ክርስቲያኖች አምላክን በመንፈስና በእውነት ያመልካሉ
“እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።”—ዮሐንስ 4:24
1. አምላክን የሚያስደስተው እንዴት ያለ አምልኮ ነው?
የይሖዋ አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ የሚኖረው አባቱ ምን ዓይነት አምልኮ እንደሚያስደስተው በግልጽ ተናግሯል። ኢየሱስ በሲካር ከተማ አቅራቢያ ባለ አንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት ሳምራዊት ሴት ልብ የሚነካ ምሥክርነት በሰጠበት ወቅት እንዲህ ብሏል:- “እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።” (ዮሐንስ 4:22-24) ከእነዚህ ቃላት ምን እንረዳለን?
2. የሳምራውያን አምልኮ የተመሠረተው በምን ላይ ነበር?
2 ሳምራውያን የተሳሳቱ ሃይማኖታዊ አመለካከቶች ነበሯቸው። በመንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፉ አድርገው የሚቀበሏቸው በራሳቸው ትርጉም የሳምራውያን ፔንታተች ብለው የሚጠሯቸውን የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ብቻ ነበር። ሳምራውያን አምላክን ባያውቁም አይሁዳውያን ግን የአምላክ ቃል እውቀት በአደራ ተሰጥቷቸው ነበር። (ሮሜ 3:1, 2) ይህም የታመኑ አይሁዳውያንና ሌሎችም ሰዎች የይሖዋን ሞገስ እንዲያገኙ አስችሏል። ሆኖም ይህ ምን ኃላፊነት አስከትሎባቸዋል?
3. አምላክን “በመንፈስና በእውነት” ለማምለክ ምን ያስፈልጋል?
3 አይሁዳውያንም ሆኑ ሳምራውያን እንዲሁም ጥንት የነበሩ ሌሎች ሰዎች ይሖዋን ለማስደሰት ምን ማድረግ ነበረባቸው? አምላክን “በመንፈስና በእውነት” እንዲያመልኩ ይጠበቅባቸው ነበር። እኛም እንዲሁ ማድረግ ይገባናል። አምላክን ልናገለግለው የሚገባው በቅንዓት መንፈስ እንዲሁም በፍቅርና በእምነት በተሞላ ልብ ተነሳስተን ቢሆንም አምላክን በመንፈስ ለማምለክ ቅዱስ መንፈሱን ማግኘትና ሕይወታችንን በእርሱ መምራት ይኖርብናል። የአምላክን ቃል በማጥናትና ተግባራዊ በማድረግ መንፈሳችን ወይም ውስጣዊ ስሜታችን ከመንፈሱ ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ይኖርብናል። (1 ቆሮንቶስ 2:8-12) በተጨማሪም አምልኮታችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ በእውነት መቅረብ ይኖርበታል። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ከሚገልጸው ሐሳብ ጋር መስማማት አለበት።
እውነት ሊገኝ ይችላል
4. አንዳንዶች ስለ እውነት ምን አመለካከት አላቸው?
4 አንዳንድ የፍልስፍና ተማሪዎች አንጻራዊ እንጂ ፍጹም እውነት የለም የሚል አመለካከት አላቸው። እንዲያውም አልፍ አልበርግ የተባሉ ስዊድናዊ ደራሲ “በፍልስፍናው መስክ ለሚነሱ ብዙ ጥያቄዎች ቁርጥ ያለ መልስ መስጠት አይቻልም” በማለት ጽፈዋል። እውነት አንጻራዊ ነው የሚለው አባባል ትክክል ነውን? ኢየሱስ ክርስቶስ እንደዚያ ብሎ አላስተማረም።
5. ኢየሱስ ወደ ዓለም የመጣው ለምን ነበር?
