እንደ ኤልያስ ታማኝ ትሆናላችሁ?
“እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ።” —ሚልክያስ 4:5
1. እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ከገቡ ከ500 ዓመት ገደማ በኋላ ምን ተከሰተ?
‘ወተትና ማር የምታፈስስ አገር።’ (ዘጸአት 3:7, 8) ይሖዋ አምላክ በ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ከግብፅ ባርነት ነፃ ካወጣቸው በኋላ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ምድር ከላይ ካለው መግለጫ ጋር የሚስማማ ነበር። አምስት መቶ ዘመናት ካለፉ በኋላ ግን የአሥሩ የእስራኤል ነገዶች መንግሥት ለከፋ ረሃብ ተጋለጠ። ሣሩ ሁሉ ደረቀ። ድርቁ እንስሳትን ጨረሳቸው። ለሦስት ዓመት ተኩል ዝናብ ጠብ አላለም። (1 ነገሥት 18:5፤ ሉቃስ 4:25) ለዚህ ሁሉ መቅሰፍት ምክንያት የሆነው ምንድን ነው?
2. በእስራኤል ሕዝብ ላይ ለደረሰው ቀውስ ምክንያቱ ምን ነበር?
2 ይህን ቀውስ ያመጣው ክህደት ነው። ንጉሥ አክዓብ የአምላክን ሕግ በመጣስ ኤልዛቤል የተባለች የከነዓናውያን ንግሥት አገባና የበኣል አምልኮን በእስራኤል ምድር እንድታስፋፋ ፈቀደላት። ከዚህ ይባስ ብሎም በዋና ከተማዋ በሰማርያ ለዚህ የሐሰት አምላክ የሚሆን ቤተ መቅደስ ሠራ። በዚህም የተነሳ እሥራኤላውያን የበኣል አምልኮ የተትረፈረፈ እህል ያስገኝልናል ብለው በማመን ተታለሉ! ልክ ይሖዋ እንዳስጠነቀቀው ‘ከመልካሚቱ ምድር ፈጥነው የመጥፋት’ አደጋ ላይ ወደቁ።—ዘዳግም 7:3, 4፤ 11:16, 17፤ 1 ነገሥት 16:30-33
አስደናቂው የአምላክነት ፈተና
3. ነቢዩ ኤልያስ በእስራኤላውያን ዋነኛ ችግር ላይ ትኩረት ያደረገው እንዴት ነበር?
3 ረሃቡ እንደ ጀመረ የአምላክ ታማኝ ነቢይ የነበረው ኤልያስ ለንጉሥ አክዓብ “በፊቱ የቆምሁት የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! ከአፌ ቃል በቀር በእነዚህ ዓመታት ጠልና ዝናብ አይሆንም አለው።” (1 ነገሥት 17:1) ንጉሡ በዚህ ቃል ፍጻሜ መሠረት ለገጠመው መራራ ተሞክሮ በእስራኤል ላይ መጥፎ ነገር እንዲደርስ አድርገሃል ሲል ኤልያስን ተጠያቂ አድርጎታል። ይሁን እንጂ ኤልያስ የበኣል አምልኮን በማስፋፋት ከሃዲ የሆኑት አክዓብና ቤተሰቡ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ መሆናቸውን ተናገረ። ለአከራካሪው ጉዳይ እልባት ለማስገኘት የይሖዋ ነቢይ 450 የበኣል ነቢያትንና 400 የማምለኪያ ዐፀድ ነቢያትን ጨምሮ ሁሉንም እስራኤላውያን ወደ ቀርሜሎስ ተራራ እንዲሰበስብ ለንጉሥ አክዓብ ነገረው። ይህ ወቅት ለድርቁ መፍትሄ ያስገኛል በሚል ተስፋ ሳይሆን አይቀርም አክዓብና ተገዥዎቹ ተሰባሰቡ። ሆኖም ኤልያስ ከዚህ ይበልጥ አሳሳቢ ወደሆነ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጥ አደረገ። “እስከ መቼ ድረስ በሁለት አሳብ ታነክሳላችሁ?” ብሎ ከጠየቀ በኋላ “እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤ በኣል ግን አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ” በማለት ተናገረ። እስራኤላውያን የሚናገሩት ጠፋቸው።—1 ነገሥት 18:18-21
4. አምላክነትን በሚመለከት ለተነሳው ግድድር እልባት ለማስገኘት ኤልያስ ምን ሐሳብ አቀረበ?
