የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የሉቃስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
የማቴዎስ ወንጌል በዋነኝነት የተጻፈው ለአይሁዳውያን አንባቢያን ሲሆን የማርቆስ ወንጌል ደግሞ አይሁዳውያን ላልሆኑ ሰዎች እንደሆነ ይታመናል። የሉቃስ ወንጌል የተጻፈው ግን ከሁሉም ብሔራት ለተውጣጡ ሕዝቦች ነው። ከ56-58 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ የተጻፈው የሉቃስ ወንጌል ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የተሟላ ዘገባ ይዟል።
ሉቃስ ለሌሎች ሰዎች ከልብ የሚያስብና ጠንቃቃ ሐኪም እንደመሆኑ መጠን ወንጌሉን የጻፈው ‘ሁሉን ከመሠረቱ [ጀምሮ] በጥንቃቄ ከመረመረ በኋላ’ ነው። ይህ ዘገባ ከ3 ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ድረስ ያሉትን የ35 ዓመታት ታሪክ ይሸፍናል። (ሉቃስ 1:3) በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ከሚገኙት ታሪኮች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት በሌሎቹ የወንጌል ዘገባዎች ውስጥ አይገኙም።
ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ ያከናወነው የስብከት እንቅስቃሴ
ሉቃስ፣ መጥምቁ ዮሐንስና ኢየሱስ በተወለዱበት ወቅት ስለነበሩት ሁኔታዎች ከዘረዘረ በኋላ ዮሐንስ አገልግሎቱን የጀመረው ጢባርዮስ ቄሣር በነገሠ በ15ኛው ዓመት ማለትም በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጸደይ ወቅት እንደሆነ ገልጿል። (ሉቃስ 3:1, 2) ዮሐንስ ኢየሱስን ያጠመቀው በዚያው ዓመት በመጸው ወቅት ላይ ነበር። (ሉቃስ 3:21, 22) በ30 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ‘ኢየሱስ ወደ ገሊላ በመመለስ በምኩራባቸው ያስተምር ጀመር።’—ሉቃስ 4:14, 15
ኢየሱስ የመጀመሪያ የስብከት ጉዞውን ያደረገው ወደ ገሊላ ነበር። ለሕዝቡም “ወደ ሌሎቹም ከተሞች ሄጄ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል መስበክ ይገባኛል” አላቸው። (ሉቃስ 4:43) ዓሣ አጥማጅ የነበረው ስምዖንና ሌሎች ሰዎችም አብረውት ሄደዋል። ኢየሱስ ‘ከእንግዲህ ሰውን የምታጠምዱ ትሆናላችሁ’ ብሏቸዋል። (ሉቃስ 5:1-11፤ ማቴ. 4:18, 19) ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሁለተኛውን የስብከት ጉዞውን ባደረገበት ወቅት 12ቱ ሐዋርያትም አብረውት ነበሩ። (ሉቃስ 8:1) በሦስተኛው የስብከት ጉዞ ወቅት ግን “የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲሰብኩና የታመሙትን እንዲፈውሱ” 12ቱን ሐዋርያት ላካቸው።—ሉቃስ 9:1, 2
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
1:35—አምላክ፣ ኢየሱስ እንዲጸነስ ለማድረግ በማርያም ማሕፀን ውስጥ ያለውን እንቁላል ተጠቅሟል? አምላክ በገባው ቃል መሠረት ማርያም የምትወልደው ልጅ የአብርሃም፣ የይሁዳና የዳዊት እውነተኛ የልጅ ልጅ እንዲሆን ከተፈለገ በማርያም ማሕፀን ውስጥ ያለውን እንቁላል መጠቀም ግድ ነበር። (ዘፍ. 22:15, 18፤ 49:10፤ 2 ሳሙ. 7:8, 16) ይሁን እንጂ የአምላክን ልጅ ፍጹም ሕይወት ወደ ማርያም ማሕፀን በማዘዋወርና ጽንሱ እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ድርሻ ነበረው። (ማቴ. 1:18) መንፈስ ቅዱስ የማርያም አለፍጽምና ወደ ጽንሱ እንዳይተላለፍና ጽንሱ ሲፈጠር ጀምሮ ምንም ዓይነት እንከን እንዳይገጥመው እንክብካቤ ሳያደርግለት አይቀርም።
