ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፋቸውን የመጨረሻ ቀናት በዓይነ ሕሊና መመልከት
ጊዜው 33 እዘአ ሲሆን ኒሳን የሚባለው የአይሁዳውያን ወር ሰባተኛ ቀን ነው። የሮማ ግዛት በሆነችው በይሁዳ በመፈጸም ላይ ያሉትን ክንውኖች በመመልከት ላይ ነህ እንበል። ኢየሱስ ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ በለመለመ መስክ ከተሸፈነችው ከኢያሪኮ ተነሥተው አቧራማና ጠመዝማዛ የሆነውን አቀበት እየወጡ ናቸው። ሌሎች በርካታ ሰዎችም ዓመታዊውን የማለፍ በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዙ ነው። ይሁን እንጂ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ያስቡ የነበረው ስለዚህ አድካሚ አቀበት ብቻ አልነበረም።
አይሁዳውያን ከሮማ ቀንበር ነፃ የሚያወጣቸውን መሲሕ ሲጠባበቁ ኖረዋል። የናዝሬቱ ኢየሱስ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ሲጠበቅ የቆየው አዳኝ መሆኑን ብዙዎች አምነዋል። ኢየሱስ ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል ስለ አምላክ መንግሥት ሲናገር ቆይቷል። የታመሙትን ፈውሷል፤ እንዲሁም የተራቡትን መግቧል። በእርግጥም ለሕዝቡ መጽናናትን አምጥቶላቸዋል። ይሁን እንጂ በወቅቱ የነበሩት ሃይማኖታዊ መሪዎች ኢየሱስ በድፍረት ስላወገዛቸው በጣም በመናደዳቸው እሱን ለማስገደል ቆርጠው ተነሥተዋል። ሆኖም ኢየሱስ ይህን ቢያውቅም ከደቀ መዛሙርቱ ፊት ሆኖ ወደዚያ እየተጓዘ ነው።—ማርቆስ 10:32
ፀሐይዋ ከደብረ ዘይት ተራራ በስተጀርባ ስታሽቆለቁል ኢየሱስና ጓደኞቹ የሚቀጥሉትን ስድስት ሌሊቶች ወደሚያሳልፉባት ወደ ቢታንያ መንደር ደረሱ። በዚያም ወዳጆቻቸው አልዓዛር፣ ማርያምና ማርታ በደስታ ተቀበሏቸው። ምሽቱ ከሞቃቱ ጉዞ እረፍት የሚሰጥ ቀዝቀዝ ያለ አየር የነበረው ከመሆኑም በላይ ኒሳን 8 የሚውለው ሰንበት መጀመሩን የሚያበስር ነበር።—ዮሐንስ 12:1, 2
ኒሳን 9
ከሰንበት በኋላ ኢየሩሳሌም ውካታ በሞላበት እንቅስቃሴ ተውጣለች። በሺህ የሚቆጠሩ ጎብኚዎች የማለፍን በዓል ለማክበር ቀደም ሲል ወደ ከተማይቱ ጎርፈዋል። ይሁን እንጂ የምንሰማው ጫጫታ ከዚህ በፊት በዚህ የዓመቱ ክፍለ ጊዜ ከነበረው በጣም የተለየ ነው። አእምሮው በጥያቄ የተሞላው ሕዝብ ወደ ከተማይቱ በሮች በሚወስዱት ጠባብ መንገዶች እየተጣደፈ በመጓዝ ላይ ይገኛል። እየተጋፉ እነዚያን የተጨናነቁ በሮች አልፈው ሲወጡ እንዴት ያለ ዕይታ አጋጠማቸው! በደስታ የተዋጡ ሰዎች ከቤተ ፋጌ ተነሥተው የደብረ ዘይትን ተራራ ቁልቁል በመውረድ ላይ ናቸው። (ሉቃስ 19:37) የዚህ ሁሉ ትርጉም ምንድን ነው?
