የዓለምን ብርሃን ተከተሉ
“የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል።” — ዮሐንስ 8:12
1. የብርሃን አስፈላጊነት ምን ያህል ነው?
ብርሃን ባይኖር ኖሮ ምን ለማድረግ እንችል ነበር? ከዓመት እስከ ዓመት በየዕለቱ ስንነቃ የ24 ሰዓታት ጨለማ ቢሆን ምን ሊመስል ይችል እንደነበር እስቲ አስበው። ብርሃን ከሌለ ቀለም ስለማይኖር ቀለም የሌለበት ዓለም ምን ሊመስል እንደሚችል ገምት። ብርሃን ባይኖር ኖሮ እኛም በሕይወት ለመኖር አንችልም ነበር! ለምን? ምክንያቱም አረንጓዴ ተክሎች ፎቶ ሲንተሲስ በሚባለው አሠራር አማካኝነት የምንመገበውን ምግብ ማለትም አዝርእትን፣ አታክልትንና ፍራፍሬዎችን ሲያዘጋጁ የሚጠቀሙት በብርሃን ነው። እውነት ነው፤ አንዳንድ ጊዜ የእንስሳትን ሥጋ እንበላለን። ይሁን እንጂ እነዚያ እንስሳት የሚመገቡት አትክልትን ወይም አትክልት ተመጋቢ የሆኑ ሌሎች እንስሳትን ነው። ስለዚህ ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ በብርሃን ላይ የተመካ ነው።
2. ምን ኃይለኛ የብርሃን ምንጮች አሉ? ይህስ ስለ ይሖዋ ምን ይነግረናል?
2 ብርሃናችን የሚመጣው ኮከብ ከሆነችው ከፀሐይ ነው። ፀሐያችን በጣም ከፍተኛ መጠን ያለው ብርሃን የምትሰጥ ብትሆንም እንኳን መካከለኛ መጠን ያላት ኮከብ ነች። ብዙዎቹ ከዋክብት ከፀሐይ በጣም ይበልጣሉ። እኛ የምንኖርበት ሚልኪዌይ የሚባለው ጋላክሲ ወይም የከዋክብት ረጨት ከመቶ ቢልዮን የሚበልጡ ከዋክብትን ይዟል። ከዚህ በተጨማሪ በጽንፈ ዓለም ውስጥ በቢልዮኖች የሚቆጠሩ በጣም ብዙ ጋላክሲዎች (የከዋክብት ረጨቶች) አሉ። ምንኛ የሚያስደንቅ የከዋክብት ጭፍራ ነው! ከእነዚህ ከዋክብት የሚፈነጠቀው ብርሃን ምንኛ ታላቅ ነው! እነዚህን ሁሉ የፈጠረው ይሖዋ እንዴት ያለ ታላቅ የብርሃን ምንጭ ነው! ኢሳይያስ 40:26 “ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም” ሲል ይገልጻል።
ሌላ ዓይነት ብርሃን
3. ከይሖዋ የሚመጣው መንፈሳዊ ብርሃን ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
3 ይሖዋ መንፈሳዊ የማየት ችሎታና ማስተዋል እንዲኖረን የሚያስችለን የሌላ ዓይነት ብርሃንም ምንጭ ነው። አንድ መዝገበ ቃላት “ኢንላይትን” የተባለውን የእንግሊዝኛ ቃል “እውቀት፣ የተግባር መመሪያና መንፈሳዊ ማስተዋል መስጠት” በማለት ይተርጉመዋል። “ኢንላይትንድ” የተባለውን ቃል ደግሞ “ከድንቁርና እና ከተሳሳተ እውቀት ነፃ መሆን” የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። ከይሖዋ የሚመጣው መንፈሳዊ ብርሃን ለእኛ የሚደርሰን ከቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ በሚገኘው ትክክለኛ እውቀት አማካኝነት ነው። አምላክ ማን እንደሆነና ዓላማዎቹ ምን እንደሆኑ ለማወቅ የሚያስችለን ይህ ትክክለኛ እውቀት ነው። “በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ:- በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና።” (2 ቆሮንቶስ 4:6) ስለዚህ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው እውነት ከድንቁርናና ከተሳሳተ እውቀት ነፃ ያወጣናል። ኢየሱስ “እውነትን ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ብሏል። — ዮሐንስ 8:32
4, 5. ከይሖዋ የሚመጣው እውቀት ለሕይወታችን እንደ ብርሃን ሆኖ ሊያገለግለን የሚችለው እንዴት ነው?
