ነቅቶ መጠበቅ የሚያስፈልግበት ጊዜ
“አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል። . . . እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።”—ማርቆስ 13:10, 13
1. መጽናትና ደፋር መሆን የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
በዚህ ጠማማና እምነተ ቢስ ትውልድ መካከል ስንኖር መጽናት ያስፈልገናል! በኢየሱስ ዘመን እንደ ነበረው ሁሉ ከ1914 ጀምሮ ያለው የሰዎች ትውልድ ብልሹ ሆኗል። በአሁኑ ጊዜ ይህ ምግባረ ብልሹነት በመላው ዓለም ተሰራጭቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ “አስጨናቂ” በማለት የገለጸው ይህ “የመጨረሻ ቀን” የሰው ልጆችን በማሠቃየት ላይ ነው። ‘ክፉዎችና አታላዮች በክፋት እየባሱ መሄዳቸውን ቀጥለዋል።’ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው “ዓለም በሞላው በክፉው” በሰይጣን ዲያብሎስ ተይዟል። እርሱም በአሁኑ ጊዜ ምድርን ለማጥፋት የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ላይ ነው። ሆኖም ተስፋ አትቁረጡ! ጽድቅን ለሚያፈቅሩ በሙሉ ዘላቂ እፎይታ የሚያመጣላቸው መጪው “ታላቅ መከራ” አለ።—2 ጢሞቴዎስ 3:1–5, 13፤ 1 ዮሐንስ 5:19፤ ራእይ 7:14
2. አንድ ትንቢት በ1914 የተፈጸመው እንዴት ነው?
2 ይሖዋ ጨቋኝ የሆኑ የሰው ዘር ጠላቶችን ለማጥፋት ቅድመ ዝግጅት እንዲሆን በአሁኑ ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በሰማይ በዙፋን ላይ ማስቀመጡ ያስደስታል። (ራእይ 11:15) መሲሕ በመጀመሪያ በመጣበት ወቅት እንደ ሆነው ሁሉ በዚህ መቶ ዘመንም ዳንኤል የጻፈው አንድ አስደናቂ ትንቢት ይፈጸማል። ዳንኤል 4:16, 17, 32 የአንድ ንጉሣዊ መስተዳድር ምድርን የመግዛት መብት “ለሰባት ዘመናት” እንደሚቋረጥ ይነግረናል። ሰባቱ ዘመናት በከፍተኛ ደረጃ ሲፈጸሙ እያንዳንዳቸው 360 ‘ቀናትን’ የያዙ ሰባት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዓመታት ወይም 2, 520 ዓመታት ይሆናሉ።a እነዚህ ዘመናት ባቢሎን የእስራኤልን መንግሥት ከረገጠችበት ከ607 ከዘአበ ይጀመሩና ኢየሱስ ሕጋዊ መብት ያለው የሰው ልጆች ንጉሥ ሆኖ በሰማይ በዙፋን ላይ እስከ ተቀመጠበት እስከ 1914 ድረስ ያለውን ጊዜ ያጠቃልላሉ። በዚያን ጊዜ “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” አበቁ። (ሉቃስ 21:24 አዓት) ይሁን እንጂ ብሔራት ሥልጣናቸውን ለመጪው መሲሐዊ መንግሥት ለማስረከብ አሻፈረኝ ብለዋል።—መዝሙር 2:1–6, 10–12፤ 110:1, 2
3, 4. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ሁኔታዎች በዘመናችን ካሉት ሁኔታዎች ጋር ማወዳደር የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) ከዚህ ጉዳይ ጋር የሚያያዙ ምን ጥያቄዎች ሊነሡ ይችላሉ?
