እውነት ነፃ የሚያወጣን እንዴት ነው?
1 በአንድ ወቅት ኢየሱስ በእርሱ ላመኑት አይሁዶች “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ብሏቸው ነበር። (ዮሐ. 8:32) ኢየሱስ የተናገረው ከተራ የዜግነት መብቶች ስለሚበልጥና ሃብታም ድሃ፣ የተማረ ያልተማረ ሳይባል ሁሉም ሰው ሊያገኘው ስለሚችለው ነፃነት ነበር። ኢየሱስ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ስለሚያወጣ እውነት አስተምሯል። “ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ” መሆኑን ኢየሱስ ተናግሯል። (ዮሐ. 8:34) ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ‘ከጥፋት ባርነት ነፃ ወጥተው ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት የሚደርሱበትን’ ጊዜ በጉጉት እንደምንጠባበቅ አያጠራጥርም!—ሮሜ 8:21
2 ስለ ኢየሱስና የአምላክን ዓላማ በማስፈጸም ረገድ ስለተጫወተው ሚና የሚናገረው እውነት እንዲህ ዓይነቱን ነፃነት ያስገኛል። ይህ እውነት ኢየሱስ ለእኛ ሲል ስላቀረበው ቤዛዊ መሥዋዕት የሚገልጸውን እውቀትም ያጠቃልላል። (ሮሜ 3:24) የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መቀበላችንና ለዚህ እውነት ራሳችንን በታዛዥነት ማስገዛታችን በአሁኑ ጊዜም እንኳን ከፍርሃት፣ ከተስፋ መቁረጥና ከማንኛውም ዓይነት ጎጂ ልማድ ነፃ ያወጣናል።
3 ከፍርሃትና ከተስፋ መቁረጥ ነፃ መውጣት:- ክፋት በምድር ላይ የተስፋፋበትን ምክንያትና በቅርቡም ከምድር ገጽ እንደሚወገድ ማወቃችን ዛሬ በዓለም ላይ ባሉት ሁኔታዎች ተስፋ እንዳንቆርጥ ያደርገናል። (መዝ. 37:10, 11፤ 2 ጢሞ. 3:1፤ ራእይ 12:12) እውነት ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ከሚናገሩት የሐሰት ትምህርቶችም ነፃ ያወጣናል። ሙታን ሊጎዱን እንደማይችሉ፣ በሲኦል ለዘላለም እየተሰቃዩ እንዳልሆኑና አምላክ በመንፈሳዊው ዓለም ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ ሲል ሰዎች እንዲሞቱ እንደማያደርግ እናውቃለን።—መክ. 9:5፤ ሥራ 24:15
4 ልጃቸውን በአደጋ ያጡ አንድ አባትና እናት ይህን እውነት ማወቃቸው ኃዘናቸውን መቋቋም እንዲችሉ ረድቷቸዋል። እናትየው እንዲህ ትላለች:- “ልጃችንን በትንሣኤ እስክናገኘው ድረስ በሕይወታችን ውስጥ በምንም ነገር ሊሞላ የማይችል ክፍተት እንዳለ ይሰማናል። ያም ሆኖ ሐዘናችን ጊዜያዊ ብቻ እንደሆነ ተገንዝበናል።”
5 ጎጂ ከሆኑ ልማዶች ነፃ መውጣት:- የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አንድ ሰው አመለካከቱንና ባሕርያቱን እንዲለውጥ በመርዳት ጎጂ ከሆኑ ልማዶች ነፃ ያወጣዋል። (ኤፌ. 4:20-24) ሐቀኛና ታታሪ መሆን ድህነትን ለማሸነፍ ያስችላል። (ምሳሌ 13:4) የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር ማሳየት ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት እንዲሻሻል ያደርጋል። (ቆላ. 3:13, 14) ክርስቲያናዊ የራስነት ሥርዓትን ማክበር በቤተሰብ ውስጥ የሚነሱ ችግሮችን ለመቀነስ ይረዳል። (ኤፌ. 5:33-6:1) ከስካር፣ ከጾታ ብልግና፣ ትንባሆ ከማጨስና ሱስ የሚያስይዙ ዕፆችን ከመጠቀም መራቅ ጤንነታችንን በመጠበቅ ረገድ አስተዋጽኦ ያደርጋል።—ምሳሌ 7:21-23፤ 23:29, 30፤ 2 ቆሮ. 7:1
6 ለዘጠኝ ዓመታት ያህል አደገኛ ዕፆችን ይወስድ የነበረ አንድ ወጣት ከዚህ ሱስ ለመላቀቅ ተቸግሮ ነበር። አንድ ቀን መንገድ ላይ የምታገለግል አንዲት አስፋፊ ታነጋግረዋለች። ወጣቱ ጽሑፍ ከወሰደ በኋላ ምሥክሮቹ ቤቱ መጥተው እንዲጠይቁት ቀጠሮ ያዙ። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ከሁለት ወራት በኋላ ዕፅ መውሰዱን ሙሉ በሙሉ ያቆመ ሲሆን ለስምንት ወራት ያህል ካጠና በኋላ ተጠመቀ። ወንድሙና የወንድሙ ባለቤት ከነበረበት ሱስ መላቀቅ እንደቻለ ሲመለከቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ።
7 ሌሎችም ነፃነት እንዲያገኙ እርዷቸው:- ዕድሜያቸውን ሙሉ በሐሰት ትምህርቶች ተተብትበው የኖሩ ሰዎች የአምላክ ቃል የሚያስገኘውን ነፃነት በቀላሉ ለመረዳት ይከብዳቸው ይሆናል። በመሆኑም እነዚህን ሰዎች ለመርዳት ትጋት የተሞላበት ጥረትና ጥሩ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል። (2 ጢሞ. 4:2, 5) ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ ‘ለተማረኩት ነፃነትን በማወጁ’ ሥራ በቅንዓት መካፈል ይገባናል። (ኢሳ. 61:1) ክርስቲያናዊ ነፃነት የዘላለም ሕይወት ስለሚያስገኝ ውድ ነገር ነው።—1 ጢሞ. 4:16