“ይሖዋ፣ መሐሪና ሞገስ ያለው አምላክ”
“እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት።”—ዘጸአት 34:6
1. (ሀ) የሚወዷቸው ሰዎች ንጹሑን አምልኮ ትተው በመውጣታቸው ምክንያት ላዘኑ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ምን ማጽናኛ ይሰጣል? (ለ) ይሖዋ የባዘኑትን የሚመለከታቸው እንዴት ነው?
አንድ ክርስቲያን አባት “ሴት ልጄ ከአሁን በኋላ የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆን እንደማትፈልግ ነገረችኝ” ብሏል። “ለቀናት፣ ለሳምንታት፣ አልፎ ተርፎም ለወራት እርር ድብን ስል ከረምኩ። ከሞት የከፋ ነበር።” በእርግጥ አንድ የምንወደው ሰው ከንጹሕ የአምልኮ ጎዳና ወጥቶ ሲባዝን ማየት ያሳዝናል። እንዲህ ያለ ነገር አጋጥሞህ ያውቃልን? አጋጥሞህ የሚያውቅ ከሆነ ይሖዋ እንደሚያዝንልህ ማወቅህ ያጽናናሃል። (ዘጸአት 3:7፤ ኢሳይያስ 63:9) ሆኖም ይሖዋ እነዚህን የባዘኑትን ሰዎች እንዴት ይመለከታቸዋል? ተመልሰው የእሱን ሞገስ እንዲያገኙ በምሕረት ግብዣ እንደሚያቀርብላቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። በሚልክያስ ዘመን የነበሩትን ዓመፀኛ አይሁዶች “ወደ እኔ ተመለሱ፣ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” ሲል ለምኗቸዋል።—ሚልክያስ 3:7
2. ምሕረት የይሖዋ ባሕርይ አቢይ ክፍል መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያሳየው እንዴት ነው?
2 ሙሴ በሲና ተራራ ላይ በነበረበት ጊዜ የአምላክ ምሕረት ጎላ ተደርጎ ተገልጾለታል። በዚያም ይሖዋ “መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት” በማለት ራሱን ገልጿል። (ዘጸአት 34:6) ይህ መግለጫ ምሕረት የይሖዋ ባሕርይ አቢይ ክፍል መሆኑን ያጎላል። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጴጥሮስ “ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ [ይፈልጋል]” ሲል ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 3:9) እርግጥ የአምላክ ምሕረት ገደብ የለሽ አይደለም። ይሖዋ “በፍጹም ሳይቀጣ እንደማያልፍ” ለሙሴ ተነግሮታል። (ዘጸአት 34:7 NW፤ 2 ጴጥሮስ 2:9) ሆኖም ‘አምላክ ፍቅር ነው፤’ ምሕረት ደግሞ የዚህ ባሕርይ ዋነኛ ገጽታ ነው። (1 ዮሐንስ 4:8፤ ያዕቆብ 3:17) ይሖዋ “ቁጣውን ለዘላለም አይጠብቅም” እንዲሁም “ምሕረትን [“ፍቅራዊ ደግነትን፣” NW] ይወድዳል።”—ሚክያስ 7:18, 19
3. ኢየሱስ ለምሕረት ያለው አመለካከት ጻፎችና ፈሪሳውያን ከነበራቸው አመለካከት የሚለየው እንዴት ነበር?
3 ኢየሱስ የሰማያዊ አባቱ ፍጹም ነጸብራቅ ነበር። (ዮሐንስ 5:19) ጥፋተኛ የሆኑ ሰዎችን በርኅራኄ መያዙ የኃጢአት ድርጊታቸውን አቃልሎ መመልከቱ ሳይሆን የአካል ሕመም ላለባቸው ሰዎች የነበረው ዓይነት ጥልቅ የአሳቢነት ስሜት መግለጫ ነበር። (ከማርቆስ 1:40, 41 ጋር አወዳድር።) አዎን፣ ኢየሱስ ምሕረትን በአምላክ ሕግ ውስጥ ከሚገኙ ‘ዋና ነገሮች’ መካከል መድቦታል። (ማቴዎስ 23:23) ከዚህ በተቃራኒ ግን ስለ ፍትሕ የነበራቸው አስተሳሰብ አብዛኛውን ጊዜ ለምሕረት ምንም ቦታ የማይሰጥ የነበረውን ጻፎችንና ፈሪሳውያንን ተመልከት። ኢየሱስ ከኃጢአተኞች ጋር የነበረውን ግንኙነት በተመለከቱ ጊዜ “ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል ከእነርሱም ጋር ይበላል” በማለት አጉረመረሙ። (ሉቃስ 15:1, 2) ኢየሱስ ለከሰሱት ሰዎች ሦስት ምሳሌዎችን በመጠቀም መልስ የሰጠ ሲሆን ሦስቱም ምሳሌዎች የአምላክን ምሕረት ያጎሉ ነበር።
4. ኢየሱስ ምን ሁለት ምሳሌዎችን ተናግሯል? ምሳሌዎቹ የያዙት ቁም ነገርስ ምንድን ነው?