4 የእውነተኛው መንፈሳዊ ብርሃን ምንጭ የሆነው ይሖዋ “በእውቀት ፍጹም” ነው። (ኢዮብ 37:16) በተጨማሪም መዝሙር 119:105 ስለ አምላክ ሲናገር “ሕግህ [ቃልህ አዓት ] ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴ ብርሃን ነው” ይላል። ስለዚህ ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ ቀጥሎ የምንወስደውን እርምጃ ብቻ ሳይሆን ወደፊት የምንሄድበትንም ጎዳና በመንፈሳዊ ሊያበራልን ይችላል። ከዚህ ብርሃን ውጭ ብንኖር ሕይወት ጠመዝማዛና ተራራማ በሆነ መንገድ ላይ ምንም ዓይነት ብርሃን በሌለበት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ መብራት የሌለውን መኪና እንደመንዳት ያህል ይሆንብን ነበር። ከአምላክ የሚመጣው መንፈሳዊ ብርሃን የመኪናው የፊት መብራት ከሚሰጠው ብርሃን ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ብርሃኑ ጎዳናውን ስለሚያበራልን የምንሄድበትን አቅጣጫ አስተካክለን እንድንመለከት ያስችለናል።
5 በኢሳይያስ 2:2–5 ላይ ያለው ትንቢት በዘመናችን አምላክ እውነተኛውን አምልኮ ለመማርና በእርሱም ለመመላለስ ይችሉ ዘንድ መንፈሳዊ ብርሃን ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎችን ከአሕዛብ ሁሉ እየሰበሰበ እንዳለ ያሳያል። ቁጥር 3 “እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን” ይላል። ቁጥር 5 ደግሞ “ኑ፣ በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] ብርሃን እንሂድ” በማለት እውነት ፈላጊ የሆኑ ሰዎችን ይጋብዛቸዋል።
6. ከይሖዋ የሚመጣው ብርሃን በመጨረሻው ወዴት ይመራናል?
6 ስለዚህ ይሖዋ ለሕይወት የግድ አስፈላጊ የሆኑ የሁለት ዓይነት ብርሃናት ምንጭ ነው። እነርሱም ከግዑዝ አካላት የሚወጣው ብርሃንና መንፈሳዊ ብርሃን ናቸው። አካላዊው ብርሃን በአሁኑ ጊዜ አካላችን ምናልባት 70 ወይም 80 አለዚያም ከዚያ ትንሽ በለጥ ለሚሉ ዓመታት በሕይወት እንዲኖር ይረዳዋል። መንፈሳዊው ብርሃን ግን በገነቲቱ ምድር ወደሚገኝ ዘላለማዊ ሕይወት ይመራል። ሁኔታው ኢየሱስ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት እንደተናገረው ነው። — ዮሐንስ 17:3
በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ያለ ዓለም
7. ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ መንፈሳዊ ብርሃን የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
7 ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ መንፈሳዊ ብርሃን ያስፈልገናል። እንደ ማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 2 ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 3 ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ወደዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ በጣም እንደተቃረብን ያመለክታሉ። በዘመናችን የተፈጸሙት አሠቃቂ ሁኔታዎች እንደሚመጡ እነዚህም ሆኑ ሌሎች ትንቢቶች አስቀድመው በመናገር “በመጨረሻው ቀን” ውስጥ እንደምንገኝ አሳውቀውናል። በእነዚህ ትንቢቶች በትክክል እንደተነገረው ይህ መቶ ዘመን እልቂትና መከራ የተፈራረቁበት ሆኗል። ወንጀልና ሽብር ፈጠራ አስፈሪ ወደሆነ ደረጃ አድገዋል። ጦርነቶች ከአንድ መቶ ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል። እንደ አስፈሪው ኤድስ ያሉ በሽታዎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እየቀሠፉ ናቸው። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ እስከ ዛሬ ድረስ 160,000 የሚያክሉ ሰዎች በኤድስ ሞተዋል። የቤተሰብ አንድነት ፈራርሷል፤ የጾታ ሥነ ምግባርም ጊዜ እንዳለፈበት ተደርጎ ይታያል።
8. በአሁኑ ጊዜ በሰው ልጆች ፊት የተደቀነው ሁኔታ ምንድን ነው? ለምንስ?
