ይህ መጽሐፍ እምነት ሊጣልበት የሚችል ነውን?
“ከማንኛውም የዓለማዊ ታሪክ መጽሐፍ ይበልጥ በውስጡ ስለያዘው ታሪክ እውነተኝነት አስተማማኝ ማስረጃ ያገኘሁት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው።”—ሰር አይዛክ ኒውተን፣ እውቅ እንግሊዛዊ ሳይንቲስት።1
ይህ መጽሐፍ፣ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ሊጣልበት የሚችል መጽሐፍ ነውን? የሚጠቅሳቸው ሰዎች በእርግጥ በሕይወት የኖሩ፣ የሚጠራቸው ቦታዎች በእርግጥ የነበሩና የሚተርካቸው ክንውኖች በእርግጥ የተፈጸሙ ናቸውን? ከሆኑ ጠንቃቃና ሐቀኛ በሆኑ ጸሐፊዎች የተጻፉ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሊኖር ይገባል። በእርግጥም ማስረጃዎች አሉ። አብዛኞቹ ማረጋገጫዎች በምድር ከርስ ውስጥ ተቀብረው የተገኙ ሲሆን በራሱ በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙት ማረጋገጫዎችም በርካታ ናቸው።
ማስረጃዎቹን ቆፍሮ ማውጣት
መጽሐፍ ቅዱስ በሚጠቅሳቸው ቦታዎች የተቀበሩት ጥንታውያን የዕደ ጥበብ ሥራዎች ተቆፍረው መውጣታቸው የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪካዊና ጂኦግራፊያዊ ትክክለኛነት አረጋግጧል። አርኪኦሎጂስቶች ካገኟቸው ማስረጃዎች ጥቂቶቹን ብቻ እንመልከት።
የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ከጊዜ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ የሆነውን ዳዊት የተባለ ደፋር ወጣት እረኛ አሳምረው ያውቃሉ። ስሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 1,138 ጊዜ የሚገኝ ሲሆን ብዙ ጊዜ የዳዊትን ሥርወ መንግሥት የሚያመለክተው የ“ዳዊት ቤት” የሚለው ሐረግ 25 ጊዜ ተጠቅሷል። (1 ሳሙኤል 16:13፤ 20:16) ይሁን እንጂ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዳዊት በእርግጥ የኖረ ሰው መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ አልተገኘም ነበር። ታዲያ ዳዊት በሕይወት ያልኖረ ሐሳብ የወለደው ሰው ነበርን?
በ1993 በፕሮፌሰር አቭርሃም ቢራን የተመራ አርኪኦሎጂስቶች ቡድን በጣም አስደናቂ የሆነ ግኝት አገኘ። ይህ ግኝታቸው ኢዝራኤል ኤክስፕሎረሽን ጆርናል በተባለ መጽሔት ተዘግቧል። ቴል ዳን ተብሎ በሚጠራው በእስራኤል ሰሜናዊ ክፍል በሚገኝ ጥንታዊ ጉብታ ላይ አንድ ጥቁር ጥርብ ድንጋይ አገኙ። በዚህ ድንጋይ ላይ “የዳዊት ቤት” እና “የእስራኤል ንጉሥ” የሚል ጽሑፍ ተቀርጾበታል።2 ይህ ጽሕፈት በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተቀረጸ ሲሆን ከእስራኤል በስተ ምሥራቅ ይኖሩ የነበሩ አራምውያን የተባሉ የእስራኤል ጠላቶች ያቆሙት የድል ሐውልት ክፍል ነው። ይህ የድንጋይ ቅርጽ ልዩ ግምት የተሰጠው ለምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ቢራንና ባልደረባቸው የሆኑት ፕሮፌሰር ዮሴፍ ናቨህ ያቀረቡትን ሪፖርት መሠረት በማድረግ ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው ያሠፈረው ጽሑፍ “ዳዊት የሚለው ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ሌላ ጥንታዊ በሆነ ጽሑፍ ላይ ሲገኝ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው”3 ብሏል።