3 ሰባኛው የዓመታት ሳምንትም (29–36 እዘአ) ሆነ 1914 ተቃርበው በነበሩበት ወቅት ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ሰዎች መሲሕ ይመጣል ብለው ሲጠባበቁ ነበር። እንደ ተጠበቀውም መጣ! ሆኖም በሁለቱም ወቅቶች ኢየሱስ የመጣበት መንገድ ከተጠበቀው የተለየ ነበር። በተጨማሪም በሁለቱም ወቅቶች በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ከአጭር ጊዜ በኋላ በመጨረሻ አንድ ክፉ “ትውልድ” መለኮታዊ ፍርድ ተበይኖበታል ወይም ይበየንበታል።—ማቴዎስ 24:34
4 ባለፈው ርዕሳችን ላይ ኢየሱስ እንዲገደል የጠየቀው ክፉ የአይሁድ ትውልድ እንዴት ወደ ፍጻሜው እንደመጣ ተመልክተን ነበር። ታዲያ በአሁኑ ጊዜ እሱን የሚቃወመው ወይም ችላ የሚለው መጥፎ የሰው ልጆች ትውልድ ምን ይሆናል? በዚህ እምነተ ቢስ ትውልድ ላይ የሚፈረደው መቼ ነው?
“ነቅታችሁ ጠብቁ”!
5. (ሀ) ይሖዋ የወሰነውን ‘ቀንና ሰዓት’ ማወቅ የማያስፈልገን በየትኛው በቂ ምክንያት ነው? (ለ) በማርቆስ ዘገባ መሠረት ኢየሱስ ትንቢቱን የደመደመው የትኛውን ተገቢ ምክር በመስጠት ነው?
5 ኢየሱስ ወደ “ታላቅ መከራ” የሚያመሩትን ሁኔታዎች ከተነበየ በኋላ አክሎ ሲናገር “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም” ብሏል። (ማቴዎስ 24:3–36፤ ማርቆስ 13:3–32) ሁኔታዎቹ የሚፈጸሙበትን ትክክለኛ ጊዜ ማወቅ አያስፈልገንም። ከዚህ ይልቅ ትኩረታችን ቀንን በማስላት ላይ ሳይሆን ነቅቶ በመጠበቅ፣ ጠንካራ እምነት በመገንባትና ይሖዋን በማገልገሉ ተግባር በመጠመድ ላይ መሆን ይኖርበታል። ኢየሱስ ታላቅ ትንቢቱን የደመደመው እንዲህ በማለት ነበር፦ “የተወሰነው ጊዜ መቼ እንደሆነ ስለማታውቁ አትዘናጉ፤ ነቅታችሁ ኑሩ። . . . ነቅታችሁ ጠብቁ። . . . ለእናንተ እንደ ነገርኳችሁ ሁሉ ለሁሉም ነቅታችሁ ጠብቁ እላለሁ።” (ማርቆስ 13:33–37 አዓት) ዛሬ ባለው የጨለመ ዓለም ውስጥ አደጋ ተጋርጧል። ዘወትር ንቁዎች መሆን አለብን!—ሮሜ 13:11–13
6. (ሀ) እምነታችን በምን ላይ በጥብቅ መመሥረት ይኖርበታል? (ለ) ‘ቀኖቻችንን ልንቆጥር’ የምንችለው እንዴት ነው? (ሐ) በመሠረቱ፣ ኢየሱስ “ትውልድ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
6 ስለዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች የሚገልጹትን በመንፈስ አነሣሽነት የተነገሩ ትንቢቶች በትኩረት መከታተል ብቻ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ውድ መሥዋዕትና አምላክ ይህን መሥዋዕት መሠረት በማድረግ በሰጣቸው አስደናቂ ተስፋዎቸ ላይ እምነታችን መልሕቅ እንዲጥል ማድረግ ይኖርብናል። (ዕብራውያን 6:17–19፤ 9:14፤ 1 ጴጥሮስ 1:18, 19፤ 2 ጴጥሮስ 1:16–19) የይሖዋ ሕዝቦች የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ ለማየት ካላቸው ጉጉት የተነሣ አንዳንድ ጊዜ “ታላቁ መከራ” የሚጀምርበትን ጊዜ ለመገመት ሞክረዋል። ሌላው ቀርቶ ከ1914 ጀምሮ ያለው