ምዕራፍ 100
ስለ አሥሩ ምናን የተናገረው ምሳሌ
ኢየሱስ ስለ አሥሩ ምናን የተናገረው ምሳሌ
ኢየሱስ እየተጓዘ ያለው ወደ ኢየሩሳሌም ቢሆንም አሁንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዘኬዎስ ቤት ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። ደቀ መዛሙርቱ “የአምላክ መንግሥት” በቅርቡ እንደሚቋቋምና ኢየሱስ እንደሚነግሥ ያምናሉ። (ሉቃስ 19:11) ኢየሱስ መሞት እንዳለበት እንዳላስተዋሉ ሁሉ ከአምላክ መንግሥት መቋቋም ጋር በተያያዘ ያላቸው አመለካከትም የተሳሳተ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ፣ መንግሥቱ የሚቋቋመው ከረጅም ጊዜ በኋላ መሆኑን እንዲገነዘቡ ለመርዳት አንድ ምሳሌ ነገራቸው።
ኢየሱስ “አንድ መስፍን ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተረክቦ ለመመለስ ወደ ሩቅ አገር ሊሄድ ተነሳ” በማለት ምሳሌውን ጀመረ። (ሉቃስ 19:12) እንዲህ ዓይነቱ ጉዞ ጊዜ ይወስዳል። ወደ “ሩቅ አገር” ይኸውም ወደ ሰማይ የተጓዘው “መስፍን” ኢየሱስ እንደሆነ በግልጽ መረዳት ይቻላል፤ በዚያም አባቱ ንጉሣዊ ሥልጣን ይሰጠዋል።
በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው “መስፍን” ከመሄዱ በፊት አሥር ባሪያዎች ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው አንድ የብር ምናን ከሰጣቸው በኋላ “እስክመጣ ድረስ ነግዱበት” አላቸው። (ሉቃስ 19:13) የብር ምናን ውድ ዋጋ ያለው ገንዘብ ነው። የእርሻ ሠራተኛ የሆነ ሰው፣ አንድ ምናን እንዲከፈለው ከሦስት ወር በላይ መሥራት አለበት።
ኢየሱስ ከዚህ ቀደም ደቀ መዛሙርቱን ከመከር ሠራተኞች ጋር አመሳስሏቸዋል፤ በመሆኑም በምሳሌው ላይ የተጠቀሱት አሥር ባሪያዎች እነሱን እንደሚያመለክቱ አስተውለው መሆን አለበት። (ማቴዎስ 9:35-38) እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ቃል በቃል አዝመራ ሰብስበው እንዲያመጡ አልጠየቃቸውም። አዝመራው የሚያመለክተው በአምላክ መንግሥት ውስጥ ቦታ የሚኖራቸውን ሌሎች ደቀ መዛሙርት ነው። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ ያላቸውን ጊዜና ጉልበት አልፎ ተርፎም ጥሪታቸውን በሙሉ በመጠቀም ተጨማሪ የመንግሥቱ ወራሾችን ያፈራሉ።
ኢየሱስ በዚህ ምሳሌ ላይ የጠቀሰው ሌላስ ነገር አለ? “የአገሩ ሰዎች [መስፍኑን] . . . ይጠሉት ስለነበር እሱ ከሄደ በኋላ ‘ይህ ሰው በእኛ ላይ እንዲነግሥ አንፈልግም’ ብለው እንዲነግሩላቸው መልእክተኞች ላኩ” ብሏል። (ሉቃስ 19:14) ደቀ መዛሙርቱ፣ አይሁዳውያን ኢየሱስን እንዳልተቀበሉት እንዲያውም አንዳንዶች ሊገድሉት እንደሚፈልጉ ያውቃሉ። ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ አብዛኞቹ አይሁዳውያን ደቀ መዛሙርቱን በማሳደድ ለእሱ ምን አመለካከት እንዳላቸው አሳይተዋል። እነዚህ ተቃዋሚዎች፣ ኢየሱስ ንጉሣቸው እንዲሆን እንደማይፈልጉ ግልጽ አድርገዋል።—ዮሐንስ 19:15, 16፤ የሐዋርያት ሥራ 4:13-18፤ 5:40