4 እስራኤላውያን ለብዙ ዓመታት የይሖዋን አምልኮ ከበኣል አምልኮ ጋር ለመደባለቅ ሲጥሩ ቆይተዋል። አምላክነትን በሚመለከት ለተነሳው ጥያቄ እልባት ለማስገኘት ኤልያስ አንድ ወሳኝ ሐሳብ አቀረበ። ለመሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን ለራሱ ያዘጋጃል። ሌላ አንድ ወይፈን ደግሞ የበኣል ነቢያት ያዘጋጃሉ። ከዚያም ኤልያስ “እናንተም የአምላካችሁን ስም ጥሩ፣ እኔም የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶም በእሳት የሚመልስ አምላክ፣ እርሱ አምላክ ይሁን” አለ። (1 ነገሥት 18:23, 24) ለቀረበው ጸሎት መልስ ከሰማይ እሳት ሲወርድ በዓይነ ሕሊናችሁ ተመልከቱ!
5. የበኣል አምልኮ ዋጋ ቢስ መሆኑ የተጋለጠው እንዴት ነው?
5 የበኣል ነቢያት እንዲጀምሩ ኤልያስ ግብዣ አቀረበላቸው። አንድ ወይፈን አዘጋጁና በመሠዊያው ላይ አስቀመጡት። ከዚያም በመሠዊያው ዙሪያ እያሸበሸቡ “በኣል ሆይ፣ ስማን” እያሉ ይጸልዩ ጀመር። ይህንንም “ከጠዋት እስከ ቀትር ድረስ” አደረጉ። ‘እስቲ በኃይል ጮክ በሉ’ በማለት ኤልያስ አሾፈባቸው። በኣል አጣዳፊ ጉዳይ ገጥሞት ይሆናል ወይም “ተኝቶ እንደ ሆነ መቀስቀስ ያስፈልገዋል።” ወዲያውም የበኣል ነቢያት እንደ እብድ ሆኑ። ተመልከቱ! ደማቸው እስኪፈስ ድረስ ገላቸውን በካራ ይቧጭሩ ጀመር። 450ዎቹም ሰዎች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በአንድ ላይ ሲጮኹ እንዴት ያለ ጫጫታ ሊፈጠር እንደሚችል ገምቱ! ሆኖም ምንም መልስ የለም።—1 ነገሥት 18:26-29
6. አምላክነትን በማስመልከት ለተነሳው ፈተና ኤልያስ ምን ዝግጅት አደረገ?
6 አሁን የኤልያስ ተራ ነው። እሱም የይሖዋን መሠዊያ አደሰ፣ በመሠዊያው አጠገብ አንድ ጉድጓድ ቆፈረ፤ እንዲሁም መሥዋዕቱን በሥርዓት አስቀመጠ። ከዚያም በእንጨቱና በመሥዋዕቱ ላይ ውኃ አፈሰሰ። ጉድጓዱ እስኪሞላ ድረስ አሥራ ሁለት ጋን ውኃ በመሥዋዕቱ ላይ ፈሰሰ። ኤልያስ “አቤቱ፣ የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፣ አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ፣ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ፣ ይህንም ሁሉ በቃልህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይገለጥ። አንተ አቤቱ፣ አምላክ እንደ ሆንህ፣ ልባቸውንም ደግሞ እንደ መለስህ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፣ አቤቱ፣ ስማኝ” ብሎ ሲጸልይ ሁኔታው ምን ያህል ልብ እንደሚሰቅል ገምት።—1 ነገሥት 18:30-37
7, 8. (ሀ) ኤልያስ ላቀረበው ጸሎት ይሖዋ መልስ የሰጠው እንዴት ነው? (ለ) በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ምን ነገር ተፈጸመ?