ትውልድ ምን ያህል ዕድሜ ሊኖረው እንደሚችል በማስላት ታላቁን መከራ ከዚህ ጋር ለማገናኘት ሞክረዋል። ይሁን እንጂ “ጥበበኛ ልብ” እንዲኖረን የምናደርገው አንድ ትውልድ ምን ያህል ዓመታት ወይም ቀናት እንደሚኖሩት በማውጣትና በማውረድ ሳይሆን ለይሖዋ ውዳሴ በሚያመጣ መንገድ ‘ቀኖቻችንን እንዴት እንደምንቆጥር’ በማሰብ ነው። (መዝሙር 90:12 አዓት) ኢየሱስ የተጠቀመበት “ትውልድ” የሚለው ቃል ጊዜን ለመለካት የሚያስችል ደንብ የሚሰጥ ሳይሆን በተለየ ጠባያቸው ተለይተው የሚታወቁ በአንድ ታሪካዊ ዘመን የሚገኙ ሰዎችን የሚያመለክት ነው።b
7. አንድ የታሪክ ምሁር ስለ “የ1914 ትውልድ” የጻፉት ምን ብለው ነው? ይህስ ከኢየሱስ ትንቢት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?
7 ከላይ ከተጠቀሰው ሐሳብ ጋር በመስማማት የታሪክ ምሁር የሆኑት ሮበርት ቮል ዘ ጀነሬሽን ኦቭ 1914 (የ1914 ትውልድ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “አንድ ታሪካዊ ትውልድ በተወሰኑ ዓመታት ሊሰላ አይችልም። . . . በተወሰኑ ዓመታት ክልል ውስጥ ያለ ነገር አይደለም” ሲሉ ጽፈዋል። ይሁን እንጂ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት “ካለፉት ዘመናት በጣም የተለየ” እንደሆነ ከገለጹ በኋላ በዚህ ጉዳይ ላይ አክለው ሲናገሩ “ከጦርነቱ በሕይወት የተረፉት ሰዎች በነሐሴ 1914 ከዚያ በፊት የነበረ አንድ ዓለም ጠፍቶ በሌላ ዓለም ስለመተካቱ ያላቸው እምነት ከአእምሮአቸው ሊጠፋ አልቻለም” ብለዋል። ይህ ምንኛ እውነት ነው! ይህ አነጋገር በጉዳዩ ዋና ቁም ነገር ላይ የሚያተኩር ነው። “ይህ ትውልድ” ከ1914 ጀምሮ በጣም አስደንጋጭ የሆኑ ለውጦች ደርሰውበታል። ምድር በሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ደም ስትርስ ተመልክቷል። ጦርነት፣ የዘር ጭፍጨፋ፣ ሽብርተኝነት፣ ወንጀልና ዓመፅ በመላው ዓለም ተስፋፍቷል። ረሃብ፣ በሽታና የሥነ ምግባር ብልግና በዓለማችን ላይ የስጋት ጥላ አጥልቷል። ኢየሱስ “እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” በማለት ተንብዮ ነበር።—ሉቃስ 21:31, 32
8. የይሖዋ ነቢያቶች ንቁ ሆኖ የመገኘትን አስፈላጊነት ያጎሉት እንዴት ነው?
8 አዎን፣ መሲሐዊው መንግሥት ሙሉ በሙሉ ድል የሚቀዳጅበት ጊዜ ቀርቧል! ታዲያ ዘመናትን ማስላት ወይም ደግሞ ቃል በቃል የአንድ “ትውልድ” ዕድሜ ምን ያህል እንደሆነ መመርመር ፋይዳ ይኖረዋልን? ፈጽሞ አይኖረውም! ዕንባቆም 2:3 “ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፣ ወደ ፍጻሜውም ይቸኩላል፣ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱም አይዘገይም” ይላል። ይሖዋ ፍርድ የሚሰጥበት ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ በፍጥነት እየቀረበ ነው።—ኤርምያስ 25:31–33፤ ሚልክያስ 4:1
9. ከ1914 ጀምሮ የተከሰቱት ሁኔታዎች ጊዜው አጭር እንደሆነ የሚያሳዩት እንዴት ነው?
