ኢየሱስ ሕይወቱና አገልግሎቱ
አልፎ ተሰጠና ተወሰደ
ጲላጦስ ብዙ መከራ የደረሰበትንና እርጋታ ያልተለየውን የኢየሱስ ፊት ተመልክቶ ልቡ ተነካና ሊፈታው ፈለገ። የካህናት አለቆች ግን ይበልጡኑ ተቆጡ። ምንም ነገር የክፋት እቅዳቸውን እንዳያደናቅፍባቸው ቆርጠዋል። ስለዚህ እንደገና “ስቀለው፣ ስቀለው!” እያሉ ጮሁ።
ጲላጦስም ነገሩ አናደደውና “እናንተ ራሳችሁ ወስዳችሁ ስቀሉት” አላቸው። አይሁዳውያን ቀደም ብለው እንደተናገሩት ሳይሆን ከባድ ሃይማኖታዊ ወንጀል የሠሩ ሰዎችን የመግደል ሥልጣን ነበራቸው። ከዚያም ጲላጦስ ቢያንስ ለአምስተኛ ጊዜ “እኔስ ምንም በደል አላገኘሁበትም” በማለት ስለ ኢየሱስ ንጽሕና መሰከረ።
አይሁዳውያን የፖለቲካ ክሳቸው እንዳላዋጣቸው ሲገነዘቡ ኢየሱስ ከብዙ ሰዓቶች በፊት በአይሁድ ሸንጎ ቀርቦ በነበረበት ጊዜ አቅርበውበት ወደነበረው ክስ በመመለስ አምላክን ተሳድቦአል የሚል ሃይማኖታዊ ክስ አቀረቡበት። “እኛ ሕግ አለን፣ እንደ ሕጋችንም ሊሞት ይገባዋል፣ ራሱንም የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎአልና” አሉት።
ይህ ክስ ለጲላጦስ አዲስ ክስ ነበር። በዚህም ምክንያት ይበልጡኑ ፈራ። እስከ አሁን ድረስ ከሚስቱ ሕልምና ከኢየሱስ የባሕርይ ጥንካሬ ኢየሱስ ተራ ሰው አለመሆኑን ተገንዝቦ ነበር። የአምላክ ልጅ ስለመሆኑ ግን የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ጲላጦስ ኢየሱስ የገሊላ ሰው መሆኑን ያውቅ ነበር። ታዲያ ከዚያ ጊዜ በፊት በሕይወት ይኖር የነበረበት ዘመን ይኖር ይሆን? ዳግመኛ ወደ ቤተ መንግሥቱ ወሰደውና “አንተ ከወዴት ነህ?” አለው።
ኢየሱስ ምንም መልስ አልሰጠውም። ቀደም ሲል እርሱ ንጉስ እንደሆነና መንግሥቱም ከዚህ ዓለም እንዳልሆነ ነግሮት ነበር። አሁን የሚናገረው ማንኛውም ነገር ምንም ፋይዳ አይኖረውም። ጲላጦስ ግን የተናቀ መሰለውና በጣም ተቆጣ። ስለዚህ ጲላጦስ “አትነግረኝምን? ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን?” አለው።
ኢየሱስም በአክብሮት “ከላይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልነበረህም” ሲል መለሰለት። አምላክ ሰብአዊ ገዥዎች ምድርን እንዲያስተዳድሩ ሥልጣን ስለመስጠቱ መናገሩ ነበር። ቀጥሎም “ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ኃጢአቱ የባሰ ነው” አለው። በእውነትም በኢየሱስ ላይ ለደረሰው መከራ ሁሉ ከጲላጦስ ይልቅ በይበልጥ ተጠያቂ የሚሆኑት ሊቀካህናት ቀያፋና ተባባሪዎቹ፣ እንዲሁም ይሁዳ አስቆረቱ ናቸው።
ጲላጦስ በኢየሱስ ድፍረት በጣም ስለተደነቀና መለኮትነት ይኖረው ይሆናል ብሎ ስለፈራ አሁንም እንደገና ሊፈታው ሙከራ አደረገ። አይሁዳውያን ግን በብርቱ ተቃወሙት። ያቀረቡበትን የፖለቲካ ክስ በማደስ “ይህንስ ብትፈታው የቄሳር ወዳጅ አይደለህም። ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ የቄሣር ተቃዋሚ ነው” እያሉ አስፈራሩት።
