የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ክርስቲያናዊ አንድነት ሲባል በሁሉም ነገር አንድ መሆን ማለት ነውን?
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አንድነት መኖሩ በጣም አስፈላጊ ነው። በመሠረተ ትምህርቶች ረገድ የሚፈጠር ልዩነት ከፍተኛ አለመግባባት፣ ጥል፣ አልፎ ተርፎም ጠላትነት ያስከትላል። (ሥራ 23:6-10) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 14:33) ከዚህ የተነሣ ክርስቲያኖች አንድ ንግግር እንዲናገሩ እንዲሁም በአንድ ልብና በአንድ አሳብ የተባበሩ እንዲሆኑ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 1:10
እነዚህ ቃላትና ተመሳሳይ የሆኑ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦች ክርስቲያኖች በማንኛውም ዘርፍ አንድ ዓይነት እንዲሆኑ የሚያበረታቱ ናቸውን? (ዮሐንስ 17:20-23፤ ገላትያ 3:28) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጾ በሚገኘው መሠረት እውነተኛ ክርስትና በግለሰቦች ባህርይ ረገድ ልዩነት መኖሩን ያወግዛልን? ሁሉም ክርስቲያኖች በአንድ መልክ እንዲቀረጹ ይጠበቅባቸዋልን?
አምላክ በግለሰብ ደረጃ ወደ ራሱ ይስበናል
አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ተራውን ሕዝብ እገሌ ከገሌ ሳይል ለመቆጣጠር የተዘጋጀ የመጨቆኛ መሣሪያ ነው የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው። እርግጥ አንዳንድ የሃይማኖት ቡድኖች መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ መልኩ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ተጠቅመውበታል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለቅዱሳን ጽሑፎችና ለመለኮታዊው ደራሲያቸው ከዚህ ፍጹም የተለየ አመለካከት ነበረው። አምላክን የገለጸው ለፍጥረታቱ በሙሉ በጥልቅ የሚያስብ አካል አድርጎ ነበር።
በዮሐንስ 6:44 ላይ ኢየሱስ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” በማለት ተናግሯል። እዚህ ላይ የገባው ግሥ አምላክ ሰዎችን ያለ ፍላጎታቸው ወደ ራሱ እንደሚስብ አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ልብን በመማረክ ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ሰዎችን ወደ ራሱ ይስባል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደገለጹት ‘አእምሯችን እንዲያምን ለማድረግ አምላክ የሚያሳድረው ተጽእኖ’ አለ። ፈጣሪ ሰብዓዊውን ቤተሰብ የራሳቸው ስብዕና የሌላቸው ሰዎች ስብስብ አድርጎ አይመለከተውም። ግለሰቦችን ከገመገመ በኋላ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ወደ ራሱ ይስባል።—መዝሙር 11:5፤ ምሳሌ 21:2፤ ሥራ 13:48
ሐዋርያው ጳውሎስ ከሁኔታዎች ጋር ራሱን እንዴት ያስማማ እንደነበር ተመልከት። ግለሰቦች የተለያዩ ፍላጎቶች እንዳሏቸው ከመገንዘቡም በላይ እያንዳንዱ ብሔረሰብ ወይም መደብ የራሱ የሆነ አመለካከት ያለው መሆኑን አምኖ ተቀብሎ ነበር። ከዚያም ከሁኔታዎቹ ጋር የሚስማማ አቀራረብ ተጠቅሟል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አይሁድንም እጠቅም ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ... ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ።”—1 ቆሮንቶስ 9:20-22
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ ሰዎችን ሁሉ በአንድ ዓይን አልተመለከተም፤ ወይም ሁሉንም በአንድ ዓይነት መንገድ አልቀረባቸውም። እንደሚከተለው ሲል አበረታቷቸዋል:- “ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፣ በጨው እንደ ተቀመመ፣ በጸጋ ይሁን።” (ቆላስይስ 4:6) አዎን፣ ጳውሎስና ሌሎቹ ክርስቲያኖች አንድን ሰው ለመርዳት እያንዳንዱ ሰው ከሌላው የተለየ መሆኑን መገንዘብና ማክበር ነበረባቸው።
የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ
ይህ በግለሰብ ደረጃ ለአንድ ሰው የሚሰጠው ክብር ሰውየው የክርስቲያን ጉባኤ አባል ከሆነ በኋላም ይቀጥላል። የአምላክ ሕዝቦች በሥልጣን ላይ ካሉት ሰዎች ምርጫ ጋር ሙሉ በሙሉ ለመስማማት ሲሉ ባህሪዎቻቸውን ትተው ፍጹም አንድ ዓይነት ይሆናሉ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የተለያየ ዓይነት ባህርይ፣ ችሎታ፣ ልማድና አመለካከት ያላቸው ናቸው። የእያንዳንዱን ግለሰብ ስብዕና እንደ ሳንካ ወይም ጠንቅ አድርጎ የሚመለከተው አይኖርም። ይህ ሁኔታ አምላክ መጀመሪያም የነበረው ዓላማ ነው።
ይህም በመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለጻድቅ ሰዎች ቃል በተገባው አዲስ ዓለም ሰዎች ፍጹም በሚሆኑበት ጊዜም የተለያየ ባህርይ ይኖራቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋልa (እንግሊዝኛ) የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክለፒዲያ “ፍጽምና” በሚለው ርዕስ ሥር የሚከተለውን ትክክለኛ ሐሳብ ይሰጣል:- “ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ሰዎች እንደሚገምቱት ፍጽምና ሲባል በሁሉም ነገር አንድ መሆን ማለት አይደለም። የይሖዋ ‘ፍጹም ሥራ’ ውጤት የሆነው ስፍነ-እንሰሳ (ዘፍ[ጥረት] 1:20-24፤ ዘዳ[ግም] 32:4) ብዙ ዓይነት እንስሳትን ያቀፈ ነው።”
ማስተዋል አክሎ እንዲህ ብሏል:- “በተመሳሳይም የፕላኔቷ ምድር ፍጹም መሆን፣ ዓይነት፣ ለውጥ ወይም ልዩነት ቦታ አይኖራቸውም ማለት አይደለም፤ ቀላልና ውስብስብ፣ ያጌጠና ያላጌጠ፣ መራራና ጣፋጭ፣ ሸካራና ለስላሳ፣ ለጥ ያለው መስክና ጥቅጥቅ ያለ ጫካ፣ ተራራና ሸለቆ ይኖራል። የምድር ፍጽምና በፀደይ መግቢያ ላይ የሚኖረውን ደስ የሚል ነፋሻ አየር፣ በበጋ የሚኖረውን ሙቀትና ጥርት ያለ ሰማይ፣ በበልግ የሚታዩትን አስደሳች ቀለማትና በመሬት ላይ ተነጥፎ የሚታየውን ማራኪ የበረዶ ክምር ያቀፈ ይሆናል። (ዘፍ[ጥረት] 8:22) በመሆኑም ፍጹም የሆኑ ሰዎች አንድ ዓይነት ስብዕና፣ ክህሎትና ችሎታ ያላቸው አይሆኑም።”
ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት
ይሁን እንጂ እውነተኛ ክርስትና ራስ ወዳድ በመሆን በዙሪያችን ላሉ ሰዎች ደንታ ቢስ መሆንን አያበረታታም። ሐዋርያው ጳውሎስ ሌሎችን ላለማደናቀፍ ሲል በእያንዳንዱ የሕይወት ዘርፍና በምግባሩ ረገድ ጥንቃቄ ያደርግ ነበር። ለቆሮንቶስ ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሏል:- “አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም።” (2 ቆሮንቶስ 6:3) አንዳንድ ጊዜ የግል ፍላጎቶቻችንን ተወት አድርገን ከእኛ ምርጫ ይልቅ ሌሎች ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ቅድሚያ መስጠት አለብን። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች ሲጽፍ “ሥጋን አለመብላት ወይንንም አለመጠጣት ወንድምህም የሚሰናከልበትን አለማድረግ መልካም ነው” ብሏል።—ሮሜ 14:21
በተመሳሳይም ዛሬ አንድ ሰው በመጠጥ ረገድ ራሱን የመቆጣጠር ችግር ካለበት ሰው ጋር በሚሆንበት ጊዜ ላለመጠጣት ሊመርጥ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 10:23, 24) ይህን የሚያደርገው ከሌላኛው ሰው ምርጫ ጋር የግድ መስማማት ስላለበት ሳይሆን እንዲህ ማድረጉ ላቅ ያለ የደግነትና የፍቅር መግለጫ ስለሆነ ነው። “ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና።” ኢየሱስ ራሱን የቻለ ግለሰብ ቢሆንም የሌሎችን ስሜት በመጫን የራሱን ምርጫ ለማስፈጸም አልጣረም።—ሮሜ 15:3
ያም ሆኖ ግን ከእውነተኛ ክርስትና ማራኪ ገጽታዎች ውስጥ አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች እስካልተጣሱ ድረስ የግለሰቦችን መብትና ምርጫ የሚያከብር መሆኑ ነው። አምላክ ከሌላው የተለየን አድርጎ እንደሠራን ያስተምራል። በ1 ቆሮንቶስ 2:11 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው?” የሌሎችን አመለካከት ለመረዳት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ሆኖም ይህ ጥቅስ እያንዳንዳችን ፈጣሪያችንና እኛ ብቻ ልናስተውል የምንችለው ልዩ የሆነ ስብዕና እንዳለን ያሳያል። በመረጥነው መንገድ የምናሳየው “የተሰወረ የልብ ሰው” አለን።—1 ጴጥሮስ 3:4