7 ኤልያስ ላቀረበው ጸሎት ምላሽ በመሆን ‘የይሖዋ እሳት ወደቀችና የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ እንጨቱንም ድንጋዮቹንም አፈሩንም በላች፣ በጉድጓዱም ውስጥ ያለውን ውኃ ላሰች።’ ሕዝቡም በግንባራቸው ተደፉና “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እርሱ [“እውነተኛ፣” NW] አምላክ ነው፣ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እርሱ [“እውነተኛ፣” NW] አምላክ ነው አሉ።” (1 ነገሥት 18:38, 39) አሁን ኤልያስ ወሳኝ የሆነ እርምጃ ወሰደ። “ከበኣል ነቢያት አንድ ሰው እንዳያመልጥ ያዙ” ብሎ አዘዘ። በቂሶን ሸለቆ ከታረዱ በኋላ ጥቁር ደመና ሰማዩን ሞላው። ወዲያውም የወረደው ከባድ ዝናብ የድርቁ ፍጻሜ እንዲሆን አደረገ!—1 ነገሥት 18:40-45፤ ከዘዳግም 13:1-5 ጋር አወዳድር።
8 እንዴት ያለ ታላቅ ቀን ነበር! በዚህ አስደናቂ የአምላክነት ፈተና ይሖዋ ድል ተቀዳጀ። ከዚህም በላይ ይህ ክስተት የብዙ እስራኤላውያን ልብ ወደ አምላክ ዞር እንዲል አድርጓል። በዚህና በሌሎች መንገዶች ኤልያስ እውነተኛ ነቢይ መሆኑ ተረጋገጠ፤ እንዲሁም ወደፊት ለሚፈጸም ነገር ትንቢታዊ ጥላ ሆኖ አገለገለ።
“ነቢዩ ኤልያስ” ገና ይመጣል?
9. በሚልክያስ 4:5, 6 ላይ ምን ትንቢት ተነግሯል?
9 ከጊዜ በኋላ አምላክ በነቢዩ ሚልክያስ አማካኝነት “እነሆ፣ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ። መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል” በማለት ትንቢት ተናግሯል። (ሚልክያስ 4:5, 6) ኤልያስ በሕይወት ይኖር የነበረው እነዚህ ቃላት ከመነገራቸው 500 ከሚያክሉ ዓመታት በፊት ነበር። እነዚህ ቃላት ትንቢት እንደመሆናቸው መጠን በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያን ትንቢቱን የሚፈጽመውን የኤልያስን መምጣት በጉጉት ይጠባበቁ ነበር።—ማቴዎስ 17:10
10. ትንቢት የተነገረለት ኤልያስ ማን ነበር? እንዴትስ እናውቃለን?
10 ታዲያ ይመጣል ተብሎ የተነገረለት ኤልያስ ማን ሆኖ ተገኘ? ኢየሱስ ክርስቶስ “ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፣ ግፈኞችም ይናጠቋታል። ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፤ ልትቀበሉትስ ብትወዱ፣ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው” ብሎ በተናገረ ጊዜ የኤልያስ ማንነት ግልጽ ሆነ። አዎን፣ መጥምቁ ዮሐንስ ትንቢት የተነገረለት የኤልያስ አምሳያ ነበር። (ማቴዎስ 11:12-14፤ ማርቆስ 9:11-13) አንድ መልአክ ለዮሐንስ አባት ለዘካርያስ እንደተናገረው ዮሐንስ ‘የኤልያስ መንፈስና ኃይል ያረፈበት’ ስለ ሆነ ‘የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ አሰናድቷል።’ (ሉቃስ 1:17) ዮሐንስ ያከናውን የነበረው ጥምቀት አንድ ሰው በሕጉ ላይ ከፈጸመው ኃጢአት ንስሐ መግባቱን በሕዝብ ፊት የሚያሳይበትና አይሁድን ወደ ክርስቶስ የሚመራ ነበር። (ሉቃስ 3:3-6፤ ገላትያ 3:24) ስለዚህ የዮሐንስ ተግባር ‘የተዘጋጀ ሕዝብ ለይሖዋ ማሰናዳት’ ነበር።
11. በጰንጠቆስጤ ዕለት “የጌታን ቀን” በማስመልከት ጴጥሮስ ምን ተናገረ? ፍጻሜውንስ ያገኘው መቼ ነበር?