4 በመጀመሪያ ኢየሱስ፣ የጠፋችበትን አንድ በግ ለመፈለግ ሲል 99 በጎችን ትቶ ስለ ሄደ ሰው ተናግሯል። ሊያጎላ የፈለገው ነጥብ ምን ነበር? “ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።” ቀጥሎ ኢየሱስ የጠፋባትን አንድ ድሪም ትፈልግ ስለነበርና ባገኘችውም ጊዜ ስለተደሰተች ሴት ተናግሯል። የምሳሌው ትርጉም ምን ነበር? “ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።” ኢየሱስ ሦስተኛውን ምሳሌ በታሪክ መልክ አቅርቦታል።a ብዙዎች እስከ ዛሬ ከተነገሩት አጫጭር ታሪኮች ሁሉ የላቀ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህን ታሪክ መመርመራችን የአምላክን ምሕረት ለማድነቅና ለመኮረጅ ይረዳናል።—ሉቃስ 15:3-10
አንድ ዓመፀኛ ልጅ ከቤት ወጣ
5, 6. በኢየሱስ ሦስተኛ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ታናሽ ልጅ አድናቆት እንደጎደለው ያሳየው እንዴት ነው?
5 “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ አባቱን:- አባቴ ሆይ፣ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፣ ከዚያም እያባከነ ገንዘቡን በተነ።”—ሉቃስ 15:11-13b
6 እዚህ ላይ ታናሹ ልጅ አድናቆት እንደጎደለው አሳይቷል። በመጀመሪያ የውርስ ድርሻው እንዲሰጠው ጠየቀ፤ ከዚያም ‘ብኩን በመሆን’ ገንዘቡን በተነ። ‘ብኩንነት’ የሚለው ቃል “መረን የለቀቀ አኗኗር” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ነው። አንድ ምሁር ቃሉ “ከፍተኛ የሆነ የባሕርይ መበላሸትን ያመለክታል” ብለዋል። በመሆኑም በኢየሱስ ታሪክ ላይ የተጠቀሰው ታናሽ ልጅ አብዛኛውን ጊዜ አባካኝ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ቃሉ አለአግባብ በግዴለሽነት ገንዘብ የሚበትንንና የሚያጠፋ ሰው የሚያመለክት ነው።
7. በዛሬው ጊዜ ከአባካኙ ልጅ ጋር የሚመሳሰሉት እነማን ናቸው? እንዲህ ዓይነቶቹ ብዙዎቹ ግለሰቦች ወደ ‘ሩቅ አገር’ ለመሄድና በራሳቸው ፈቃድ እየተመሩ መኖር የሚፈልጉትስ ለምንድን ነው?