a ይህን የድንጋይ ጽሑፍ በተመለከተ ልብ ሊባል የሚገባው ሌላም ነገር አለ። “የዳዊት ቤት” የሚለው ሐረግ የተጻፈው እንደ አንድ ቃል ሆኖ ነው። ፕሮፌሰር አንሰን ሬኒ የተባሉት የቋንቋ ሊቅ እንዲህ በማለት ያብራራሉ:- “የሁለት ቃላት ጥምረት . . . በሚገባ የታወቀ የተጸውኦ ስም ሆኖ የሚያገለግል ከሆነ በሁለቱ ቃላት መካከል የቃላት መከፋፈያ እንዲኖር አይደረግም። ‘የዳዊት ቤት’ የሚለው ሐረግ ደግሞ በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አጋማሽ ላይ የፖለቲካና የጂኦግራፊ የተጸውኦ ስም ሆኖ ያገለግል ነበር።”5 ስለዚህ ንጉሥ ዳዊትና ሥርወ መንግሥቱ በጥንቱ ዓለም በሚገባ የታወቁ ነበሩ ማለት ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰችው ነነዌ የተባለች ታላቋ የአሦር ከተማ በእርግጥ የነበረች ከተማ ናትን? አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች እስከ 19ኛው መቶ ዘመን ድረስ የነነዌን ሕልውና ለማመን ፈቃደኛ አልሆኑም ነበር። በ1849 ግን ሰር ኦስተን ሄንሪ ሌያርድ የጥንትዋ ነነዌ ክፍል በሆነ ኩዩንጂክ በተባለ ቦታ የንጉሥ ሰናክሬብን ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ ቆፍረው አወጡ። በዚህ ጊዜ ተቺዎች የሚናገሩት አጡ። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ፍርስራሾች ሌላ ተጨማሪ መረጃም ተገኝቷል። በጥሩ ሁኔታ ተጠብቆ በቆየ አንድ ክፍል ግድግዳዎች ላይ አንዲት የተመሸገች ከተማ ስትወረርና የከተማዋ ምርኮኞች በወራሪው ንጉሥ ፊት ሲያልፉ የሚያሳይ ሥዕል ተገኝቷል። በንጉሡ አናት ላይ “የዓለም ንጉሥ፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬብ በኒሜዱ ላይ፣ ማለትም በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ የለኪሶ ምርኮ በፊቱ በሰልፍ ሲያልፍ” የሚል ጽሑፍ አለ።6
ይህ በብሪትሽ ሙዚየም ሊታይ የሚችለው ሥዕልና ጽሑፍ መጽሐፍ ቅዱስ ለኪሶ የተባለችው የይሁዳ ከተማ በሰናክሬብ ስለመያዝዋ በ2 ነገሥት 18:13, 14 ከሚገልጸው ዘገባ ጋር ይስማማል። ሌያርድ ይህ ግኝት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን በመግለጽ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ከእነዚህ ግኝቶች በፊት በሕዝቅያስና [የይሁዳ ንጉሥ ነው] በሰናክሬብ መካከል የተደረጉትን ጦርነቶች በተመለከተ ጦርነቶቹ በራሱ በሰናክሬብ አማካኝነት በተደረጉበት ዘመን የተጻፈና መጽሐፍ ቅዱስ መዝግቦ ያቆየውን ታሪክ በዝርዝር የሚያረጋግጥ የታሪክ ማስረጃ ነነዌ በነበረችበት ሥፍራ አፈርና ትቢያ ተጭኖት ይገኛል ወይም ሊገኝ ይችላል ብሎ ያሰበ ማን አለ?”7
