ኃጢአትን መናዘዝ በሰው መንገድ ነው ወይስ በአምላክ?
በካቶሊኮች ዘንድ የንስሐ ኑዛዜ ባለፉት መቶ ዓመታት ትልቅ ለውጥ አድርጓል። በካቶሊክ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያዎቹ ዘመናት ኑዛዜና ንስሐ የሚጠየቁት ለከባድ ኃጢአቶች ብቻ ነበር። ይህን በሚመለከት ሃይማኖት በመካከለኛዎቹ ዘመናት በምዕራቡ ዓለም ውስጥ የተባለው መጽሐፍ “እስከ ስድስተኛው መቶ ዓመት መጨረሻ ድረስ የንስሐ ቅጣት በጣም ጥብቅ ነበር። የቁርባን ሥነ ሥርዓት የሚፈጸመው በአንድ ሰው ሕይወት አንድ ጊዜ ብቻ ነበር። የንስሐ ኑዛዜ የሚደረገው በሕዝብ ፊት ነበር። የንስሐ ቅጣቱም ረዥምና ጽኑ ነበር።” በማለት ይናገራል።
እንዲህ ዓይነቱ የንስሐ ቅጣት የቱን ያህል ጽኑ ነበር? በ1052 አንድ የንስሐ ቅጣት የተወሰነበት ተናዛዥ በቤልጂየም ከሚገኘው ብሩጅዝ እስከ ኢየሩሳሌም በእግሩ እንዲሄድ ታዞ ነበር! የክርስትና እምነት በምዕራቡ ዓለም 1400-1700 የተሰኘው መጽሐፍ “ካቶሊኮች እስከ 1700 ድረስ የንስሐ ጸሎታቸውን ለመጸለይ በቅዱስ የውሃ ጉድጓዶችና ምንጮች እስከ አንገታቸው ድረስ በበረዶው ላይ እንዲዘፈቁ ይንበረከኩ ነበር” ብሏል። በዚያ ዘመን የንስሐ ቅጣቱ ካላበቃ ፍታት አይሰጥም ነበርና ብዙዎች ኑዛዜያቸውን ለሞት እስኪቀርቡ ድረስ ያዘገዩት ነበር።
ዘመናዊው የኑዛዜ ልማድ የተጀመረው መቼ ነበር? ሃይማኖት በመካከለኛዎቹ ዘመናት በምዕራቡ ዓለም ውስጥ የተሰኘው መጽሐፍ “አዲሱ ዓይነት የንስሐ ቅጣት የመጣው በስድስተኛው መቶ ዓመት መጨረሻ ላይ በፈረንሳይ አገር በሴልቲክ መነኮሳት አስጀማሪነት ነው። ይህ ልማድ ንስሐ የገባው ሰው ለቄሱ ኃጢአቱን በግል የሚናዘዝበት የሹክታ ኑዛዜ ነበር። እሱም ከገዳማት መንፈሳዊ ምክር የመስጠት ልማድ የተወሰደ ነበር” በማለት ይናገራል። በቀድሞ የገዳማት ልማድ መሠረት መነኩሳቱ ድክመቶቻቸውን ለማሸነፍ የሚያስችል መንፈሳዊ እርዳታ ለማግኘት እርስ በርሳቸው ኃጢአታቸውን ይናዘዙ ነበር። በአዲሱ የሹክታ ኑዛዜ ግን “ኃጢአትን የማስተሰረይን ትልቅ ሥልጣን” ቤተክርስቲያኗ ለቄሶች ሰጥታለች።—አዲሱ የካቶሊክ ኢሳይክሎፔዲያ
ኢየሱስ ከተከታዮቹ ለአንዳንዶቹ እንዲህ ዓይነቱን ሥልጣን በእርግጥ ሰጥቶ ነበርን? አንዳንዶችን ወደዚህ መደምደሚያ የመራ ኢየሱስ የተናገረው ምን ነገር አለ?