ተመልከት! የናዝሬቱ ኢየሱስ በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ እየመጣ ነው። ሰዎች ልብሳቸውን በመንገዱ ላይ ከፊቱ ሲያነጥፉ ይታያል። ሌሎች ደግሞ አዲስ የተቆረጡ የዘንባባ ዝንጣፊዎችን እያውለበለቡ “በጌታ [“በይሖዋ፣” NW] ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው” እያሉ በደስታ ይጮኻሉ።—ዮሐንስ 12:12-15
ሕዝቡ ወደ ኢየሩሳሌም እየተቃረበ ሲመጣ ኢየሱስ ከተማዋን ተመልክቶ በጣም ተረበሸ። አለቀሰላት፤ ከዚያ ከተማዋ እንደምትወድም ትንቢት ሲናገር እንሰማዋለን። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ በመሄድ ሕዝቡን ያስተማረ ሲሆን ወደ እሱ የመጡትን ዕውሮችና ሽባዎች ፈውሷል።—ማቴዎስ 21:14፤ ሉቃስ 19:41-44, 47
ሊቀ ካህናቱና ጻፎች ይህን ተመልክተው ነበር። ኢየሱስ ያደረጋቸውን አስገራሚ ነገሮችና ሕዝቡ መደሰቱን ሲያዩ ምን ያህል ተበሳጭተው ነበር! ፈሪሳውያን ንዴታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው “መምህር ሆይ፣ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስ “እላችኋለሁ፣ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ” ብሎ መለሰላቸው። ኢየሱስ ከመሄዱ በፊት በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚካሄደውን የንግድ ሥራ ተመለከተ።—ሉቃስ 19:39, 40፤ ማቴዎስ 21:15, 16፤ ማርቆስ 11:11
ኒሳን 10
ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ የደረሰው ቀደም ብሎ ነበር። ትናንት የአባቱ የይሖዋ አምላክ አምልኮ መነገጃ ሲሆን በመመልከቱ በጣም ተበሳጭቶ ነበር። ስለዚህ በታላቅ ቅንዓት ተነሣስቶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሰዎች ማስወጣት ጀመረ። ከዚያም የእነዚያን ስስታም ገንዘብ ለዋጮች ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮች ወንበሮች ገለባበጠ። ኢየሱስ “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፣ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው።”—ማቴዎስ 21:12, 13
የካህናት አለቆች፣ ጻፎችና የሕዝቡ ታላላቆች የኢየሱስን ድርጊትና ለሕዝብ የሚሰጠውን ምሥክርነት ሊታገሡት አልቻሉም። እሱን ለመግደል ምንኛ ተቅበጥብጠው ነበር! ይሁን እንጂ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገርመውና “ሲሰሙት ተንጠልጥለውበት” ስለነበረ ምንም ሊያደርጉበት አልቻሉም። (ሉቃስ 19:47, 48) ምሽቱ እየተቃረበ ሲመጣ ኢየሱስና ጓደኞቹ ሌሊቱን ወደሚያርፉበት ወደ ቢታንያ ደስ የሚል የእግር ጉዞ አደረጉ።
ኒሳን 11