1:62—ዘካርያስ ድዳና ደንቆሮ ሆኖ ነበር? አልሆነም። ዘካርያስ የገጠመው የመናገር ችግር ብቻ ነበር። እርግጥ፣ ሌሎች ልጁ ማን ተብሎ እንዲጠራ እንደሚፈልግ ለማወቅ “በምልክት” ጠይቀውታል፤ ይህን ያደረጉት ግን መስማት ስለማይችል አልነበረም። ሚስቱ ለልጃቸው ያወጣችለትን ስም ሰምቶ መሆን አለበት። በዚህ ጊዜ ሌሎች ሰዎች ልጁ ማን ተብሎ እንዲጠራ እንደሚፈልግ ለማወቅ በምልክት ሳይጠይቁት አልቀሩም። በኋላም ዘካርያስ አንደበቱ ብቻ እንደተፈታለት መነገሩ የመስማት ችግር እንዳልነበረበት ይጠቁማል።—ሉቃስ 1:13, 18-20, 60-64
2:1, 2—“የመጀመሪያው የሕዝብ ቆጠራ” የተከናወነበት ወቅት መጠቀሱ ኢየሱስ የተወለደበትን ጊዜ እንድናውቅ የሚረዳን እንዴት ነው? በአውግስጦስ ቄሣር የግዛት ዘመን ከአንድ ጊዜ በላይ የሕዝብ ቆጠራ ተካሂዶ ነበር። የዳንኤል 11:20 ፍጻሜ የሆነው የመጀመሪያው የሕዝብ ቆጠራ የተካሄደው በ2 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በ6 ወይም በ7 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነበር። (ሥራ 5:37) የሶርያ ገዥ የነበረው ቄሬኔዎስ በሕዝብ ቆጠራዎቹ ወቅት የነበረ መሆኑ ሁለት ጊዜ ተሹሞ እንደነበር በግልጽ ያሳያል። ሉቃስ የጠቀሰው የመጀመሪያው የሕዝብ ቆጠራ ኢየሱስ በ2 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደተወለደ ይጠቁማል።
2:35—የማርያም ነፍስ “በሰይፍ” እንደሚወጋ የሚገልጸው ሐሳብ ምን ትርጉም አለው? ይህ ሐሳብ ማርያም፣ አብዛኛው ሕዝብ የኢየሱስን መሲሕነት አለመቀበሉን ስታይ የሚያጋጥማትን ጭንቀትና በአሰቃቂ ሁኔታ በመሞቱ የሚሰማትን ሐዘን የሚጠቁም ነው።—ዮሐ. 19:25
9:27, 28—ማቴዎስና ማርቆስ፣ ኢየሱስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ የተለወጠው ለደቀ መዛሙርቱ በመንግሥቱ እስኪመጣ ድረስ ከመካከላቸው “ሞትን የማይቀምሱ” እንዳሉ ከተናገረ “ከስድስት ቀን” በኋላ እንደሆነ ሲገልጹ ሉቃስ ግን “ከስምንት ቀን” በኋላ መሆኑን የተናገረው ለምንድን ነው? (ማቴ. 17:1፤ ማር. 9:2) ሉቃስ ሁለት ቀን የጨመረው ኢየሱስ ቃል የገባበትንና ተአምራዊ በሆነ መንገድ የተለወጠበትን ቀን አስቦ ሳይሆን አይቀርም።
9:49, 50—ኢየሱስ፣ በዚህ ዘገባ ላይ የተጠቀሰው ግለሰብ እሱን ተከትሎት ባይሄድም አጋንንት እንዳያስወጣ ያልከለከለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ግለሰቡን ያላስቆመው በወቅቱ የክርስቲያን ጉባኤ ስላልተቋቋመ ነበር። በመሆኑም ግለሰቡ በኢየሱስ ስም ለማመንም ሆነ አጋንንት ለማስወጣት ቃል በቃል ኢየሱስን ተከትሎ መሄድ አይጠበቅበትም ነበር።—ማር. 9:38-40
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:32, 33፤ 2:19, 51:- ማርያም የትንቢቱ ፍጻሜ የሆኑ ክንውኖችን በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር። እኛስ ኢየሱስ ‘የዓለምን መጨረሻ’ አስመልክቶ የተናገራቸውን ትንቢቶች በዛሬው ጊዜ ከምናያቸው ሁኔታዎች ጋር በማወዳደር የትንቢቱን ፍጻሜ እናስተውላለን?—ማቴ. 24:3
