ሰላም
“ሰላም” ተብሎ የተተረጎመው ሻሎም የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ከጦርነት ወይም ከሚረብሽ ነገር ነፃ መሆንን ያመለክታል (መሳ 4:17፤ 1ሳሙ 7:14፤ 1ነገ 4:24፤ 2ዜና 15:5፤ ኢዮብ 21:9)፤ ይህ ቃል ጤና መሆንን፣ ከጉዳት መጠበቅን፣ ደህና መሆንን (ዘፍ 37:14)፣ መልካም ነገር ማግኘትን (ዘፍ 41:16)፣ ወዳጅነትን (መዝ 41:9) እና ሙሉነትን ሊያመለክት ይችላል (ኤር 13:19)። ሰላም ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃልም (ኤይሬኔ) ሻሎም እንደተባለው የዕብራይስጥ ቃል በተለያዩ መንገዶች የተሠራበት ሲሆን ከግጭት ነፃ ከመሆን በተጨማሪ ደህና መሆንን፣ መዳንን እና ስምምነት ማድረግን ሊያመለክት ይችላል። ቃሉ ‘መልካም ይሁንልህ’ ወይም ‘ይሳካልህ’ ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ካለው ‘በሰላም ሂድ’ ከሚለው የስንብት መግለጫ ጋር በተያያዘም ተሠርቶበታል።—ማር 5:34፤ ሉቃስ 7:50፤ 8:48፤ ያዕ 2:16፤ ከ1ሳሙ 1:17፤ 20:42፤ 25:35፤ 29:7፤ 2ሳሙ 15:9 እና 2ነገ 5:19 ጋር አወዳድር።
“ሰላም” ተብሎ የተተረጎመው ቃል መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ከተሠራበት ትርጉም ጋር ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ስለማይሆን ምን ለመግለጽ እንደገባ ለመወሰን ዓውዱን ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል፣ ‘በሰላም መሰናበት’ የሚለው ሐረግ አንድ ሰው፣ እንዲሄድ ፈቃድ ከሰጠው አካል ጉዳት ይደርስብኛል ብሎ ሳይፈራ በወዳጃዊ መንፈስ መሰነባበቱን ሊያመለክት ይችላል። (ዘፍ 26:29፤ 44:17፤ ዘፀ 4:18) አንድ ሰው ከጦርነት ‘በሰላም ተመለሰ’ ሲባል ደግሞ ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ወይም ድል አድርጎ ተመለሰ ማለት ነው። (ዘፍ 28:21፤ ኢያሱ 10:21፤ መሳ 8:9፤ 11:31፤ 2ዜና 18:26, 27፤ 19:1) አንድን ሰው ሰላም መሆኑን መጠየቅ ግለሰቡ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ መጠየቅ ማለት ነው። (ዘፍ 29:6፤ 43:27 ባለማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም፣ ግርጌ) ለአንድ ሰው ‘ሰላምን መመኘት’ ሲባል ለዚያ ሰው የሚበጅ ነገር መመኘትን ያመለክታል። (ዘዳ 23:6) አንድ ሰው በሰላም አረፈ ወይም በሰላም ወደ መቃብር ወረደ ሲባል ግለሰቡ ዕድሜ ጠግቦ ሞተ ወይም የሚመኘውን ነገር ካገኘ በኋላ ሞተ ማለት ሊሆን ይችላል። (ከዘፍ 15:15፤ ሉቃስ 2:29 እና 1ነገ 2:6 ጋር አወዳድር።) ኢዮስያስን በተመለከተ “በሰላም በመቃብርህ ታርፋለህ” ተብሎ የተነገረው ትንቢት ኢዮስያስ በኢየሩሳሌም ላይ እንደሚደርስ የተነገረው ጥፋት ከመምጣቱ በፊት እንደሚሞት ያመለክት ነበር። (2ነገ 22:20፤ 2ዜና 34:28፤ ከ2ነገ 20:19 ጋር አወዳድር።) በኢሳይያስ 57:1, 2 ላይ ጻድቅ ሰው ሲሞት ሰላም እንደሚያገኝና ከመከራ እንደሚተርፍ ተገልጿል።