ገና ማለዳ ቢሆንም ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የደብረ ዘይትን ተራራ አልፈው ወደ ኢየሩሳሌም እየሄዱ ነው። ወደ ቤተ መቅደሱ እንደ ደረሱ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ኢየሱስን ለመተናኮል ፈጣኖች ሆኑ። በቤተ መቅደሱ ውስጥ በነበሩት የገንዘብ ለዋጮችና ነጋዴዎች ላይ የወሰደው እርምጃ ገና ከአእምሯቸው አልጠፋም። ጠላቶቹ “በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” የሚል የተንኮል ጥያቄ ጠየቁት። ኢየሱስም መልሶ “እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው?” አላቸው። ተቃዋሚዎቹ አንድ ላይ ተሰባስበው “ከሰማይ ብንል:- እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ከሰው ግን ብንል፣ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን” በማለት ተማከሩ። ግራ በመጋባት “አናውቅም” የሚል ደካማ መልስ ሰጡት። ኢየሱስ “እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም” ሲል ረጋ ብሎ መለሰ።—ማቴዎስ 21:23-27
የኢየሱስ ጠላቶች እሱን ለማሳሰር የሚያስችላቸውን ነገር እንዲናገር በማድረግ ሊያጠምዱት ሞከሩ። “ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስ “የግብሩን ብር አሳዩኝ” አለ። ከዚያም “ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት?” ብሎ ጠየቃቸው። “የቄሣር” ነው አሉ። ኢየሱስ ለሁሉም በግልጽ በሚሰማበት ሁኔታ “የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” በማለት በሚያስገርም መንገድ መለሰላቸው።—ማቴዎስ 22:15-22
ኢየሱስ ጠላቶቹን ሊቃወሙት በማይችሉት የመከራከሪያ ነጥብ ዝም ካሰኛቸው በኋላ በተሰበሰበው ሕዝብና በደቀ መዛሙርቱ ፊት ክፉኛ ነቀፋቸው። ጻፎችንና ፈሪሳውያንን ያለ ፍርሃት ሲያወግዛቸው አዳምጥ። “እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ” አለ። እውር መሪዎችና ግብዞች መሆናቸውን በመግለጽ በእነሱ ላይ የሚመጡትን ተከታታይ ወዮታዎች በድፍረት ተናግሯል። ኢየሱስ “እናንተ እባቦች፣ የእፉኝት ልጆች፣ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?” አለ።—ማቴዎስ 23:1-33
ኢየሱስ እነዚህን ኃይለኛ የውግዘት ቃላት የተናገረው የሌሎች ሰዎችን መልካም ባሕርያት ማየት ስለማይችል አይደለም። ከዚያ በኋላ ሰዎች በቤተ መቅደሱ የመዋጮ ሳጥን ውስጥ ገንዘብ ሲጥሉ ተመለከተ። አንዲት ችግረኛ መበለት ምንም ሳታስቀር ያሏትን ዋጋቸው በጣም አነስተኛ የሆኑ ሁለት ሳንቲሞች ስትጥል ማየት ምን ያህል ስሜትን የሚነካ ነበር! ኢየሱስ በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት እንደተናገረው ካላቸው ‘ትርፍ’ ብዙ መዋጮ ካደረጉት ሁሉ የሚበልጥ ጥላለች። ኢየሱስ እጅግ ሩኅሩኅ በመሆኑ አንድ ሰው ማድረግ የሚችለውን የቱንም ያህል ነገር ቢያደርግ በጥልቅ ያደንቃል።—ሉቃስ 21:1-4
አሁን ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ በመሄድ ላይ ነው። አንዳንድ ደቀ መዛሙርቱ ቤተ መቅደሱ “በመልካም ድንጋይና በተሰጠው ሽልማት እንዳጌጠ” በመናገር ስለ ውበቱ አወሱ። ኢየሱስ “ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል” ሲላቸው በጣም ተገረሙ። (ሉቃስ 21:5, 6) ሐዋርያቱ ኢየሱስን ተከትለው በሕዝብ ከተጨናነቀው ከተማ ሲወጡ ምን ማለቱ እንደሆነ ያስቡ ነበር።