2:37:- የሐና ምሳሌ በታማኝነትና ‘በጸሎት በመጽናት’ እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ “መሰብሰባችንን” ባለመተው ይሖዋን ማምለክ እንዳለብን ያስተምረናል።—ሮሜ 12:12፤ ዕብ. 10:24, 25
2:41-50:- ዮሴፍ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ይሰጥ የነበረ ከመሆኑም ባሻገር ቤተሰቡን በቁሳዊም ሆነ በመንፈሳዊ ተንከባክቧል። በዚህ ረገድ ለቤተሰብ ራሶች ጥሩ ምሳሌ ትቷል።
4:4:- በአምላክ ቃል ላይ ሳናሰላስል አንድም ቀን እንዲያልፈን መፍቀድ አይኖርብንም።
6:40:- የአምላክን ቃል የሚያስተምር ሰው ለተማሪዎቹ ጥሩ ምሳሌ መሆን አለበት። ሌሎች እንዲያደርጉት የሚያስተምረውን ነገር ራሱም መፈጸም ይኖርበታል።
8:15:- ‘ቃሉን መጠበቅና በመጽናት ፍሬ ማፍራት’ ከፈለግን የአምላክን ቃል መመገብ፣ መረዳትና ከፍ አድርገን መመልከት አለብን። መጽሐፍ ቅዱስንም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ስናነብ ጸሎት የታከለበት ማሰላሰል ማድረጋችን እጅግ አስፈላጊ ነው።
ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ መደምደሚያ ላይ ያከናወነው የስብከት እንቅስቃሴ
ኢየሱስ 70 ሰዎችን በመምረጥ በይሁዳ ወደሚገኙ ከተሞችና ቦታዎች ከእሱ ቀድመው እንዲሄዱ አደረገ። (ሉቃስ 10:1 የ1954 ትርጉም) ኢየሱስ ‘በከተሞችና በመንደሮች እያስተማረ’ ያልፍ ነበር።—ሉቃስ 13:22
በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሚከበረው የፋሲካ በዓል ከመድረሱ አምስት ቀናት ቀደም ብሎ ኢየሱስ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ እንዲሁም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሓፍት ዘንድ መናቅ፣ መገደልና በሦስተኛውም ቀን ከሙታን መነሣት አለበት” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው ቃል የሚፈጸምበት ጊዜ ደርሶ ነበር።—ሉቃስ 9:22, 44
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
10:18—ኢየሱስ ለ70ዎቹ ደቀ መዛሙርት “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ” ያላቸው ምን ለመግለጽ ፈልጎ ነው? ኢየሱስ፣ ሰይጣን ከሰማይ እንደተባረረ መግለጹ አልነበረም። ሰይጣን ከሰማይ የተባረረው ኢየሱስ በ1914 በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነው። (ራእይ 12:1-10) ኢየሱስ እንዲህ ያለበትን ምክንያት በእርግጠኝነት መናገር ባንችልም ወደፊት የሚከናወነውን ነገር እንደተፈጸመ አድርጎ የተናገረው፣ ሰይጣን ከሰማይ መባረሩ የማይቀር መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ ለመግለጽ ሳይሆን አይቀርም።
14:26—የክርስቶስ ተከታዮች ዘመዶቻቸውን ‘መጥላት’ ያለባቸው ከምን አንጻር ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘መጥላት’ የሚለው ቃል አንድን ሰው ወይም ነገር ከሌላኛው አሳንሶ መውደድን ሊያመለክት ይችላል። (ዘፍ. 29:30, 31) ክርስቲያኖች ዘመዶቻቸውን ‘ይጠላሉ’ ሲባል ከኢየሱስ አስበልጠው አይወዷቸውም ማለት ነው።—ማቴ. 10:37