አሁንም ጲላጦስ የተደቀነበትን አደገኛ ሁኔታ ቢገነዘብም ዳግመኛ ኢየሱስን አወጣላቸውና “እነሆ ንጉሣችሁ” በማለት የመጨረሻ ሙከራ አደረገ።
እነርሱ ግን “አስወግደው፣ አስወግደው፣ ስቀለው” እያሉ ጮሁ።
ጲላጦስም የሚያደርገው ነገር ጠፍቶት “ንጉሣችሁን ልስቀለውን” ብሎ ጠየቃቸው።
አይሁዳውያን ከሮማውያን አገዛዝ ብዙ መከራ ደርሶባቸው ነበር። የሮማውያንን ግዛት አጥብቀው እንደሚጠሉ የታወቀ ነበር። ይሁን እንጂ ሊቀ ካህናቱ በግብዝነት “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” አሉ።
ጲላጦስም በፖለቲካዊ ሹመቱና በስሙ ላይ ነቀፌታ እንዳይመጣበት ፈርቶ ለአይሁዳውያን አቤቱታ ተሸነፈ። ኢየሱስን አሳልፎ ሰጠው። ወታደሮቹ አልብሰውት የነበረውን ቀይ ልብስ አውልቀው መደረቢያውን አለበሱት። ኢየሱስ ወደ ሚሰቀልበት ቦታ ሲወሰድ የሚሰቀልበትን እንጨት ራሱ እንዲሸከም ተደረገ።
አሁን ዕለቱ ዐርብ ኒሣን 14 ቀን ሆኖአል። ሰዓቱም ወደ ረፋዱ እንዲያውም ወደ እኩለ ቀን ተቃርቦአል። ኢየሱስ ከሐሙስ ሌሊት ጀምሮ እንቅልፍ ካለማግኘቱም ሌላ የተለያዩ መከራዎች ተፈራርቀውበታል። በዚህም ምክንያት ጉልበቱ ዛለና የተጫነበትን እንጨት መሸከም አቃተው። በመንገድ ያልፍ የነበረ ቄሬናዊ ስምዖን የተባለ አፍሪካዊ ሰው እንዲሸከምለት ተደረገ። በመንገድ በሚያልፉበት ጊዜ ብዙ ሰዎች፣ ደረታቸውን እየመቱ የሚያለቅሱለት ሴቶች ጭምር ተከተሉት።
ኢየሱስ ወደ ሴቶቹ መለስ ብሎ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች ለእኔስ አታልቅሱልኝ፤ ዳሩ ግን መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዐን ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። በዚያን ጊዜ ተራራዎችን በላያችን ውደቁ፣ ኮረብቶችንም ሰውሩን ይሉ ዘንድ ይጀምራሉ። በእርጥብ እንጨት እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ በደረቀውስ እንዴት ይሆን?”
ኢየሱስ ገና በአይሁድ ሕዝብ መካከል ስላለና በእርሱ የሚያምኑ ቀሪዎች በመካከሉ ስላሉ ገና እርጥበት ስላልተለየው የአይሁድ ሕዝብ ዛፍ መናገሩ ነበር። እነዚህ ከሕዝቡ መካከል ሲወሰዱ ግን የሚቀረው የደረቀ ግንድ ብቻ፣ የጠወለገ ብሔራዊ ድርጅት ብቻ ይሆናል። የሮማ ጭፍሮች የይሖዋ ፍርድ አስፈጻሚዎች በመሆን የአይሁድን ብሔር ሲያጠፉ ታላቅ ልቅሶና ወዮታ ይሆናል። ዮሐንስ 19:6-17፤ 18:31፤ ሉቃስ 23:24-31፤ ማቴዎስ 27:31, 32፤ ማርቆስ 15:20, 21
◆ ሃይማኖታዊ መሪዎች የፖለቲካ ክሳቸው እንዳላዋጣቸው ሲገነዘቡ በኢየሱስ ላይ ምን ዓይነት ክስ አቀረቡበት?
◆ ጲላጦስ በይበልጥ የፈራው ለምን ሊሆን ይችላል?
◆ በኢየሱስ ላይ ለደረሰው ነገር ሁሉ ይበልጥ በደለኛ የሚሆኑት እነማን ናቸው?
◆ ካህናቱ ጲላጦስ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጣቸው ያደረጉት እንዴት ነው?
◆ ኢየሱስ ላለቀሱለት ሴቶች ምን አላቸው? ስለ ዛፉ መርጠብና መድረቅ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?