ምዕራፍ አሥራ ሁለት
“ያለምሳሌ አይነግራቸውም ነበር”
1-3. (ሀ) ከኢየሱስ ጋር የሚጓዙት ደቀ መዛሙርት ምን ለየት ያለ መብት አግኝተዋል? ኢየሱስስ፣ ያስተማራቸውን ትምህርቶች በቀላሉ ማስታወስ እንዲችሉ የረዳቸው እንዴት ነው? (ለ) ውጤታማ የሆኑ ምሳሌዎች በቀላሉ ከአእምሮ የማይጠፉት ለምንድን ነው?
ከኢየሱስ ጋር የሚጓዙት ደቀ መዛሙርት ብዙዎች ሊያገኙት ያልቻሉትን ለየት ያለ መብት አግኝተዋል። ታላቁ አስተማሪ ራሱ ሲያስተምር መስማት ችለዋል። የአምላክን ቃል ሲያብራራና አስደሳች የሆኑ እውነቶችን ሲያስተምር በጆሯቸው የመስማት አጋጣሚ አግኝተዋል። ለአሁኑ፣ ኢየሱስ የተናገራቸውን ውድ የሆኑ ነገሮች በአእምሯቸውና በልባቸው መያዝ ያስፈልጋቸዋል፤ ምክንያቱም የተናገራቸው ነገሮች በጽሑፍ የሚሰፍሩበት ጊዜ ገና አልደረሰም።a ኢየሱስም ቢሆን ትምህርቶቹን ማስታወስ ቀላል እንዲሆንላቸው አድርጓል። እንዴት? ግሩም በሆነው የማስተማሪያ ዘዴው በተለይም ምሳሌዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠቀም ነው።
2 በእርግጥም፣ ውጤታማ የሆኑ ምሳሌዎች በቀላሉ ከአእምሮ አይጠፉም። አንድ ደራሲ እንደተናገሩት ምሳሌዎች “ጆሮን ወደ ዓይን ይለውጣሉ”፤ እንዲሁም “አድማጮች የሚሰሙትን ነገር በዓይነ ሕሊናቸው እንዲሥሉት የማድረግ ኃይል አላቸው።” በጥቅሉ ሲታይ፣ ምስሎች አእምሯችን ትምህርት መቀበል ቀላል እንዲሆንለት ያደርጋሉ፤ በመሆኑም ምሳሌዎች ከበድ ያለን ሐሳብ እንኳ በቀላሉ ለመረዳት ያስችሉናል። ምሳሌዎች በቃላት ላይ ሕይወት ይዘራሉ፤ ይህም ትምህርቱ በአእምሯችን ውስጥ ለዘለቄታው እንዲቀረጽ ያደርጋል።
3 ምሳሌዎችን ግሩም አድርጎ በመጠቀም ረገድ የኢየሱስ ክርስቶስን ያህል የተዋጣለት አስተማሪ በምድር ላይ የለም። ኢየሱስ የተናገራቸው ምሳሌዎች እስከ ዛሬም ድረስ በቀላሉ ይታወሳሉ። ኢየሱስ በዚህ የማስተማሪያ ዘዴ ብዙ ጊዜ የተጠቀመው ለምንድን ነው? ምሳሌዎቹን ውጤታማ ያደረጋቸው ምንድን ነው? እኛስ ይህን የማስተማሪያ ዘዴ መልመድ የምንችለው እንዴት ነው?
ኢየሱስ በምሳሌዎች ያስተማረው ለምንድን ነው?
4, 5. ኢየሱስ ምሳሌዎችን የተጠቀመው ለምንድን ነው?