11 ዮሐንስ እንደ “ኤልያስ” ሆኖ የሚያከናውነው ሥራ “የጌታ ቀን” መቅረቡን የሚያሳይ ነበር። አምላክ በጠላቶቹ ላይ እርምጃ የሚወስድበትና ሕዝቦቹን የሚያድንበት ያ ቀን መቅረቡን ሐዋርያው ጴጥሮስም አመልክቶ ነበር። በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት የተከናወኑት ተአምራዊ ክስተቶች ኢዩኤል የአምላክ መንፈስ እንደሚፈስ የተነበየው ትንቢት ፍጻሜ መሆኑን አመልክቷል። ጴጥሮስ “ታላቁና አስፈሪው የእግዚአብሔር ቀን” ከመምጣቱ በፊት ይህ እንደሚፈጸም መናገሩ ነበር። (ሥራ 2:16-21 የ1980 ትርጉም፤ ኢዩኤል 2:28-32) ይሖዋ ልጁን በናቀው ሕዝብ ላይ የሮም ሠራዊት መጥቶ መለኮታዊ ፍርድ እንዲያስፈጽም በማድረግ ትንቢቱ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደረገው በ70 እዘአ ነበር።—ዳንኤል 9:24-27፤ ዮሐንስ 19:15
12. (ሀ) ጳውሎስና ጴጥሮስ ስለሚመጣው “የጌታ ቀን” ምን ተናገሩ? (ለ) ኤልያስ ባከናወነው ሥራ የሚወከል አንድ ተጨማሪ ነገር ፍጻሜውን ማግኘት የነበረበት ለምንድን ነው?
12 ሆኖም ከ70 እዘአ በኋላ ከዚያ የበለጠ ነገር ይመጣ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ “የጌታን ቀን” መምጣት ከኢየሱስ ክርስቶስ መገኘት ጋር አያይዞ ተናግሯል። ከዚህም በላይ ሐዋርያው ጴጥሮስ ገና ወደፊት ከሚመጣው “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ጋር በማያያዝ ስለዚያ ቀን ተናግሯል። (2 ተሰሎንቄ 2:1, 2፤ 2 ጴጥሮስ 3:10-13) ‘የይሖዋ ቀን’ በ70 እዘአ ከመምጣቱ በፊት አጥማቂው ዮሐንስ የኤልያስ ዓይነት ሥራ እንዳከናወነ ልብ በሉ። ይህ ሁሉ፣ ኤልያስ ባከናወነው ዓይነት ሥራ የሚወከል አንድ ተጨማሪ ነገር ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ያመለክታል። ይህ ነገር ምንድን ነው?
የኤልያስ መንፈስ አላቸው
13, 14. (ሀ) ኤልያስ ባከናወነው ነገርና በጊዜያችን ያሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሚያከናውኑት ሥራ መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ? (ለ) ከሃዲዋ ሕዝበ ክርስትና ምን አድርጋለች?
