-
የስብከቱ ሥራ ያስገኘው ውጤት—‘አዝመራው ነጥቷል’የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
-
-
1, 2. (ሀ) ደቀ መዛሙርቱ ግራ የተጋቡት ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ የተናገረው ስለ የትኛው የመከር ሥራ ነው?
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ግራ ተጋብተዋል። ኢየሱስ “ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” አላቸው። ኢየሱስ እየጠቆማቸው ወዳለው አቅጣጫ ሲመለከቱ ግን ዓይናቸው ውስጥ የገባው የነጣ አዝመራ ሳይሆን አረንጓዴ የሆነ ለምለም የገብስ ቡቃያ ነበር። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ ‘ስለ የትኛው አዝመራ ነው የሚያወራው? መከር ሊገባ ገና የተወሰኑ ወራት ይቀሩ የለም እንዴ?’ ብለው አስበው ሊሆን ይችላል።—ዮሐ. 4:35
2 ኢየሱስ ግን ቃል በቃል ስለሚከናወነው የመከር ሥራ እየተናገረ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በዚህ ወቅት፣ ከመንፈሳዊው የመከር ሥራ ማለትም ሰዎችን ከመሰብሰብ ጋር በተያያዘ አስፈላጊ የሆኑ ሁለት ትምህርቶችን ለደቀ መዛሙርቱ እያስተማራቸው ነበር። እነዚህ ትምህርቶች ምንድን ናቸው? መልሱን ለማግኘት እስቲ ይህን ዘገባ በስፋት እንመርምር።
ለሥራ የቀረበ ጥሪ እና የሚገኘው ደስታ
3. (ሀ) ኢየሱስ “አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” ብሎ የተናገረው ለምን ሊሆን ይችላል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) (ለ) ኢየሱስ፣ የተናገረውን ነገር ግልጽ ያደረገው እንዴት ነው?
3 ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይህን ውይይት ያደረገው በ30 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ቦታው ሰማርያ ውስጥ በምትገኝ ሲካር የተባለች ከተማ አቅራቢያ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ወደ ከተማይቱ ሲገቡ ኢየሱስ በአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ። በዚያም ለአንዲት ሴት መንፈሳዊውን እውነት ነገራት፤ ይህች ሴት፣ ኢየሱስ ያስተማራት እውነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደባትም። ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ሲመለሱ ሴትየዋ የተማረቻቸውን አስደናቂ እውነቶች ለምታውቃቸው ሰዎች ለመናገር በፍጥነት ወደ ሲካር ሄደች። ሴትየዋ የተናገረችው ነገር የሰዎቹን የማወቅ ጉጉት ስለቀሰቀሰው ብዙዎቹ ኢየሱስን ለማግኘት በጥድፊያ ወደ ውኃው ጉድጓድ መጡ። ኢየሱስ አሻግሮ በርቀት ያለውን ሜዳ ሲቃኝ በርካታ ሳምራውያን በብዛት ሆነው ሲመጡ ተመለከተ፤ “ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” ብሎ የተናገረው በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም።a ኢየሱስ እየተናገረ ያለው ስለ መንፈሳዊ አዝመራ መሆኑን ለመጠቆም “አጫጁ . . . ለዘላለም ሕይወት ፍሬ እየሰበሰበ ነው” በማለት አክሎ ተናገረ።—ዮሐ. 4:5-30, 36
4. (ሀ) ኢየሱስ የመከሩን ሥራ በተመለከተ የትኞቹን ሁለት አስፈላጊ ትምህርቶች አስተምሯል? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
4 ኢየሱስ መንፈሳዊውን የመከር ሥራ በተመለከተ ያስተማራቸው ሁለት አስፈላጊ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው? የመጀመሪያው፣ ሥራው አጣዳፊ ነው የሚለው ነው። “አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” ሲል ተከታዮቹን ለሥራ እንዲንቀሳቀሱ ማበረታታቱ ነበር። ኢየሱስ፣ ሥራው ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ ደቀ መዛሙርቱ በደንብ እንዲገነዘቡ ለማድረግ ሲል “አሁንም እንኳ አጫጁ ደሞዙን እየተቀበለ . . . ነው” አላቸው። በእርግጥም አዝመራው መሰብሰብ ጀምሯል፤ በመሆኑም ዛሬ ነገ ሳይሉ ወዲያውኑ ሥራ መጀመር አለባቸው። ሁለተኛው ትምህርት ደግሞ ሠራተኞቹ ደስተኞች ናቸው የሚለው ነው። ኢየሱስ፣ ዘሪዎቹም ሆኑ አጫጆቹ “በአንድነት ደስ ይላቸዋል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 4:35ለ, 36) ኢየሱስ “ብዙ ሳምራውያን በእሱ [በማመናቸው]” ተደስቶ መሆን አለበት፤ ደቀ መዛሙርቱም በመከሩ ሥራ በሙሉ ነፍሳቸው መካፈላቸው ከፍተኛ ደስታ ያስገኝላቸዋል። (ዮሐ. 4:39-42) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተፈጸመው ይህ ታሪክ፣ እስከ ዛሬ ከተካሄዱት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ መንፈሳዊ የመከር ሥራ በሚከናወንበት በዚህ ዘመን የሚኖረውን ሁኔታ የሚያሳይ በመሆኑ በዛሬው ጊዜ ላለን ክርስቲያኖች ልዩ ትርጉም አለው። ታዲያ ይህ ዘመናዊ የመከር ሥራ የጀመረው መቼ ነው? በሥራው የሚካፈሉት እነማን ናቸው? ምን ውጤትስ ተገኝቷል?
-
-
የስብከቱ ሥራ ያስገኘው ውጤት—‘አዝመራው ነጥቷል’የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
-
-
a ኢየሱስ “አዝመራው እንደነጣ” የተናገረው በርካታ ሳምራውያን ነጭ ልብስ ለብሰው ወደ እሱ እየመጡ መሆናቸውን ስለተመለከተ ሊሆን ይችላል።
-