ሰላም ማግኘት። ሰላም የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታ (ገላ 5:22) ስለሆነ ይሖዋ የሰላም አምላክና (1ቆሮ 14:33፤ 2ቆሮ 13:11፤ 1ተሰ 5:23፤ ዕብ 13:20) የሰላም ምንጭ ነው። (ዘኁ 6:26፤ 1ዜና 22:9፤ መዝ 4:8፤ 29:11፤ 147:14፤ ኢሳ 45:7፤ ሮም 15:33፤ 16:20) በዚህም ምክንያት እውነተኛ ሰላም ማግኘት የሚችሉት ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት መፈጸሙ ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ስለሚያበላሽበት ግለሰቡ እንዲረበሽ ያደርገዋል። መዝሙራዊው “ከኃጢአቴም የተነሳ አጥንቶቼ ሰላም የላቸውም” በማለት ተናግሯል። (መዝ 38:3) በመሆኑም ሰላምን የሚፈልጉና የሚከተሉ ሰዎች ‘ክፉ ከሆነ ነገር መራቅና መልካም የሆነውን ማድረግ’ አለባቸው። (መዝ 34:14) ጽድቅ በሌለበት ሰላም ሊኖር አይችልም። (መዝ 72:3፤ 85:10፤ ኢሳ 32:17) በዚህ ምክንያት ክፉዎች ሰላም ሊኖራቸው አይችልም። (ኢሳ 48:22፤ 57:21፤ ከኢሳ 59:2-8 ጋር አወዳድር።) በሌላ በኩል ግን ለይሖዋ ያደሩና ሕጉን የሚወዱ (መዝ 119:165) እንዲሁም ትእዛዛቱን የሚፈጽሙ ሰዎች ሰላም ያገኛሉ።—ኢሳ 48:18
ክርስቶስ ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ ሥጋዊ አይሁዳውያንም ሆኑ አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች ከይሖዋ አምላክ ጋር ሰላም አልነበራቸውም። አይሁዳውያን የአምላክን ሕግ ስለተላለፉ በሕጉ እርግማን ሥር ወድቀው ነበር። (ገላ 3:12, 13) ከአምላክ ቃል ኪዳን ውጭ የነበሩት አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎችም ቢሆኑ “በዓለም ውስጥ ያለ ተስፋና ያለ አምላክ” ይኖሩ ነበር። (ኤፌ 2:12) ይሁን እንጂ ሁለቱም ወገኖች በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ዝምድና የሚመሠርቱበት አጋጣሚ ተሰጣቸው። ኢየሱስ በተወለደበት ዕለት መላእክት ለእረኞቹ “በምድርም አምላክ ሞገስ ለሚያሳያቸው ሰዎች ሰላም ይሁን” በማለት በተናገሩት መልእክት ላይ ይህ ዝግጅት ተገልጿል።—ሉቃስ 2:14
ኢየሱስና ተከታዮቹ ያወጁት ሰላማዊ መልእክት ‘ለሰላም ወዳዶች’ ማለትም ከአምላክ ጋር ለመታረቅ የሚፈልጉ ሰዎችን የሚማርክ ነበር። (ማቴ 10:13፤ ሉቃስ 10:5, 6፤ ሥራ 10:36) በሌላ በኩል ደግሞ መልእክቱን አንዳንዶች ሲቀበሉት ሌሎች ግን ባለመቀበላቸው በቤተሰብ አባላት መካከል መከፋፈል ፈጥሮ ነበር። (ማቴ 10:34፤ ሉቃስ 12:51) አብዛኞቹ አይሁዳውያን መልእክቱን ሳይቀበሉት በመቅረታቸው ‘የሰላምን መንገድ’ ሳያስተውሉ ቀሩ፤ ይህ የሰላም መንገድ ንስሐ መግባትንና የኢየሱስን መሲሕነት መቀበልን እንደሚጨምር ግልጽ ነው። (ከሉቃስ 1:79፤ 3:3-6 እና ዮሐ 1:29-34 ጋር አወዳድር።) ይህን ሳያደርጉ በመቅረታቸው ኢየሩሳሌም በ70 ዓ.ም. በሮም ሠራዊት እንድትጠፋ ተደርጋለች።—ሉቃስ 19:42-44