7 በዛሬው ጊዜ ከአባካኙ ልጅ ጋር የሚመሳሰሉ ሰዎች አሉን? አዎን። በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም ስጋት የሌለበትን የሰማያዊ አባታችንን የይሖዋን “ቤት” ትተው የሚወጡ መኖራቸው ያሳዝናል። (1 ጢሞቴዎስ 3:15) ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ በአምላክ ቤት ያለው ሁኔታ በጣም ጥብቅ እንደሆነና ዘወትር የሚከታተሉንን የይሖዋ ዓይኖች እንደ ጥበቃ ሳይሆን ነፃነት እንደሚያሳጡ ነገሮች አድርገው ይመለከቷቸዋል። (ከመዝሙር 32:8 ጋር አወዳድር።) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተምራ ብታድግም ከጊዜ በኋላ የአልኮልና የዕፅ ሱሰኛ የሆነች የአንዲትን ክርስቲያን ሴት ሁኔታ ተመልከት። በሕይወቷ ያሳለፈችውን ያንን የጨለማ ወቅት መለስ ብላ በማስታወስ እንዲህ ትላለች:- “ራሴን በራሴ ሕይወቴን የተሻለ ማድረግ እንደምችል ማረጋገጥ ፈልጌ ነበር። ያሻኝን ነገር ማድረግ ፈለግሁ፤ ማንም ይህን አድርጊ ያን አታድርጊ እንዲለኝ አልፈለግሁም።” አባካኙ ልጅ እንዳደረገው ይህች ወጣት በራሷ መመራት ፈለገች። የሚያሳዝነው በፈጸመቻቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ድርጊቶች የተነሳ ከክርስቲያን ጉባኤ ተወገደች።—1 ቆሮንቶስ 5:11–13
8. (ሀ) ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች በሚቃረን መንገድ ለመኖር ለሚፈልጉ ሰዎች ምን እርዳታ ሊደረግላቸው ይችላል? (ለ) አንድ ሰው የአምልኮ ጉዳይን በተመለከተ የሚያደርገውን ምርጫ በጥሞና ሊያስብበት የሚገባው ለምንድን ነው?
8 የእምነት አጋራችን የነበረ ሰው ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር የሚጋጭ አኗኗር ሲመርጥ ማየት በእርግጥም ልብን በሐዘን የሚሰብር ነገር ነው። (ፊልጵስዩስ 3:18) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎችም ሆኑ ሌሎች ኃጢአተኛውን ለማስተካከል ይጥራሉ። (ገላትያ 6:1) ያም ሆኖ ግን ማንም ሰው የክርስቲያን ደቀ መዝሙርነትን ቀንበር እንዲሸከም አይገደድም። (ማቴዎስ 11:28–30፤ 16:24) ወጣቶችም እንኳ ዕድሜያቸው ሲደርስ አምልኮን በተመለከተ የግል ምርጫ ማድረግ አለባቸው። ሁላችንም ነፃ ምርጫ ያለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንሰጣለን። (ሮሜ 14:12) በተጨማሪም ‘የዘራነውን እንደምናጭድ’ የተረጋገጠ ነው፤ በኢየሱስ ምሳሌ የተገለጸው አባካኝ ልጅ ብዙም ሳይቆይ ይህን ተገንዝቧል።—ገላትያ 6:7, 8
በሰው አገር ሳለ ተስፋው ጨለመበት
9, 10. (ሀ) አባካኙ ልጅ ምን የሁኔታዎች ለውጥ አጋጥሞት ነበር? ምንስ እርምጃ ወሰደ? (ለ) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ እውነተኛውን አምልኮ ትተው የሚወጡ አንዳንዶች ምን ዓይነት መጥፎ ሁኔታ ውስጥ እንደሚወድቁ በምሳሌ አስረዳ።
9 “ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፣ እርሱም ይጨነቅ ጀመር። ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፣ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው። እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፣ የሚሰጠውም አልነበረም።”—ሉቃስ 15:14-16
10 አባካኙ ልጅ ችግር ላይ ቢወድቅም ወደ ቤቱ የመመለስ ሐሳብ ግን ገና ወደ አእምሮው አልመጣም። ከዚያ ይልቅ የዚያ አገር ተወላጅ ወደሆነ አንድ ሰው ተጠጋና እሪያ የማሰማራት ሥራ ሰጠው። የሙሴ ሕግ እሪያዎች ርኩስ እንስሳት መሆናቸውን ስለሚናገር እንዲህ ያለው ሥራ በአንድ አይሁዳዊ ዘንድ ተቀባይነት እንደማይኖረው የታወቀ ነው። (ዘሌዋውያን 11:7, 8) ሆኖም አባካኙ ልጅ ሕሊናውን የሚረብሽ ምንም ነገር ቢያጋጥመው ስሜቱን በውስጡ አፍኖ መያዙ የግድ ነበር። ደግሞም የዚያ አገር ተወላጅ የሆነው አሠሪው ከባዕድ አገር ለመጣ አንድ ችግረኛ ስሜት ይጨነቃል ብሎ ሊጠብቅ አይችልም። አባካኙ ልጅ የደረሰበት መከራ የንጹሑን አምልኮ ቀጥ ያለ ጎዳና ጥለው የሚወጡ በጊዜያችን የሚገኙ ብዙዎች ከሚገጥማቸው ነገር ጋር ተመሳሳይ ነው። እነዚህ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ቀደም ሲል አሳፋሪ እንደሆኑ አድርገው ይቆጥሯቸው የነበሩ ድርጊቶችን መፈጸም ይጀምራሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ወጣት በ17 ዓመቱ በልጅነቱ ባገኘው ክርስቲያናዊ ትምህርት መመራት አቆመ። “የጾታ ብልግና መፈጸምና አደገኛ ዕፆችን መውሰዴ ለዓመታት ያከማቸኋቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች ጨርሰው ከአእምሮዬ ደመሰሱት” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። ከዚያም ይህ ወጣት በጦር መሣሪያ አስፈራርቶ በመዝረፍና በግድያ ተወንጅሎ እስር ቤት ገባ። ምንም እንኳ ከጊዜ በኋላ በመንፈሳዊ ቢያገግምም ‘በኃጢአት ለሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ’ ሲል ምን ያህል ከፍተኛ ዋጋ እንደከፈለ አስቡት!—ከዕብራውያን 11:24–26 ጋር አወዳድር።
11. የአባካኙን ልጅ ችግር ይበልጥ ያባባሰበት ምን ነበር? በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች ዓለም የሚያቀርባቸው መስህቦች ‘ከንቱ ማታለያዎች’ ሆነው ያገኟቸውስ እንዴት ነው?
11 አባካኙ ልጅ ‘ምንም ነገር የሚሰጠው ሰው’ ማጣቱ ችግሩን አባብሶበታል። አዲስ ያፈራቸው ወዳጆቹ የት ደረሱ? አሁንማ ቤሳ ቤስቲን የሌለው ድሃ ስለሆነ ‘ማን ይፈልገዋል።’ (ምሳሌ 14:20) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ከእምነት የሚወጡ ብዙዎች የዚህ ዓለም መስህቦችና አመለካከቶች ‘ከንቱ ማታለያዎች’ ሆነው ያገኟቸዋል። (ቆላስይስ 2:8) ለተወሰነ ጊዜ ከአምላክ ድርጅት ወጥታ የነበረች አንዲት ወጣት “ከይሖዋ አመራር በመራቄ ብዙ መከራና ሐዘን ደርሶብኛል” ስትል ተናግራለች። “ከዓለም ጋር ተመሳስዬ ለመኖር ጥረት አድርጌ ነበር፤ ሆኖም ሙሉ በሙሉ እነሱን መምሰል ስላልቻልኩ ገሸሽ አደረጉኝ። የሚመራው አባት እንደሚፈልግ የጠፋ ልጅ የሆንኩ ያህል ተሰምቶኝ ነበር። ይሖዋ እንደሚያስፈልገኝ የተገነዘብኩት በዚህ ጊዜ ነው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከይሖዋ ተለይቶ መኖርን እርም አልኩኝ።” በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው አባካኝ ልጅ ተመሳሳይ ወደሆነ ግንዛቤ ደርሷል።
አባካኙ ልጅ ወደ ልቡ ተመለሰ
12, 13. በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች ወደ ልባቸው እንዲመለሱ የረዳቸው ምንድን ነው? (ሣጥኑን ተመልከት።)
12 “ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ:- እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና:- አባቴ ሆይ፣ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፣ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ። ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ።”—ሉቃስ 15:17-20
13 አባካኙ ልጅ ‘ወደ ልቡ ተመለሰ።’ በሕልም ዓለም ውስጥ እንዳለ ያክል ለተወሰነ ጊዜ ደስታን ሲያሳድድ ከቆየ በኋላ ሲባንን በምን ዓይነት መንፈሳዊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገነዘበ። አዎን፣ ይህ ወጣት ተሳስቶ ቢወድቅም የመነሳት ተስፋ ነበረው። አንዳንድ መልካም ባሕርያት ሊኖሩት ይችላሉ። (ምሳሌ 24:16፤ ከ2 ዜና መዋዕል 19:2, 3 ጋር አወዳድር።) በዛሬው ጊዜ ከአምላክ መንጋ ስለሚወጡ ሰዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? በዚያም ሆነ በዚህ ዓመፀኛ አካሄዳቸው በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ላይ ኃጢአት መሥራታቸውን ስለሚያረጋግጥ እነዚህ ሰዎች ምንም ተስፋ የላቸውም ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ይሆናልን? (ማቴዎስ 12:31, 32) እንዲህ ለማለት አይቻልም። አንዳንዶቹ በዓመፀኛ አካሄዳቸው የተነሳ ብዙ ሥቃይ ካሳለፉ በኋላ ወደ ልባቸው ይመለሳሉ። አንዲት እህት ከአምላክ ድርጅት ውጪ ስላሳለፈችው ጊዜ ስትናገር “ለአንዲት ቀን እንኳ ይሖዋ ከአእምሮዬ ጠፍቶ አያውቅም” ብላለች። “አንድ ቀን እንዲያው በሆነ መንገድ ወደ እውነት እንዲመልሰኝ ዘወትር እጸልይ ነበር።”—መዝሙር 119:176
14. አባካኙ ልጅ ምን ለማድረግ ወሰነ? ይህን በማድረጉስ ትሕትና ያሳየው እንዴት ነበር?