5 እስቲ የሚከተለው ውይይት ሲደረግ በቦታው እንደነበርን አድርገን እናስብ:- ጊዜው በ33 እዘአ መጀመሪያ አካባቢ ሲሆን ኢየሱስ በሮማዊው አገረ ገዥ በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት ቆሟል። ኢየሱስ ጲላጦስን “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ” አለው። ጲላጦስም “እውነት ምንድር ነው?” በማለት ጠየቀ። ሆኖም ኢየሱስ ተጨማሪ ማብራሪያ እስኪሰጠው አልጠበቀም።—ዮሐንስ 18:36-38
6. (ሀ) “እውነት” ምን ፍቺ ተሰጥቶታል? (ለ) ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጠው ተልእኮ ምንድን ነው?
6 ዌብስተርስ ናይንዝ ኒው ኮሊጂዬት ዲክሽነሪ የተባለው መዝገበ ቃላት “እውነት” ለሚለው ቃል ተጨባጭ የሆኑ ነገሮች፣ ክስተቶችና ሐቆች ስብስብ የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የመሠከረው እንዲያው በጥቅሉ እውነት ስለሚባል ነገር ሁሉ ነበርን? አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እርሱ የተናገረው እውነት በአንድ የተወሰነ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነበር። “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት ተከታዮቹ ይህን እውነት እንዲሰብኩ ኃላፊነት ሰጥቷቸው ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) ‘የሥርዓቱ መጨረሻ’ ከመምጣቱ በፊት የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች ‘የወንጌልን እውነት’ በምድር ዙሪያ መስበክ አለባቸው ማለት ነው። (ማቴዎስ 24:3፤ ገላትያ 2:14) እንዲህ ሲያደርጉ ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት የተናገራቸው ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። (ማቴዎስ 24:14) ስለሆነም የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ እውነትን ለአሕዛብ እያስተማሩ ያሉት እነማን እንደሆኑ ለይተን ማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነው።
እውነትን መማር የምንችለው እንዴት ነው?
7. ይሖዋ የእውነት ምንጭ መሆኑን እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
7 ይሖዋ የመንፈሳዊ እውነት ምንጭ ነው። እንዲያውም መዝሙራዊው ዳዊት ይሖዋን “የእውነት አምላክ” በማለት ጠርቶታል። (መዝሙር 31:5፤ 43:3) ኢየሱስ የአባቱ ቃል እውነት መሆኑን ከመግለጹም በላይ “ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 6:45፤ 17:17፤ ኢሳይያስ 54:13) ከዚህ በግልጽ እንደምንረዳው እውነትን የሚፈልጉ ሁሉ ከታላቁ አስተማሪ ከይሖዋ መማር ይኖርባቸዋል ማለት ነው። (ኢሳይያስ 30:20, 21) እውነትን የሚፈልጉ ሰዎች ‘የአምላክን እውቀት’ መቅሰም ያስፈልጋቸዋል። (ምሳሌ 2:5) ይሖዋ ደግሞ በተለያዩ መንገዶች እውነትን አስተምሯል።
8. አምላክ እውነትን ያስተማረው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
8 ለምሳሌ ያህል አምላክ ሕጉን ለእስራኤላውያን ያስተላለፈው በመላእክት በኩል ነበር። (ገላትያ 3:19) አብርሃምንና ያዕቆብን እንደሚባርካቸው ቃል የገባላቸው በሕልም አማካኝነት ነበር። (ዘፍጥረት 15:12-16፤ 28:10-19) ኢየሱስ በተጠመቀበት ጊዜ አምላክ ከሰማይ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ ሲናገር ተሰምቷል። (ማቴዎስ 3:17) እንዲሁም አምላክ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነሳስተው እውነትን በጽሑፍ እንዲያሰፍሩ በማድረጉ አመስጋኞች ነን። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) እንግዲያው የአምላክን ቃል በመማር ‘በእውነት ላይ እምነት ማሳደር’ እንችላለን።—2 ተሰሎንቄ 2:13
እውነት እና የአምላክ ልጅ
9. አምላክ እውነትን ለማሳወቅ በልጁ የተጠቀመው እንዴት ነው?