“የመንግሥቱ ቁልፎች”
አንድ ጊዜ ኢየሱስ ለሐዋርያው ጴጥሮስ “የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ። በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ ምድር የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል” ብሎት ነበር። (ማቴዎስ 16:19) ኢየሱስ “የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻዎች” ወይም የመንግሥተ ሰማያት ቁልፎች ሲል ምን ማለቱ ነበር? ኢየሱስ “መክፈቻ” ወይም ቁልፍ የሚለውን ቃል የተጠቀመበትን ሌላ ቦታ ብንመለከት ምን ማለቱ እንደሆነ በተሻለ ሁኔታ ይገባናል።
ኢየሱስ የሙሴ ሕግ ዕውቀት ለነበራቸው የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች “እናንተ ሕግ አዋቂዎች የዕውቀትን መክፈቻ ስለወሰዳችሁ ወዮላችሁ ራሳችሁ አልገባችሁም የሚገቡትንም ከለከላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ሉቃስ 11:52) ሌሎችን የት እንዳይገቡ ነው የከለከሉት? በማቴዎስ 23:13 ላይ ኢየሱስ እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።” እውነትም የአይሁድ ካህናት ብዙዎችን በሰማይ ከኢየሱስ ጋር የመሆንን መብት በማሳጣት በሩን ዘግተውባቸዋል። እነዚያ የሃይማኖት መሪዎች የወሰዱት “ቁልፍ” ኃጢአትን ይቅር ከማለት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ቁልፉ ከአምላክ የሚገኘው እውቀት ነበር።
በተመሳሳይም ለጴጥሮስ የተሰጡት መክፈቻዎች የማን ኃጢአት ይቅር እንዲባልለት ወይም እንዲያዝበት ለአምላክ ለማስታወቅ ያለውን ስልጣን አያመለክቱም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ሰጠሹን እውቀት ጴጥሮስ በአገልግሎቱ አማካኝነት በማሰራጨት ወደ ሰማይ የሚወስደውን መንገድ የመክፈት ታላቅ መብቱን ያመለክታሉ። ይህንንም በመጀመሪያ ለአይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነትም ለተለወጡት ከዚያም ለሳምራውያን በመጨረሻም ላልተገረዙ አሕዛብ ሠርቶበታል።—ሥራ 2:1-41፤ 8:14-17፤ 10:1-48
“በምድር የምታሥሩት ሁሉ”
ኢየሱስ ለጴጥሮስ የነገረውን በኋላ ለሌሎች ደቀመዛሙርትም ነግሯቸዋል፦ “በምድር የምታሥሩት ሁሉ በሰማይ የታሠረ ይሆናል። በምድር የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።” (ማቴዎስ 18:18) እዚህ ላይ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ምን ዓይነት የውክልና ሥልጣን ነው የሰጣቸው? በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያመለክተው ኢየሱስ በግለሰብ አማኞች መካከል የሚነሳ አለመግባባት ስለመፍታትና ጉባኤውንም ንስሐ ከማይገቡ ክፉ አድራጊዎች ስለማጽዳት እየተናገረ ነበር።—ማቴዎስ 18:15-17
የአምላክን ሕግ በከባድ ሁኔታ መጣስን በሚመለከቱ ጉዳዮች ግን በጉባኤው ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ጉዳዮቹን ሊያመዛዝኑና አንድ በደለኛ ሰው “መታሠር” (እንደ ጥፋተኛ መታየት) ወይም “መፈታት” (ከጥፋተኛነት ነፃ መሆን) እንዳለበት መወሰን ይኖርባቸዋል። ይህ ማለት ሰማይ የሰዎችን ውሳኔ ይከተላል ማለት ነውን? አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪ የሆኑት ሮበርት ያንግ እንዳመለከቱት በደቀመዛሙርቱ የሚደረግ ማንኛውም ውሣኔ በሰማይ የሚደረገውን ውሣኔ ይከተላል እንጂ አይቀድምም። ቁጥር 18 ቃል በቃል እንደሚከተለው መነበብ አለበት ይላሉ፦ “በምድር የምታሥሩት በሰማይ የታሠረውን መሆን አለበት።”
በእርግጥም ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች የሚደረግ ማንኛውም ውሣኔ በሰማያዊ ፍርድ ቤት ባሉትም ይጸናል ብሎ ማሰብ ምክንያተቢስ ነው። ከዚህ ይልቅ ክርስቶስ የሾማቸው ተወካዮች ጉባኤውን በንጽህና ለመጠበቅ የሱን መመሪያ ይከተላሉ ማለት የበለጠ ምክንያታዊ ነው። ይህንም የሚያደርጉት በሰማይ በተወሰኑት መሠረታዊ ሥርዓቶች መሠረት ውሣኔ በማድረግ ነው። ይህን ለማድረግም ኢየሱስ ራሱ ይመራቸዋል።—ማቴዎስ 18:20
አንድ ሰው የሌላውን ሰው ዘላለማዊ ዕድል እስከመወሰን ድረስ “እንደ አባታዊ ዳኛ ሆኖ ክርስቶስ ሊወክል” ይችላልን?(አዲሱ የካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ) ምንም እንኳን “(በካቶሊክ የሃይማኖት ሊቃውንት ዘንድ) በቃላት ባይገልጹትም በበደሉ በእውነት የሚያዝን ሰው እጅግ ጥቂት መሆኑን ቢያምኑም “ኑዛዜን የሚሰሙ ቀሳውስት እከሌ ከእከሌ ሳይሉ ፍታት ይሰጣሉ።” (አዲሱ ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ) በእርግጥም አንድ ቄስ ፍታት መስጠት ወይም ኃጢአተኛን ይቅር ማለት እምቢ ሲል ተሰምቶ የሚታወቀው መቼ ነው? ይህ ሊሆን የሚችለው አንድ ግለሰብ ቄስ ኃጢአተኛው ከልብ ይጸጸት አይጸጸት ለመወሰን የማይችል ስለማይመስለው ሳይሆን አይቀርም። እንዲህ ከሆነስ ፍታት ለመስጠት ስልጣን አለኝ ለምን ይላል?