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ሰላምና ፀጥታ በሰፈነበት የደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጠው ነበር። የኢየሩሳሌምንና የቤተ መቅደሱን ውበት በመመልከት ላይ እያሉ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ ኢየሱስ ስለ ተነበየው ነገር ተጨማሪ ማብራሪያ በመፈለግ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት:- “ንገረን፣ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው?”—ማቴዎስ 24:3፤ ማርቆስ 13:3, 4
ታላቁ አስተማሪ በሰጠው መልስ ላይ ትኩረት የሚስብ ትንቢት ተናግሯል። ታላላቅ ጦርነቶች፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የምግብ እጥረት እንዲሁም ወረርሽኝ በሽታዎች እንደሚከሰቱ ተንብዮአል። ኢየሱስ የመንግሥቱ ምሥራች በዓለም ዙሪያ እንደሚሰበክም ተናግሯል። በተጨማሪም “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል” ሲል አስጠንቅቋል።—ማቴዎስ 24:7, 14, 21፤ ሉቃስ 21:10, 11
ኢየሱስ ስለ ‘መገኘቱ ምልክት’ ሌሎች ገጽታዎች ሲናገር አራቱ ሐዋርያት በትኩረት ያዳምጡት ነበር። ‘ነቅቶ የመጠበቅን’ አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጾታል። ለምን? “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁም” በማለት ተናግሯል።—ማቴዎስ 24:42፤ ማርቆስ 13:33, 35, 37
ይህ ለኢየሱስና ለሐዋርያቱ የማይረሳ ቀን ነበር። እንዲያውም ኢየሱስ ከመታሰሩ፣ ለፍርድ ከመቅረቡና ከመገደሉ በፊት ለሕዝብ በሚሰጠው አገልግሎት የተካፈለበት የመጨረሻው ቀን ይህ ነው። ጊዜው እየመሸ በመሆኑ ወደ ቢታንያ በሚወስደው አጭር የአቀበት መንገድ ላይ ጉዞ ጀመሩ።
ኒሳን 12 እና 13
ኢየሱስ ኒሳን 12ን ያሳለፈው ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በተረጋጋ ሁኔታ ነበር። ሃይማኖታዊ መሪዎቹ ሊገድሉት እንደፈልጉ አውቋል። ስለዚህ በሚቀጥለው ቀን የሚያከብረውን የማለፍ በዓል እንዲያደናቅፉበት አልፈለገም። (ማርቆስ 14:1, 2) በማግስቱ ማለትም በኒሳን 13 ሕዝቡ ለማለፍ በዓል የመጨረሻ ዝግጅት ለማድረግ በሥራ ተወጥሯል። ከሰዓት በኋላ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም በሚገኝ ደርብ ላይ የማለፍ በዓልን እንዲያሰናዱ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላካቸው። (ማርቆስ 14:12-16፤ ሉቃስ 22:8) ፀሐይ ከመጥለቋ ከጥቂት ጊዜ በፊት ኢየሱስና የተቀሩት አሥር ሐዋርያቱ የመጨረሻውን የማለፍ በዓል ለማክበር ወደ እነሱ ሄዱ።
ኒሳን 14፣ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ
መሸትሸት ሲል በደብረ ዘይት ተራራ ላይ የወጣችው ሙሉ ጨረቃ ኢየሩሳሌምን በደብዛዛ ብርሃን ሸፈነቻት። ኢየሱስ ከ12ቱ ጋር በአንድ በተሰናዳ ትልቅ ክፍል ውስጥ በተዘጋጀ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠዋል። “ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር” አለ። (ሉቃስ 22:14, 15) ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስ ተነስቶ ከላይ የለበሰውን ልብስ አውልቆ በአንድ ጥግ ሲያስቀምጥ ሲመለከቱ ሐዋርያቱ ተገረሙ። የማድረቂያ ጨርቅ ይዞ መጣና በመታጠቢያ ሳህን ውኃ አድርጎ እግሮቻቸውን ማጠብ ጀመረ። በትሕትና ማገልገልን በተመለከተ የተሰጠ እንዴት ያለ የማይረሳ ትምህርት ነው!—ዮሐንስ 13:2-15
ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ማለትም የአስቆሮቱ ይሁዳ ለሃይማኖታዊ መሪዎች አሳልፎ ሊሰጠው ማቀዱን ያውቃል። በጣም ተጨንቆ መሆን አለበት። “ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል” አላቸው። ሐዋርያቱ በዚህ እጅግ አዘኑ። (ማቴዎስ 26:21, 22) የማለፍን በዓል ካከበሩ በኋላ ኢየሱስ ይሁዳን “የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ አለው።”—ዮሐንስ 13:27
ይሁዳ ከሄደ በኋላ ኢየሱስ ለሞቱ መታሰቢያ የሚሆነውን ራት አስተዋወቀ። እርሾ ያልገባበትን ቂጣ አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካቀረበ በኋላ ለ11ዱ ቆርሶ ሰጣቸው። “ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ። ከዚያም ቀይ የወይን ጠጅ የያዘውን ጽዋ አነሣ። የምስጋና ጸሎት ካቀረበ በኋላ ጽዋውን ሰጣቸውና እንዲጠጡት ነገራቸው። ኢየሱስ “ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” ሲል አክሎ ተናገረ።—ሉቃስ 22:19, 20፤ ማቴዎስ 26:26-28
በዚያ ወሳኝ ምሽት ኢየሱስ ለታመኑ ሐዋርያቱ የወንድማማች መዋደድ አስፈላጊ መሆኑን ጨምሮ ሌሎች ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን አስተምሯቸዋል። (ዮሐንስ 13:34, 35) “አጽናኝ” የሆነውን መንፈስ ቅዱስ እንደሚቀበሉ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገሮች በሙሉ እንዲያስታውሱ ይረዳቸዋል። (ዮሐንስ 14:26) ከመሸ በኋላ ስለ እነሱ ልባዊ ጸሎት ሲያቀርብ ሲሰሙት በጣም ተበረታተው መሆን አለበት። (ዮሐንስ ምዕራፍ 17) የውዳሴ መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ከደርቡ ወጥተው በቀዝቃዛው ሌሊት ኢየሱስን ተከትለው ሄዱ።
ኢየሱስና ሐዋርያቱ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻግረው ከሚወዷቸው ቦታዎች ወደ አንዱ ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ አቀኑ። (ዮሐንስ 18:1, 2) ኢየሱስ ትንሽ ራቅ ብሎ ሲጸልይ ሐዋርያቱ ይጠብቁት ነበር። አምላክ እንዲረዳው አጥብቆ ሲለምን የተሰማውን የስሜት ውጥረት በቃላት ለመግለጽ ያዳግታል። (ሉቃስ 22:44) አቋሙን ቢያጎድፍ በውድ ሰማያዊ አባቱ ላይ የሚከመረውን ስድብ ገና ለገና ሲያስበው በጣም ተጨነቀ።
ኢየሱስ ጸሎቱን ገና ከመጨረሱ የአስቆሮቱ ይሁዳ ሰይፍ ከታጠቁ፣ ጎመድና ችቦ ከያዙ ሰዎች ጋር መጣ። ይሁዳ ኢየሱስን አቅፎ እየሳመው “መምህር ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን” አለው። ኢየሱስን እንዲያስሩ ለሰዎቹ ምልክት መስጠቱ ነው። ጴጥሮስ በቅጽበት ሰይፉን ከሰገባው መዝዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ ጆሮ ቆረጠው። ኢየሱስ የሰውየውን ጆሮ ፈወሰና “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ” አለው።—ማቴዎስ 26:47-52