4 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ምሳሌዎችን ለመጠቀም የመረጠባቸውን ሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ይገልጽልናል። አንደኛው ምክንያት፣ በምሳሌዎች መጠቀሙ ትንቢት እንዲፈጸም የሚያደርግ መሆኑ ነው። ማቴዎስ 13:34, 35 እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ። እንዲያውም ያለምሳሌ አይነግራቸውም ነበር፤ ይህም የሆነው ‘አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ . . .’ ተብሎ በነቢዩ የተነገረው እንዲፈጸም ነው።” ማቴዎስ የጠቀሰው ነቢይ የመዝሙር 78:2 ጸሐፊ ነው። ይህ መዝሙራዊ በአምላክ መንፈስ ተመርቶ ይህን ሐሳብ የጻፈው ኢየሱስ ከመወለዱ ከብዙ መቶ ዘመናት ቀደም ብሎ ነው። እስቲ ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስብ። ይሖዋ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት መሲሑ በምሳሌዎች እንዲያስተምር ወስኖ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ ይህን የማስተማሪያ ዘዴ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው በግልጽ ማየት ይቻላል።
5 ሁለተኛ፣ ኢየሱስ ምሳሌዎችን የተጠቀመው ልበ ‘ደንዳና’ የሆኑ ሰዎችን ለመለየት ነው። (ማቴዎስ 13:10-15፤ ኢሳይያስ 6:9, 10) ኢየሱስ የተናገራቸው ምሳሌዎች የሰዎችን ውስጣዊ ዝንባሌ የሚያጋልጡት በምን መንገድ ነው? አንዳንድ ጊዜ ምሳሌዎችን የሚጠቀመው፣ አድማጮቹ የተናገረውን ነገር ይበልጥ እንዲያስረዳቸው እንዲጠይቁት ሲል ነበር። ትሑት የሆኑ ሰዎች ያልገባቸውን ነገር ለመጠየቅ ፈቃደኞች ናቸው፤ ኩሩ ወይም ግድየለሽ ሰዎች ግን አይጠይቁም። (ማቴዎስ 13:36፤ ማርቆስ 4:34) በመሆኑም የኢየሱስ ምሳሌዎች እውነትን ለተራቡ ሰዎች እውነትን ገልጠውላቸዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኩሩ ልብ ላላቸው ሰዎች እውነትን ሸሽገውባቸዋል።
6. የኢየሱስ ምሳሌዎች ምን ጥቅሞች ነበሯቸው?
6 የኢየሱስ ምሳሌዎች ሌሎች ጥቅሞችም ነበሯቸው። የሰዎችን ፍላጎት በመቀስቀስ ለመስማት እንዲጓጉ ያደርጋሉ። በአእምሮ ውስጥ ምስል ስለሚፈጥሩ ከበድ ያሉ ትምህርቶችን መረዳት ቀላል እንዲሆን ያግዛሉ። በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው የኢየሱስ ምሳሌዎች አድማጮቹ ያስተማራቸውን ነገሮች እንዲያስታውሱ ረድተዋቸዋል። ከማቴዎስ 5:3 እስከ 7:27 ተመዝግቦ የሚገኘው የተራራው ስብከት ኢየሱስ ምሳሌያዊ አገላለጾችን በብዛት እንደሚጠቀም የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው። አንድ ምሁር እንደገለጹት ይህ የተራራ ስብከት ከ50 በላይ ዘይቤያዊ አነጋገሮችን ይዟል። ይህ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት አንድ እውነታ አስታውስ፤ የተራራውን ስብከት ድምፃችንን ከፍ አድርገን እናንብበው ብንል በ20 ደቂቃ ገደማ ልንጨርሰው እንችላለን። ኢየሱስ በአማካይ በየ20 ሴኮንዱ አንድ ዘይቤያዊ አነጋገር ተጠቅሟል ማለት ነው! ታዲያ ይህ ኢየሱስ ዘይቤያዊ አገላለጾች ያላቸውን ኃይል እንደተገነዘበ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ አይደለም?
7. ምሳሌዎችን በመጠቀም ረገድ ኢየሱስን መኮረጅ ያለብን ለምንድን ነው?