ይሁን እንጂ ‘የሰላምን ምሥራች’ የተቀበሉት አይሁዳውያንም ቢሆኑ ኃጢአተኞች ስለሆኑ ከይሖዋ ጋር ሰላም እንዲኖራቸው ኃጢአታቸው ሊሰረይላቸው ይገባ ነበር። ኃጢአት እንዲሰረይ የሚያደርገው ደግሞ የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው። ቀደም ሲል በትንቢት እንደተነገረው “በእሱ ላይ የደረሰው ቅጣት ለእኛ ሰላም አስገኘልን፤ በእሱም ቁስል የተነሳ እኛ ተፈወስን።” (ኢሳ 53:5) ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ መሥዋዕታዊ ሞት መሞቱ ለሙሴ ሕግ መሻር መሠረት ሆኗል፤ ሕጉ በአይሁዳውያንና አይሁዳውያን ባልሆኑ ሕዝቦች መካከል መከፋፈል ፈጥሮ ነበር። በመሆኑም ሁለቱም ወገኖች ክርስቲያን ሲሆኑ ከአምላክ ጋርም ሆነ እርስ በርሳቸው ሰላም ሊኖራቸው ችሏል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሁለቱን ወገኖች አንድ ያደረገውና ይለያያቸው የነበረውን በመካከል ያለ ግድግዳ ያፈረሰው እሱ [ኢየሱስ] ሰላም አምጥቶልናልና። ሁለቱን ወገኖች ከራሱ ጋር አንድነት እንዲኖራቸው በማድረግ አንድ አዲስ ሰው መፍጠርና ሰላም ማስፈን ይችል ዘንድ በሥጋው አማካኝነት ጠላትነትን ይኸውም ትእዛዛትንና ድንጋጌዎችን የያዘውን ሕግ አስወገደ፤ እንዲሁም ይህን ያደረገው በመከራው እንጨት ሁለቱን ወገኖች አንድ አካል አድርጎ ከአምላክ ጋር ሙሉ በሙሉ ለማስታረቅ ነው፤ ምክንያቱም በገዛ አካሉ ጠላትነትን አስወግዷል። እሱም መጥቶ ከአምላክ ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተም ሆነ ወደ እሱ ቀርበው ለነበሩት የሰላምን ምሥራች አወጀ፤ ምክንያቱም እኛ፣ የሁለቱም ወገን ሕዝቦች በእሱ አማካኝነት በአንድ መንፈስ ወደ አብ በነፃነት መቅረብ እንችላለን።”—ኤፌ 2:14-18፤ ከሮም 2:10, 11 እና ቆላ 1:20-23 ጋር አወዳድር።
አንድ ክርስቲያን “የአምላክ ሰላም” ይኸውም ከይሖዋ አምላክ ጋር ውድ ዝምድና በማፍራቱ የሚያገኘው ሰላምና መረጋጋት ለኑሮ ስለሚያስፈልጉት ነገሮች ከልክ በላይ እንዳይጨነቅ ልቡንና አእምሮውን ይጠብቅለታል። ይሖዋ አምላክ ለአገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚያሟላላቸውና ለጸሎቶቻቸው መልስ እንደሚሰጥ ይተማመናል። ይህም ልቡንና አእምሮውን ያረጋጋለታል። (ፊልጵ 4:6, 7) በተመሳሳይም ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እሱ የአምላክ ልጅ እንደሆነ እምነት ስላላቸው ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ሰላም ልባቸውንና አእምሯቸውን አረጋግቶታል። ኢየሱስ፣ በአካል ከእነሱ ጋር የማይሆንበት ጊዜ እንደሚመጣ የነገራቸው ቢሆንም የሚጨነቁበት ወይም በፍርሃት የሚርዱበት ምንም ምክንያት አልነበረም። ኢየሱስ እርዳታ የሚያገኙበትን ዝግጅት ሳያደርግ ትቷቸው አልሄደም፤ በመሆኑም መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው ቃል ገባላቸው።—ዮሐ 14:26, 27፤ 16:33፤ ከቆላ 3:15 ጋር አወዳድር።
ክርስቲያኖች ያገኙትን ሰላም አቅልለው ሊመለከቱት አይገባም። “ሰላማዊ ግንኙነት” ሊኖራቸው ይገባ ነበር፤ በሌላ አባባል የቻሉትን ሁሉ ጥረት አድርገው ሰላም በማስፈንና እንዳይጠፋ በማድረግ ሰላም ፈጣሪዎች መሆን ነበረባቸው። (1ተሰ 5:13) ክርስቲያኖች በመካከላቸው ያለው ሰላም ተጠብቆ እንዲኖር የእምነት አጋሮቻቸውን ላለማሰናከል ጥንቃቄ ማድረግ ነበረባቸው። (ሮም 14:13-23) ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ሰላም ፈጣሪዎች ደስተኞች ናቸው፤ የአምላክ ልጆች ይባላሉና” በማለት ተናግሯል። (ማቴ 5:9፤ ከያዕ 3:18 ጋር አወዳድር።) ክርስቲያኖች የተቻላቸውን ጥረት በማድረግ ሰላምን እንዲከተሉና ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው ተመክረዋል። (2ጢሞ 2:22፤ ዕብ 12:14፤ 1ጴጥ 3:11፤ 2ጴጥ 3:14) በመሆኑም የአምላክ ጠላቶች እንዲሆኑ ከሚያደርጓቸው ሥጋዊ ምኞቶች ጋር መዋጋት ነበረባቸው። (ሮም 8:6-8) “ሰላም ለእናንተ ይሁን” እንደሚለው ያሉ የጸሎት ይዘት ያላቸው የመልካም ምኞት መግለጫዎች የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ከእሱ ጋር ሰላማዊ ዝምድና መመሥረት አስፈላጊ መሆኑን ያጎላሉ።