13 ኤልያስ ያከናወነው ሥራ አጥማቂው ዮሐንስ ላከናወነው ሥራ ብቻ ሳይሆን ወደ “ጌታ ቀን” በሚያመራው በዚህ አስጨናቂ ዘመን የሚኖሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለሚያከናውኑት ሥራም ጥላነት አለው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) የኤልያስ ዓይነት መንፈስና ኃይል ያላቸው የእውነተኛው አምልኮ ታማኝ ደጋፊዎች ሆነዋል። ይህም ምንኛ ተገቢ ነበር! በኤልያስ ዘመን የበኣል አምልኮ በእስራኤል ተስፋፍቶ እንደነበረ ሁሉ የክርስቶስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላም ከእውነተኛው ክርስትና ክህደት ብቅ ብሏል። (2 ጴጥሮስ 2:1) አስመሳይ ክርስቲያኖች ክርስትናን ከሐሰተኛ የሃይማኖት ትምህርቶችና ልማዶች ጋር መቀላቀል ጀመሩ። ለምሳሌ ያህል ሰው የማትሞት ነፍስ አለችው የሚለውን አረመኔአዊ የሆነና ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የሌለውን ትምህርት ተቀበሉ። (መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4) ከሃዲዋ ሕዝበ ክርስትና ይሖዋ የሚለውን የእውነተኛውን አምላክ ብቸኛ ስም ከመጠቀም ተቆጥባለች። ከዚህ ይልቅ ሥላሴን ያመልካሉ። ከዚህም በተጨማሪ በኢየሱስና በእናቱ በማርያም ምስል ፊት በመውደቅ የበኣል አምልኮን የሚመስል ልማድ ተከትለዋል። (ሮሜ 1:23፤ 1 ዮሐንስ 5:21) ሆኖም ነገሩ በዚህ ብቻ አያበቃም።
14 ከ19ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው በግልጽ መናገር ጀመሩ። ለምሳሌ ያህል በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የሰፈረውን የፍጥረት ዘገባ ትተው “ሳይንስ” በሚል ሽፋን ለዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ይሰግዳሉ። ይህም ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ ካስተማሯቸው ትምህርቶች ጋር በቀጥታ የሚጋጭ ነው። (ማቴዎስ 19:4, 5፤ 1 ቆሮንቶስ 15:47) እንደ ኢየሱስና የጥንት ተከታዮቹ በአሁኑ ጊዜ ያሉት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን የፍጥረት ዘገባ ይደግፋሉ።—ዘፍጥረት 1:27
15, 16. ከሕዝበ ክርስትና በተለየ መንገድ ቀጣይ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ እያገኙ ያሉት እነማን ናቸው? የሚያገኙትስ በማን በኩል ነው?
15 ዓለም “ወደ መጨረሻው ቀን” ዘልቆ በገባ መጠን ሕዝበ ክርስትና መንፈሳዊ ረሃብ አጥቅቷታል። (ዳንኤል 12:4፤ አሞጽ 8:11, 12) ይሁን እንጂ ይሖዋ በረሃቡ ዘመን ኤልያስን እንደመገበው ሁሉ የቅቡዓን ክርስቲያኖች አነስተኛ ቡድንም ዘወትር አምላክ የሚሰጣቸውን መንፈሳዊ ምግብ ‘በተገቢው ጊዜ’ በማግኘት ደስታ አግኝተዋል። (ማቴዎስ 24:45፤ 1 ነገሥት 17:6, 13-16) በአንድ ወቅት ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው የሚታወቁት እነዚህ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ታማኝ አገልጋዮች ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መጠሪያ ስም ተቀበሉ።—ኢሳይያስ 43:10
16 ኤልያስ “አምላኬ ይሖዋ ነው” ከሚለው የስሙ ትርጉም ጋር ተስማምቶ ኖሯል። የይሖዋ ምድራዊ አገልጋዮች ዋነኛ መጽሔት የሆነው መጠበቂያ ግንብ በአምላክ ስም ያለማቋረጥ ይጠቀማል። እንዲያውም የመጽሔቱ ሁለተኛ እትም (በነሐሴ 1879) የይሖዋ እጅ ከበስተኋላው እንዳለ ያለውን ትምክህት ገልጿል። ይህ መጽሔትና የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሚያትማቸው ሌሎች ጽሑፎችም የአምላክ ቃል የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኝነት በመደገፍ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የሌለውን የሕዝበ ክርስትናንም ሆነ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችውን የታላቂቱ ባቢሎንን ሌሎች አባላት ትምህርቶች አጋልጧል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17፤ ራእይ 18:1-5
በፈተና ጊዜ ታማኝ መሆን
17, 18. የበኣል ነቢያት በመታረዳቸው ምክንያት ኤልዛቤል የተሰማት ስሜት ምን ነበር? ሆኖም ኤልያስ እርዳታ ያገኘው እንዴት ነበር?