8 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞው ዋና ጸሐፊ ሀቬር ፔሬዝ ዴኴያር እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ድኅነት የኅብረተሰቦችን አንድነትና ውሕደት እያዳከመ መሆኑን የዓለም ሁኔታ ከፍተኛ ማረጋገጫ ይሰጣል።” “በአሁኑ ጊዜ ከአንድ ቢልዮን የሚበልጡ ሰዎች የሚኖሩት ፍጹም በሆነ ድኅነት ውስጥ ነው” እንዲሁም “ረሀብ ለረብሻና ለውጊያ መባባስ መንሥኤ ሆኗል” በማለት አስገንዝበዋል። እነዚህ “አስፈሪ መከራዎች በመንግሥታት ጥረት ሊፈወሱ የማይችሉ ናቸው” ብለዋል። ተደማጭነት ያለው የአንድ ድርጅት መሪ “በአሁኑ ጊዜ በኅብረተሰቦች ፊት የተደቀነው ዋነኛ ችግር ኅብረተሰብ ሊገዛ የማይቻል መሆኑ ነው” ሲሉ ደምድመዋል። “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ” የሚለው የመዝሙር 146:3 ቃል ምን ያህል እውነት ነው!
9. የሰው ልጆችን ለዋጠው ጨለማ ይበልጥ ተጠያቂ የሆኑት እነማን ናቸው? ከዚህ ኃይልና ግፊት ሊገላግለን የሚችለው ማን ነው?
9 ዛሬ ያለው ሁኔታ በኢሳይያስ 60:2 ላይ “እነሆ፣ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል” ተብሎ አስቀድሞ እንደተነገረው ነው። ይህ አብዛኛውን የምድር ነዋሪ የሸፈነው ድቅድቅ ጨለማ የመጣው ሰዎች ከይሖዋ የሚገኘውን መንፈሳዊ ብርሃን ስለማይቀበሉ ነው። ለዚህ መንፈሳዊ ጨለማ መንስዔ የብርሃን አምላክ ዋነኛ ጠላቶች የሆኑት ሰይጣን ዲያብሎስና አጋንንቱ ናቸው። “የዚህ የጨለማ ዓለም ገዢዎች” እነርሱ ናቸው። (ኤፌሶን 6:12) 2 ቆሮንቶስ 4:4 እንደሚለው ዲያብሎስ “የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው” የማያምኑትን ሰዎች አሳብ ያሳወረ ‘የዚህ የነገሮች ሥርዓት አምላክ’ ነው። የሰይጣንን ኃይልና ግፊት ሊያስቀር የሚችል ሰብዓዊ አገዛዝ አይገኝም። ይህን ሊያደርግ የሚችለው አምላክ ብቻ ነው።
“ታላቅ ብርሃን”
10. በዘመናችን ብርሃን በሰው ልጆች ላይ እንደሚፈነጥቅ ኢሳይያስ አስቀድሞ የተናገረው እንዴት ነው?
10 አብዛኛው የሰው ዘር በከባድ ጨለማ የተዋጠ ቢሆንም በኢሳይያስ 60:2, 3 ላይ የአምላክ ቃል እንዲህ በማለት ይተነብያል:- “ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ . . . ይመጣሉ።” ይህም መንፈሳዊ ብርሃን ያገኘው የይሖዋ እውነተኛ አምልኮ በዚህ በመጨረሻው ቀን ጸንቶ እንደሚቋቋም ተስፋ ከሚሰጠው የኢሳይያስ ምዕራፍ 2 ትንቢት ጋር የሚስማማ ነው። በቁጥር 2 እና 3 ላይ እንደተገለጸው “አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ። . . . ብዙዎች አሕዛብ ሄደው:- ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር [ወደ ይሖዋ አዓት] ተራራ . . . እንውጣ፤ . . . ይላሉ።” ይህ ተራራ ከፍ ከፍ ያለው የይሖዋ እውነተኛ አምልኮ ነው። ስለዚህ ምንም እንኳን ዓለም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ቢሆንም የአምላክ ብርሃን በሰው ልጆች መካከል እየፈነጠቀ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከጨለማ እንዲወጡ በማድረግ ላይ ነው።
11. ከማንም ይበልጥ የይሖዋን ብርሃን እንደሚያንጸባርቅ የተነገረለት ማን ነበር? ስምዖንስ እርሱን ለይቶ ያሳወቀው እንዴት ነው?