ሁሉም ነገር የተፈጸመው በፍጥነት ነበር! ኢየሱስ ተይዞ ታሰረ። ሐዋርያቱ ፈርተውና ተደናግረው ጌታቸውን ጥለው ሸሹ። ኢየሱስ ቀደም ሲል ሊቀ ካህናት ወደነበረው ወደ ሐና ተወሰደ። ከዚያም የወቅቱ ሊቀ ካህናት ወደሆነው ወደ ቀያፋ ተወስዶ ተመረመረ። ጠዋት ላይ ኢየሱስ አምላክን ሰድበሃል ተብሎ በሳንሄድሪን ፍርድ ቤት በሐሰት ተከሰሰ። ቀጥሎም ቀያፋ ወደ ሮማዊው አገረ ገዥ ወደ ጴንጤናዊው ጲላጦስ እንዲወሰድ አደረገ። ጲላጦስ የገሊላ ገዥ ወደሆነው ወደ ሄሮድስ አንቲጳስ ላከው። ሄሮድስና ወታደሮቹ በኢየሱስ ላይ አሾፉበት። ከዚያም ወደ ጲላጦስ መልሰው ላኩት። ኢየሱስ ጥፋት የሌለበት መሆኑን ጲላጦስ አረጋገጠ። ይሁን እንጂ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ እንዲፈርድ አስገደዱት። ኢየሱስ የስድብና የዱላ መዓት ከወረደበት በኋላ ያለ ምንም ርኅራኄ ወደ ጎልጎታ ተወስዶ በመከራ እንጨት ላይ ተቸንክሮ በአሰቃቂ ሁኔታ ተሰቃይቶ ሞተ።—ማርቆስ 14:50–15:39፤ ሉቃስ 23:4-25
የኢየሱስ ሞት በሕይወቱ ላይ ዘላቂ ጉዳት የሚያስከትል ቢሆን ኖሮ በታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት አሳዛኝ ነገሮች ሁሉ የከፋ ይሆን ነበር። የሚያስደስተው ግን እንዲህ አልሆነም። ደቀ መዛሙርቱ ኒሳን 16, 33 እዘአ ከሞት መነሳቱን ሲያዩ ተገርመው ነበር። ከጊዜ በኋላ ከ500 የሚበልጡ ሰዎች ኢየሱስ እንደገና ሕያው መሆኑን ሊያረጋግጡ ችለዋል። ከትንሣኤው ከ40 ቀናት በኋላ የታመኑ ተከታዮቹን ያቀፈ አንድ ቡድን ወደ ሰማይ ሲያርግ ተመልክቶታል።—ሥራ 1:9-11፤ 1 ቆሮንቶስ 15:3-8
የኢየሱስ ሕይወትና አንተ
ይህ አንተን ጨምሮ ሁላችንንም የሚነካን እንዴት ነው? የኢየሱስ አገልግሎት፣ ሞቱና ትንሣኤው ይሖዋ አምላክን ከፍ ከፍ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ የታላላቅ ዓላማዎቹ ፍጻሜ የተመካው በእነዚህ ነገሮች ላይ ነው። (ቆላስይስ 1:18-20) በኢየሱስ መሥዋዕት መሠረት ኃጢአታችን ይቅር እንዲባልልንና ከይሖዋ አምላክ ጋር የግል ዝምድና እንዲኖረን ስለሚያስችሉን በጣም አስፈላጊያችን ናቸው።—ዮሐንስ 14:6፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2
ሌላው ቀርቶ ሙታንም እንኳን በዚህ ይነካሉ። አምላክ ተስፋ በሰጠባት ገነታዊ ምድር ውስጥ ለመኖር ተመልሰው ሕያው እንዲሆኑ የኢየሱስ ትንሣኤ በር ከፍቶላቸዋል። (ሉቃስ 23:39-43፤ 1 ቆሮንቶስ 15:20-22) ስለ እነዚህ ጉዳዮች ይበልጥ ለማወቅ የምትፈልግ ከሆነ በአቅራቢያህ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ተገኝተህ ሚያዝያ 11, 1998 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሚያዝያ 3, 1990) የሚከበረውን የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል እንድታከብር እንጋብዝሃለን።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“የወንበዶች ዋሻ”