17 ቀሳውስት ሐሰተኝነታቸው ሲጋለጥ የተሰማቸው ስሜት ኤልያስ የበኣል ነቢያትን እንደገደለ ኤልዛቤል በሰማች ጊዜ የተሰማት ዓይነት ስሜት ነው። እንደምትገድለው በመሃላ በማረጋገጥ ለይሖዋ ታማኝ ነቢይ መልእክት ላከችበት። ኤልዛቤል ብዙ የአምላክ ነቢያትን ገድላ ስለነበር ይህ እንዲያው የተነገረ ማስፈራሪያ አልነበረም። ኤልያስም በመፍራት በደቡባዊ ምዕራብ በኩል ወዳለው ወደ ቤርሳቤህ ሸሸ። ሎሌውን እዛ ትቶ ተጨማሪ ጉዞ በማድረግ ወደ ምድረ በዳ ዘልቆ ሄደና እንዲሞት ጸለየ። ይሁን እንጂ ይሖዋ ነቢዩን አልተወውም። ወደ ኮሬብ ተራራ ለሚያደርገው ረዥም ጉዞ ለማዘጋጀት አንድ መልአክ ለኤልያስ ተገለጠለት። በዚህ መንገድ ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ ለሚርቀውና 40 ቀን ለሚፈጀው ጉዞ የሚሆን ስንቅ ተቀበለ። በታላቅ ነፋስ፣ በምድር መናወጥና በእሳት አማካኝነት አስፈሪ ኃይል ከተገለጠ በኋላ አምላክ በኮሬብ አነጋገረው። ይሖዋ በእዚህ መግለጫ ውስጥ አልነበረም። እነዚህ የመንፈስ ቅዱሱ ወይም የአንቀሳቃሽ ኃይሉ መግለጫዎች ነበሩ። ከዚያም ይሖዋ ነቢዩን አነጋገረው። ይህ ተሞክሮ ኤልያስን ምን ያህል እንዳጠነከረው ገምቱ። (1 ነገሥት 19:1-12) እኛም የእውነተኛው አምልኮ ጠላቶች ሲዝቱብን ልክ እንደ ኤልያስ በፍርሃት ብንዋጥስ? በኤልያስ የታየው ተሞክሮ ይሖዋ ሕዝቡን እንደማይጥል እንድንገነዘብ ሊረዳን ይገባል።—1 ሳሙኤል 12:22
18 ኤልያስ ነቢይ ሆኖ የሚሠራቸው ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚኖሩ አምላክ ገልጾ ነበር። ከዚህም በላይ ኤልያስ በእስራኤል የቀረ የእውነተኛው አምላክ አገልጋይ እርሱ ብቻ እንደሆነ አድርጎ ቢያስብም ይሖዋ ለበኣል ያልሰገዱ 7,000 ሰዎችን አሳየው። ከዚያም አምላክ ኤልያስን ወደ ምድብ ሥራው ላከው። (1 ነገሥት 19:13-18) እንደ ኤልያስ የእውነተኛ አምልኮ ጠላቶች እኛንም ሊያሳድዱን ይችላሉ። ኢየሱስ እንደተነበየው ለከፍተኛ ስደት ልንጋለጥ እንችላለን። (ዮሐንስ 15:17-20) አንዳንድ ጊዜም ስጋት ላይ ልንወድቅ እንችላለን። ይሁን እንጂ መለኮታዊ ማረጋገጫ እንዳገኘውና በይሖዋ አገልግሎት በታማኝነት እንደጸናው እንደ ኤልያስ ልንሆን እንችላለን።
19. በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን ነገር ደረሰባቸው?