9 አምላክ እውነትን ለሰው ልጆች ለመግለጥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በእጅጉ ተጠቅሟል። (ዕብራውያን 1:1-3) እንዲያውም እንደ ኢየሱስ እውነትን የተናገረ ሰው የለም። (ዮሐንስ 7:46) ወደ ሰማይ ካረገ በኋላም እንኳ ከአባቱ ያገኘውን እውነት አሳውቋል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ዮሐንስ ‘ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውን በእርሱም የተገለጠውን’ ራእይ ተመልክቷል።—ራእይ 1:1-3
10, 11. (ሀ) ኢየሱስ የሰበከው እውነት ከምን ጋር ዝምድና አለው? (ለ) ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረው እውነት እውን እንዲሆን ያደረገው እንዴት ነው?
10 ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ለእውነት ለመመሥከር እንደሆነ ለጴንጤናዊው ጲላጦስ ነግሮት ነበር። ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት ይህ እውነት እርሱ ንጉሥ በሆነለት የአምላክ መንግሥት አማካኝነት ከሚረጋገጠው የይሖዋ ሉዓላዊነት ጋር ዝምድና እንዳለው አሳይቷል። ሆኖም ኢየሱስ ስለ እውነት የሰጠው ምሥክርነት በመስበክና በማስተማር ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረው እውነት ፍጻሜውን እንዲያገኝም አድርጓል። በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ፤ እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፣ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው።”—ቆላስይስ 2:16, 17
11 ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ በቤተ ልሔም በተወለደ ጊዜ አስቀድሞ የተነገረው እውነት ፍጻሜውን አግኝቷል። (ሚክያስ 5:2፤ ሉቃስ 2:4-11) በተጨማሪም ዳንኤል በትንቢት በተናገረው መሠረት ኢየሱስ በ69ኛው ‘የዓመታት ሳምንታት’ መጨረሻ ላይ መሲህ ስለመሆኑ አስቀድሞ የተነገረው እውነት ፍጻሜውን አግኝቷል። ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው ኢየሱስ በአምላክ ፊት ራሱን ለጥምቀት ባቀረበበትና በመንፈስ ቅዱስ በተቀባበት በ29 እዘአ ነበር። (ዳንኤል 9:25፤ ሉቃስ 3:1, 21, 22) በተጨማሪም ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪ በመሆን መንፈሳዊ ብርሃን መፈንጠቁም እውነት እውን እንዲሆን አስችሏል። (ኢሳይያስ 9:1, 2, 6, 7፤ 61:1, 2፤ ማቴዎስ 4:13-17፤ ሉቃስ 4:18-21) ከዚህም በላይ ኢየሱስ በሞተበትና ትንሣኤ ባገኘበት ጊዜም እውነት በተጨባጭ ታይቷል።—መዝሙር 16:8-11፤ ኢሳይያስ 53:5, 8, 11, 12፤ ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 1:29፤ ሥራ 2:25-31
12. ኢየሱስ ‘እኔ እውነት ነኝ’ ሊል የቻለው ለምንድን ነው?
12 እውነት ኢየሱስ ክርስቶስ ባደረጋቸውና በሚያደርጋቸው ነገሮች ላይ ያተኮረ በመሆኑ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ለማለት ችሏል። (ዮሐንስ 14:6) ሰዎች፣ ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ያለውን ቦታ በመገንዘብ ‘ለእውነት ከቆሙ’ መንፈሳዊ ነጻነት ያገኛሉ። (ዮሐንስ 8:32-36፤ 18:37) በበግ የተመሰሉ ሰዎች እውነትን ተቀብለው ኢየሱስን በእምነት ስለሚከተሉ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ።—ዮሐንስ 10:24-28
13. ቅዱስ ጽሑፋዊውን እውነት ከየትኞቹ ሦስት አቅጣጫዎች እንመረምራለን?