አንድ ርህሩህ ዳኛ ወንጀለኞችን እንዲያውም የማይታረሙ ልማደኛ ሕግ አፍራሾችን ሳይቀር በወንጀላቸው እንዳዘኑ በሚገልጹበት ሥነ ሥርዓት ስለተሳተፉ ብቻ አዘውትሮ በነፃ ስለሚለቅበት አንድ የሕግ ችሎታ እስቲ አስብ። ይህ ሁኔታ ክፉ አድራጊዎቹን ሊያስደስት ቢችልም እንዲህ ዓይነቱ የተሳሳተ የምሕረት አመለካከት ለፍትሕ ሊኖር የሚገባውን አክብሮት በጥብቅ ያመነምነዋል። ታዲያ በካቶሊክ ቤተክርሰቲያን የሚደረገው ዓይነት የኃጢአት ኑዛዜ ሰዎችን በኃጢአት መንገድ እንዲጸኑ በእርግጥ አያጠነክራቸውምን?—መክብብ 8:11
“ኑዛዜ ያን ኃጢአት ለወደፊቱ ላለመድገም የመሞከርን ዝንባሌ አያስገኝም” ትላለች ሮማና ከሰባት ዓመት ዕድሜዋ ጀምራ እንደ አንዲት ካቶሊካዊት መጠን ስታደርገው በነበረው በራሷ የመናዘዝ ተሞክሮ ላይ በመመርኮዝ። ጨምራ “ኃጢአትን መናዘዝ አምላክ ምንጊዜም ይቅር ባይ እንደሆነና ፍጹም ያልሆነው ሥጋችሁ እንድታደርጉ የሚመራችሁን ሁሉ ይቅር ይላል የሚለውን ሐሳብ ያሳድራል። ትክክል የሆነውን ለማድረግ ጥልቅ ምኞትን አያሳድርም” ብላለች።a
በዮሐንስ 20:22, 23 ላይ የተመዘገቡት የኢየሱስ ቃላትስ? እዚያ ላይ ለደቀመዛሙርቱ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል። የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል” ብሎ ነግሮአቸዋል። እዚህ ላይ ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን ለይቶ መስጠቱ አይደለምን?
ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ ለብቻው ተነጥሎ ሲታይ እንደዚያ የሚል ይመስላል። ይሁን እንጂ እነዚህ ቃላት በማቴዎስ 18:15-18 እና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኃጢአት ኑዛዜና ይቅርታ ስለ ማድረግ ከሚያስተምራቸው ሌሎች ነገሮች ሁሉ አንጻር ሲታይ ምን ብለን መደምደም አለብን? ኢየሱስ በዮሐንስ 20:22, 23 ንስሐ የማይገቡ ከባድ ኃጢኣት ፈጻሚዎችን ከጉባኤው ለማውጣት ለደቀመዛሙርቱ ሥልጣን መስጠቱ ነው። የዚያኑ ያህልም ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ለተጸጸቱ ኃጢአተኞች ምህረት እንዲያደርጉና ይቅር እንዲሉ ሥልጣን ሰጥቷል። ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱ ማንኛውም ኃጢአት ለቄስ መናዘዝ አለባቸው ብሎ መናገሩ እንዳልነበረ አያጠራጥርም።
በጉባኤው ውስጥ ያሉት ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ከባድ ኃጢአት የሚሠሩትን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው በዚህ መንገድ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። እንዲህ ዓይነቶቹ ውሣኔዎችም የሚደረጉት በአምላክ መንፈስ ቅዱስ መሪነትና በኢየሱስ ክርስቶስና በቅዱሳን ጽሑፎች አማካኝነት ከተሰጡት መመሪያዎች ጋር በመስማማት ነው። (ከሥራ 5:1-5፤ ከ1 ቆሮንቶስ 5:1-5, 11-13 ጋር አወዳድር) እነዚያ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ለሚያደርጉት ውሣኔ ከሰማይ የሚሰጠውን መመሪያ ይከተላሉ እንጂ ሰማይ ውሣኔያቸውን እንዲቀበል አያስገድዱም።
“እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ”