አሥሩ ባሪያዎች ‘መስፍኑ ንጉሣዊ ሥልጣኑን’ ተረክቦ እስኪመለስ ድረስ ምናናቸውን የተጠቀሙበት እንዴት ነው? ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ከጊዜ በኋላ ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተረክቦ ሲመጣ ገንዘብ የሰጣቸው ባሪያዎች ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ለማወቅ አስጠራቸው። በመሆኑም የመጀመሪያው ቀርቦ ‘ጌታዬ፣ ምናንህ አሥር ምናን ትርፍ አስገኝቷል’ አለው። ጌታው ‘ጎበዝ፣ አንተ ጥሩ ባሪያ! በጣም አነስተኛ በሆነው ነገር ታማኝ ሆነህ ስለተገኘህ በአሥር ከተሞች ላይ ሥልጣን ተሰጥቶሃል’ አለው። ሁለተኛው ደግሞ ቀርቦ ‘ጌታዬ፣ ምናንህ አምስት ምናን አስገኝቷል’ አለ። ይሄኛውንም ‘አንተም በአምስት ከተሞች ላይ ተሹመሃል’ አለው።”—ሉቃስ 19:15-19
ደቀ መዛሙርቱ፣ የተሰጣቸውን ንብረት አቅማቸው በፈቀደ መጠን ተጠቅመው ተጨማሪ ደቀ መዛሙርት እንዳፈሩት ባሪያዎች እንደሆኑ ከተሰማቸው ኢየሱስ እንደሚደሰትባቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። እንዲህ ያለ ትጋት በማሳየታቸው ኢየሱስ እንደሚሸልማቸውም መተማመን ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ ሁሉም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ተመሳሳይ ሁኔታ፣ አጋጣሚ ወይም ችሎታ የላቸውም። ያም ቢሆን “ንጉሣዊ ሥልጣኑን” የተቀበለው ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በታማኝነት የሚያደርጉትን ጥረት የሚመለከት ከመሆኑም ሌላ ይባርካቸዋል።—ማቴዎስ 28:19, 20
ኢየሱስ ምሳሌውን ሲደመድም የጠቀሰው ባሪያ ግን ቀደም ሲል ከተጠቀሱት የተለየ ነው፤ እንዲህ አለ፦ “ሆኖም ሌላኛው [ባሪያ] መጥቶ እንዲህ አለ፦ ‘ጌታዬ፣ በጨርቅ ጠቅልዬ የደበቅኩት ምናንህ ይኸውልህ። ይህን ያደረግኩት ጨካኝ ሰው ስለሆንክ ፈርቼህ ነው፤ አንተ ያላስቀመጥከውን የምትወስድ፣ ያልዘራኸውንም የምታጭድ ሰው ነህ።’ ጌታውም እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉ ባሪያ፣ በራስህ ቃል እፈርድብሃለሁ። ያላስቀመጥኩትን የምወስድ፣ ያልዘራሁትንም የማጭድ ጨካኝ ሰው እንደሆንኩ ታውቅ ኖሯል ማለት ነው? ታዲያ ገንዘቤን ለምን ለገንዘብ ለዋጮች አልሰጠህም? እንደዚህ አድርገህ ቢሆን ኖሮ ስመጣ ከነወለዱ እወስደው ነበር።’ ከዚያም በዚያ ቆመው የነበሩትን ሰዎች ‘ምናኑን ውሰዱበትና አሥር ምናን ላለው ስጡት’ አላቸው።”—ሉቃስ 19:20-24
ይህ ባሪያ የጌታውን መንግሥት ሀብት ለመጨመር ጥረት ስላላደረገ ያለውን አጥቷል። ሐዋርያቱ፣ ኢየሱስ በአምላክ መንግሥት ላይ መግዛት የሚጀምርበትን ጊዜ እየጠበቁ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ስለዚህ ባሪያ ከተናገረው ሐሳብ አንጻር፣ እነሱም ትጉ ካልሆኑ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ቦታ እንደማይኖራቸው ሳይገባቸው አይቀርም።
ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ፣ ታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ይበልጥ ጥረት እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይገባል። ኢየሱስ ንግግሩን ሲደመድም “እላችኋለሁ፣ ላለው ሁሉ ተጨማሪ ይሰጠዋል፤ ከሌለው ሰው ላይ ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል” አለ። አክሎም ‘በእነሱ ላይ እንዲነግሥ’ ያልፈለጉት ጠላቶቹ እንደሚገደሉ ገለጸ። ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ ጉዞውን በመቀጠል ወደ ኢየሩሳሌም አቀና።—ሉቃስ 19:26-28