13 ኢየሱስና የአምላክ መንፈስ እርዳታ የነበራቸው ደቀ መዛሙርቱ ያስተማሩት እውነት ለእውነተኛው የክርስትና እምነት መሠረት ሆኗል። በመሆኑም ‘ለእምነት ታዛዥ’ የሆኑ ሁሉ ‘በእውነት ውስጥ መመላለሳቸውን ይቀጥላሉ።’ (ሥራ 6:7 አ.መ.ት ፤ 3 ዮሐንስ 3, 4) ታዲያ በዛሬው ጊዜ በእውነት እየተመላለሱ ያሉት እነማን ናቸው? ለአሕዛብ ሁሉ እውነትን እያስተማሩ ያሉትስ እነማን ናቸው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን በተመለከተ (1) ስለ ሃይማኖታዊ እምነቶቻቸው፣ (2) ስለ አምልኮ ሥርዓታቸውና (3) ስለ አኗኗራቸው በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን እውነት እንመረምራለን።
እውነት እና ሃይማኖታዊ እምነቶች
14, 15. የጥንት ክርስቲያኖችም ሆኑ ዛሬ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው?
14 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ለይሖዋ ቃል ከፍተኛ አክብሮት ነበራቸው። (ዮሐንስ 17:17) ሃይማኖታዊ እምነቶቻቸውንና ልማዶቻቸውን የሚመዝኑት በአምላክ ቃል ነበር። በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን የኖረው የእስክንድርያው ክሌመንት “ግሩም የሆኑ ባሕርያትን ለማዳበር የሚጣጣሩ ሁሉ አምነው ለሚቀበሏቸው ነገሮች ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎችን እስኪያገኙ ድረስ እውነትን ለማግኘት የሚያደርጉትን ፍለጋ አያቆሙም” በማለት ተናግሯል።
15 የይሖዋ ምሥክሮችም እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ አክብሮት አላቸው። ‘ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈና ለትምህርት እንደሚጠቅም’ ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) እንግዲያው የጥንት ክርስቲያኖች ያምኑባቸው ከነበሩት ትምህርቶች መካከል አንዳንዶቹን እየመረመርን በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መመሪያቸው አድርገው የሚከተሉት የይሖዋ አገልጋዮች ከተማሯቸው ነገሮች ጋር እናወዳድር።
ስለ ነፍስ እውነቱ ምንድን ነው?
16. ስለ ነፍስ እውነቱ ምንድን ነው?
16 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እምነታቸው በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ ስለነበር ስለ ነፍስ እውነቱን አስተምረዋል። አምላክ ሰውን ሲፈጥረው ‘ሰው ሕያው ነፍስ’ እንደሆነ ያውቁ ነበር። (ዘፍጥረት 2:7 አ.መ.ት ) ከዚህም በላይ የሰው ነፍስ ሟች እንደሆነች አውቀዋል። (ሕዝቅኤል 18:4፤ ያዕቆብ 5:20) በተጨማሪም ‘ሙታን አንዳች እንደማያውቁ’ ተገንዝበው ነበር።—መክብብ 9:5, 10
17. የሙታንን የወደፊት ተስፋ እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ?