ታዲያ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ኃጢአታቸውን ለመናዘዝ ተገቢው ጊዜ መቼ ነው? ለየጥቃቅኑ ድክመት ሳይሆን ከባድ ኃጢአት በሚፈጸምበት ጊዜ ግለሰቡ ኃላፊነት ላላቸው የጉባኤው የበላይ ተመልካቾች መናዘዝ አለበት። ኃጢአቱ ከፍተኛ ባይሆንም ሕሊናው ከመጠን በላይ ከረበሸው መናዘዙና መንፈሳዊ ዕርዳታ መፈለጉ ታላቅ ጥቅም አለው።
ይህን በሚመለከት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ ያዕቆብ እንዲህ ይላል፦ “ከእናንተ (በመንፈሳዊ) የታመመ ማንም ቢኖር የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎችን ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል፤ ጌታም ያስነሳዋል። ኃጢአትንም ሠርቶ እንደሆነ ይሰረይለታል። እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ፤ እያንዳንዳችሁ ስለሌላው ይጸልይ።”—ያዕቆብ 5:14-16
በእነዚህ ቃላት ውስጥ መደበኛ የሆነ ሥነ ሥርዓትን የሚከተል ኃጢአትን ጆሮ ላይ ሹክ በማለት የመናዘዝ ሐሳብ አይገኝም። ከዚህ ይልቅ አንድ ክርስቲያን መጸለይ እንደማይችል እስኪሰማው ድረስ የኃጢአት ሸክም ሲጫነው የጉባኤውን የተሾሙ ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች ከሱ ጋር እንዲጸልዩ ሊጠራ ይገባዋል ማለት ነው። በመንፈስ እንዲያገግም ለመርዳት የአምላክን ቃል ዘይት ይጠቀማሉ።—መዝሙር 141:5፤ ከሉቃስ 5:31, 32 እንዲሁም ከራእይ 3:18 ጋር አወዳድር።
እዚህ ላይ ሊታወስ የሚገባው “ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” ያለው የዮሐንስ መጥምቁ ምክር ነው። (ማቴዎስ 3:8 ከሥራ 26:20 ጋር አወዳድር) በእውነት የተጸጸተ ኃጢአተኛ የኃጢአተኛነት መንገዱን ይተዋል። በደሉን ለአምላክ የሚናዘዝ የተጸጸተ ኃጢአተኛ ልክ እንደ ጥንቱ እሥራኤል ንጉሥ እንደ ዳዊት ምህረትን ይቀበላል። ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ኃጢአቴን ላንተ አስታወቅሁ። በደሌንም አልሸፈንኩም [ለይሖዋ (አዓት)] መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ። አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ።”—መዝሙር 32:5
ባሕላዊ የንስሐ ቅጣቶች እንዲህ ዓይነቱን ይቅርታ አያስገኙም። ይቅርታ የሚሰጠው አምላክ ብቻ ነው። እርሱም ፍጹም ፍትሕ የሚጠይቀውን ሁሉ ከግምት ያስገባል፤ ይሁን እንጂ ምህረቱ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅሩን ይገልጻል። እንዲሁም የሱ ምህረት በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕትነት ላይ የተመሠረተው የማይገባን ደግነቱ መግለጫ ነው። ይህ ምህረት የሚዘረጋውም በአምላክ አመለካከት መጥፎ ከሆነው ለተመለሱት የተጸጸቱ ኃጢአተኞች ነው። (መዝሙር 51:7፤ ኢሳይያስ 1:18፤ ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 3:23-26) በይሖዋ አምላክ ይቅር የተባሉ ብቻ ናቸው የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት። እንዲህ ዓይነቱን ምህረት ለመቀበልም በሰው መንገድ ሳይሆን በአምላክ መንገድ መናዘዝ አለብን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህን አቋም ከማርቆስ 3:29ና ከዕብራውያን 6:4-6፤ 10:26 ጋር አወዳድር።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳዊት ኃጢአቱን ለይሖዋ ተናዘዘ፤ እርሱም ይቅር አለለት