ኢየሱስ ስስታም ነጋዴዎች የአምላክን ቤተ መቅደስ “የወንበዶች ዋሻ” አድርገውታል ብሎ ለመናገር የተገደደበት በቂ ምክንያት ነበረው። (ማቴዎስ 21:12, 13) አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ የሌሎች አገር ሰዎች የቤተ መቅደሱን ቀረጥ ለመክፈል የያዙትን የውጭ ምንዛሪ ተቀባይነት ወዳለው ገንዘብ መለወጥ ነበረባቸው። አልፍሬድ ኢድርሺም ዘ ላይፍ ኤንድ ታይምስ ኦቭ ዘ መሳያ በተባለው መጽሐፋቸው እንዳብራሩት ገንዘብ ለዋጮቹ ከማለፍ በዓል አንድ ወር በፊት በአዳር 15 የሮማ ቁጥጥር ሥር በነበሩ ግዛቶች ንግዳቸውን የመጀመር ልማድ ነበራቸው። እየጎረፈ ከሚመጣው አይሁዳዊና ወደ ይሁዲነት የተለወጠ ሕዝብ ትርፍ ለመዛቅ ሲሉ ከአዳር 25 ጀምሮ በቤተ መቅደሱ አካባቢ ለመነገድ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ ነበር። ነጋዴዎች ለሚመነዝሩት ለእያንዳንዱ ሳንቲም ክፍያ በመጠየቅ የጦፈ ንግድ ያካሂዱ ነበር። ኢየሱስ ወንበዶች የሚለውን ቃል መጠቀሙ እንደሚያመለክተው ለምንዛሬው የሚጠይቁት ክፍያ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሣ ቃል በቃል ከድሆች ገንዘብ የመንጠቅ ያህል ነበር።
አንዳንዶች ለመሥዋዕት የሚያቀርቡትን የራሳቸውን እንስሳ ለማምጣት አይችሉም ነበር። የራሱን እንስሳ ለማምጣት የቻለ ሰው ደግሞ ገንዘብ ከፍሎ በቤተ መቅደሱ በሚገኝ አንድ ተቆጣጣሪ እንስሳውን ማስመርመር ነበረበት። ብዙዎች ረዥም ርቀት ተጉዘው ያመጡት እንስሳ ተቀባይነት እንዳያጣ በመስጋት እዚያው በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሌዋውያን “ተቀባይነት ያገኘ” እንስሳ ከብልሹ ነጋዴዎች ይገዛሉ። አንድ ምሁር “በርካታ ድሃ ገበሬዎች ገንዘባቸውን የሚዘረፉት በዚያ ነበር” ብለዋል።
በአንድ ወቅት ሊቀ ካህናቱ ሐና እና ቤተሰቡ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ በቤተ መቅደሱ ነጋዴዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድሩ እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ አለ። የረቢዎች ጽሑፎች “የሐና ወንዶች ልጆች [በቤተ መቅደስ] የንግድ ትርዒት” ማዘጋጀታቸውን ይናገራሉ። በቤተ መቅደሱ ክልል ውስጥ ከገንዘብ ለዋጮችና ከእንስሳት ሽያጭ የሚሰበሰበው ቀረጥ የሐና እና የቤተሰቡ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነበር። አንድ ምሁር እንዳሉት ኢየሱስ ነጋዴዎቹን በማባረር የወሰደው እርምጃ “የካህናቱን ክብር ለመንካት የታለመ ብቻ ሳይሆን በገቢ ምንጫቸውም ላይ ያነጣጠረ ነበር።” ጠላቶቹ የተነሣሡበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ሊገድሉት እንደፈለጉ የተረጋገጠ ነበር!—ሉቃስ 19:45-48
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
የኢየሱስ ሰብዓዊ ሕይወት የመጨረሻ ቀናት
ኒሳን 33 እዘአ የተከናወኑ ድርጊቶች ታላቅ ሰው*
7 ዓርብ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ 101 አን. 1
ከኢያሪኮ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዙ
( በዕብራውያኑ አቆጣጠር መሠረት አንድ ዕለት
የሚጀምረውም ሆነ የሚያልቀው ምሽት ላይ ቢሆንም
ኒሳን 7 የሚውለው እሁድ፣ ሚያዝያ 5, 1998 ነው)
8 ዓርብ ምሽት ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ቢታንያ ደረሱ፤ 101
ሰንበት ጀመረ አን. 2-4