—ሮም 1:7፤ 1ቆሮ 1:3፤ 2ቆሮ 1:2፤ ገላ 1:3፤ 6:16፤ ኤፌ 1:2፤ 6:23፤ ፊልጵ 1:2
ክርስቲያኖች ሌሎችም ሰላም እንዲያገኙ ይፈልጉ ነበር። በመሆኑም ‘የሰላምን ምሥራች ተጫምተው በመቆም’ በመንፈሳዊ ውጊያቸው ቀጥለውበታል። (ኤፌ 6:15) በጉባኤ ውስጥም እንኳ ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውቀት የሚጻረሩ የተሳሳቱ ሐሳቦችን ይዋጉ ነበር፤ ምክንያቱም እንዲህ ያሉት ሐሳቦች ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና ያበላሻሉ። (2ቆሮ 10:4, 5) ሆኖም ከእውነት ያፈነገጡትን ሰዎች በሚያስተካክሉበት ጊዜም እንኳ የቃላት ጦርነት አይከፍቱም ወይም ክርክር አይገጥሙም ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ ከትክክለኛው ጎዳና የወጡ ሰዎችን ሲረዳ ማድረግ ያለበትን ነገር አስመልክቶ ሲመክረው እንዲህ ብሎታል፦ “የጌታ ባሪያ ሊጣላ አይገባውምና፤ ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር፣ ለማስተማር ብቁ የሆነና በደል ሲደርስበት ራሱን የሚገዛ፣ እንዲሁም ቀና አመለካከት የሌላቸውን በገርነት የሚያርም ሊሆን ይገባዋል። ምናልባትም አምላክ ትክክለኛ የእውነት እውቀት ያገኙ ዘንድ ለንስሐ ያበቃቸው ይሆናል፤ እነሱም ዲያብሎስ ፈቃዱን ያደርጉ ዘንድ በሕይወት እንዳሉ አጥምዶ እንደያዛቸው በመረዳት ወደ ልቦናቸው ተመልሰው ከእሱ ወጥመድ ሊወጡ ይችላሉ።”—2ጢሞ 2:24-26
ሰላም የሰፈነበት አገዛዝ። ‘ገዢነት በጫንቃው’ ላይ የሆነው የአምላክ ልጅ “የሰላም መስፍን” ተብሎ ተጠርቷል። (ኢሳ 9:6, 7) በመሆኑም ክርስቶስ ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ለጴጥሮስ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” ብሎት ነበር፤ ይህም አገልጋዮቹ በሥጋዊ ጦርነት ለመካፈል የጦር መሣሪያ መታጠቅ እንደሌለባቸው ያሳያል። (ማቴ 26:52) ሰዎች ክርስቲያን ሲሆኑ በምሳሌያዊ አነጋገር “ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ [ቀጥቅጠዋል]።” ስለ ጦርነት መማር አቁመዋል። (ኢሳ 2:4) ይህ ሐሳብም ሆነ አምላክ በጥንት ጊዜ በተለይም እስራኤል ውስጥ በሰለሞን የግዛት ዘመን ያደረጋቸው ነገሮች ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበት ጊዜ ሰላም እንደሚሰፍን ያመለክታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የሰለሞንን የግዛት ዘመን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “በዙሪያው ባለው አካባቢ ሁሉ ሰላም ሰፍኖለት ነበር። በሰለሞን ዘመን ከዳን አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ በይሁዳና በእስራኤል የሚገኝ እያንዳንዱ ሰው ከገዛ ወይኑና ከበለስ ዛፉ ሥር ያለ ስጋት ይኖር ነበር።” (1ነገ 4:24, 25፤ 1ዜና 22:9) ከሌሎች ጥቅሶችም በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው (ከመዝ 72:7, 8፤ ሚክ 4:4፤ ዘካ 9:9, 10 እና ማቴ 21:4, 5 ጋር አወዳድር) በሰለሞን (የስሙ ትርጉም “ሰላም” ማለት ነው) የግዛት ዘመን የነበረው ሰላም፣ ከሰለሞን በሚበልጠው በክርስቶስ ኢየሱስ አገዛዝ ሥር ለሚኖረው ሰላም ጥላ ሆኖ አገልግሏል።