7 የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን የኢየሱስን የማስተማሪያ ዘዴ መኮረጅ እንፈልጋለን፤ ይህም የምሳሌ አጠቃቀምን ይጨምራል። ቅመሞች ምግብ እንደሚያጣፍጡ ሁሉ ውጤታማ ምሳሌዎችም ትምህርቱ ይበልጥ ማራኪ እንዲሆን ያደርጋሉ። በደንብ የታሰበባቸው ምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ በጣም አስፈላጊ የሆኑ እውነቶችን በቀላሉ ለመረዳትም ያስችላሉ። የኢየሱስን ምሳሌዎች ውጤታማ ያደረጓቸውን አንዳንድ ምክንያቶች እስቲ እንመልከት። እንዲህ ማድረጋችን ይህን ጠቃሚ የማስተማሪያ ዘዴ እንዴት በሚገባ ልንጠቀምበት እንደምንችል ለማስተዋል ይረዳናል።
ቀላል ንጽጽር መጠቀም
8, 9. ኢየሱስ ቀላል የሆኑ ንጽጽሮችን እንደተጠቀመ የሚያሳዩ ምሳሌዎች ጥቀስ። የተጠቀመባቸው ንጽጽሮች ውጤታማ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምንድን ነው?
8 ኢየሱስ ሲያስተምር ጥቂት ቃላትን ብቻ የያዙ ያልተወሳሰቡ ንጽጽሮችን ብዙ ጊዜ ይጠቀም ነበር። ሆኖም እነዚህ ጥቂት ቃላት በአእምሮ ውስጥ ቁልጭ ብለው የሚታዩ ምስሎችን ይፈጥራሉ፤ ወሳኝ መንፈሳዊ እውነቶችን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግም ያግዛሉ። ለምሳሌ ደቀ መዛሙርቱን ለኑሮ ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ከልክ በላይ መጨነቅ እንደሌለባቸው ሲያስተምር “የሰማይ ወፎችን” እና ‘የሜዳ አበቦችን’ ጠቅሶ ነበር። ወፎች አይዘሩም እንዲሁም አያጭዱም፤ የሜዳ አበቦችም ቢሆኑ አይፈትሉም እንዲሁም አይሸምኑም። ያም ሆኖ አምላክ ይንከባከባቸዋል። ነጥቡ ግልጽ ነው፦ አምላክ ወፎችንና አበቦችን የሚንከባከባቸው ከሆነ ‘ከሁሉ አስቀድመው የአምላክን መንግሥት የሚፈልጉ’ ሰዎችን እንደሚንከባከባቸው ምንም ጥርጥር የለውም።—ማቴዎስ 6:26, 28-33
9 ኢየሱስ ተለዋጭ ዘይቤዎችንም በብዛት ተጠቅሟል፤ እነዚህ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ይበልጥ ኃይል ያላቸው ንጽጽሮች ናቸው። ተለዋጭ ዘይቤ አንድን ነገር ሌላ ነገር እንደሆነ አድርጎ የሚገልጽ ዘይቤ ነው። በዚህ ጊዜም ቢሆን ኢየሱስ የተጠቀመበት ንጽጽር ቀላል ነው። በአንድ ወቅት ደቀ መዛሙርቱን “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” ብሏቸው ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ይህ ዘይቤ የሚያስተላልፈው መልእክት ቁልጭ ብሎ እንደታያቸው ጥያቄ የለውም፤ በንግግራቸውም ሆነ በተግባራቸው የእውነት ብርሃን ለሌሎች ደምቆ እንዲታይ በማድረግ ሰዎች ለአምላክ ክብር እንዲሰጡ መርዳት እንዳለባቸው መግለጹ ነበር። (ማቴዎስ 5:14-16) ኢየሱስ የተጠቀመባቸው ሌሎች ተለዋጭ ዘይቤዎችም አሉ፤ ለምሳሌ “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ” እንዲሁም “እኔ የወይኑ ተክል ነኝ፤ እናንተ ደግሞ ቅርንጫፎቹ ናችሁ” ብሏል። (ማቴዎስ 5:13፤ ዮሐንስ 15:5) እንዲህ ያሉት ዘይቤያዊ አነጋገሮች ቀላል ቢሆኑም ኃይለኛ መልእክት ያስተላልፋሉ።