አርኪኦሎጂስቶች የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ሌሎች በርካታ የዕደ ጥበብ ሥራዎችን፣ ማለትም የሸክላ ዕቃዎችን፣ የሕንጻ ፍርስራሾችን፣ የሸክላ ጽላቶችን፣ ገንዘቦችን፣ ሰነዶችን፣ ሐውልቶችንና የተቀረጹ ጽሑፎችን አግኝተዋል። የመሬት ቆፋሪዎች አብርሃም የኖረባትንና የንግድና የሃይማኖታዊ ጉዳዮች ማዕክል የሆነችውን የከለዳውያን ከተማ ኡርን አግኝተዋል።8 (ዘፍጥረት 11:27-31) በ19ኛው መቶ ዘመን ተቆፍሮ የወጣው የናቦኒደስ ዜና መዋዕል ባቢሎን በ539 ከዘአበ በታላቁ ቂሮስ እጅ ስለመውደቋ ይተርካል። ይህ ታሪክ ዳንኤል ምዕራፍ 5 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል።9 በጥንቷ ተሰሎንቄ በተገኘ አንድ ቅስት ላይ በተገኘ የጽሑፍ ቅርጽ ላይ (ስብርባሪዎቹ በብሪትሽ ሙዚየም ይገኛሉ) “ፖሊታርኮች” የሚባሉ የከተማ ገዥዎች ስም ዝርዝር ተገኝቷል። ይህ ቃል በጥንቱ የግሪክኛ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ የማይገኝ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ ግን ተጠቅሞበታል።10 (ሥራ 17:6 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) የሉቃስ ትክክለኛነት በሌሎች ዝርዝር ሁኔታዎች ረገድ እንደተረጋገጠ ሁሉ በዚህ ረገድም ተረጋግጧል።—ከሉቃስ 1:3 ጋር አወዳድር።
ይሁን እንጂ አርኪኦሎጂስቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይቅርና እርስ በርሳቸው እንኳን ሙሉ በሙሉ የሚስማሙ አይደሉም። ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ሊጣልበት የሚችል መጽሐፍ ስለመሆኑ በራሱ በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኛቸው በርካታ ማስረጃዎች አሉ።
በሐቀኝነት የቀረበ ጽሑፍ
ሐቀኛ የሆኑ ታሪክ ጸሐፊዎች መዝግበው የሚያቆዩት ድሎቻቸውን (ሰናክሬብ ለኪሶን ስለመቆጣጠሩ እንደሚናገረው የጽሑፍ ቅርጽ) ብቻ ሳይሆን ሽንፈቶቻቸውን፣ የተሳኩላቸውን ክንውኖች ብቻ ሳይሆን ያልተሳኩላቸውን፣ ጠንካራ ጎኖቻቸውን ብቻ ሳይሆን ድክመቶቻቸውን ጭምር ይመዘግባሉ። ይህን የመሰለ ሐቀኝነት የሚታይባቸው ዓለማዊ ታሪኮች እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው።
ዳንኤል ዲ ሉከንቢል ስለ አሦራውያን ታሪክ ጸሐፊዎች ሲናገሩ “የነገሥታቱ ጉረኝነት ብዙውን ጊዜ ታሪካዊ ክንውኖችን እንዲያጣምሙና እንዲበርዙ ይገፋፋቸው እንደነበረ ግልጽ ነው” ብለዋል።11 የአሦር ንጉሥ የአሱርናሲርፓል ዜና መዋዕል ነገሥታቱ ለነበራቸው ራስን የመካብ ባሕርይ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። “ባለ ትልቅ ግርማ ነኝ፣ ጌታ ነኝ፣ እጅግ ከፍ ያልኩ ነኝ፣ ኃያል ነኝ፣ የተከበርኩ ነኝ፣ ማዕረግ የተሰጠኝ ነኝ፣ ከሁሉ በላይ ነኝ፣ ጀግና ነኝ፣ እንደ አንበሳ ጎበዝ ነኝ፣ አርበኛ ነኝ!”12 ታዲያ ይህን በመሰለ ዜና መዋዕል ላይ የተጻፉትን ነገሮች በሙሉ እንደ እውነተኛ ታሪክ ለመቀበል ትችላለህን?