9 የክርስቶስ መንግሥት በ1914 መግዛት ስትጀምር ሰይጣን ወደ ምድር ተጣለ። በዚህም ምክንያት ‘ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እኛ ስለ ወረደ በምድር ላይ . . . ወዮታ’ አስከትሏል። (ራእይ 12:12) ይህ ጊዜ ሰይጣን ከገዛባቸው በሺ የሚቆጠሩ ዓመታት ጋር ሲወዳደር በእርግጥም ጥቂት ነው። መንግሥቱ ቀርቧል! ስለሆነም ይሖዋ በዚህ ክፉ ትውልድ ላይ ፍርድ የሚሰጥበት ቀንና ሰዓት ደርሷል!—ምሳሌ 3:25፤ 10:24, 25
የሚያልፈው “ትውልድ”
10. “ይህ ትውልድ” ከኖኅ ዘመን ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
10 “እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ ቃሌ ግን አያልፍም” የሚለውን በማቴዎስ 24:34, 35 ላይ የሚገኘውን የኢየሱስ አነጋገር በጥልቀት እንመርምረው። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ከዚያ ቀጥለው ያሉት የኢየሱስ ቃላት ‘ማንም ቀኑንና ሰዓቱን እንደማያውቅ’ ያሳያሉ። ከዚህ የበለጠ አስፈላጊ የሆነው በዙሪያችን የከበበን ይህ ትውልድ ከሚያመጣቸው ወጥመዶች መሸሻችን እንደሆነ ጠቁሟል። ይህም በመሆኑ ኢየሱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ሲያክል እንዲህ ብሏል፦ “የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፣ ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፣ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩ፣ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፣ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:36–39) ኢየሱስ እዚህ ላይ በዘመኑ የነበረውን ትውልድ ከኖኅ ዘመን ትውልድ ጋር አወዳድሮታል።—ዘፍጥረት 6:5, 9፤ የአዓት የግርጌ ማስታወሻ።
11. ማቴዎስና ሉቃስ በዘገቡት መሠረት ኢየሱስ ‘ትውልዶችን’ ያወዳደረው እንዴት ነው?
11 ሐዋርያት ኢየሱስ ‘ትውልዶችን’ ከሌላ ዘመን ጋር ሲያወዳድር ሲሰሙ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አልነበረም። ምክንያቱም ከጥቂት ቀናት በፊት ስለ ራሱ ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የሰው ልጅ . . . ብዙ መከራ እንዲቀበል ከዚህም ትውልድ እንዲጣል ይገባዋል። በኖኅ ዘመንም እንደ ሆነ ፣ በሰው ልጅ ዘመን ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።” (ሉቃስ 17:24–26 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ስለዚህ ማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና ሉቃስ ምዕራፍ 17 ተመሳሳይ ነገሮችን ያወዳድራሉ። በኖኅ ዘመን “ሥጋን የለበሰ ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበር።” በጥፋት ውኃ የጠፋውም “ይህ ትውልድ” ነበር። በኢየሱስ ዘመን “ይህ ትውልድ” ተብሎ የተጠሩት ኢየሱስን ሳይቀበሉ የቀሩት ከሃዲ የአይሁድ ሕዝቦች ነበሩ።—ዘፍጥረት 6:11, 12፤ 7:1
12, 13. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ማለፍ ያለበት “ይህ ትውልድ” የትኛው ነው? (ለ) በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች ይህን “ክፉና ጠማማ ትውልድ” የሚቋቋሙት እንዴት ነው?
