ምዕራፍ 99
ኢየሱስ ዓይነ ስውሮችን ፈወሰ እንዲሁም ዘኬዎስን ረዳው
ማቴዎስ 20:29-34 ማርቆስ 10:46-52 ሉቃስ 18:35–19:10
ኢየሱስ በኢያሪኮ የዓይነ ስውሮችን ዓይን አበራ
ቀረጥ ሰብሳቢው ዘኬዎስ ንስሐ ገባ
ኢየሱስና አብረውት የሚጓዙት ሰዎች ኢያሪኮ ደረሱ፤ ኢያሪኮ ከኢየሩሳሌም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ትርቃለች። ኢያሪኮ ሁለት ከተሞችን አጣምራ ይዛለች፤ በጥንቱ የአይሁዳውያን ከተማ እና በሮማውያን ዘመን በተገነባው አዲሱ ከተማ መካከል የአንድ ኪሎ ሜትር ተኩል ያህል ርቀት አለ። ኢየሱስና ሕዝቡ ከአንደኛው ከተማ ወጥተው ወደ ሌላኛው ከተማ ሲቃረቡ ሁለት ዓይነ ስውር ለማኞች የሕዝቡን ውካታ ሰሙ። ከዓይነ ስውሮቹ አንዱ በርጤሜዎስ ይባላል።
በርጤሜዎስና ጓደኛው፣ ኢየሱስ በዚያ እያለፈ መሆኑን ሲሰሙ “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልን!” እያሉ መጮኽ ጀመሩ። (ማቴዎስ 20:30) ከሕዝቡ መሃል አንዳንዶች ተቆጥተው ዝም እንዲሉ ቢነግሯቸውም ጭራሽ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው መጮኻቸውን ቀጠሉ። ኢየሱስ ረብሻውን ሰማና ቆመ። ከዚያም የሚጮኹትን ሰዎች እንዲጠሯቸው አብረውት ያሉትን ጠየቃቸው። ሰዎቹም ዓይነ ስውር ወደሆኑት ለማኞች ሄዱና አንደኛውን “አይዞህ! ተነስ፤ እየጠራህ ነው” አሉት። (ማርቆስ 10:49) ዓይነ ስውሩ በጣም ከመደሰቱ የተነሣ መደረቢያውን ጥሎ ዘሎ በመነሳት ወደ ኢየሱስ ሄደ።
ኢየሱስ “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። ሁለቱም ዓይነ ስውሮች “ጌታ ሆይ፣ ዓይናችንን አብራልን” ብለው ለመኑት። (ማቴዎስ 20:32, 33) ኢየሱስም በጣም አዘነላቸውና ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ፤ ከዚያም ትኩረቱን አንደኛው ሰው ላይ በማድረግ “ሂድ፣ እምነትህ አድኖሃል” አለው። (ማርቆስ 10:52) ለማኞቹ ዓይናቸው በራ፤ ሁለቱም አምላክን እንዳከበሩ ጥርጥር የለውም። ሕዝቡም የሆነውን ሲያዩ አምላክን አወደሱ። ዓይነ ስውር የነበሩት ሰዎች ኢየሱስን መከተል ጀመሩ።
ኢየሱስ፣ ኢያሪኮን አቋርጦ ሲያልፍ በጣም ብዙ ሕዝብ እየተከተለው ነው። ሁሉም፣ ዓይነ ስውሮቹን የፈወሰውን ሰው ለማየት ፈልገዋል። ሕዝቡ ኢየሱስን ዙሪያውን ስለከበቡት አንዳንዶች በጨረፍታ እንኳ ሊያዩት አልቻሉም። