ምዕራፍ 130
ኢየሱስ አልፎ ተሰጠ፤ ከዚያም ሊገደል ተወሰደ
ማቴዎስ 27:31, 32 ማርቆስ 15:20, 21 ሉቃስ 23:24-31 ዮሐንስ 19:6-17
ጲላጦስ ኢየሱስን ሊፈታው ሞከረ
ኢየሱስ ተፈረደበት፤ ወደሚገደልበት ቦታም ተወሰደ
ኢየሱስ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የተንገላታና የተዘበተበት ቢሆንም ጲላጦስ እሱን ለመልቀቅ ያደረገው ሙከራ የካህናት አለቆቹና ተባባሪዎቻቸው እንዲራሩለት አላደረጋቸውም። ኢየሱስን ከመግደል ምንም ነገር እንዳያግዳቸው ቆርጠዋል። “ይሰቀል! ይሰቀል!” እያሉ መጮኻቸውን ቀጠሉ። ጲላጦስም “እኔ ምንም ጥፋት ስላላገኘሁበት ራሳችሁ ወስዳችሁ ግደሉት” አላቸው።—ዮሐንስ 19:6
አይሁዳውያን ኢየሱስ ላይ ያቀረቡት ፖለቲካዊ ክስ ለሞት የሚያበቃ እንደሆነ ጲላጦስን ማሳመን አልቻሉም፤ ይሁንና ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ክስ ቢያቀርቡስ? ኢየሱስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ቀርቦ በነበረበት ጊዜ የሰነዘሩትን ‘አምላክን ተሳድቧል’ የሚል ክስ እንደገና አነሱ። አይሁዳውያኑ “እኛ ሕግ አለን፤ ይህ ሰው ደግሞ ራሱን የአምላክ ልጅ ስላደረገ በሕጉ መሠረት መሞት አለበት” አሉ። (ዮሐንስ 19:7) ይህ ለጲላጦስ አዲስ ክስ ነው።
ጲላጦስ ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፤ ከዚያም የደረሰበትን ከባድ ሥቃይ በጽናት የተቋቋመውንና ሚስቱ በሕልሟ ያየችውን ኢየሱስን መፍታት የሚችልበትን መንገድ መፈለግ ጀመረ። (ማቴዎስ 27:19) አይሁዳውያን፣ እስረኛው “የአምላክ ልጅ” እንደሆነ መናገሩን አስመልክቶ የሰነዘሩት አዲስ ክስስ? ጲላጦስ፣ ኢየሱስ የገሊላ ሰው መሆኑን ያውቃል። (ሉቃስ 23:5-7) ይሁንና “ለመሆኑ ከየት ነው የመጣኸው?” ብሎ ጠየቀው። (ዮሐንስ 19:9) ጲላጦስ፣ ኢየሱስ ከዚያ በፊት በሕይወት ይኖር እንደነበረና ምናልባትም ከአማልክት ዘንድ የመጣ እንደሆነ አስቦ ይሆን?
