ሴኬም—በሸለቆ ውስጥ የምትገኝ ከተማ
ሴኬም አምላክ ለሕዝቦቹ በመረጠው ምድር እምብርት በጌባልና በገሪዛን ተራራ መሃል ባለ አመቺ ስፍራ የምትገኝ ከተማ ነች። ከአራት ሺህ ዓመታት ያህል በፊት ይሖዋ ለአብርሃም “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” ሲል ቃል የገባለት እዚህ ቦታ ነበር።— ዘፍጥረት 12:6, 7
ከዚህ የተስፋ ቃል ጋር በመስማማት የአብርሃም የልጅ ልጅ የሆነው ያዕቆብ በሴኬም ከሰፈረ በኋላ “አምላክ የእስራኤል አምላክ ነው” ተብሎ የሚጠራ አንድ መሠዊያ ሠራ። ያዕቆብ ለቤተሰቡና ለከብቶቹ የሚሆን ውኃ ለማግኘት እዚህ ቦታ የውኃ ጉድጓድ ሳይቆፍር አይቀርም። ይህ የውኃ ጉድጓድ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ “የያዕቆብ ጒድጓድ” ተብሎ ተጠርቷል።— ዘፍጥረት 33:18-20 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ፤ ዮሐንስ 4:5, 6, 12
ሆኖም የያዕቆብ ቤተሰብ አባላት በሙሉ ለእውነተኛ አምልኮ ቅንዓት አላሳዩም። ሴት ልጁ ዲና በሴኬም ከሚገኙ ከነዓናውያን ልጃገረዶች መካከል ጓደኞች ለማግኘት ጥረት አድርጋለች። ገና ልጅ የነበረችው ዲና ከቤተሰቧ ተለይታ በአቅራቢያቸው ባለችው ከተማ ውስጥ ወዳሉ ወጣቶች በመሄድ ጓደኞች ማበጀት ጀመረች።
ዘወትር ወደ ከተማቸው የምትመጣውን (ብቻዋን ሳይሆን አይቀርም) ይህችን ድንግል ወጣት በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ወጣት ወንዶች እንዴት ተመለክተዋት ይሆን? የአገሩ አለቃ ልጅ “አያት፤ ወሰዳትም ከእርስዋም ጋር ተኛ፣ አስነወራትም።” ዲና ሥነ ምግባር ከጎደላቸው ከነዓናውያን ጋር በመዋል በራስዋ ላይ ችግር የፈጠረችው ለምን ነበር? በእሷ ዕድሜ ካሉ ልጃገዶች ጋር አብራ ለመዋል በመፈለጓ ምክንያት ነበርን? እንደ አንዳንዶቹ ወንድሞቿ ሁሉ ግትርና በራሷ ሐሳብ የምትመራ ነበረችን? የዘፍጥረትን መጽሐፍ ዘገባ አንብብና ልጃቸው ወደ ሴኬም መሄዷ ባስከተለባቸው አሳዛኝ ውጤቶች ምክንያት ያዕቆብና ልያ የተሰማቸውን ጭንቀትና ሐፍረት ለመረዳት ሞክር።— ዘፍጥረት 34:1-31፤ 49:5-7፤ በተጨማሪም ሰኔ 15, 1985 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 31 ተመልከት።