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ዘኬዎስ ነው። ዘኬዎስ በኢያሪኮና በአካባቢዋ የተሰማሩት ቀረጥ ሰብሳቢዎች አለቃ ነው። አጭር በመሆኑ ምን እየተከናወነ እንዳለ ማየት አልቻለም። በመሆኑም ዘኬዎስ ሮጦ ወደፊት በመሄድ ኢየሱስ በሚያልፍበት መንገድ ላይ ባለ የሾላ ዛፍ ላይ ወጣ። ዘኬዎስ እዚያ ሆኖ ሁሉንም ነገር በደንብ መመልከት ይችላል። ኢየሱስ እየተቃረበ ሲመጣ ዘኬዎስን ዛፉ ላይ አየው፤ ከዚያም “ዘኬዎስ፣ ዛሬ ወደ አንተ ቤት ስለምመጣ ቶሎ ውረድ” አለው። (ሉቃስ 19:5) ዘኬዎስም ከዛፉ ላይ ወረደና ቤቱ ለሚመጣው ታላቅ እንግዳ ዝግጅት ለማድረግ በፍጥነት ወደ ቤቱ ሄደ።
ሕዝቡ ይህን ሲመለከቱ ማጉረምረም ጀመሩ። እነዚህ ሰዎች እንደ ኃጢአተኛ በሚቆጥሩት ሰው ቤት ኢየሱስ በእንግድነት መስተናገዱ ተገቢ እንዳልሆነ ተሰምቷቸዋል። ዘኬዎስ ሀብታም የሆነው፣ ቀረጥ ሲሰበስብ ሕዝቡን አላግባብ ገንዘብ በማስከፈል ነው።
ኢየሱስ ወደ ዘኬዎስ ቤት ሲገባ ሕዝቡ “ኃጢአተኛ ሰው ቤት ሊስተናገድ ገባ” ብለው አጉተመተሙ። ኢየሱስ ግን ዘኬዎስ ንስሐ ሊገባ እንደሚችል አስተውሏል። ደግሞም ኢየሱስ የጠበቀው ነገር ተፈጽሟል። ዘኬዎስ ተነስቶ ቆመና እንዲህ አለው፦ “ጌታ ሆይ፣ ካለኝ ሀብት ግማሹን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ከሰው የቀማሁትንም ሁሉ አራት እጥፍ እመልሳለሁ።”—ሉቃስ 19:7, 8
ይህ በእርግጥም ዘኬዎስ ከልቡ ንስሐ መግባቱን ያሳያል! ቀረጥ የሰበሰበበትን መዝገብ በማገላበጥ ከተለያዩ አይሁዳውያን የወሰደው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ ማስላት ሳይችል አይቀርም፤ ይህንንም በአራት እጥፍ ለመመለስ ቃል ገብቷል። ይህ የአምላክ ሕግ ከሚጠይቀውም በላይ ነው። (ዘፀአት 22:1፤ ዘሌዋውያን 6:2-5) ከዚህም ሌላ ዘኬዎስ ካለው ሀብት ግማሹን ለድሆች ለመስጠት ቃል ገብቷል።
ኢየሱስ፣ ዘኬዎስ ንስሐ መግባቱን በሚያሳየው በዚህ እርምጃ በመደሰቱ እንዲህ አለ፦ “ይህም ሰው የአብርሃም ልጅ ስለሆነ ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን መጥቷል። ምክንያቱም የሰው ልጅ የመጣው የጠፋውን ለመፈለግና ለማዳን ነው።”—ሉቃስ 19:9, 10
ከጥቂት ጊዜ በፊት ኢየሱስ ስለ ጠፋው ልጅ በተናገረው ታሪክ ላይ ‘የጠፉ’ ሰዎችን ሁኔታ በምሳሌ አስረድቶ ነበር። (ሉቃስ 15:11-24) አሁን ደግሞ የጠፋ ያህል የነበረውንና የተገኘውን ሰው እውነተኛ ታሪክ እንደ ምሳሌ አቅርቧል። የሃይማኖት መሪዎቹና እነሱን የሚከተሉት ሰዎች፣ ኢየሱስ እንደ ዘኬዎስ ላሉ ግለሰቦች ትኩረት በመስጠቱ ያጉረመርሙና ይነቅፉት ይሆናል። ኢየሱስ ግን እነዚህን የጠፉ የአብርሃም ልጆች መፈለጉንና መመለሱን ቀጥሏል።