19 በአንደኛው የዓለም ጦርነት ከባድ ስደት በመድረሱ ምክንያት አንዳንድ ክርስቲያኖች በፍርሃት መስበክ አቁመው ነበር። ምድር ላይ የሚያከናውኑት ሥራ አብቅቷል ብለው ማሰባቸው ስህተት ላይ ጥሏቸው ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ አልፈልጋችሁም አላላቸውም። ከዚያ ይልቅ ልክ ለኤልያስ ምግብ እንደሰጠው ሁሉ እነርሱንም በምህረቱ ደግፏቸዋል። ታማኞቹ ቅቡዓን እንደ ኤልያስ መለኮታዊ ማስተካከያዎችን ተቀብለው እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ። የመንግሥቱን መልእክት ለመስበክ የተሰጣቸውን ታላቅ መብት ለማየት ዓይኖቻቸው ተከፈቱ።
20. በዛሬው ጊዜ እንደ ኤልያስ ታማኝ የሆኑት ምን መብት አግኝተዋል?
20 ኢየሱስ ስለ መገኘቱ በተናገረው ትንቢት ውስጥ ይህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ከመጥፋቱ በፊት መጠናቀቅ ያለበት ዓለም አቀፍ ሥራ እንደሚኖር ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) ዛሬ በቅቡዓን ክርስቲያኖችና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ በሚልዮን በሚቆጠሩ ጓደኞቻቸው ይህን ሥራ በማከናወን ላይ ናቸው። ፍጻሜው እስኪመጣ ድረስ የመንግሥቱን የስብከት ሥራ የማከናወን መብት ያገኙት እንደ ኤልያስ ታማኝ የሆኑት ብቻ ናቸው።
እንደ ኤልያስ ታማኝ ሁኑ
21, 22. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በግንባር ቀደምትነት የሚያከናውኑት ሥራ ምንድን ነው? (ለ) የስብከቱ ሥራ እየተከናወነ ያለው ማን በሚሰጠው ድጋፍ ነው? ይህስ ድጋፍ ያስፈለገው ለምንድን ነው?
21 እውነተኞቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደ ኤልያስ ቀናተኛ በመሆን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሆነው እንዲሠሩት የሰጣቸውን ሥራ በኃላፊነት በማከናወን ላይ ይገኛሉ። (ማቴዎስ 24:47) አምላክ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለመኖር አስደናቂ ተስፋ የሰጣቸውን ሰዎች ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ እነዚህን ቅቡዓን 60 ለሚያክሉ ዓመታት ሲጠቀምባቸው ቆይቷል። (ማቴዎስ 28:19, 20) እነዚህ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአንፃራዊ ሁኔታ ጥቂት የሆኑት ቅቡዓን የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ሁሉ በቅንዓትና በታማኝነት ሲያከናውኑላቸው ምንኛ ይደሰቱ ይሆን!