17:34-37 [NW]—“ንሥሮች” የተባሉት እነማን ናቸው? የሚሰበሰቡበት ‘በድንስ’ ምንድን ነው? ‘የሚወሰዱት’ ወይም የሚድኑት ሰዎች ከርቀት የማየት ችሎታ ባላቸው ንሥሮች ተመስለዋል። እነሱ የሚሰበሰቡበት “በድን” ደግሞ በማይታይ ሁኔታ በመግዛት ላይ የሚገኘውን እውነተኛውን ክርስቶስና ይሖዋ የሚያቀርብላቸውን መንፈሳዊ ምግብ ያመለክታል።—ማቴ. 24:28
22:44—ኢየሱስ በጣም የተጨነቀው ለምን ነበር? በበርካታ ምክንያቶች የተነሳ ነው። ኢየሱስ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ መሞቱ በይሖዋ አምላክና በስሙ ላይ የሚያስከትለው ነገር በእጅጉ አሳስቦታል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ማግኘቱም ሆነ የመላው የሰው ዘር የወደፊት ዕጣ የተመካው በታማኝነት በመጽናቱ ላይ እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል።
23:44—ለሦስት ሰዓት የዘለቀው ጨለማ የተፈጠረው በፀሐይ ግርዶሽ ምክንያት ነው? አይደለም። የፀሐይ ግርዶሽ የሚከሰተው በፋሲካ ወቅት እንደሚሆነው ጨረቃ ሙሉ በምትሆንበት ጊዜ ሳይሆን እንደ አዲስ መታየት በምትጀምርበት ወቅት ብቻ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ በሞተበት ዕለት የተፈጠረው ጨለማ የአምላክ ተአምር ነበር።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
11:1-4:- በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ሐሳብ ኢየሱስ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ቀደም ብሎ በተራራ ስብከቱ ላይ ከተናገረው የናሙና ጸሎት ጋር ሲወዳደር የተወሰነ ልዩነት ያለው መሆኑ፣ እኛም ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ጸሎት ማቅረብ እንደሌለብን በግልጽ ያሳያል።—ማቴ. 6:9-13
11:5, 13:- ይሖዋ ለጸሎቶቻችን ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ብናውቅም በጸሎት መጽናት ይኖርብናል።—1 ዮሐ. 5:14
11:27, 28 [NW]:- እውነተኛ ደስታ የምናገኘው ጥሩ የቤተሰብ ሕይወት ስላለን አሊያም ሀብታም ስለሆንን ሳይሆን የአምላክን ፈቃድ በታማኝነት ስንፈጽም ነው።
11:41:- ምጽዋት የምንሰጠው በፍቅርና በፈቃደኝነት መንፈስ ተነሳስተን መሆን ይኖርበታል።
12:47, 48:- ከባድ ኃላፊነት እያለበት ኃላፊነቱን በአግባቡ የማይወጣ ሰው፣ ምን ኃላፊነት እንደተሰጠው ከማያውቅ ወይም ኃላፊነቱ የሚጠይቅበትን ነገር ሙሉ በሙሉ ካልተረዳ ሰው ይበልጥ ተጠያቂ ይሆናል።
14:28, 29:- እንደ አቅማችን መኖር ጥበብ ነው።
22:36-38:- ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ሰይፍ እንዲይዙ የነገራቸው ራሳቸውን ለመጠበቅ ወይም ለመከላከል እንዲችሉ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ደቀ መዛሙርቱ አልፎ በተሰጠበት ምሽት ሰይፍ መያዛቸው ኢየሱስ አንድ ትልቅ ትምህርት እንዲያስተምራቸው ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮለታል፤ ይህም “ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” የሚለው ነው።—ማቴ. 26:52
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዮሴፍ ለቤተሰብ ራሶች ግሩም ምሳሌ ትቶላቸዋል
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ከሌሎቹ የወንጌል ዘገባዎች ሁሉ ይበልጥ የተሟሉ መረጃዎችን ዘግቧል