“ድምፁን ያውቃሉ”
“ይሖዋ እረኛዬ ነው።” እነዚህ የመዝሙር 23 የመክፈቻ ቃላት ናቸው። (አዓት) በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ እንደተገለጸው ቅዱሳን ጽሑፎች ይሖዋ አምላክን ከእረኛ ጋር ያመሳስሉታል። እንዲህ ይላል:– “መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፣ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፣ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።”—ኢሳይያስ 40:11
ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲሁ ከእረኛ ጋር ተመሳስሏል። እርሱ እንዲህ ብሎ ነበር:– “መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።” (ዮሐንስ 10:11) ኢየሱስ “በጎቹም ድምፁን [የእረኛውን ድምፅ] ይሰሙታል፣ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል” ብሏል። ጨምሮም “በጎቹም ድምፁን [የእረኛውን ድምፅ] ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፣ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና” ሲል ተናግሯል።—ዮሐንስ 10:2–5
ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ጥቅሶች ስናነብ ይሖዋ አምላክም ሆነ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በአእምሯችን እንደተሳሉት ሰዎች ናቸው። ምሳሌያዊ በጎቻቸውን በእንክብካቤና በፍቅር ይይዟቸዋል። በዚህም ምክንያት በግ መሰል የሆኑ ሰዎች ፍቅርና ጥበቃ እንዳገኙ ይሰማቸዋል፤ ስጋትም የለባቸውም።
ይህ ዓይነቱ ዝምድና በጎች ከእረኞቻቸው ጋር ካላቸው ግንኙነት ጋር ተመሳስሏል። ጥንት በ1831 ጆን ሃርሌይ በዚህ ረገድ የታዘቡትን ነገር ጽፈው ነበር። በግሪክ አገር እረኞች ለበጎቻቸው ስም ማውጣታቸው የተለመደ ነገር እንደነበረ ገልጸዋል። እረኛው በጎቹን በስማቸው ሲጠራቸው፣ በጎቹ እርሱን ይከተሉታል። እሳቸው ይህን ከጻፉ ከ51 ዓመታት በኋላ በ1882 ጄ ኤል ፖርተርም ተመሳሳይ ነገር መታዘባቸውን ገልጸው ነበር። እረኞች በጎቻቸውን “ልዩ በሆነ ቀጭን ድምፅ . . . ሲጠሯቸውና” በጎቹም በጥሪያቸው መሠረት በታዛዥነት እረኞቻቸውን ከኋላ ከኋላቸው ሲከተሏቸው እኚህ ሰው ራሳቸው ተመልክተዋል። በዚያው ዓመት ዊልያም ኤም ቶምሰን በጎች እረኞቻቸውን እየተከተሉ እንዲሄዱና የእረኞቻቸውን ድምፅ እንዲያስታውሱ ማስተማር እንደሚቻል ተደጋጋሚ ሙከራዎች ማረጋገጣቸውን ጽፈዋል።
በቅርብ ዓመታትስ በእረኞችና በበጎቻቸው መካከል እንዲህ ዓይነቱ ልዩ ዝምድና ታይቷልን? አዎን። በናሽናል ጂኦግራፊ የመስከረም 1993 እትም ላይ አውስትራሊያዊዋ ተጓዥ ሮቢን ዴቪድሰን በህንድ ሰሜን ምዕራብ ያሉትን የራባሪ ከብት አርቢዎች አስመልክተው እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል፦ “እያንዳንዱ እረኛ እንደየሁኔታው በትንሹም ቢሆን ለየት የሚል አጠራር አለው። እረኞች በጎቻቸው ጠዋት ጠዋት ከጉሮኗቸው እንዲወጡ፣ ወደ ውኃ መጠጫቸው እንዲመጡ፣ እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን እንዲያደርጉ የሚጣሩበት ጥሪ አላቸው። እያንዳንዳቸው የራሳቸውን በጎች የትኞቹ እንደሆኑ እንዲሁም የሌሎቹ ደግሞ የትኞቹ እንደሆኑ ያውቃሉ። ጠዋት ጠዋት የያንዳንዱ ሰው መንጋ በጎቹ ሁሉ በአንድነት ከተሰበሰቡበት ከትልቁ መንጋ ይነጠልና እረኛውን እየተከተለ ይሄዳል።”
ኢየሱስ ቀደም ሲል በተጠቀሱት አራት ተጓዦች የተገለጸውን ሁኔታ ልብ ብሎት እንደነበረ አያጠራጥርም። ይህንን መገንዘቡ በጎቹ ድምፁን እንደሚያውቁት የገለጸበት ምሳሌ ከእውነታው ያልራቀ እንዲሆን አግዞታል። አንተስ፤ ከኢየሱስ በጎች አንዱ ነህን? ድምፁን ታውቀዋለህን? ካወቅከውስ ታዳምጠዋለህን? ያስተማራቸው ትምህርቶች እውነት መሆናቸውን አውቀህ ከተቀበልክና ለሌሎች ካሳወቅክ እንዲሁም ትዕዛዛቱን አክብረህ ይሖዋን በማምለኩ ረገድ ሲመራህ ከተከተልከው የይሖዋ አምላክንና የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅራዊና ርኅራኄ የተሞላበት ጥበቃ ማግኘት ትችላለህ።—ዮሐንስ 15:10