን ባወጣ ኖሮ ይህን ያህል ደስታ አላገኝም ነበር” በማለት ተናግራለች። አዎ፣ አይሪን አገልግሎቷን እንደ ውድ ሀብት አድርጋ ትመለከታለች!
11. ስደት ቢኖርም እንኳ መስበካችንን መቀጠላችን ምን ጥሩ ውጤት ያስገኛል?
11 አገልግሎታችንን እንደ ውድ ሀብት አድርገን የምንመለከት ከሆነ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ስደት ቢደርስብንም እንኳ መስበካችንን እንቀጥላለን። (ሥራ 14:19-22) በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ወንድሞቻችን ከባድ ስደት ደርሶባቸዋል። ሆኖም ልክ እንደ ጳውሎስ በጽናት መስበካቸውን ቀጥለዋል። ወንድሞች የመስበክ መብታችንን ለማስጠበቅ ሲሉ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት ቀርበው ተሟግተዋል። ወንድም ናታን ኖር በ1943 በዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስለተገኘ ድል ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እነዚህን ድሎች ያገኘነው በእናንተ ጥረት ነው። አስፋፊዎች ማገልገላቸውን ባይቀጥሉ ኖሮ፣ ከፍተኛው ፍርድ ቤት እንድንቀርብ የሚያደርገን ጉዳይ አይኖርም ነበር፤ ይሁንና እናንተ አስፋፊዎች ማለትም በዓለም ዙሪያ የምትገኙ ወንድሞች መስበካችሁን በመቀጠላችሁ ምክንያት በስደቱ ላይ ድል መቀዳጀት ችለናል። ይህ ብያኔ የተላለፈው የጌታ ሕዝቦች ጸንተው በመቆም ድል ስለነሱ ነው።” በሌሎች አገሮች የሚገኙ ወንድሞችም ጸንተው በመቆማቸው ተመሳሳይ ድሎች ተገኝተዋል። በእርግጥም ለአገልግሎቱ ያለን ፍቅር ስደትን እንድንቋቋም ያስችለናል።
12. ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ ምን ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል?
12 አገልግሎታችንን ከይሖዋ እንደተቀበልነው ውድ ሀብት አድርገን የምንመለከት ከሆነ “ሰዓት በመቁጠር” ብቻ አንረካም። ከዚህ ይልቅ ‘ምሥራቹን በተሟላ ሁኔታ ለመመሥከር’ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን። (ሥራ 20:24፤ 2 ጢሞ. 4:5) ይሁንና ለሌሎች የምናስተምረው ነገር ምንድን ነው? ከአምላክ ያገኘነውን ሌላ ውድ ሀብት እስቲ እንመልከት።
አምላክ የገለጠልን ውድ እውነቶች
13, 14. ኢየሱስ በማቴዎስ 13:52 ላይ የጠቀሰው ‘የከበረ ሀብት ማከማቻ’ ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው? ይህን ‘የከበረ ሀብት ማከማቻ’ መሙላት የምንችለውስ እንዴት ነው?
13 ሦስተኛው መንፈሳዊ ሀብታችን አምላክ የገለጠልን ውድ እውነት ነው። ይሖዋ የእውነት አምላክ ነው። (2 ሳሙ. 7:28፤ መዝ. 31:5) ለጋስ አባት እንደመሆኑ መጠን ለሚፈሩት ሰዎች መለኮታዊ እውነቶችን ይገልጥላቸዋል። እውነትን መጀመሪያ ከሰማንበት ጊዜ አንስቶ ከቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ከክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን፣ እንዲሁም ከትላልቅና ሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን የተለያዩ እውነቶችን ስንማር ቆይተናል። በጊዜ ሂደት ተጨማሪ እውነቶችን እያገኘን ስንሄድ ኢየሱስ የገለጸው ዓይነት አሮጌና አዲስ እውነቶችን የያዘ ‘የከበረ ሀብት ማከማቻ’ ይኖረናል። (ማቴዎስ 13:52ን አንብብ።) እነዚህን እውነቶች ልክ እንደተሸሸገ ሀብት የምንፈልጋቸው ከሆነ ይሖዋ ‘የከበረ ሀብት ማከማቻችንን’ ውድ በሆኑ አዳዲስ እውነቶች እንድንሞላ ይረዳናል። (ምሳሌ 2:4-7ን አንብብ።) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