14 ሆኖም ከእውነት መንገድ ወጥተው የባዘኑ ሰዎች ምን ማድረግ ይችላሉ? በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ኮብላይ ልጅ ወደ ቤቱ ተመልሶ ለመሄድና አባቱን ይቅርታ ለመለመን ወስኗል። “ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ” ብሎ ለመጠየቅ ቆረጠ። አንድ ሞያተኛ በተፈለገው ጊዜ ሊባረር የሚችል የቀን ሠራተኛ ነበር። ይህ ደግሞ ከሞላ ጎደል እንደ አንድ የቤተሰብ አባል ተደርጎ ይቆጠር ከነበረ ባሪያ ያነሰ ደረጃ ያለው ነበር። ስለዚህ አባካኙ ልጅ ቀደም ሲል ወደነበረው የልጅነት ቦታ እንዲመለስ የመጠየቅ ሐሳብ አልነበረውም። ከቀን ወደ ቀን ለአባቱ ያለውን ታማኝነት እንደ አዲስ ለማስመስከር ሲል የመጨረሻውን አነስተኛ ቦታ ለመቀበል ፈቃደኛ ነበር። ይሁን እንጂ አባካኙ ልጅ ያላሰበው ነገር ጠበቀው።
ሞቅ ያለ አቀባበል
15–17. (ሀ) አባትየው ልጁን በተመለከተ ጊዜ ምን አደረገ? (ለ) አባትየው ለልጁ የሰጠው ልብስ፣ ቀለበትና ጫማ ምን ያመለክታሉ? (ሐ) አባትየው ግብዣ ማዘጋጀቱ ምን ያሳያል?
15 “እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፣ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው። ልጁም:- አባቴ ሆይ፣ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፣ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም [“ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ፣” NW] አለው። አባቱ ግን ባሪያዎቹን አለ:- ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፣ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፤ የሰባውን ፊሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፣ እንብላም ደስም ይበለን፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም። ደስም ይላቸው ጀመር።”—ሉቃስ 15:20–24
16 ማንኛውም አፍቃሪ ወላጅ ልጁ እንደገና ወደ መንፈሳዊነት ሲመለስ ለማየት ይጓጓል። በመሆኑም የአባካኙ ልጅ አባት ልጄ ይመለሳል ብሎ ተስፋ በማድረግ በየቀኑ መንገድ መንገዱን ያይ እንደነበር ልንገምት እንችላለን። አሁን ልጁ ወደ እሱ ሲመጣ ተመለከተ! መቼም የልጁ መልክና ቁመና እንደተለወጠ ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም አባቱ “ገና ሩቅ ሳለ” አወቀው። የተቦጫጨቀውን ልብስና የተጎሳቆለውን ገጽታ ሳይሆን ልጁን ተመለከተ፤ ሊቀበለውም ሮጠ!