10. በምታስተምርበት ጊዜ ምሳሌዎችን እንዴት መጠቀም እንደምትችል የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎች ጥቀስ።
10 አንተስ በምታስተምርበት ጊዜ ምሳሌዎችን መጠቀም የምትችለው እንዴት ነው? ረጅምና ብዙ ዝርዝር ጉዳዮች የያዙ ታሪኮችን ማምጣት አያስፈልግህም። ቀላል ንጽጽሮችን ለማሰብ ሞክር። ለአብነት ያህል፣ ከአንድ ሰው ጋር ስለ ትንሣኤ እየተወያየህ ሳለ ሙታንን ማስነሳት ለይሖዋ ቀላል እንደሆነ በምሳሌ ማስረዳት ፈለግክ እንበል። ታዲያ ምን ንጽጽር መጣልህ? መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን ከእንቅልፍ ጋር ያመሳስለዋል። ስለሆነም እንዲህ ማለት ትችላለህ፦ “የተኛን ሰው በቀላሉ መቀስቀስ እንደምንችል ሁሉ አምላክም የሞቱ ሰዎችን በቀላሉ ሊያስነሳቸው ይችላል።” (ዮሐንስ 11:11-14) በሌላ በኩል ደግሞ ልጆችን ጥሩ አድርጎ ለማሳደግ ፍቅርና እንክብካቤ እንደሚያስፈልግ በምሳሌ ማስረዳት ፈለግክ እንበል። ምን ምሳሌ መጠቀም ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ልጆች “እንደ ወይራ ዛፍ ቡቃያዎች [ናቸው]” የሚል ንጽጽር ይጠቀማል። (መዝሙር 128:3) በመሆኑም እንዲህ ማለት ትችላለህ፦ “አንድ ተክል የፀሐይ ብርሃንና ውኃ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ልጆችም ፍቅርና እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል።” የምትጠቀምበት ንጽጽር ቀላል በሆነ መጠን አድማጮችህም ነጥቡን መረዳት የዚያኑ ያህል ቀላል ይሆንላቸዋል።
ከዕለት ተዕለት ሕይወት የተወሰዱ ምሳሌዎች
11. የኢየሱስ ምሳሌዎች በልጅነቱ በገሊላ የተመለከታቸውን ነገሮች የሚያንጸባርቁ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ።
11 ኢየሱስ ከሰዎች ሕይወት ጋር የተያያዙ ምሳሌዎችን በመጠቀም ረገድ የተዋጣለት ነበር። ከተጠቀመባቸው ምሳሌዎች ብዙዎቹ፣ ባደገባት በገሊላ የተመለከታቸውን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች የሚያንጸባርቁ ናቸው። እስቲ ስለ ልጅነት ሕይወቱ ለአንድ አፍታ አስብ። እናቱ እህል ስትፈጭ፣ ሊጥ ውስጥ እርሾ ስትጨምር፣ በዘይት የሚሠራ መብራት ስታበራ ወይም ቤት ስትጠርግ ተመልክቶ መሆን አለበት። (ማቴዎስ 13:33፤ 24:41፤ ሉቃስ 15:8) ዓሣ አጥማጆች መረባቸውን በገሊላ ባሕር ላይ ሲጥሉ የመመልከት አጋጣሚ ነበረው። (ማቴዎስ 13:47) ልጆች በገበያ ቦታ ሲጫወቱ ያየባቸው ብዙ አጋጣሚዎችም ይኖራሉ። (ማቴዎስ 11:16) ኢየሱስ በምሳሌዎቹ ላይ የጠቀሳቸውን ሌሎች የተለመዱ ነገሮችም በልጅነቱ ተመልክቶ መሆን አለበት፤ ለምሳሌ ዘር ሲዘራ፣ ሠርግ ሲደገስ እንዲሁም አዝመራ ወቅቱን ጠብቆ ለአጨዳ ሲደርስ መመልከቱ አይቀርም።—ማቴዎስ 13:3-8፤ 25:1-12፤ ማርቆስ 4:26-29
12, 13. ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ በተናገረው ምሳሌ ላይ “ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ” የሚወስደውን መንገድ መጥቀሱ ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው?