12 እንግዲያውስ የኢየሱስ ትንቢት የመጨረሻ ፍጻሜውን በሚያገኝበት በዛሬው ጊዜ “ይህ ትውልድ” የሚሉት ቃላት የክርስቶስን መገኘት ምልክት የሚያዩትን ነገር ግን ሕይወታቸውን ሳያስተካክሉ የሚቀሩትን በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች የሚያመለክት ይመስላል። እኛ ግን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደ መሆናችን መጠን ‘የዚህ ትውልድ’ የአኗኗር ዘይቤ እንዲለውጠን አንፈለግም። ‘ዘመኑ ስለ ቀረበ’ ምንም እንኳ በዓለም ውስጥ ብንሆንም የዓለም ክፍል መሆን የለብንም። (ራእይ 1:3፤ ዮሐንስ 17:16) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት አሳስቦናል፦ “በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጎራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ በእነርሱም መካከል . . . በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ።”—ፊልጵስዩስ 2:14, 15፤ ቆላስይስ 3:5–10፤ 1 ዮሐንስ 2:15–17
13 “እንደ ብርሃን” የምንታየው ንጹሕ ክርስቲያናዊ ባሕርይ በማሳየት ብቻ አይደለም። ከሁሉም በላይ ይህን ማድረግ የምንችለው ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ሲል የሰጠንን ትንቢታዊ ተልእኮ በመፈጸም ነው። (ማቴዎስ 24:14) መጨረሻው መቼ እንደሚመጣ ማንም ሊያውቅ አይችልም። ሆኖም ምሥክርነቱ አምላክን የሚያረካውን ያህል “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ከተሰጠ በኋላ የክፉ ሰዎች ጥርቅም የሆነው ‘የዚህ ትውልድ’ ፍጻሜ እንደሚሆን እናውቃለን።—ሥራ 1:8
‘ያቺ ቀንና ሰዓት’
14. ኢየሱስና ጳውሎስ “ጊዜያትንና ወራትን” በተመለከተ ምን ማሳሰቢያ ሰጥተዋል? እኛስ እንዴት ያለ ምላሽ መስጠት ይኖርብናል?
14 በመላው ዓለም የሚሰጠው ምሥክርነት አምላክ ያሰበውን ያህል ከተከናወነ በኋላ የዚህ ዓለም ሥርዓት የሚጠፋበት ‘ቀንና ሰዓት’ ይሆናል። ቀኑን በቅድሚያ ማወቅ አያስፈልገንም። ይህም በመሆኑ ሐዋርያው ጳውሎስ የኢየሱስን ምሳሌ ተከትሎ እንዲህ በማለት አሳስቧል፦ “ወንድሞች ሆይ፣ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ የጌታ ቀን፣ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፣ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ ፣ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም።” ጳውሎስ ያተኮረበትን “ሲሉ” የሚለውን ቃል አስተውሉ። አዎን፣ ስለ “ሰላምና ደኅንነት” ሲወራ ባልታሰበ ወቅት አምላክ በድንገት ፍርድ ይሰጣል። ጳውሎስ “እንግዲያስ እንንቃ በመጠን እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ” በማለት የሰጠው ምክር ምንኛ ተገቢ ነው!—1 ተሰሎንቄ 5:1–3, 6፤ በተጨማሪም ከ7–11 ያሉትን ቁጥሮች ተመልከት፤ ሥራ 1:7
15, 16. (ሀ) አርማጌዶን ከጠበቅነው በላይ ይርቃል ብለን ማሰብ የማይኖርብን ለምንድን ነው? (ለ) በቅርቡ የይሖዋ ሉዓላዊነት ከፍ ከፍ የሚለው እንዴት ነው?