17 አባትየው ልጁ ጋ ሲደርስ አንገቱን እቅፍ አድርጎ ሳመው። ከዚያም ልብስ፣ ቀለበትና ጫማ እንዲሰጡት ባሪያዎቹን አዘዘ። ልብሱ እንዲሁ ተራ ልብስ ሳይሆን “ከሁሉ የተሻለ” ምናልባትም ለተከበረ እንግዳ የሚቀርብ በጌጣ ጌጥ የተንቆጠቆጠ ልብስ ሳይሆን አይቀርም። አብዛኛውን ጊዜ ባሪያዎች ቀለበትና ጫማ አድርገው ስለማይታዩ አባትየው ልጁ እንደገና የቤተሰቡ አባል በመሆን ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ማግኘቱን ግልጽ ማድረጉ ነበር። ሆኖም አባትየው ሌላም ነገር አድርጓል። የልጁን መመለስ ለማክበር ግብዣ እንዲዘጋጅ አዘዘ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይህ ሰው ልጁን ይቅርታ ያደረገለት ቅር እያለው ወይም የልጁ መመለስ ስላስገደደው አልነበረም፤ ይቅርታ ሊያደርግለት ፈልጎ ነበር። የልጁ መመለስ ከልብ አስደስቶት ነበር።
18, 19. (ሀ) የአባካኙ ልጅ ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምርሃል? (ለ) ይሖዋ ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ጋር በነበረው ግንኙነት ካደረገው ነገር ለመገንዘብ እንደሚቻለው የአንድን ኃጢአተኛ መመለስ ‘የሚጠባበቀው’ እንዴት ነው?
18 ታዲያ የአባካኙ ልጅ ታሪክ እንድናመልከው መብት ስለሰጠን አምላካችን ምን ያስተምረናል? በመጀመሪያ ይሖዋ “መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት” መሆኑን ያስተምረናል። (ዘጸአት 34:6) በእርግጥም ምሕረት የአምላክ አቢይ ባሕርይ ነው። ምሕረቱ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች የሚይዝበት የተለመደ መንገድ ነው። ከዚያም ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ ይሖዋ “ይቅር ለማለት ዝግጁ” መሆኑን ያስተምረናል። (መዝሙር 86:5 NW) ምሕረቱን ሊዘረጋ የሚያስችለው መሠረት ለማግኘት ሲል ኃጢአተኛ የሰው ልጆች የልብ ለውጥ አድርገው እንደሆነ ለማየት በጥንቃቄ ይመለከታል ሊባል ይቻላል።—2 ዜና መዋዕል 12:12፤ 16:9
19 ለምሳሌ ያህል አምላክ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረውን ግንኙነት ተመልከት። ይሁዳና ኢየሩሳሌም ‘ከእግር እስከ ራስ የታመሙ’ መሆናቸውን እንዲናገር ይሖዋ ነቢዩ ኢሳይያስን በመንፈስ አነሳስቶት ነበር። ሆኖም እንዲህ ሲልም ተናግሯል:- “እግዚአብሔር ይራራላችሁ ዘንድ ይታገሣል [“ይጠባበቃል፣” NW]፣ ይምራችሁም ዘንድ ከፍ ከፍ ይላል።” (ኢሳይያስ 1:5, 6፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን፤ 30:18፤ 55:7፤ ሕዝቅኤል 33:11) በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ እንደተገለጸው አባት ይሖዋም ‘መንገድ መንገዱን ይመለከታል’ ለማለት ይቻላል። የእሱን ቤት ትቶ የወጣ ማንኛውም ሰው ቢሆን ይመለሳል ብሎ በጉጉት ይጠባበቃል። ከአንድ አፍቃሪ አባት የምንጠብቀው ይህንን አይደለምን?—መዝሙር 103:13
20 የይሖዋ ምሕረት በየዓመቱ ብዙዎችን ወደ ልባቸው ብሎም ወደ እውነተኛው አምልኮ እንዲመለሱ አድርጓቸዋል። ይህ የሚወዷቸውን ሰዎች ምንኛ ያስደስት ይሆን! ለምሳሌ ያህል በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን ክርስቲያን አባት ውሰድ። ደስ የሚለው ነገር ሴት ልጁ በመንፈሳዊ አገግማ በአሁኑ ጊዜ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች። “በዚህ አሮጌ ዓለም ውስጥ ከዚህ የበለጠ ምን ደስታ አለ?” በማለት ተናግሯል። “የኃዘን እንባዬ ወደ ደስታ እንባ ተለውጧል።” ይሖዋም ደስ እንደሚለው የተረጋገጠ ነው!—ምሳሌ 27:11
21 ይሁን እንጂ የአባካኙ ልጅ ታሪክ የሚገልጸው ሌላም ነገር አለ። ኢየሱስ የይሖዋን ምሕረትና የጻፎችና ፈሪሳውያንን ድርቅ ያለ ፍርድ ለማነጻጸር ሲል የጀመረውን ታሪክ ቀጥሏል። ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነና ለእኛ ምን ትርጉም እንዳለው በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ምሳሌዎች የግድ በእውን የተፈጸሙ መሆን የለባቸውም። ከዚህም በላይ የእነዚህ ምሳሌዎች ዓላማ ሥነ ምግባራዊ ትምህርት ማስተማር ስለሆነ ለእያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ ትርጉም ለመስጠት መሞከር አስፈላጊ አይደለም።
b የዚህ ምሳሌ ትንቢታዊ ቁም ነገር በመጠበቂያ ግንብ 4–110 ገጽ 16, 17 ላይ ተብራርቷል።
ለክለሳ ያህል
◻ ኢየሱስ ለምሕረት ያለው አመለካከት ከፈሪሳውያን አመለካከት የሚለየው እንዴት ነበር?