12 ኢየሱስ በምሳሌዎቹ ላይ አድማጮቹ በደንብ የሚያውቋቸውን ዝርዝር ነገሮች ጠቅሷል። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚገልጸውን ምሳሌ የጀመረው እንዲህ በማለት ነበር፦ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ በዘራፊዎች እጅ ወደቀ፤ እነሱም ከገፈፉትና ከደበደቡት በኋላ በሞትና በሕይወት መካከል ጥለውት ሄዱ።” (ሉቃስ 10:30) ኢየሱስ “ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ” የሚወስደውን መንገድ እንደጠቀሰ ልብ በል። ምሳሌውን የተናገረው በይሁዳ ሆኖ ነው፤ ኢየሩሳሌም ኢየሱስ ካለበት ብዙም አትርቅም፤ ስለዚህ አድማጮቹ በምሳሌው ላይ የተጠቀሰውን መንገድ እንደሚያውቁት ጥርጥር የለውም። መንገዱ፣ በተለይ ብቻውን ለሚጓዝ ሰው አደገኛ በመሆኑ ይታወቅ ነበር። ጠመዝማዛና ጭር ያለ በመሆኑ አድብተው ለሚዘርፉ ወንበዴዎች ምቹ ነበር።
13 ኢየሱስ “ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ” ስለሚወስደው መንገድ ሌሎች የሚታወቁ ዝርዝር ነገሮችንም ጠቅሷል። በምሳሌው መሠረት በመጀመሪያ አንድ ካህን ቀጥሎም አንድ ሌዋዊ በዚያ መንገድ አልፈዋል፤ ሆኖም አንዳቸውም ቆም ብለው ጉዳት የደረሰበትን ሰው ለመርዳት አልሞከሩም። (ሉቃስ 10:31, 32) ካህናት ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ሲሆን ሌዋውያን ደግሞ ያግዟቸዋል። ብዙ ካህናትና ሌዋውያን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሥራ በማይኖራቸው ጊዜ በኢያሪኮ ይቀመጣሉ፤ በኢያሪኮና በኢየሩሳሌም መካከል ያለው ርቀት 21 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። ስለዚህ በዚያ መንገድ ላይ ካህን ወይም ሌዋዊ ሲያልፍ ማየት የተለመደ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ የጠቀሰው ሰው ‘ከኢየሩሳሌም እየወረደ’ እንደነበር ልብ በል። ኢየሱስ ይህን ያለበት ምክንያት ለአድማጮቹ ግልጽ ነው። ኢየሩሳሌም ከኢያሪኮ ከፍ ባለ ቦታ ላይ ትገኝ ነበር። ስለዚህ አንድ ሰው “ከኢየሩሳሌም” ተነስቶ ወደ ኢያሪኮ የሚጓዝ ከሆነ ‘ወረደ’ መባሉ ምክንያታዊ ነው።b ኢየሱስ ምሳሌውን የተናገረው አድማጮቹን በአእምሮው ይዞ እንደሆነ ግልጽ ነው።
14. ምሳሌዎችን ስንጠቀም አድማጮቻችንን ግምት ውስጥ ማስገባት የምንችለው እንዴት ነው?
14 እኛም ምሳሌዎችን ስንጠቀም አድማጮቻችንን ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን። የምንጠቀምባቸውን ምሳሌዎች ስንመርጥ አድማጮቻችንን በተመለከተ ልናስብባቸው የምንችላቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ዕድሜያቸውን፣ ባሕላቸውን፣ አስተዳደጋቸውንና ሥራቸውን ግምት ውስጥ ልናስገባ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ግብርና ዝርዝር ጉዳዮችን የሚጠቅስ ምሳሌ ከከተማ ይልቅ በገጠር ለሚኖር ሰው በቀላሉ ይገባዋል። የአድማጮቻችንን አኗኗርና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ማለትም ልጆቻቸውን፣ ቤታቸውን፣ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያቸውንና የሚመገቡትን ምግብ መሠረት በማድረግም ለእነሱ የሚስማሙ ምሳሌዎችን መምረጥ እንችላለን።
ከፍጥረት የተወሰዱ ምሳሌዎች
15. ኢየሱስ ስለ ፍጥረት ጥልቅ እውቀት ያለው መሆኑ ሊያስገርመን የማይገባው ለምንድን ነው?