ኢየሱስ ንጉሥ እንደሆነ፣ ሆኖም መንግሥቱ ከዚህ ዓለም እንዳልሆነ በቀጥታ ለጲላጦስ ነግሮታል። ኢየሱስ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ እንዳልሆነ ስለተሰማው ለጲላጦስ ጥያቄ መልስ አልሰጠም። ኢየሱስ ጸጥ ሲለው ጲላጦስ ክብሩ እንደተነካ ስለተሰማው ድንገት ግንፍል ብሎ “መልስ አትሰጠኝም? ልፈታህም ሆነ ልገድልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅም?” አለው።—ዮሐንስ 19:10
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን አይኖርህም ነበር። ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው የባሰ ኃጢአት ያለበት ለዚህ ነው።” (ዮሐንስ 19:11) ኢየሱስ ይህን ያለው አንድ ሰው በአእምሮው ይዞ ላይሆን ይችላል። ከዚህ ይልቅ ቀያፋና ግብረ አበሮቹ እንዲሁም የአስቆሮቱ ይሁዳ ከጲላጦስ የበለጠ ተጠያቂነት እንዳለባቸው መግለጹ ነው።
ጲላጦስ በኢየሱስ ንግግርም ሆነ ምግባር ከመደነቁም በላይ ከአማልክት ዘንድ የመጣ ሊሆን እንደሚችል በማሰብ ይበልጥ ስለፈራ እሱን ለመፍታት በድጋሚ ጥረት አደረገ። ይሁንና አይሁዳውያን ጲላጦስን ሊያስፈራው የሚችል ሌላ ነጥብ አነሱ። “ይህን ሰው ከፈታኸው አንተ የቄሳር ወዳጅ አይደለህም። ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሰው ሁሉ የቄሳር ተቃዋሚ ነው” ሲሉ አስፈራሩት።—ዮሐንስ 19:12
አገረ ገዢው ኢየሱስን ዳግመኛ ወደ ውጭ በማውጣት በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሕዝቡን “እነሆ፣ ንጉሣችሁ!” አላቸው። አይሁዳውያኑ ግን ሐሳባቸውን አልቀየሩም። “አስወግደው! አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም “ንጉሣችሁን ልግደለው?” ሲል ጠየቃቸው። አይሁዳውያን የሮማውያን አገዛዝ ያስመረራቸው ቢሆንም የካህናት አለቆቹ አፍ አውጥተው “ከቄሳር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ሲሉ መለሱ።—ዮሐንስ 19:14, 15
ጲላጦስ፣ የአይሁዳውያኑን ውትወታ ላለመቀበል ድፍረት ስላጣ በመጨረሻ ለጥያቄያቸው ተንበረከከ፤ በመሆኑም ኢየሱስን እንዲገድሉት አሳልፎ ሰጣቸው። ወታደሮቹ ቀዩን ልብስ ገፈው የራሱን መደረቢያዎች አለበሱት። ኢየሱስን ሲወስዱት የራሱን የመከራ እንጨት እንዲሸከም አደረጉት።
አሁን ዓርብ፣ ኒሳን 14 እኩለ ቀን እየተቃረበ ነው። ኢየሱስ ከሐሙስ ማለዳ ጀምሮ አልተኛም፤ በዚያ ላይ ደግሞ መከራና ሥቃይ ሲፈራረቅበት ቆይቷል። ስለዚህ እንጨቱን ተሸክሞ ሲሄድ ኃይሉ ተሟጠጠ። በመሆኑም ወታደሮቹ፣ አፍሪካ ውስጥ ከምትገኘው ከቀሬና የመጣውን ስምዖን የተባለ መንገደኛ እንጨቱን ተሸክሞ ኢየሱስ ወደሚገደልበት ቦታ እንዲወስድ አስገደዱት። ብዙ ሕዝብ እየተከተለው ነው፤ ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ በሐዘን ደረታቸውን እየደቁ ያለቅሳሉ።
ኢየሱስ የሚያለቅሱትን ሴቶች እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፣ ለእኔ አታልቅሱ። ይልቁንስ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ፤ ሰዎች ‘መሃን የሆኑ ሴቶች፣ ያልወለዱ ማህፀኖችና ያላጠቡ ጡቶች ደስተኞች ናቸው!’ የሚሉበት ቀን ይመጣልና። በዚያን ጊዜ ተራሮችን ‘በላያችን ውደቁ!’ ኮረብቶችንም ‘ሸሽጉን!’ ይላሉ። ዛፉ እርጥብ ሆኖ ሳለ እንዲህ ካደረጉ በደረቀ ጊዜማ ምን ይከሰት ይሆን?”—ሉቃስ 23:28-31
ኢየሱስ እየተናገረ ያለው ስለ አይሁድ ብሔር ነው። ብሔሩ፣ እየደረቀ ቢሆንም ትንሽ እርጥበት እንደቀረው ዛፍ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስና በእሱ የሚያምኑ አንዳንድ አይሁዳውያን አሉ። አምላክ እነዚህን ሰዎች ከብሔሩ እንዲወጡ ሲያደርጋቸው ግን የሚቀረው ልክ እንደደረቀ ዛፍ በመንፈሳዊ ሁኔታ የሞተ ብሔር ነው። የሮም ሠራዊት የአምላክ ፍርድ አስፈጻሚ ሆኖ የአይሁድን ሕዝብ በሚያጠፋበት ጊዜ ታላቅ ለቅሶ ይሆናል!