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ግን ከዚህ ፈጽሞ በተለየ ሁኔታ የሐቀኝነት ባሕርይ አሳይተዋል። የእስራኤላውያን መሪ የነበረው ሙሴ የወንድሙን የአሮንን፣ የእህቱን የማርያምን፣ የወንድሙን ልጆች የናዳብንና የአቢዩድን፣ እንዲሁም የሕዝቡንና የገዛ ራሱን ስህተቶች በግልጽ ጽፏል። (ዘጸአት 14:11, 12፤ 32:1-6፤ ዘሌዋውያን 10:1, 2፤ ዘኁልቁ 12:1-3፤ 20:9-12፤ 27:12-14) ንጉሥ ዳዊት የሠራቸው ከባድ በደሎች በጽሑፍ እንዲሰፍሩ ተደርገዋል እንጂ ተሸፋፍነው እንዲቀሩ አልተደረገም። የተጻፉት ደግሞ ንጉሥ ዳዊት በሥልጣን ላይ እያለ ነበር። (2 ሳሙኤል ምዕራፍ 11 እና 24) በስሙ የሚጠራ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የጻፈው ማቴዎስ ሐዋርያት (እርሱም ሐዋርያ ነበር) ስለ የራሳቸው ማዕረግና ቦታ እንደተጣሉና ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት ምሽት ጥለውት ሄደው እንደነበረ ተርኳል። (ማቴዎስ 20:20-24፤ 26:56) በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን መልእክቶች የጻፉት ጸሐፊዎች በአንዳንዶቹ ቀደምት የክርስቲያን ጉባኤዎች ውስጥ የጾታ ብልግናና መከፋፈልን ጨምሮ ሌሎች ችግሮች እንደነበሩ ገልጸዋል። እነዚህን ችግሮች አድበስብሰው ለማለፍ አልፈለጉም።—1 ቆሮንቶስ 1:10-13፤ 5:1-13
እንዲህ ያለው ግልጽነትና ሐቀኝነት ያልተለየው አጻጻፍ ለእውነት ጥልቅ የሆነ አሳቢነት የነበራቸው ጸሐፊዎች እንደነበሩ ያረጋግጣል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የሚወዷቸው ሰዎች፣ ሕዝቦቻቸውና ራሳቸው ጭምር ዝቅተኛ ግምት እንዲሰጣቸው የሚያደርጉ መረጃዎችን ለመጻፍ ፈቃደኞች ከነበሩ ይህ በጽሑፎቻቸው እንድንታመን በቂ ምክንያት አይሆነንምን?
በዝርዝር ጉዳዮች ረገድም ትክክለኛ ነው
አንድ ጉዳይ በፍርድ ቤት በሚደመጥበት ጊዜ የምስክሮች ቃል እውነተኝነት በሚናገሯቸው ጥቃቅን ጭብጦች ሊመዘን ይችላል። ጥቃቅን በሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች የሚሰጠው ምስክርነት እርስ በርሱ የሚስማማ ከሆነ ቃሉ ትክክለኛና ሐቅ እንደሆነ ሲታመን እርስ በርሱ የሚጋጭ ከሆነ ግን ከራሱ ፈጥሮ የተናገረው ምስክርነት እንደሆነ ይታመናል። በሌላው በኩል ደግሞ ምንም ዓይነት እንከን የማይገኝለትና በጥቃቅን ዝርዝር ጉዳዮች ሳይቀር በሚገባ የተቀናበረ ምስክርነት ከሆነ ሐሰተኛ ምስክርነት ሆኖ ሊታይ ይችላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “ምስክርነት” በዚህ ረገድ ሲመዘን እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አስደናቂ የሆነ የእርስ በርስ ስምምነት አላቸው። በጥቃቅን ዝርዝር ጉዳዮች ሳይቀር እርስ በርሳቸው ይስማማሉ። ይሁን እንጂ ስምምነታቸው እርስ በርሳቸው ተመካክረው ያደረጉት እስኪመስል ድረስ ሆን ተብሎ በጥንቃቄ የተቀናበረ አይደለም። በመካከላቸው ባለው ተመሳሳይነት ረገድ ምንም የተቀነባበረ ሴራ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ጸሐፊዎቹ ተደጋግፈው የሚገኙት ሆን ብለው አይደለም። ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የነበረው ማቴዎስ “ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ቤት ገብቶ አማቱን በንዳድ ታማ ተኝታ አያት” ሲል ጽፏል። (ማቴዎስ 8:14፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) እዚህ ላይ ማቴዎስ ለተነሳበት ርዕሰ ጉዳይ አስፈላጊ ያልሆነ ዝርዝር ጉዳይ ጠቅሷል። ጴጥሮስ ያገባ ሰው እንደነበረ አመለከተ። ጳውሎስ ይህን ሐቅ በመደገፍ “እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና . . . እንደ ኬፋም ክርስቲያን ሚስት ይዤ የመዞር መብት የለኝምን?” ሲል ጽፏል።