22 ይህ የስብከት ሥራ የሚከናወነው በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ ላይ በመደገፍ ኃይል በሚያገኙ ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች ነው። ጻድቅ ሰው የሚያቀርበው ጸሎት ምን ያህል ኃይል እንዳለው ለመግለጽ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ የነቢዩን ጸሎት እንደ ምሳሌ አድርጎ በመጥቀስ “ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ” በማለት ተናግሯል። (ያዕቆብ 5:16-18) ኤልያስ ሁልጊዜ ትንቢት የሚናገርና ተዓምር የሚሠራ ሰው አልነበረም። አንድ ሰብዓዊ ሰው ያለው ዓይነት ስሜቶችና ድክመቶች ነበሩበት። ሆኖም አምላክን በታማኝነት አገልግሏል። እኛም አምላክ ስለሚረዳንና ስለሚደግፈን እንደ ኤልያስ ታማኝ መሆን እንችላለን።
23. ታማኝ ለመሆንና ብሩህ አመለካከት ለመያዝ ጥሩ ምክንያት ያለን በምን የተነሳ ነው?
23 ታማኝ ለመሆንና ብሩህ አመለካከት ለመያዝ ጥሩ ምክንያቶች አሉን። “የጌታ ቀን” በ70 እዘአ ከመምጣቱ በፊት አጥማቂው ዮሐንስ የኤልያስ ዓይነት ሥራ አከናውኗል። ቅቡዓን ክርስቲያኖችም በኤልያስ መንፈስና ኃይል አምላክ የሰጠውን ተመሳሳይ ሥራ በዓለም ዙሪያ አከናውነዋል። ይህም “የጌታ ቀን” በጣም ቅርብ መሆኑን በማያሻማ መንገድ ያረጋግጣል።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ በቀርሜሎስ ተራራ የይሖዋ አምላክነት የተረጋገጠው እንዴት ነበር?
◻ ‘የሚመጣው ኤልያስ’ ማን ነበር? ምንስ አከናወነ?
◻ በዛሬው ጊዜ ያሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የኤልያስ ዓይነት መንፈስ እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?
◻ እንደ ኤልያስ ታማኝ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ኤልያስ የተነጠቀው ወደ የትኛው ሰማይ ነው?
“[ኤልያስ እና ኤልሳዕ] ሲሄዱም፣ እያዘገሙም ሲጫወቱ፣ እነሆ፣ የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ።”—2 ነገሥት 2:11
እዚህ ላይ “ሰማይ” ተብሎ የተጠቀሰው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? አንዳንድ ጊዜ ቃሉ አምላክና መላእክቱ የሚኖሩበትን መንፈሳዊ ቦታ ያመለክታል። (ማቴዎስ 6:9፤ 18:10) በተጨማሪም “ሰማይ” ግዑዙን ጠፈር ሊያመለክት ይችላል። (ዘዳግም 4:19) እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ቃል አእዋፋት የሚበሩበትንና ነፋስ የሚነፍስበትን የምድርን ከባቢ አየር ለማመልከት ይጠቀምበታል።—መዝሙር 78:26፤ ማቴዎስ 6:26
ታዲያ ኤልያስ ከእነዚህ ሰማያት መካከል የወጣው ወደየትኛው ሰማይ ነው? ኤልያስ የምድርን ከባቢ አየር አቋርጦ ወደ ሌላኛው የምድር ክፍል እንደሄደ ከሁኔታዎቹ ለመረዳት ይቻላል። ኤልያስ ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮራም ደብዳቤ መላኩ ከብዙ ዓመታትም በኋላ ቢሆን በምድር ላይ ይኖር እንደነበር ያሳያል። (2 ዜና መዋዕል 21:1, 12-15) ኤልያስ ይሖዋ አምላክ ወደሚኖርበት መንፈሳዊ መኖሪያ እንዳልወጣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከብዙ ጊዜ በኋላ “ከሰማይ ከወረደው በቀር” ማለትም ከራሱ ከኢየሱስ በቀር “ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም” ብሎ በተናገረ ጊዜ ጉዳዩን የበለጠ ግልጽ አድርጎታል። (ዮሐንስ 3:13) ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሰማይ እንዲሄዱ አጋጣሚው የተከፈተላቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞተና ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ነው።—ዮሐንስ 14:2, 3፤ ዕብራውያን 9:24፤ 10:19, 20