ከ300 ዓመታት ገደማ በኋላ ቲኦክራሲያዊ መመሪያዎችን መናቅ የሚያስከትለው ውጤት እንደገና በግልጽ ታይቷል። ኢያሱ በእስራኤል ታሪክ ውስጥ ሲታወስ የሚኖር አንድ ስብሰባ በሴኬም ውስጥ አዘጋጅቶ ነበር። በዚህ ሸለቆ ውስጥ የነበረውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ከስድስት የእስራኤል ነገዶች የተውጣጡ ከአንድ ሚልዮን በላይ የሆኑ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በገሪዛን ተራራ ፊት ለፊት ቆመዋል። ከሸለቆው ማዶ ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ሌሎቹ ስድስት የእስራኤል ነገዶች በጌባል ተራራ ፊት ለፊት ቆመዋል።a በተጨማሪም ከታች በቃል ኪዳኑ ታቦት አጠገብ በሁለት ወገን በተሰበሰቡት እስራኤላውያን መሃል ካህናቱና ኢያሱ ቆመዋል። እንዴት ያለ አስደሳች መቼት ነው!— ኢያሱ 8:30-33
ከእነዚህ እጅግ ብዙ የሆኑ ሰዎች በላይ ከፍ ብለው የሚታዩት ሁለት ተራራዎች ፈጽሞ ተቃራኒ የሆነ ውበትና ምድረ በዳነት ይታይባቸው ነበር። ገሪዛን አረንጓዴና ለምለም ሆኖ ሲታይ ጌባል ግን በአብዛኛው አመድማና የተራቆተ ነው። እስራኤላውያን ኢያሱ እስኪናገር ድረስ እየተጠባበቁ እርስ በርሳቸው በደስታ ሲነጋገሩ በዓይነ ሕሊናህ ይታይሃል? በዚህ ተፈጥሮአዊ የስብሰባ ቦታ እያንዳንዱ ድምፅ ያስተጋባል።
ኢያሱ ‘የሙሴን ሕግ መጽሐፍ’ ባነበበበት ከአራት እስከ ስድስት ሰዓት በሚያህል ጊዜ ውስጥ ሕዝቡም ይሳተፍ ነበር። (ኢያሱ 8:34, 35) እያንዳንዱ በረከት ከተነበበ በኋላ በገሪዛን ተራራ ፊት ለፊት ያሉት እስራኤላውያን አሜን! ያሉ ሲሆን በጌባል ተራራ ፊት ለፊት ያሉት ደግሞ እያንዳንዱን እርግማን አሜን! በማለት ጠበቅ አድርገው ይገልጻሉ። የጌባል ተራራ ጠፍ መሆን ሕዝቡ አለመታዘዝ የሚያመጣባቸውን አስከፊ ሁኔታ እንዲያስታውሱ ሳያደርጋቸው አይቀርም።
ኢያሱ “አባቱን ወይም እናቱን የሚያቃልል ርጉም ይሁን” ሲል አስጠንቅቋል። ከአንድ ሚልዮን በላይ የሆኑ ሰዎች በኅብረት “አሜን!” ብለው መለሱ። ኢያሱ ይህ ነጎድጓዳማ ድምፅ ፀጥ እስኪል ድረስ ከጠበቀ በኋላ “የባልንጀራውን የድንበር ምልክት የሚገፋ ርጉም ይሁን” ሲል ይቀጥላል። እንደገና ስድስቱ ነገዶች ከአያሌ መጻተኞች ጋር ሆነው “አሜን!” ብለው ይጮሃሉ። (ዘዳግም 27:16, 17) እዚያ ቦታ ብትኖር ኖሮ በሁለቱ ተራሮች መካከል የተካሄደውን ይህን ስብሰባ ትረሳው ነበርን? በአእምሮህ ውስጥ የመታዘዝ አስፈላጊነት በማይፋቅ ሁኔታ ይጻፍ አልነበረምን?