—ማቴ 12:42
በሰዎችና በእንስሳት መካከል የሚኖረው ሰላም። ይሖዋ አምላክ እስራኤላውያን፣ ታዛዦች ከሆኑ ምን እንደሚያገኙ እንዲህ በማለት ቃል ገብቶላቸው ነበር፦ “በምድሪቱ ሰላም አሰፍናለሁ፤ እናንተም ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ፤ እኔም አደገኛ አውሬዎች በምድሪቱ እንዳይኖሩ አደርጋለሁ።” (ዘሌ 26:6) በመሆኑም የዱር አራዊት በተወሰነላቸው ክልል ውስጥ የሚኖሩ ከመሆኑም ሌላ በእስራኤላውያንና በቤት እንስሶቻቸው ላይ ጉዳት አያደርሱም ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ እስራኤላውያን ታዛዦች ካልሆኑ ይሖዋ ምድራቸው በውጭ አገር ሠራዊት እንድትወረርና እንድትጠፋ ይፈቅዳል። ይህ ደግሞ የሕዝቡ ቁጥር እንዲመናመን ያደርጋል፤ የዱር አራዊቱም ቁጥር ይበዛል። በዚህም የተነሳ አራዊቱ ቀደም ሲል ሰዎች ይኖሩባቸው ወደነበሩ ሰፈሮች በመግባት ከጥፋት በተረፈው ሕዝብና በቤት እንስሶቻቸው ላይ ጉዳት ያደርሳሉ።—ከዘፀ 23:29፤ ዘሌ 26:22 እና 2ነገ 17:5, 6, 24-26 ጋር አወዳድር።
ከዱር አራዊት ጋር በተያያዘ ለእስራኤላውያን ቃል የተገባላቸው ሰላም የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት በኤደን የአትክልት ስፍራ ሳሉ ከነበራቸው ሰላም ይለያል፤ ምክንያቱም አዳምና ሔዋን በሁሉም እንስሳት ላይ ሙሉ ሥልጣን ነበራቸው። (ዘፍ 1:28) በአንጻሩ ደግሞ ከአዳም ጋር የሚመሳሰል ሥልጣን እንደሚኖረው በትንቢት የተነገረለት ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው። (መዝ 8:4-8፤ ዕብ 2:5-9) በመሆኑም በሰዎችና በእንስሳት መካከል እንደገና ሰላም የሚሰፍነው ‘ከእሴይ ጉቶ የሚወጣው ቀንበጥ’ በተባለለት ወይም አምላክ ‘አገልጋዬ ዳዊት’ በማለት በጠራው በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ሥር ነው። (ኢሳ 11:1, 6-9፤ 65:25፤ ሕዝ 34:23-25) እንደ ተኩላና የበግ ጠቦት በመሳሰሉት እንስሳት መካከል ሰላም እንደሚኖር በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የተገለጸው ሐሳብ በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ቃል በቃል ፍጻሜ ስላላገኘ ትንቢቱ ምሳሌያዊ ትርጉም ያለው እንደሆነ ግልጽ ነው። ጎጂና አራዊት መሰል ባሕርይ የነበራቸው ሰዎች የጭካኔ መንገዳቸውን ትተው ይበልጥ ገራም ከሆኑት ጎረቤቶቻቸው ጋር በሰላም እንደሚኖሩ ትንቢት ተነግሯል። ይሁን እንጂ ትንቢቱ በአምላክ ሕዝቦች መካከል የሚኖሩትን ሰላማዊ ሁኔታዎች በምሳሌያዊ መንገድ ለመግለጽ እንስሳትን መጠቀሙ ልክ በኤደን እንደነበረው ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ግዛት ሥር ቃል በቃል በእንስሳት መካከል ሰላም እንደሚኖር ያመለክታል።