b (1 ቆሮንቶስ 9:5፤ ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ጳውሎስ ይህን የጻፈው በእርሱ ላይ ለተሰነዘረው አግባብ ያልሆነ ትችት መልስ ሲሰጥ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 9:1-4) ይህ አነስተኛ የሆነ ሐቅ፣ ማለትም ጴጥሮስ ያገባ ሰው ስለመሆኑ ጳውሎስ የተናገረው ሐቅ በአጋጣሚ የተነገረ እንጂ የማቴዎስ ታሪክ ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ ታስቦ የተነገረ አይደለም።
አራቱም የወንጌል ጸሐፊዎች ማለትም ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ሠይፉን መዝዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ ጆሮ እንደቆረጠ ጽፈዋል። “የባርያውም ስም ማልኮስ ነበረ” በማለት አስፈላጊ የማይመስል ዝርዝር ጉዳይ አክሎ የጻፈው ግን ዮሐንስ ብቻ ነው። (ዮሐንስ 18:10, 26) ዮሐንስ ብቻ የሰውዬውን ስም የጠቀሰው ለምንድን ነው? ታሪኩ ጥቂት ቁጥሮች ዝቅ ይልና በሌላ በየትም ቦታ ያልተጠቀሰ አንድ አነስተኛ ሐቅ አስፍሯል። ዮሐንስ “በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ” ሰው ነበር። በተጨማሪም የሊቀ ካህናቱ ቤተሰብና አገልጋዮች የሚያውቁት ሰው ሲሆን እርሱም ያውቃቸው ነበር። (ዮሐንስ 18:15, 16) ስለዚህ ዮሐንስ ጉዳት የደረሰበትን ሰው በስም መጥቀሱና ከሰውዬው ጋር የማይተዋወቁት ሌሎቹ ጸሐፊዎች በስም አለመጥቀሳቸው ተገቢ ነው።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በአንድ ታሪክ ላይ ሳይጠቀሱ የታለፉ ዝርዝር ጉዳዮች በሌላ ቦታ ላይ በአጋጣሚ ተጠቅሰው እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ በአይሁዳውያን የሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት እንደቀረበ የሚናገረው የማቴዎስ ትረካ “በጥፊ መትተው ክርስቶስ ሆይ፣ በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገርልን” ያሉት ሰዎች እንደነበሩ ገልጿል። (ማቴዎስ 26:67, 68፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) በጥፊ የመታው ሰው እዚያው እፊቱ ቆሞ እያለ ኢየሱስ ማን በጥፊ እንደመታው ‘ትንቢት እንዲናገር’ የጠየቁት ለምንድን ነው? ማቴዎስ አይገልጽልንም። ይሁን እንጂ ሌሎቹ ሁለት የወንጌል ጸሐፊዎች በዚህ ትረካ ላይ የጎደለውን ነገር አሟልተዋል። የኢየሱስ አሳዳጆች በጥፊ ከመመታቱ በፊት ፊቱን ሸፍነውት ነበር። (ማርቆስ 14:65፤ ሉቃስ 22:64) ማቴዎስ እያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ ሳይጠቀስ እንዳያልፍ ተጠንቅቆ አልጻፈም።
የዮሐንስ ወንጌል እጅግ ብዙ ሰዎች የኢየሱስን ትምህርት ለማዳመጥ ስለተሰበሰቡበት ሁኔታ ይነግረናል። ታሪኩ እንደሚለው ኢየሱስ ሰዎቹን በተመለከተ ጊዜ “ፊልጶስን:- እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን?” ብሎ ጠየቀው። (ዮሐንስ 6:5) ኢየሱስ በዚያ ከነበሩት ደቀ መዛሙርት ለይቶ ፊልጶስን እንጀራ የት ሊገዙ እንደሚችሉ የጠየቀው ለምንድን ነው? ጸሐፊው ምክንያቱን አይነግረንም። ይሁን እንጂ ሉቃስ ስለዚሁ ጉዳይ በሚተርከው ዘገባው ላይ ይህ ነገር የተፈጸመው በገሊላ ባሕር ሰሜናዊ ዳርቻ በምትገኘው በቤተሳይዳ ከተማ አቅራቢያ እንደሆነ ገልጿል። የዮሐንስ ወንጌል ደግሞ ቀደም ሲል “ፊልጶስም . . . ከቤተሳይዳ” እንደነበረ ገልጿል። (ዮሐንስ 1:45፤ ሉቃስ 9:10) ስለዚህ ኢየሱስ በዚያ አቅራቢያ የምትገኘው ከተማ ነዋሪ የነበረ ሰው መጠየቁ ተገቢ ነበር። በዝርዝር ጉዳዮች ረገድ ያለው ስምምነትና መደጋገፍ በጣም አስደናቂ ቢሆንም ሆን ተብሎ ታስቦ የተደረገ አይደለም።