ይህ ከሆነ ከ20 ያህል ዓመታት በኋላ ኢያሱ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ውሳኔያቸውን ለማጠናከር ሕዝቡን እንደገና በሴኬም ሰበሰበ። ሁሉም ሰው ማድረግ ያለበትን ምርጫ በፊታቸው አስቀመጠላቸው። “የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] እናመልካለን” አላቸው። (ኢያሱ 24:1, 15) ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው በሴኬም ያደረጓቸው እነዚህ እምነት የሚያጠነክሩ ስብሰባዎች በእነሱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል። እስራኤላውያን ኢያሱ ከሞተ በኋላ ለብዙ ዓመታት የእሱን የታማኝነት ምሳሌ ኮርጀዋል።— ኢያሱ 24:31
ይህ ከሆነ ከ15 መቶ ዘመናት በኋላ ኢየሱስ ከገሪዛን ተራራ ግርጌ በሚገኝ አንድ ቦታ ተቀምጦ አስደሳች ውይይት አድርጓል። ኢየሱስ ረጅም ጉዞ በማድረጉ ምክንያት ደክሞት ስለ ነበር የውኃ እንስራ የተሸከመች አንዲት ሳምራዊት ሴት ስትመጣ በያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ ተቀምጦ ነበር። አይሁዳውያን በሳምራውያን ዕቃ ውኃ ሊጠጡ ይቅርና ፈጽሞ ስለማይነጋገሩ ኢየሱስ ውኃ እንድታጠጣው ሲጠይቃት ሴትዮዋ በጣም ተገረመች። (ዮሐንስ 4:5-9) ኢየሱስ ቀጥሎ የተናገራቸው ቃላት ከዚህ የበለጠ አስገርመዋታል።
“ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፣ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል።” (ዮሐንስ 4:13, 14) ከዚህ ጥልቅ የውኃ ጉድጓድ ውኃ መቅዳት አድካሚ ሥራ ስለ ነበር ሴትዮዋ ኢየሱስ የገባላትን ቃል ለማግኘት ምን ያህል ፍላጎት እንደነበራት ገምት። ከዚህም በተጨማሪ ታሪካዊ ጠቀሜታ ቢኖራቸውም እንኳ ኢየሩሳሌምም ሆነች የገሪዛን ተራራ ወደ አምላክ ለመቅረብ የግድ አስፈላጊ የሆኑ ሃይማኖታዊ ቦታዎች እንዳልሆኑ ገለጸላት። ተፈላጊው ነገር የልብ ዝንባሌና አኗኗር እንጂ ቦታው አይደለም። ኢየሱስ “እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት ያመልኩታል” ብሏል። “በእርግጥም አብ እንደ እነዚህ ያሉትን እየፈለገ ነው።” (ዮሐንስ 4:23 NW) እነዚህ ቃላት ምንኛ የሚያጽናኑ ነበሩ! ይህ ሸለቆ እንደገና ሰዎች ይሖዋን እንዲያገለግሉ ማበረታቻ ያገኙበት ቦታ ሆነ።
በዛሬው ጊዜ የናቡለስ ከተማ በጥንታዊቷ ሴኬም ፍርስራሽ አጠገብ ትገኛለች። አሁንም ቢሆን የገሪዛንና የጌባል ተራራዎች ቀደም ሲል ለተከናወኑት ድርጊቶች ምሥክር ሆነው በሸለቆው ውስጥ ጎልተው ይታያሉ። ከተራሮቹ ግርጌ የሚገኘው የያዕቆብ ጉድጓድ እስካሁን ድረስ ሊጎበኝ ይችላል። እዚህ ቦታ የተከናወኑትን ድርጊቶች ስናሰላስል ኢያሱና ኢየሱስ እንዳስተማሩን እውነተኛውን አምልኮ ከፍ ከፍ የማድረግን አስፈላጊነት እናስታውሳለን።— ከኢሳይያስ 2:2, 3 ጋር አወዳድር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በገሪዛን ተራራ ፊት ለፊት የቆሙት ስድስት ነገዶች ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዮሴፍና ብንያም ነበሩ። በጌባል ተራራ ፊት ለፊት የቆሙት ስድስት ነገዶች ደግሞ ሮቤል፣ ጋድ፣ አሴር፣ ዛብሎን፣ ዳንና ንፍታሌም ነበሩ።— ዘዳግም 27:12, 13
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (የቅርብ ምሥራቅ ታሪክ) Est.