17 በሌላ በኩል የጥንቶቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመታሰቢያ መቃብር ውስጥ ያሉ ሙታን ትንሣኤ እንዳላቸው ወይም ዳግም ሕይወት እንደሚያገኙ ጠንካራ እምነት ነበራቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ” በማለት ይህን እምነት ግልጽ አድርጎ አስቀምጦታል። (ሥራ 24:15) ክርስቲያን እንደሆነ የሚነገርለት ሚኑኪየስ ፌሊክስ ከጊዜ በኋላ “አምላክ ራሱ የፈጠረውን ሰው እንደገና በአዲስ መልክ ሊሠራው አይችልም ብሎ የሚከራከር ሰው ካለ ምንኛ ሰነፍ ወይም ማስተዋል የጎደለው ነው?” በማለት ጽፎ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮችም እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ስለ ሰው ነፍስ፣ ስለ ሞትና ስለ ትንሣኤ ቅዱስ ጽሑፉ የሚያስተምረውን እውነት በጥብቅ ይከተላሉ። እስቲ አሁን ደግሞ ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ እንመልከት።
እውነት እና የሥላሴ ትምህርት
18, 19. ሥላሴ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት አይደለም ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
18 የጥንት ክርስቲያኖች አምላክ፣ ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ ሥላሴ ናቸው የሚል አመለካከት አልነበራቸውም። ዚ ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- ‘ሥላሴ የሚለው ቃልም ሆነ መሠረተ ትምህርት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ፈጽሞ አይገኝም። ኢየሱስና ተከታዮቹም ቢሆኑ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኘው “እስራኤል ሆይ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው” ከሚለው የዕብራይስጥ ጸሎት ጋር የሚቃረን ሐሳብ ለማምጣት አልሞከሩም። (ዘዳ. 6:4)’ ክርስቲያኖች የሮማውያንን ሦስት አማልክትም ሆነ ሌሎች አማልክትን አያመልኩም ነበር። ይሖዋ ብቻ መመለክ እንዳለበት ኢየሱስ የተናገረውን ተቀብለዋል። (ማቴዎስ 4:10) ከዚህም በላይ ክርስቶስ “ከእኔ አብ ይበልጣል” በማለት የተናገረውን ቃል ያምናሉ። (ዮሐንስ 14:28) ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው አመለካከት ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው።
19 የጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች በአምላክ፣ በክርስቶስና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለው ልዩነት ግራ አጋብቷቸው አያውቅም። እንዲያውም ደቀ መዛሙርትን የሚያጠምቁት በሥላሴ ስም ሳይሆን (1) በአብ (2) በወልድ እና (3) በመንፈስ ቅዱስ ስም ነበር። በተመሳሳይም የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ስለሚያስተምሩ በአምላክ፣ በልጁና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቀው ያውቃሉ።—ማቴዎስ 28:19
እውነት እና ጥምቀት
20. የጥምቀት እጩዎች ስለ ምን ነገር ማወቅ ያስፈልጋቸዋል?
20 እውነትን በማስተማር ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ኢየሱስ ተከታዮቹን አዝዞ ነበር። እነዚህ ሰዎች ለጥምቀት ብቁ እንዲሆኑ የቅዱሳን ጽሑፎችን መሠረታዊ እውቀት መማር ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ ያህል የአብን እንዲሁም የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥልጣንና ቦታ ማወቅ ይኖርባቸዋል። (ዮሐንስ 3:16) እንዲሁም የጥምቀት እጩዎች መንፈስ ቅዱስ ራሱን የቻለ አካል ሳይሆን የአምላክ ኃይል መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል።—ዘፍጥረት 1:2 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ
21, 22. መጠመቅ ያለባቸው ያመኑ ሰዎች ብቻ ናቸው የምትለው ለምንድን ነው?
21 የጥንት ክርስቲያኖች ያጠምቁ የነበረው እውቀት አግኝተው ንስሐ የገቡትንና ፈቃዱን ለማድረግ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለአምላክ የወሰኑትን ሰዎች ብቻ ነበር። በ33 እዘአ በጰንጤቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም ተሰብስበው የነበሩት አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ቀደም ሲልም የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች እውቀት ነበራቸው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ መሲሁ የሰጠውን ምሥክርነት ሲሰሙ 3, 000 የሚያክሉ ሰዎች ‘ቃሉን ተቀብለው ተጠምቀዋል።’—ሥራ 2:41፤ 3:19–4:4፤ 10:34-38
22 በክርስትና እምነት የሚጠመቁት ያመኑ ሰዎች ብቻ ናቸው። በሰማርያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች እውነትን ተቀብለው “ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እየሰበከላቸው ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ፣ ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ።” (ሥራ 8:12) ወደ ይሁዲነት የተለወጠውና ስለ ይሖዋ እውቀት የነበረው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የተጠመቀው፣ ፊልጶስ ስለ መሲሁ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንዳገኘ ካስረዳው በኋላ ነበር። (ሥራ 8:34-36) ከጊዜ በኋላም ጴጥሮስ ለቆርኔሌዎስና ለሌሎች አሕዛብ ‘አምላክን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ ሰው በእርሱ ዘንድ የተወደደ እንደሆነ’ እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምን ሁሉ የኃጢአት ይቅርታ እንደሚያገኝ አብራርቷል። (ሥራ 10:34, 35, 43፤ 11:18) ይህ ሁሉ ኢየሱስ “ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠው ትእዛዝ ፍጻሜ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ሥራ 1:8) ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች ይህንኑ ሥርዓት በመከተል መሠረታዊ የሆኑ የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀት ያገኙና ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሰዎች ብቻ እንዲጠመቁ ያደርጋሉ።
23, 24. ክርስቲያናዊ ጥምቀት መከናወን የሚኖርበት እንዴት ነው?