15 “ይህ ትውልድ” ስለሚሉት ቃላት ያገኘነው ይህ ይበልጥ ትክክለኛ የሆነ አመለካከት አርማጌዶን ከዚህ በፊት ካሰብነው በላይ ሩቅ እንደሚሆን ያሳያልን? ፈጽሞ አያሳይም! እኛ በጭራሽ ‘ቀኑንና ሰዓቱን’ ባናውቅም ይሖዋ ምን ጊዜም ያውቀዋል። ቀኑን አይለውጠውም። (ሚልክያስ 3:6) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ዓለም ወደ መጨረሻው ጥፋት እያመራ ነው። ነቅቶ የመጠበቅ አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳሳቢ ሆኗል። ይሖዋ ‘በቅርቡ የሚሆነውን ነገር’ ስለ ገለጸልን ወቅቱ ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ በመረዳት አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ይኖርብናል።—ራእይ 1:1፤ 11:18፤ 16:14, 16
16 ጊዜው ወደ ፊት እየገፋ በሄደ መጠን ይሖዋ በመላው የሰይጣን ሥርዓት ላይ ጥፋት የሚያመጣበት ጊዜ እየተቃረበ ስለሚመጣ ነቅታችሁ ጠብቁ! (ኤርምያስ 25:29–31) ይሖዋ “ታላቅ እሆናለሁ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] እንደ ሆንሁ ያውቃሉ” ብሏል። (ሕዝቅኤል 38:23) ይህን ቁርጥ ያለ እርምጃ የሚወስድበት ‘የይሖዋ ቀን’ ቀርቧል!—ኢዩኤል 1:15፤ 2:1, 2፤ አሞጽ 5:18–20፤ ሶፎንያስ 2:2, 3
ጽድቅ የሚሰፍንበት “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር”
17, 18. (ሀ) ኢየሱስና ጴጥሮስ በተናገሩት መሠረት “ይህ ትውልድ” የሚያልፈው እንዴት ነው? (ለ) ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የሚያሳዩ ባሕርያትንና ተግባራትን በተመለከተ ነቅተን መጠበቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
17 ኢየሱስ ‘የግድ መፈጸም ስላለባቸው ነገሮች’ ሲናገር “ሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ ቃሌ ግን አያልፍም” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 24:34, 35) ኢየሱስ ይህን ሲናገር “የዚህ ትውልድ” “ሰማይና ምድር” የሆኑትን ገዢዎችና ተገዢዎች በአእምሮው ሳይዝ አልቀረም። ሐዋርያው ጴጥሮስ “እግዚአብሔርን የማያመልኩ ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ” ለእሳት ስለ ተጠበቁት ‘አሁን ስላሉት ሰማያትና ምድር’ ሲጠቅስ በተመሳሳይ ቃላት ተጠቅሟል። ቀጥሎም ‘[መንግሥታዊ] ሰማያት’ ከብልሹው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ወይም ከ“ምድር” እና ከኃጢአተኝነት ተግባሮቿ ጋር ‘የሚያልፉበት የጌታ ቀን’ እንዴት ‘እንደ ሌባ ሆኖ’ እንደሚመጣ ገልጿል። ከዚያም ሐዋርያው እንዲህ በማለት መክሮናል፦ “በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ይፈታል።” ከዚያ በኋላ ምን ይሆናል? ጴጥሮስ ‘ጽድቅ በሚኖርባት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር’ ላይ እንድናተኩር አድርጓል።—2 ጴጥሮስ 3:7, 10–13c
18 ይህ “አዲስ ሰማይ” ማለትም በክርስቶስ ኢየሱስና በተባባሪ ነገሥታቱ የሚመራው መንግሥት “አዲስ ምድር” በሆነ ጻድቅ የሰው ልጆች ማኅበረሰብ ላይ በረከቶች ያፈሳል። የዚህ ማኅበረሰብ እጩ አባል ነህን? ከሆንህ ወደፊት በምታገኘው በዚህ ታላቅ ተስፋ የምትደሰትበት ምክንያት አለህ!—ኢሳይያስ 65:17–19፤ ራእይ 21:1–5
19. በአሁኑ ጊዜ ምን ታላቅ መብት ልናገኝ እንችላለን?