በአንዳንድ ሁኔታዎች አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮች አለመጠቀሳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን ቃል ይበልጥ አሳማኝ እንዲሆን አድርጓል። ለምሳሌ ያህል የ1ኛ ነገሥት ጸሐፊ በእስራኤል ምድር ስለነበረ አስከፊ ድርቅ ጽፏል። ድርቁ በጣም የከፋ ከመሆኑ የተነሳ ንጉሡ የፈረሶቹንና የበቅሎዎቹን ሕይወት የሚያቆይበት ውኃና ሣር አጥቶ ነበር። (1 ነገሥት 17:7፤ 18:5) ይሁን እንጂ ይኸው ታሪክ ነቢዩ ኤልያስ አንድ ካሬ ሜትር መጠን ሊኖረው የሚችል ጉድጓድ የሚሞላ ውኃ (መሥዋዕት ሲያቀርብ የሚጠቀምበት) ወደ ቀርሜሎስ ተራራ እንዲያመጡለት እንደጠየቀ ይናገራል። (1 ነገሥት 18:33-35) ያን የመሰለ ድርቅ እያለ ይህን የሚያክል ውኃ ከየት መጣ? የአንደኛ ነገሥት መጽሐፍ ጸሐፊ ይህን ለማብራራት ያደረገው ጥረት የለም። ይሁን እንጂ በእስራኤል የሚኖር ማንኛውም ሰው ቀርሜሎስ በሜዲትራንያን ባሕር ዳርቻ ላይ እንደሚገኝ ያውቃል። ይህም በአጋጣሚ በዚሁ ታሪክ ላይ ዝቅ ብሎ ተገልጿል። (1 ነገሥት 18:43) ስለዚህ የባሕር ውኃ በቀላሉ ማግኘት ይቻል ነበር። ይህ በሌሎች ጉዳዮች ረገድ ዝርዝር ጉዳዮችን በጥንቃቄ የመዘገበ መጽሐፍ ሐቅ መስሎ የቀረበ ልብ ወለድ ታሪክ ቢሆን ኖሮ ይህን የሚያህል የማስመሰል ችሎታ ያለው ጸሐፊ ይህን የመሰለ ግራ የሚያጋባ ነገር እንዲኖር ያደርግ ነበርን?
ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ሊጣልበት የሚችል መጽሐፍ ነውን? አርኪኦሎጂስቶች መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሳቸው ሕዝቦች፣ ቦታዎችና ክንውኖች በእርግጥ የነበሩ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ በርካታ የዕደ ጥበብ ሥራዎች አግኝተዋል። በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ማስረጃ ደግሞ ከዚህ ይበልጥ አሳማኝ ነው። ሐቀኛ የሆኑት ጸሐፊዎች የተፈጸሙትን ሁኔታዎች ሲጽፉ የማንንም ስህተት፣ የገዛ ራሳቸውን ስህተት ጭምር ለመሸፋፈን አልሞከሩም። ሆን ተብሎ ሳይሆን በአጋጣሚ ተደጋጋፊ ሆነው የተገኙትን ዝርዝር ጉዳዮች ጨምሮ የጽሑፎቹ ውስጣዊ ስምምነት የመጽሐፉ “ምሥክርነት” እውነተኛ መሆኑን ያረጋግጣሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን የመሰሉ ‘እውነተኛነቱን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች’ ያሉት መጽሐፍ በመሆኑ በእርግጥም እምነት ሊጣልበት የሚችል መጽሐፍ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ከዚህ የአርኪኦሎጂ ግኝት በኋላ ፕሮፌሰር አንድሬ ለሜር ሜሻ ስቴላ የተባለው በ1868 የተገኘ የድንጋይ ሐውልት (የሞዓባውያን አለት ተብሎም ይጠራል) አንድ ጉዳት የደረሰበት ክፍል በሚታደስበት ጊዜ “የዳዊት ቤት” የሚል ሐረግ እንደተገኘበት ሪፖርት አድርገዋል።4
b “ኬፋ” “ጴጥሮስ” ለሚለው ስም ሴምያዊ ተመሳሳይ ነው።—ዮሐንስ 1:43
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቴል ዳን ቁራጭ
[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ2 ነገሥት 18:13, 14 የተጠቀሰውን የለኪሶ መወረር የሚያመለክት የአሦራውያን የግድግዳ ሥዕል