14 ጥሩ የግል ጥናት ልማድ ማዳበር እንዲሁም በአምላክ ቃልና በጽሑፎቻችን ላይ ጥልቅ ምርምር ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን ከዚህ በፊት የማናውቃቸውን ‘አዳዲስ’ እውነቶች እናገኛለን። (ኢያሱ 1:8, 9፤ መዝ. 1:2, 3) ሐምሌ 1879 የወጣው የዚህ መጽሔት የመጀመሪያ እትም እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እውነት በጣም ተንሰራፍቶ በሚገኝ የሐሰት አረም ልትዋጥ ምንም ያህል እንዳልቀራት በሕይወት ጫካ ውስጥ እንደምትገኝ ትንሽ አበባ ናት። ልታገኛት የምትሻ ከሆነ በትጋት ልትፈልጋት ይገባል። . . . የራስህ ልታደርጋት ከፈለግክ ደግሞ ጎንበስ ብለህ ማንሳት ይኖርብሃል። አንድ የእውነት አበባ ስላገኘህ ብቻ አትርካ። . . . መሰብሰብህን አታቋርጥ፤ ፍለጋህን ቀጥል።” አዎ፣ ‘የከበረ ሀብት ማከማቻችንን’ በመለኮታዊ እውነቶች ለመሙላት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ አለብን።
15. አንዳንድ እውነቶች “አሮጌ” ሊባሉ የሚችሉት ከምን አንጻር ነው? አንተ በግልህ ከእነዚህ እውነቶች መካከል ይበልጥ ከፍ አድርገህ የምትመለከተው የትኞቹን ነው?
15 ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኘንበት ወቅት ውድ የሆኑ አንዳንድ እውነቶችን ተምረናል። እነዚህ እውነቶች በክርስትና መንገድ ላይ መጓዝ ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ የተማርናቸው ከመሆናቸው አንጻር “አሮጌ” ተብለው ሊገለጹ ይችላሉ። እነዚህ ውድ እውነቶች የትኞቹ ናቸው? ይሖዋ ፈጣሪያችንና ሕይወት ሰጪያችን እንደሆነ እንዲሁም ለሰው ልጆች ዓላማ እንዳለው ተምረናል። በተጨማሪም አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ ከኃጢአትና ከሞት ነፃ እንድንወጣ ሲል ልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ እንደሰጠን ተምረናል። ከዚህም ሌላ፣ የአምላክ መንግሥት መከራን በሙሉ እንደሚያስወግድ እንዲሁም በመንግሥቱ ግዛት ሥር ሆነን በሰላምና በደስታ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዳለን ተገንዝበናል።—ዮሐ. 3:16፤ ራእይ 4:11፤ 21:3, 4
16. አንድን እውነት በተመለከተ ባለን ግንዛቤ ላይ ማስተካከያ በሚደረግበት ወቅት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
16 አንዳንድ ጊዜ ስለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ወይም ጥቅስ ባለን ግንዛቤ ላይ ማስተካከያ ይደረግ ይሆናል። በዚህ ጊዜ የቀረበውን አዲስ ትምህርት ጊዜ ወስደን በጥንቃቄ ማጥናትና ባጠናነው ላይ ማሰላሰላችን ተገቢ ነው። (ሥራ 17:11፤ 1 ጢሞ. 4:15) የተደረጉትን ትላልቅ ማስተካከያዎች ብቻ ሳይሆን በቀድሞውና በአዲሱ ግንዛቤያችን መካከል ያሉትን ጥቃቅን የሚመስሉ ልዩነቶች ጭምር ለመረዳት ጥረት እናደርጋለን። በዚህ መንገድ አዲሱን እውነት ‘በከበረ ሀብት ማከማቻችን’ ውስጥ ማስቀመጥ እንችላለን። እንዲህ ያለ ጥረት ማድረጋችን አያስቆጭም የምንለው ለምንድን ነው?