15 ኢየሱስ የተጠቀመባቸው አብዛኞቹ ምሳሌዎች ተክሎችን፣ እንስሳትንና የአየር ንብረትን ጨምሮ ስለ ተፈጥሮ ምን ያህል እውቀት እንዳለው ያሳያሉ። (ማቴዎስ 16:2, 3፤ ሉቃስ 12:24, 27) ኢየሱስ እንዲህ ያለውን እውቀት ያገኘው ከየት ነው? በገሊላ ባሳለፈው የልጅነት ሕይወቱ የፍጥረት ሥራዎችን ለመመልከት ሰፊ አጋጣሚ እንደነበረው ጥርጥር የለውም። ከሁሉ በላይ ደግሞ ኢየሱስ “የፍጥረት ሁሉ በኩር” ነው፤ ይሖዋ ሁሉንም ነገር ሲፈጥር “የተዋጣለት ሠራተኛ” ሆኖ አብሮት ሠርቷል። (ቆላስይስ 1:15, 16፤ ምሳሌ 8:30, 31) ታዲያ ኢየሱስ ስለ ፍጥረት ሥራዎች ጥልቅ እውቀት ያለው መሆኑ ምን ያስገርማል? ይህን እውቀቱን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት እንደተጠቀመበት እስቲ እንመልከት።
16, 17. (ሀ) ኢየሱስ ስለ በጎች ባሕርይ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) በጎች በእርግጥ የእረኛቸውን ድምፅ እንደሚሰሙ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
16 ኢየሱስ ራሱን “ጥሩ እረኛ” ተከታዮቹን ደግሞ ‘በጎች’ አድርጎ እንደገለጸ አስታውስ። ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ስለ በጎች ባሕርይ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ያሳያሉ። በእረኞችና በበጎቻቸው መካከል ልዩ የሆነ ቅርርብ እንዳለ ያውቃል። እነዚህ ገር የሆኑ ፍጥረታት በእረኛቸው ለመመራት ፈቃደኛ እንደሆኑና ምንም ሳያንገራግሩ ተከትለውት እንደሚሄዱ አስተውሏል። በጎች እረኛቸውን የሚከተሉት ለምንድን ነው? ኢየሱስ እንደተናገረው “ድምፁን ስለሚያውቁ” ነው። (ዮሐንስ 10:2-4, 11) በእርግጥ በጎች የእረኛቸውን ድምፅ ለይተው ያውቃሉ?
17 ጆርጅ አዳም ስሚዝ በዓይናቸው የተመለከቱትን ነገር የቅድስቲቱ አገር ታሪካዊ መልክዓ ምድር (ዘ ሂስቶሪካል ጂኦግራፊ ኦቭ ዘ ሆሊ ላንድ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ በማለት አስፍረዋል፦ “አንዳንድ ጊዜ የምሳ እረፍታችንን በይሁዳ ከሚገኙት የውኃ ጉድጓዶች በአንደኛው አጠገብ ቁጭ ብለን እናሳልፍ ነበር፤ ሦስት ወይም አራት እረኞች መንጎቻቸውን ይዘው ወደዚያ ይመጣሉ። መንጎቹ ወደ ውኃው ጉድጓድ ሲቃረቡ ይደባለቃሉ፤ ይህን ስናይ ‘እያንዳንዱ እረኛ የራሱን በግ እንዴት ይለይ ይሆን?’ የሚል ጥያቄ ተፈጥሮብን ነበር። በጎቹ ውኃ ከጠጡና ሲቦርቁ ከቆዩ በኋላ ግን እረኞቹ ተራ በተራ ከሸለቆው ወደተለያዩ አቅጣጫዎች ሄዱና የየራሳቸውን የጥሪ ድምፅ አሰሙ፤ በጎቹም እየተለዩ ወደየእረኞቻቸው ተሰበሰቡ፤ ከዚያም እንዳመጣጣቸው ተመልሰው ሄዱ።” ኢየሱስ ነጥቡን ለማስረዳት ከዚህ የተሻለ ምን ምሳሌ ሊጠቀም ይችላል? ነጥቡ ይህ ነው፤ የእሱን ትምህርቶች ለይተን የምናውቅና የምንታዘዝ እንዲሁም አመራሩን የምንከተል ከሆነ ‘የጥሩውን እረኛ’ ፍቅራዊ እንክብካቤ እናገኛለን።
18. ስለ ይሖዋ ፍጥረታት የሚገልጹ መረጃዎችን ከየት ማግኘት እንችላለን?