11 በኢሳይያስ 9:2 ላይ ያለው ትንቢት አምላክ ብርሃኑን እንዲያንጸባርቅ የሚያደርግ አንድ ሰው ወደ ዓለም እንደሚልክ በቅድሚያ ተናግሮ ነበር። ትንቢቱ “በጨለማ የሄደ ሕዝብ [ታላቅ አዓት] ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው” ሲል ይገልጻል። ይህ “ታላቅ ብርሃን” የይሖዋ ቃል አቀባይ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ብሏል። (ዮሐንስ 8:12) ኢየሱስ ገና ሕፃን በነበረበት ጊዜም እንኳን ይህን የተረዱ ሰዎች ነበሩ። ሉቃስ 2:25 ስምዖን የተባለ አንድ ሰው ‘ጻድቅና ሰው ትጉህ’ እንዲሁም “መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ” የነበረበት ሰው እንደነበረ ይናገራል። ስምዖን ሕፃኑን ኢየሱስን ባየ ጊዜ ለአምላክ እንዲህ ሲል ጸለየ:- “ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን [መሸፈኛውን አዓት] የሚገልጥ ብርሃን . . . ነው።” — ሉቃስ 2:30–32
12. ኢየሱስ ሰዎችን የሸፈነውን የጨለማ መጋረጃ ማንሳት የጀመረው መቼና እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ ከተጠመቀ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሰው ልጆችን የሸፈነውን የጨለማ ግርዶሽ ማስወገድ ጀመረ። ይህም በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ በሚመላለሱ ሰዎች ላይ ስለሚያበራው “ታላቅ ብርሃን” የሚናገረውን የኢሳይያስ 9:1 እና 2ን ትንቢት እንደፈጸመው ማቴዎስ 4:12–16 ይነግረናል። ማቴዎስ 4:17 እንዲህ ይላል:- “ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ:- መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር።” ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች ለሰዎች በመስበክ ስለ አምላክ ዓላማዎች የሚገልጸውን መንፈሳዊ ብርሃን አበራላቸው። እርሱ “በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል።” — 2 ጢሞቴዎስ 1:10 (በ1954 በታተመው አማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቁጥር 11)
13. ኢየሱስ ራሱን የገለጸው እንዴት ነው? እንዲህ ባለ እርግጠኛነት ራሱን ሊገልጽ የቻለውስ ለምን ነበር?
13 ኢየሱስ የአምላክን ብርሃን በታማኝነት አንጸባርቋል። እንዲህ አለ:- “በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። . . . እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ። ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደሆነች አውቃለሁ።” — ዮሐንስ 12:44–50
“በእርሱ ሕይወት ነበረች”
14. ኢየሱስ በዮሐንስ 1:1, 2 ላይ እንዴት ተደርጎ ተገልጿል?
14 አዎን፤ ይሖዋ ልጁን የዘላለም ሕይወትን የሚያሳይ ብርሃን እንዲሆን ወደ ምድር ልኮታል። ይህም ጉዳይ በዮሐንስ 1:1–16 ላይ ዋና ሐሳብ ሆኖ እንዴት እንደተገለጸ ልብ በል። ቁጥር 1 እና 2 እንዲህ ይነበባል:- “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፣ ቃልም እግዚአብሔር [አምላክ አዓት] ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።” እዚህ ላይ ዮሐንስ ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ “ቃል” በሚል የማዕረግ ስም ጠርቶታል። ይህም ኢየሱስ የይሖዋ አምላክ ቃል አቀባይ በመሆን የፈጸመውን ተግባር ያመለክታል። ዮሐንስ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ” ሲል ቃል የይሖዋ የፍጥረት ሥራ መጀመሪያ ማለትም “በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ” መሆኑን ማመልከቱ ነበር። (ራእይ 3:14) በአምላክ ፍጥረታት መካከል ያለው የላቀ ደረጃ ኃያል የሆነ ‘አምላክ’ ተብሎ ለመጠራቱ እውነተኛ መሠረት ይሆናል። ኢሳይያስ 9:6 “ኃያል አምላክ” ቢለውም ሁሉን ቻይ አምላክ ብሎ ግን አይጠራውም።
15. ዮሐንስ 1:3–5 ስለ ኢየሱስ ምን ተጨማሪ መረጃ ይሰጠናል?