ስለ አንድነት ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያናዊ ሚዛንን በመጠበቅ ረገድ ግሩም የሆነ ምሳሌ ትቷል። የክርስቶስ ሐዋርያ እንደመሆኑ መጠን ሥልጣን ቢኖረውም የራሱን አመለካከት በሌሎች ላይ ላለመጫን ይጠነቀቅ ነበር።
ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ በዚህ ፍጽምና በጎደለው ዓለም ውስጥ በነጠላነት መኖር ጠቃሚ መሆኑን አጥብቆ ያምናል። “እንዲህ በሚያደርጉ [የሚያገቡ] በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል” እንዲሁም “[ባሏ የሞተባት ሴት] እንደ ምክሬ ግን እንዳለች ብትኖር ደስተኛ ናት” ብሎ ሲጽፍ ራሱም ነጠላ ነበር። እነዚህ ቃላት በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ክፍል መሆናቸው አመለካከቱ ስህተት እንዳልሆነ ያሳያል። ሆኖም “ብታገባ ኃጢአት አትሠራም” ብሎም ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 7:28, 40
የሚከተሉት የጳውሎስ ቃላት እንደሚያስገነዝቡት አብዛኞቹ ሐዋርያት ያገቡ ወንዶች እንደነበሩ ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል:- “እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች እንደ ኬፋም፣ እኅት ሚስታችንን ይዘን ልንዞር መብት የለንምን?” (1 ቆሮንቶስ 9:5) ክርስቲያኖች በዚህ ጉዳይ ላይ ከጳውሎስ የተለየ ምርጫ ሊያደርጉ እንደሚችሉና ጳውሎስም ያደረጉትን ምርጫ እንደሚያከብርላቸው ያውቁ ነበር።
አምላክን የሚያመልኩ ሰዎች ከየራሳቸው ስብዕና ጋር በሚስማማ መንገድ እምነታቸውን የመግለጽ ነፃነት አላቸው። ሌላው ቀርቶ አምላክ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የየራሳቸውን የአጻጻፍ ስልት በመጠቀም እንዲጽፉ ፈቅዶላቸዋል። ለምሳሌ ያህል ነህምያ ታሪኩን የጻፈው በአንደኛ መደብ ቢሆንም ትሑት ሰው ነበር። (ነህምያ 5:6, 19) በሌላ በኩል ደግሞ ሐዋርያው ዮሐንስ ከሌላው ልቆ ለመታየት ባለመፈለጉ በወንጌል ዘገባው ውስጥ አንድም ጊዜ እንኳ ስሙን ያልጠቀሰ ሲሆን ስለ ራሱ የተናገረውም በጥቂት ቦታዎች ላይ ነው። አምላክ የሁለቱንም የአጻጻፍ ስልት የተቀበለው ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠብቀው እንዲቆዩም አድርጓል።
ሚዛናዊነትና ምክንያታዊነት የሚንጸባረቅባቸው ተመሳሳይ ምሳሌዎች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በብዛት ይገኛሉ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ክርስቲያናዊ አንድነት ሲባል በሁሉም ነገር አንድ መሆን ማለት አይደለም። እርግጥ መንፈሳዊ ባህርያት ከሌሉ የአስተዳደግና የአመለካከት ልዩነቶች መከፋፈልን ሊያስከትሉ ይችላሉ። (ሮሜ 16:17, 18) ይሁን እንጂ ‘ፍጹም የአንድነት ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን በምንለብስበት’ ጊዜ የሌሎችን ልዩ ልዩ ባህርያት መቀበልንና ማድነቅን እንማራለን።—ቆላስይስ 3:14
መጽሐፍ ቅዱስ “ስለዚህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ” ይላል። (ሮሜ 15:7) በአምላክ መንፈስ እርዳታ ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥ ባለው የተለያየ ባህርይ እየተደሰቱ አንድነትን በመጠበቅ ረገድ ጥሩ ሚዛናዊነት ሊያሳዩ ይችላሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ፈጣሪ ሰብዓዊውን ቤተሰብ የየራሳቸው ስብዕና የሌላቸው ሰዎች ስብስብ አድርጎ አይመለከተውም
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
እያንዳንዳችን ፈጣሪያችንና እኛ ብቻ ልናስተውል የምንችለው ልዩ የሆነ ስብዕና አለን