18 እኛስ ከፍጥረት ሥራዎች የተወሰዱ ምሳሌዎችን እንዴት እንደምንጠቀም መማር የምንችለው እንዴት ነው? የእንስሳትን ለየት ያለ ባሕርይ በመጥቀስ ቀላል ሆኖም ውጤታማ ንጽጽር መጠቀም ይቻላል። ስለ ይሖዋ ፍጥረታት የሚገልጹ መረጃዎችን ከየት ማግኘት እንችላለን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለተለያዩ እንስሳት የሚገልጹ ብዙ ሐሳቦችን ይዟል፤ አንዳንድ ጊዜም የእንስሳትን ባሕርይ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ይጠቀምበታል። እንደ ሜዳ ፍየል ወይም እንደ ነብር ፈጣኖች፣ እንደ እባብ ጠንቃቆች እንዲሁም እንደ ርግብ የዋሆች ስለመሆን ይናገራል።c (1 ዜና መዋዕል 12:8፤ ዕንባቆም 1:8፤ ማቴዎስ 10:16) ከመጠበቂያ ግንብ እና ከንቁ! መጽሔቶች እንዲሁም jw.org ላይ “ንድፍ አውጪ አለው?” በተባለው ዓምድ ሥር ከሚገኙት ርዕሶችና ቪዲዮዎችም ጠቃሚ መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል። በእነዚህ ጽሑፎችና ቪዲዮዎች ላይ ከይሖዋ ፍጥረታት ምን ዓይነት ቀላል ንጽጽሮች እንደተወሰዱ በማስተዋል ብዙ ትምህርት ማግኘት ትችላለህ።
ከሚታወቁ ክስተቶች የተወሰዱ ምሳሌዎች
19, 20. (ሀ) ኢየሱስ አንድን የተሳሳተ አመለካከት ለማጋለጥ በወቅቱ ያጋጠመን ክስተት የተጠቀመው እንዴት ነው? (ለ) በምናስተምርበት ጊዜ እውነተኛ ታሪኮችንና ተሞክሮዎችን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
19 እውነተኛ ታሪኮችንም ውጤታማ በሆነ መንገድ ምሳሌ አድርጎ መጥቀስ ይቻላል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ፣ አደጋ በክፉዎች ላይ የሚደርስ ቅጣት እንደሆነ ማሰብ ስህተት መሆኑን ለማጋለጥ በወቅቱ የተከሰተን አንድ ሁኔታ ጠቅሶ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “የሰሊሆም ግንብ ተንዶባቸው የሞቱት 18 ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ በደለኞች የነበሩ ይመስላችኋል?” (ሉቃስ 13:4) በእርግጥም እነዚያ 18 ሰዎች የሞቱት አምላክን የሚያስቆጣ ኃጢአት ስለፈጸሙ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ አሳዛኝ በሆነ መንገድ ሕይወታቸውን ያጡት “ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ባስከተሉት ሁኔታ ነው። (መክብብ 9:11) በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ አድማጮቹ በደንብ የሚያውቁትን ክስተት በመጥቀስ የሐሰት ትምህርትን ውድቅ አድርጓል።