15 ዮሐንስ 1:3 “ሁሉ በእርሱ ሆነ፣ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” በማለት ይናገራል። ቆላስይስ 1:16ም “በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና” ይላል። ዮሐንስ 1:4 “በእርሱ ሕይወት ነበረች፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች” ይላል። ስለዚህ ሌሎቹ የሕይወት ዓይነቶች ሁሉ በቃል አማካይነት ተፈጥረዋል። በተጨማሪም አምላክ ኃጢአተኞችና ሟች የሆኑት የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ያስቻለው በልጁ አማካኝነት ነው። በእርግጥም ኢሳይያስ 9:2 “ታላቅ ብርሃን” ብሎ የጠራው ኃያል ኢየሱስ ነው። ዮሐንስ 1:5 “ብርሃንም በጨለማ ይበራል፣ ጨለማም አላሸነፈውም” ይላል። ስህተትንና ዓመፅን ከሚወክለው ከጨለማ ተቃራኒ በሆነ ሁኔታ ብርሃን ጽድቅንና እውነትን ይወክላል። በዚህ ምክንያት ዮሐንስ ጨለማው ብርሃኑን ሊያሸንፈው እንደማይችል አመልክቷል።
16. አጥማቂው ዮሐንስ የኢየሱስ ሥራ የሚኖረውን ስፋት የጠቆመው እንዴት ነበር?
16 አሁን ደግሞ ዮሐንስ ከቁጥር 6 እስከ 9 ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ አቀረበ:- “ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ [አጥማቂው] ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ። ስለ ብርሃን [ስለ ኢየሱስ] ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱ [ዮሐንስ] ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር።” ዮሐንስ የሚመጣውን መሲህ በመጠቆም ተከታዮቹ ወደ እርሱ ዘወር እንዲሉ አድርጓል። ከጊዜ በኋላ ሁሉም ዓይነት ሰዎች ብርሃኑን እንዲቀበሉ ዕድል ተሰጣቸው። ስለዚህ ኢየሱስ የመጣው ለአይሁዳውያን ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለመላው የሰው ልጆች፣ ለሀብታሙም ሆነ ለድሀው ለማንኛውም ዘር ጥቅም ነው።
17. ዮሐንስ 1:10, 11 በኢየሱስ ዘመን ስለ ነበሩት አይሁዳውያን መንፈሳዊ ሁኔታ ምን ይነግረናል?
17 ቁጥር 10 እና 11 እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “በዓለም ነበረ፣ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፣ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፣ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።” ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት በነበረው ሕላዌ የሰው ልጅ ዓለም በእርሱ በኩል ተፈጠረ። በምድር ሳለ ግን የራሱ ወገኖች ከሆኑት አይሁዳውያን አብዛኞቹ ሳይቀበሉት ቀሩ። ክፋታቸውና ግብዝነታቸው እንዲጋለጥባቸው አልፈለጉም። ከብርሃን ይልቅ ጨለማን መረጡ።
18. ዮሐንስ 1:12, 13 አንዳንዶች የአምላክ ልጆች በመሆን ልዩ ውርሻ ሊያገኙ እንደሚችሉ የሚያሳየው እንዴት ነው?
18 ዮሐንስ በቁጥር 12 እና 13 ላይ እንዲህ አለ:- “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፣ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።” የኢየሱስ ተከታዮች ከመጀመሪያው ጀምሮ የአምላክ ልጆች እንዳልነበሩ እነዚህ ቁጥሮች ያመለክታሉ። ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት እንዲህ ያለው የልጅነት መብትም ሆነ ሰማያዊው ተስፋ ለሰው ልጆች ገና አልተከፈተም ነበር። ይሁን እንጂ የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ባስገኘው ጥቅም ያመኑ አንዳንድ የሰው ልጆች የአምላክ ልጅ የመሆን መብትና ከክርስቶስ ጋር በአምላክ ሰማያዊት መንግሥት ነገሥታት ሆነው የመግዛት ተስፋ አገኙ።
19. በዮሐንስ 1:14 ላይ እንደሚታየው ኢየሱስ የአምላክን ብርሃን በማንጸባረቅ በኩል ከማንም የበለጠ የሆነው ለምንድን ነው?
19 ቁጥር 14 “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፣ አንድ ልጅም በአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን” ሲል ያስረዳል። ኢየሱስ በምድር ሳለ የአምላክ የበኩር ልጅ ብቻ ሊያንጸባርቀው የሚችለውን የአምላክ ክብር አንጸባርቋል። ስለዚህ አምላክንና ዓላማዎቹን ልዩ በሆነ መንገድ ለሰዎች ለመግለጽ ከማንም የተሻለ ብቃት ነበረው።
20. በዮሐንስ 1:15 ላይ በተመዘገበው መሠረት አጥማቂው ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ምን ይነግረናል?
