-
“ሕዝቤን አጽናኑ”የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 1
-
-
5, 6. (ሀ) ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም የሚደረገው ረጅም ጉዞ የአምላክ የተስፋ ቃል ፍጻሜውን እንዳያገኝ እንቅፋት የማይሆነው እንዴት ነው? (ለ) አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው መመለሳቸው በሌሎች ብሔራት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ምንድን ነው?
5 ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም የሚደረገው ጉዞ ከ800 እስከ 1, 600 ኪሎ ሜትር ይፈጃል። ይህ ለመሄድ በሚመርጡት አቅጣጫ ላይ የተመካ ነው። ረጅሙ ጉዞ የአምላክ የተስፋ ቃል ፍጻሜውን እንዳያገኝ እንቅፋት ይፈጥር ይሆን? በፍጹም! ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የአዋጅ ነጋሪ ቃል:- የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፣ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካክሉ። ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፣ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማውም ይቃናል፣ ስርጓጉጡም ሜዳ ይሆናል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፣ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል፣ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።”—ኢሳይያስ 40:3-5
6 ብዙውን ጊዜ ምሥራቃውያን ገዥዎች ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ትላልቅ ድንጋዮችን በማንሳት መሸጋገሪያ በመሥራትና አባጣ ጎርባጣውን መሬት በመደልደል መንገድ የሚያዘጋጁ ሰዎችን በፊታቸው ይልኩ ነበር። ወደ አገራቸው ለሚመለሱት አይሁዳውያን ደግሞ አምላክ ራሱ ከፊት ከፊታቸው እየሄደ እንቅፋቱን ሁሉ የሚያስወግድላቸው ያህል ነበር። ደግሞም የይሖዋን ስም የተሸከመ ሕዝብ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ እነርሱን ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ የገባውን ቃል መፈጸሙ ለአሕዛብ ሁሉ ክብሩ እንዲገለጥ የሚያደርግ እርምጃ ይሆናል። እነዚያ ብሔራት ወደዱም ጠሉ ይሖዋ የገባውን ቃል የሚፈጽም አምላክ መሆኑን በዓይናቸው ለማየት ይገደዳሉ።
7, 8. (ሀ) በኢሳይያስ 40:3 ላይ የሚገኙት ቃላት በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነው? (ለ) የኢሳይያስ ትንቢት በ1919 ምን ታላቅ ፍጻሜ ነበረው?
7 የዚህ ትንቢት ፍጻሜ በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተከናወነው መልሶ ማቋቋም ብቻ ነው ማለት አይደለም። በአንደኛው መቶ ዘመንም ትንቢቱ ተፈጻሚነት ነበረው። መጥምቁ ዮሐንስ በኢሳይያስ 40:3 ፍጻሜ መሠረት “በምድረ በዳ የሚጮኽ” ሰው ድምፅ ሆኖ ብቅ ብሏል። (ሉቃስ 3:1-6) ዮሐንስ የኢሳይያስ ቃላት ለእርሱ እንደሚሠሩ በመንፈስ አነሳሽነት ተናግሯል። (ዮሐንስ 1:19-23) ከ29 እዘአ አንስቶ ዮሐንስ ለኢየሱስ ክርስቶስ መንገዱን አዘጋጅቷል።a ዮሐንስ አስቀድሞ ያሰማው የነበረው አዋጅ ሕዝቡ ቃል የተገባለትን መሲህ ይሰሙና ይከተሉ ዘንድ በጉጉት እንዲጠባበቁ አነሳስቷቸዋል። (ሉቃስ 1:13-17, 76) ይሖዋ ንስሐ የሚገቡትን ሰዎች በኢየሱስ አማካኝነት በአምላክ መንግሥት ሥር ብቻ ሊገኝ ወደሚችለው ነፃነት ይኸውም ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ወደ መሆን ይመራቸዋል። (ዮሐንስ 1:29፤ 8:32) በ1919 የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች ከታላቂቱ ባቢሎን ነፃ ወጥተው ወደ ንጹሕ አምልኮ ሲመለሱ የኢሳይያስ ቃላት ታላቅ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል።
-
-
“ሕዝቤን አጽናኑ”የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 1
-
-
a ኢሳይያስ የተናገረው የይሖዋን መንገድ ስለ ማዘጋጀት ነው። (ኢሳይያስ 40:3) ወንጌሎች ደግሞ ይህንኑ ትንቢት የሚጠቅሱት መጥምቁ ዮሐንስ ለኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ በማዘጋጀት ካከናወነው ሥራ ጋር በማያያዝ ነው። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን በመንፈስ አነሳሽነት የጻፉት ሰዎች ትንቢቱን በዚህ መልክ የተጠቀሙበት ኢየሱስ አባቱን ስለሚወክልና በእርሱም ስም ስለመጣ ነው።—ዮሐንስ 5:43፤ 8:29
-