20 እኛስ በምናስተምርበት ጊዜ እውነተኛ ታሪኮችንና ተሞክሮዎችን ምሳሌ አድርገን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ ያህል፣ የኢየሱስን መገኘት ስለሚጠቁመው ምልክት የሚገልጸውን ትንቢት ፍጻሜ እያብራራህ ነው እንበል። (ማቴዎስ 24:3-14) የምልክቱ አንዳንድ ገጽታዎች ፍጻሜያቸውን እያገኙ እንዳሉ ለማስረዳት ስለ ጦርነት፣ ስለ ረሃብ ወይም ስለ ምድር መናወጥ የሚገልጹ የቅርብ ጊዜ ዜናዎችን ልትጠቅስ ትችላለህ። ወይም አዲሱን ስብዕና መልበስ ምን ለውጦችን እንደሚጠይቅ በምሳሌ ለማስረዳት አንድ ተሞክሮ መጥቀስ ፈለግክ እንበል። (ኤፌሶን 4:20-24) እንዲህ ዓይነት ተሞክሮ ከየት ማግኘት ትችላለህ? በጉባኤህ ያሉ የእምነት ባልንጀሮችህን ተሞክሮ ወይም የይሖዋ ምሥክሮች በሚያዘጋጇቸው ጽሑፎች ላይ የወጣን ተሞክሮ መጥቀስ ትችላለህ። “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” በተባለው የjw.org ዓምድ ሥርም ተሞክሮዎች ማግኘት ትችላለህ።
21. የአምላክን ቃል ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተማር ምን ወሮታ ያስገኛል?
21 በእርግጥም ኢየሱስ የተዋጣለት አስተማሪ ነው! በዚህ ክፍል ላይ እንዳየነው ‘ማስተማርና የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ’ ዋነኛ ሥራው ነበር። (ማቴዎስ 4:23) እኛም በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዘው ሥራ ይህ ነው። ውጤታማ አስተማሪ መሆን ታላቅ ወሮታ ያስገኛል። በምናስተምርበት ጊዜ ለሌሎች መስጠታችን ነው፤ መስጠት ደግሞ ደስታ ያስገኝልናል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) እውነተኛና ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝ ነገር ለሰዎች እየሰጠን ይኸውም ስለ ይሖዋ እውነቱን እያስተማርናቸው እንደሆነ ስለምናውቅ ደስተኞች ነን። በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ የላቀው አስተማሪ ኢየሱስ የተወልንን ምሳሌ እንደምንከተል ማወቃችንም እርካታ ያስገኝልናል።
a ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ ስለ ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት የሚናገረው በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የመጀመሪያው ዘገባ የማቴዎስ ወንጌል ነው፤ ወንጌሉ የተጻፈው ኢየሱስ ከሞተ ከስምንት ዓመት ገደማ በኋላ ነው።
b በተጨማሪም ኢየሱስ እንደጠቆመው ካህኑም ሆነ ሌዋዊው ‘ከኢየሩሳሌም’ እየመጡ ነበር፤ ስለሆነም ከቤተ መቅደሱ እየተመለሱ ነበር ማለት ነው። እንግዲያው እነዚህ ሰዎች ‘የሞተ የሚመስለውን ሰው ዝም ብለውት ያለፉት እንዳይረክሱና በቤተ መቅደስ የሚሰጡት አገልግሎት ለጊዜውም ቢሆን እንዳይስተጓጎልባቸው በመፍራት ነው’ የሚል ማስተባበያ ማቅረብ አይቻልም።—ዘሌዋውያን 21:1፤ ዘኁልቁ 19:16
c መጽሐፍ ቅዱስ የእንስሳትን ባሕርይ በምሳሌያዊ መንገድ እንዴት እንደተጠቀመበት የሚያሳይ ዝርዝር ለማግኘት ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ (በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ) ጥራዝ 1 ገጽ 268, 270-271ን ተመልከት።