23 ያመኑ ሰዎች መጠመቅ ያለባቸው ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በመጥለቅ ነው። ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ከተጠመቀ በኋላ ‘ከውኃው ወጥቷል።’ (ማርቆስ 1:10) በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የተጠመቀበትን ሁኔታ ሲዘግብ “ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ” ይላል። ከዚያም ‘ከውኃው እንደወጡ’ ይናገራል። (ሥራ 8:36-40) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥምቀት ከመቀበር ጋር ተመሳስሎ መገለጹም ውኃ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መጥለቅን እንደሚጠይቅ የሚያሳይ ነው።—ሮሜ 6:4-6፤ ቆላስይስ 2:12
24 ዚ ኦክስፎርድ ኮምፓኒየን ቱ ዘ ባይብል የተባለው መጽሐፍ “ስለ ጥምቀት የሚናገሩ አንዳንድ የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች እንደሚያመለክቱት የሚጠመቀው ሰው ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ እንዲጠልቅ ይደረግ ነበር” ብሏል። ላሩስ ዱ ቨንቲዬም ሲዬክል (1928 ፓሪስ) የተባለ አንድ የፈረንሳይ የጽሑፍ ሥራ “የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ውኃ በሚገኝበት ቦታ ሁሉ ውኃ ውስጥ በመጥለቅ ይጠመቁ ነበር” የሚል አስተያየት ሰጥቷል። እንዲሁም አፍተር ጂሰስ —ዘ ትራያምፍ ኦቭ ክርስቺያኒቲ የተባለው መጽሐፍ “ከጥምቀት በፊት የጥምቀት እጩው እምነቱን ለሌሎች እንዲገልጽ የሚጠበቅበት ሲሆን ከዚያም በኢየሱስ ስም ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በመጥለቅ ይጠመቃል” ብሏል።
25. በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ስለምን ነገር ይብራራል?
25 እስከ አሁን የተመለከትነው የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የነበራቸውን እምነትና ልማድ የሚጠቁሙ ጥቂት ምሳሌዎችን ብቻ ነው። በእነርሱና በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት የሚያረጋግጡ ሌሎች ምሳሌዎችንም መጥቀስ ይቻላል። በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ዛሬ እውነትን ለሰዎች እያስተማሩ ያሉት እነማን መሆናቸውን ለይተን ለማወቅ የሚረዱ ተጨማሪ ምሳሌዎችን እንመለከታለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• አምላክ የሚቀበለው አምልኮ ምን ዓይነት ነው?
• እውነት በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ፍጻሜውን ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው?
• ስለ ሲኦልና ስለ ሞት እውነቱ ምንድን ነው?
• ክርስቲያናዊ ጥምቀት መከናወን ያለበት እንዴት ነው? የጥምቀት እጩውስ ምን ይጠበቅበታል?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ‘ለእውነት ልመሰክር መጥቻለሁ’ ሲል በጲላጦስ ፊት ተናግሯል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ‘እኔ እውነት ነኝ’ ሲል ምን ማለቱ እንደነበረ ማብራራት ትችላለህ?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያናዊ ጥምቀትን በተመለከተ እውነቱ ምንድን ነው?