ምዕራፍ 105
በበለስ ዛፍ ተጠቅሞ ስለ እምነት ማስተማር
ማቴዎስ 21:19-27 ማርቆስ 11:19-33 ሉቃስ 20:1-8
የደረቀችው የበለስ ዛፍ—ስለ እምነት አስተማረ
በኢየሱስ ሥልጣን ላይ ጥያቄ ተነሳ
ኢየሱስ ሰኞ ከሰዓት በኋላ ከኢየሩሳሌም ወጥቶ በደብረ ዘይት ተራራ ምሥራቃዊ አቀበት ላይ ወደምትገኘው ወደ ቢታንያ ተመለሰ። የሚያድረው ወዳጆቹ በሆኑት በአልዓዛር፣ በማርያምና በማርታ ቤት ሳይሆን አይቀርም።
አሁን ኒሳን 11 ማለዳ ነው። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም እንደገና መጓዝ ጀመሩ፤ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ለመጨረሻ ጊዜ የሄደው በዚህ ዕለት ነው። እንዲሁም ፋሲካን ከማክበሩ፣ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ከማቋቋሙና ሸንጎ ፊት ቀርቦ ከመገደሉ በፊት አገልግሎቱን ያከናወነበት የመጨረሻ ቀን ነው።
ከቢታንያ በመነሳት በደብረ ዘይት ተራራ አልፈው ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዙ እያለ ኢየሱስ ትናንት ጠዋት የረገማትን ዛፍ ጴጥሮስ ተመለከተ። ጴጥሮስ “ረቢ፣ ተመልከት! የረገምካት የበለስ ዛፍ ደርቃለች” አለው።—ማርቆስ 11:21
ይሁንና ኢየሱስ ዛፏ እንድትደርቅ ያደረገው ለምንድን ነው? ኢየሱስ እንዲህ ብሎ በተናገረ ጊዜ ምክንያቱን ገልጿል፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ እምነት ካላችሁና ካልተጠራጠራችሁ እኔ በበለስ ዛፏ ላይ ያደረግኩትን ማድረግ ብቻ ሳይሆን ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ብትሉት እንኳ ይሆንላችኋል። እምነት ካላችሁ በጸሎት የምትጠይቁትን ነገር ሁሉ ታገኛላችሁ።” (ማቴዎስ 21:21, 22) ይህን ሲል እምነት ተራራን እንደሚያንቀሳቅስ ከዚህ በፊት የተናገረውን ሐሳብ መድገሙ ነው።—ማቴዎስ 17:20
ስለዚህ ኢየሱስ ዛፏ እንድትደርቅ በማድረግ፣ ሐዋርያቱ በአምላክ ማመን እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ሠርቶ ማሳያ አቀረበላቸው። “በጸሎት የምትጠይቁትንና የምትለምኑትን ነገር ሁሉ እንዳገኛችሁት አድርጋችሁ እመኑ፤ ደግሞም ታገኙታላችሁ” አላቸው። (ማርቆስ 11:24) ይህ ለሁሉም የኢየሱስ ተከታዮች የሚሆን እንዴት ያለ ጠቃሚ ትምህርት ነው! በተለይ ደግሞ ሐዋርያቱ በቅርቡ ከሚያጋጥሟቸው ከባድ ፈተናዎች አንጻር ይህን ማለቱ ተገቢ ነው! ሆኖም የበለስ ዛፏ መድረቅ ከእምነት ጋር የሚያያዝበት ሌላም መንገድ አለ።
እንደዚህች የበለስ ዛፍ ሁሉ የእስራኤል ብሔርም አሳሳች መልክ አለው። ሕዝቡ ከአምላክ ጋር በቃል ኪዳን ተዛምዷል፤ እንዲሁም ሕጉን የሚጠብቅ ይመስላል። ይሁንና ብሔሩ በአጠቃላይ እምነት የለሽና መልካም ፍሬ የማያፈራ መሆኑ ታይቷል። ሌላው ቀርቶ የአምላክን ልጅ እንኳ ለመቀበል አሻፈረኝ ብሏል! በመሆኑም ኢየሱስ ፍሬያማ ያልሆነችው የበለስ ዛፍ እንድትደርቅ ማድረጉ፣ ፍሬ የማያፈራውና እምነተ ቢስ የሆነው የዚህ ብሔር የመጨረሻ ዕጣ ምን እንደሆነ ያሳያል።
ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ። ኢየሱስ እንደ ልማዱ ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዶ ማስተማር ጀመረ። የካህናት አለቆቹና የሕዝቡ ሽማግሌዎች “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? እነዚህን ነገሮች እንድታደርግስ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” አሉት። ይህን ያሉት ከአንድ ቀን በፊት ገንዘብ መንዛሪዎቹ ላይ የወሰደውን እርምጃ በአእምሯቸው ይዘው ሳይሆን አይቀርም።—ማርቆስ 11:28
ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ። እናንተም መልሱልኝ፤ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። ዮሐንስ የማጥመቅ ሥልጣን ያገኘው ከአምላክ ነው ወይስ ከሰው? መልሱልኝ።” አሁን ተቃዋሚዎቹ ፈተና ገጠማቸው። ካህናቱና ሽማግሌዎቹ ምን ብለው እንደሚመልሱለት ይማከሩ ጀመር፦ “‘ከአምላክ’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤ ደፍረን ‘ከሰው ነው’ ብንልስ? ሰዎቹ ሁሉ ዮሐንስን እንደ ነቢይ ያዩት ስለነበር ሕዝቡን ፈሩ።”—ማርቆስ 11:29-32
የኢየሱስ ተቃዋሚዎች አጥጋቢ መልስ መስጠት አልቻሉም። በመሆኑም “አናውቅም” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም “እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።—ማርቆስ 11:33