20 ቀጥሎ ሐዋርያው ዮሐንስ በቁጥር 15 ላይ እንዲህ በማለት ጻፈ:- “[አጥማቂው] ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ:- ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ።” አጥማቂው ዮሐንስ የተወለደው ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከመወለዱ ከስድስት ወራት በፊት ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ ዮሐንስ ከሠራቸው እጅግ የላቁ ሥራዎችን ስለሠራ በሁሉም መንገድ ከዮሐንስ የበለጠ ሆኗል። ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊትም በሕይወት ይኖር ስለነበር ከእርሱ በፊት ይኖር እንደነበር ዮሐንስ አስታውቋል።
ከይሖዋ የተገኙ ስጦታዎች
21. ዮሐንስ 1:16 “በጸጋ ላይ ጸጋ [በማይገባን ደግነት ላይ የማይገባንን ደግነት አዓት]” ተቀብለናል ያለው ለምንድን ነው?
21 ዮሐንስ 1:16 “እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ [በማይገባን ደግነት ላይ የማይገባን ደግነት አዓት] ተሰጥቶናልና” በማለት ምክንያታዊ ሐሳብ ያቀርባል። ምንም እንኳን የሰው ልጆች የአዳምን ኃጢአት በመውረሳቸው ምክንያት በኃጢአት የተወለዱ ቢሆኑም ይህ ክፉ ሥርዓት እንዲጠፋ፣ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከጥፋቱ ድነው ወደ አዲሱ ዓለም እንዲገቡ፣ ሙታን ትንሣኤ እንዲያገኙ፣ ኃጢአትና ሞት እንዲወገዱ እና ገነት በሆነችው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንዲገኝ የይሖዋ ዓላማ ነው። እነዚህ በረከቶች ሁሉ ለኃጢአተኞቹ የሰው ልጆች የማይገቡ ናቸው፤ ያገኟቸውም በራሳቸው ጥረት አይደለም። በክርስቶስ በኩል ከይሖዋ የተገኙ ስጦታዎች ናቸው።
22. (ሀ) ከሁሉ ይበልጥ ታላቅ የሆነው የአምላክ ስጦታ ምን እንዲገኝ አስችሏል? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ ውስጥ ምን ግብዣ ቀርቦልናል?
22 ይህ ሁሉ ነገር እንዲገኝ ያስቻለው ከሁሉ የበለጠው ታላቅ ስጦታ ምንድን ነው? “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን [የሰውን ልጆች ዓለም] እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐንስ 3:16) ስለዚህ መንፈሳዊ ብርሃንና የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ስለ አምላክና ‘ዋነኛው የሕይወት ማስገኛ’ ስለሆነው ስለ ልጁ ትክክለኛ እውቀት ማግኘታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። (ሥራ 3:15 አዓት) የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ እውነትን ለሚወዱና ሕይወትን ለሚፈልጉ ሁሉ “ና . . . የሚሰማም:- ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” በማለት የሚጋብዘው በዚህ ምክንያት ነው። — ራእይ 22:17
23. በግ መሰል የሆኑ ሰዎች ወደ ብርሃን ሲመጡ ምን ያደርጋሉ?
23 ትሑት የሆኑ በግ መሰል ሰዎች ወደ ዓለም ብርሃን መምጣት ብቻ ሳይሆን ያንን ብርሃን ይከተሉታል። “በጎቹም ድምፁን [በድምፁ ውስጥ ያለውን እውነት] ያውቃሉና ይከተሉታል።” (ዮሐንስ 10:4) በእርግጥም ‘ፍለጋውን በጥንቃቄ መከተል’ ደስ ይላቸዋል። ምክንያቱም ፍለጋውን መከተል ማለት የዘላለም ሕይወት ማግኘት ማለት እንደሆነ ያውቃሉ። — 1 ጴጥሮስ 2:21
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ከይሖዋ ምን ሁለት ዓይነት ብርሃኖች ይመጣሉ?
◻ በዘመናችን መንፈሳዊ ብርሃን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ኢየሱስ “ታላቅ ብርሃን” የሆነው በምን መንገድ ነበር?
◻ ዮሐንስ ምዕራፍ 1 ስለ ኢየሱስ ምን ይነግረናል?
◻ የዓለምን ብርሃን ለሚከተሉ ምን ስጦታዎች ይጎርፉላቸዋል?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስምዖን ኢየሱስን “ ለአሕዛብ ሁሉን [መሸፈኛውን አዓት ] የሚገልጥ ብርሃን” ብሎ ጠርቶታል