17, 18. መንፈስ ቅዱስ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
17 ኢየሱስ፣ የአምላክ መንፈስ ከዚህ በፊት የተማርናቸውን ነገሮች እንድናስታውስ ሊረዳን እንደሚችል ተናግሯል። (ዮሐ. 14:25, 26) ምሥራቹን ስንሰብክ የአምላክ መንፈስ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? ፒተር የተባለ አንድ ወንድም ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት። በ1970፣ የ19 ዓመት ወጣት በነበረበት ወቅት ብሪታንያ ውስጥ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ማገልገል ጀመረ። ከቤት ወደ ቤት በሚያገለግልበት ወቅት አንድ ጺማም የሆነ ሰው አገኘ። ፒተር ሰውየውን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማወቅ ይፈልግ እንደሆነ ጠየቀው። ሰውየው የአይሁድ ረቢ ስለነበር ይህ ወጣት መጽሐፍ ቅዱስን ሊያስተምረው ማሰቡ አስገረመው። ረቢው ፒተርን ለመፈተን “እሺ የእኔ ልጅ፣ ለመሆኑ የዳንኤል መጽሐፍ የተጻፈው በምን ቋንቋ ነው?” ሲል ጠየቀው። ፒተርም “የተወሰነው ክፍል የተጻፈው በአረማይክ ነው” ብሎ መለሰ። ፒተር እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “ረቢው መልሱን በማወቄ ተገረመ፤ ከእሱ ይበልጥ የተገረምኩት ግን እኔ ነበርኩ! መልሱን ማወቅ የቻልኩት እንዴት ነው? ወደ ቤት ተመልሼ ባለፉት ወራት የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ስመለከት የዳንኤል መጽሐፍ የተወሰነው ክፍል የተጻፈው በአረማይክ እንደሆነ የሚናገር ርዕስ አገኘሁ።” (ዳን. 2:4 ግርጌ) ከዚህ ማየት እንደምንችለው መንፈስ ቅዱስ ከዚህ በፊት ያነበብናቸውንና ‘በከበረ ሀብት ማከማቻችን’ ውስጥ ያስቀመጥናቸውን ነገሮች እንድናስታውስ ሊረዳን ይችላል።—ሉቃስ 12:11, 12፤ 21:13-15
18 ከይሖዋ የሚገኘውን ጥበብ እንደ ውድ ሀብት አድርገን የምንመለከት ከሆነ ‘የከበረ ሀብት ማከማቻችንን’ በአዲስና በአሮጌ እውነቶች እንድንሞላ ልባችን ያነሳሳናል። ለይሖዋ ጥበብ ያለን ፍቅርና አድናቆት በጨመረ መጠን የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ለመሆን ይበልጥ የታጠቅን እንሆናለን።
ያገኛችሁትን መንፈሳዊ ሀብት ጠብቁ
19. መንፈሳዊ ሀብታችንን መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው?
19 ሰይጣንም ሆነ በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም በዚህ ርዕስ ውስጥ ለተመለከትናቸው መንፈሳዊ ሀብቶች ያለን አድናቆት እንዲቀንስ ወይም እንዲጠፋ ለማድረግ ያለማሰለስ ጥረት ያደርጋሉ። እኛም ካልተጠነቀቅን በዚህ ተጽዕኖ ልንሸነፍ እንችላለን። ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ፣ የተንደላቀቀ ሕይወት የመኖር ሕልም ወይም ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ ወጥመድ ሊሆንብን ይችላል። ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ይህ ዓለምም ሆነ ምኞቱ እንደሚያልፉ ተናግሯል። (1 ዮሐ. 2:15-17) በመሆኑም ላገኘናቸው መንፈሳዊ ሀብቶች ምንጊዜም አመስጋኝ መሆን እንዲሁም እነዚህን ሀብቶች መጠበቅ ይኖርብናል።
20. መንፈሳዊ ሀብትህን ለመጠበቅ ስትል ምን ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል?
20 ለአምላክ መንግሥት ያላችሁ ፍቅር እንዲቀንስ ሊያደርግ የሚችልን ማንኛውንም ነገር ለማስወገድ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። በቅንዓት መስበካችሁን ቀጥሉ፤ ሕይወት አድን ለሆነው አገልግሎታችን ያላችሁ ፍቅር እንዲቀዘቅዝ አትፍቀዱ። መለኮታዊ እውነቶችን በትጋት መፈለጋችሁን ቀጥሉ። እንዲህ ካደረጋችሁ “ሌባ በማይደርስበት፣ ብልም ሊበላው በማይችልበት በሰማያት ለራሳችሁ የማያልቅ ውድ ሀብት [ታከማቻላችሁ]። ሀብታችሁ ባለበት ልባችሁም በዚያ ይሆናልና።”—ሉቃስ 12:33, 34
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሟ ተቀይሯል።