ቅዳሜ ሰንበት (ሰኞ፣ ሚያዝያ 6, 1998) 101, አን. 4
9 ቅዳሜ ምሽት የሥጋ ደዌ ከነበረበት ስምዖን ቤት ራት ተጋበዘ፤ 101,
ማርያም ኢየሱስን የናርዶስ ሽቱ ቀባችው፤ አን. 5-9
ብዙዎች ኢየሱስን ለማየትና ለማዳመጥ ከኢየሩሳሌም መጡ
እሁድ ድል ተጎናጽፎ ኢየሩሳሌም ገባ፤ በቤተ መቅደስ አስተማረ 102
10 ሰኞ በማለዳ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ፤ ቤተ መቅደሱን አጸዳ፤ 103, 104
ይሖዋ ከሰማይ ተናገረ
11 ማክሰኞ ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ 105 to 112,
በምሳሌዎች እየተጠቀመ አስተማረ፤ አን. 1
ፈሪሳውያንን አወገዘ፤ መበለቲቱ
ያደረገችውን መዋጮ ተመለከተ፤
ወደፊት ስለሚገኝበት ሁኔታ ምልክት ተናገረ
12 ረቡዕ በቢታንያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ቀኑን በፀጥታ አሳለፈ፤ 112,
ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ተዘጋጀ አን. 2-4
13 ሐሙስ ጴጥሮስና ዮሐንስ በኢየሩሳሌም የማለፍ በዓልን አሰናዱ፤ 112,
ኢየሱስና የተቀሩት አሥሩ ሐዋርያት አን. 5 to
አመሻሹ ላይ ወደ እነሱ ሄዱ 113, አን. 1
(ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 11, 1998)
14 ሐሙስ ምሽት የማለፍን በዓል አከበሩ፤ 113,
ኢየሱስ የሐዋርያቱን እግር አጠበ፤ አን. 2
ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ሊሰጥ ወጣ፤ እስከ 117
የሞቱን መታሰቢያ በዓል አቋቋመ
(ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ፤ ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 11, 1998)
ከእኩለ ሌሊት በኋላ በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ አልፎ ተሰጠና 118 እስከ 120
ታሰረ፤ ሐዋርያቱ ሸሹ፤በካህናት አለቃና
በሳንሄድሪን ፊት ለፍርድ ቀረበ፤ ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደ
ዓርብ ጎሕ ከቀደደበት እንደገና ወደ ሳንሄድሪን ተወሰደ፤ ወደ ጲላጦስ፣ 121 እስከ
አንስቶ ፀሐይ ከዚያ ወደ ሄሮድስ፣ እንደገና ተመልሶ ወደ ጲላጦስ ተወሰደ፤ 127
እስከ ጠለቀችበት ሞት ተፈረደበት፤ ተሰቀለ፤ ተቀበረ አን. 7
15 ቅዳሜ ሰንበት፤ የኢየሱስ መቃብር በወታደሮች እንዲጠበቅ 127
ጲላጦስ ፈቃድ ሰጠ አን. 8-10
16 እሁድ ኢየሱስ ከሞት ተነሣ 128
* እዚህ ላይ የተጠቀሱት ቁጥሮች እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ምዕራፎች ያመለክታሉ። ስለ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ማብቂያ የሚገልጽ ዝርዝር ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችን የያዘ ሰንጠረዥ ለማግኘት “ቅዱስ ጽሑፍ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው ” የተባለውን (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ ገጽ 290 ተመልከት። እነዚህ መጻሕፍት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተሙ ናቸው።