◻ በዛሬው ጊዜ ከአባካኙ ልጅ ጋር የሚመሳሰሉት እነማን ናቸው? እንዴትስ?
◻ አባካኙ ልጅ ወደ ልቡ እንዲመለስ ያደረጉት የትኞቹ ሁኔታዎች ናቸው?
◻ አባትየው ንስሐ ለገባው ልጁ ምሕረትን ያሳየው እንዴት ነበር?
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ወደ ልባቸው ተመለሱ
በአንድ ወቅት ከክርስቲያን ጉባኤ ተወግደው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ወደ ልባቸው እንዲመለሱ የረዳቸው ምንድን ነው? የሚከተሉት አስተያየቶች ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ይሰጣሉ።
“እውነት የት እንዳለ ልቤ ያውቅ ነበር። ቀደም ሲል ለብዙ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘቴ በሕይወቴ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ነበረው። እስከ መቼ ድረስ ለይሖዋ ጀርባዬን ሰጥቼ እቆያለሁ? እሱ አልተወኝም፤ እኔ ግን ትቸዋለሁ። በመጨረሻ ምን ያህል ጥፋተኛና ግትር እንደነበርኩ እንዲሁም ‘የዘራችሁትን ታጭዳላችሁ’ የሚለው የይሖዋ ቃል ሁሌም ትክክል እንደነበር አምኜ ተቀበልኩ።”—ሲ ደብልዩ
“ሕፃን ልጄ መናገር በመጀመሯ ስለ ይሖዋ ማንነትና ወደ እሱ መጸለይ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ላስተምራት ሳስብ ስሜቴ በጣም ተነካ። እንቅልፍ ሊወስደኝ አልቻለም፤ አንድ ቀን ሌሊት ወደ አንድ መናፈሻ ሄጄ አለቀስሁ። ከረዥም ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። እኔ የፈለግሁት እንደገና ከይሖዋ ጋር መወዳጀት ነበር፤ ይቅር ሊለኝ እንደሚችል ተስፋ አደረግሁ።”—ጂ ኤች
“ስለ ሃይማኖት በሚነሣበት ጊዜ እውነትን የሚያስተምረውን ሃይማኖት ምረጪ ብባል የይሖዋ ምሥክር ነበር የምሆነው እያልኩ ለሰዎች እናገር ነበር። ከዚያም የይሖዋ ምሥክር ነበርኩ፤ ሆኖም በዚያ መሠረት መመላለስ ስላልቻልኩ ተውኩት እላለሁ። ይህን በመገንዘቤ ዘወትር የጥፋተኝነትና የሐዘን ስሜት ይሰማኝ ነበር። በመጨረሻም ‘ሕይወቴ እንደተመሰቃቀለና ሥር ነቀል ለውጥ ማድረግ እንዳለብኝ’ አምኜ ተቀበልኩ።”—ሲ ኤን
“እኔና ባለቤቴ የተወገድነው ከዛሬ 35 ዓመት በፊት ነበር። ከዚያም በ1991 ሁለት ሽማግሌዎች አስደሳች ጉብኝት አደረጉልንና ወደ ይሖዋ ለመመለስ የምንችልበት አጋጣሚ ክፍት መሆኑን ነገሩን። ከስድስት ወራት በኋላ ለመመለስ በመቻላችን በጣም ተደሰትን። የባለቤቴ ዕድሜ 79 ሲሆን የእኔ ደግሞ 63 ነው።”—ሲ ኤ