19 አዎን፣ በአሁኑ ወቅትም እንኳ ጻድቅ የሰው ልጆች “ትውልድ” በመሰብሰብ ላይ ነው። በዛሬው ጊዜ ቅቡዓኑ “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሆኑት እንዲህ በማለት ከሚናገረው ከመዝሙር 78:1, 4 ጋር በሚስማማ መንገድ መለኮታዊ ትምህርት በመስጠት ላይ ነው፦ “ሕዝቤ ሆይ፣ ሕጌን አድምጡ፤ ጆሮአችሁንም ወደ አፌ ቃል አዘንብሉ።. . . ለሚመጣ ትውልድ. . . የእግዚአብሔርን ምስጋናና ኃይሉን፣ ያደረገውንም ተአምራት ተናገሩ።” (ማቴዎስ 24:45–47) በዚህ ዓመት ሚያዝያ 14 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ ከ75,500 በሚበልጡ ጉባኤዎችና ወደ 230 ገደማ በሚሆኑ አገሮች ውስጥ ከ12,000,000 በላይ የሆኑ ሰዎች ተገኝተዋል። አንተ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ነበርክን? በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምንና ‘ደኅንነት ለማግኘት የጌታን ስም የምትጠራ’ ያድርግህ።—ሮሜ 10:11–13
20. “የቀረው ጊዜ አጭር” ስለሆነ ነቅተን መጠበቅ ያለብን እንዴት ነው? ምን ተስፋ ይዘን?
20 ሐዋርያው ጳውሎስ “የቀረው ጊዜ አጭር ሆኗል” ብሏል። ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከክፉው የሰው ልጆች ትውልድ የሚመጣብንን ፈተና እና ጥላቻ እየቻልን ነቅተን የምንጠብቅበትና በይሖዋ ሥራ የምንጠመድበት ጊዜ አሁን ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:29 አዓት ፤ ማቴዎስ 10:22፤ 24:13, 14) መጽሐፍ ቅዱስ ‘በዚህ ትውልድ’ ላይ ይመጣሉ ብሎ አስቀድሞ የተናገራቸውን ነገሮች በትኩረት በመከታተል ነቅተን እንጠብቅ። (ሉቃስ 21:31–33) ከእነዚህ ነገሮች በማምለጥና መለኮታዊ ተቀባይነት አግኝተን በሰው ልጅ ፊት በመቆም በመጨረሻ የዘላለም ሕይወት ልናገኝ እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “ሰባት ዘመናት”ን በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን “መንግሥትህ ትምጣ” የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 127–39 እና 186–9 ተመልከት።
b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 918 ተመልከት።
c በተጨማሪም ኒው ዮርክ በሚገኘው በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ወደፊት ዓለምን የሚገዛው መጪው የአምላክ መንግሥት የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ገጽ 152–6 እና 180–1 ተመልከት።
የክለሳ ጥያቄዎች፦
◻ የዳንኤል 4:32ን ፍጻሜ በሚገባ በመረዳታችን በአሁኑ ጊዜ “ነቅተን መጠበቅ” ያለብን እንዴት ነው?
◻ የማቴዎስና የሉቃስ ወንጌሎች “ይህ ትውልድ” የተባለውን ለይተን እንድናውቅ የሚረዱን እንዴት ነው?
◻ “ቀኑንና ሰዓቱን” ስንጠባበቅ ምን ነገር እናስተውላለን? ለዚህስ ምላሽ መስጠት የሚኖርብን እንዴት ነው?
◻ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር”ን በተመለከተ ያለን ተስፋ ምን እንድናደርግ ያበረታታናል?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሥቃይ ላይ ያለው የሰው ዘር ይህ ዓመፀኛና ክፉ ትውልድ ሲያልፍ እፎይታ ያገኛል
[ምንጭ]
Alexandra Boulat/ Sipa Press
[ምንጭ]
ከታች በስተ ግራ፦ Luc Delahaye/Sipa Press
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መላው የሰው ዘር ክብራማ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ከፊት ለፊቱ ይጠብቀዋል