ምዕራፍ 12
ኢየሱስ ተጠመቀ
ማቴዎስ 3:13-17 ማርቆስ 1:9-11 ሉቃስ 3:21, 22 ዮሐንስ 1:32-34
ኢየሱስ ተጠመቀ፤ እንዲሁም ተቀባ
ይሖዋ፣ ኢየሱስ ልጁ እንደሆነ ተናገረ
ዮሐንስ መስበክ ከጀመረ ከስድስት ወር ገደማ በኋላ ኢየሱስ እሱ ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መጣ፤ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ 30 ዓመት ገደማ ሆኖታል። ወደ ዮሐንስ የመጣው ለምንድን ነው? እንዲሁ ሊጠይቀው አስቦ ነው? ወይስ ዮሐንስ የሚያከናውነው ሥራ ምን ያህል እየተሳካ እንደሆነ ለማየት? አይደለም፤ ኢየሱስ ወደ ዮሐንስ የመጣው ለመጠመቅ ፈልጎ ነው።
ዮሐንስ “በአንተ መጠመቅ የሚያስፈልገኝ እኔ ሆኜ ሳለ አንተ ወደ እኔ ትመጣለህ?” ሲል ለማከላከል ሞከረ። (ማቴዎስ 3:14) ዮሐንስ፣ ኢየሱስ የአምላክ ልዩ ልጅ መሆኑን ያውቃል። ማርያም፣ ኢየሱስን ፀንሳ ሳለ የዮሐንስን እናት ኤልሳቤጥን ልትጠይቅ ስትሄድ ዮሐንስ በእናቱ ማህፀን ውስጥ ሆኖ በደስታ እንደዘለለ ታስታውሳለህ። የዮሐንስ እናት ከጊዜ በኋላ ይህን ለልጇ ነግራው እንደሚሆን አያጠራጥርም። በተጨማሪም መልአኩ የኢየሱስን መወለድ በተመለከተ ስለተናገረው ነገርና ኢየሱስ በተወለደበት ሌሊት ለእረኞች ስለታዩት መላእክትም ሰምቶ መሆን አለበት።
ዮሐንስ፣ እሱ የሚያጠምቀው ከኃጢአታቸው ንስሐ የገቡ ሰዎችን እንደሆነ ያውቃል። ኢየሱስ ግን ኃጢአት የለበትም። ዮሐንስ ተቃውሞውን ቢገልጽም ኢየሱስ “ግድ የለም እሺ በለኝ፤ በዚህ መንገድ ጽድቅ የሆነውን ሁሉ መፈጸማችን ተገቢ ነው” አለው።—ማቴዎስ 3:15
ኢየሱስ መጠመቁ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? ኢየሱስ የተጠመቀው ለኃጢአት ንስሐ መግባቱን ለማመልከት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የአባቱን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን ማቅረቡን ለማሳየት ነው። (ዕብራውያን 10:5-7) ኢየሱስ አናጺ ሆኖ ሲሠራ ቆይቷል፤ አሁን ግን በሰማይ ያለው አባቱ ወደ ምድር ሲልከው እንዲያከናውነው የሰጠውን አገልግሎት የሚጀምርበት ጊዜ ደርሷል። ለመሆኑ ዮሐንስ፣ ኢየሱስን በሚያጠምቅበት ጊዜ እንግዳ የሆነ ነገር እንደሚፈጸም የጠበቀ ይመስልሃል?
ዮሐንስ በወቅቱ የሆነውን በኋላ ላይ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “በውኃ እንዳጠምቅ የላከኝ ራሱ ‘በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው፣ መንፈስ ሲወርድበትና ሲያርፍበት የምታየው ያ ሰው ነው’ አለኝ።” (ዮሐንስ 1:33) በመሆኑም ዮሐንስ እሱ ከሚያጠምቃቸው ሰዎች በአንዱ ላይ የአምላክ መንፈስ እንደሚወርድ ይጠብቅ ነበር። ከዚህ አንጻር፣ ኢየሱስ ከውኃው ውስጥ በወጣ ጊዜ ‘የአምላክ መንፈስ በእሱ ላይ እንደ ርግብ ሲወርድ’ መመልከቱ ዮሐንስን አላስገረመው ይሆናል።—ማቴዎስ 3:16
ሆኖም ኢየሱስ ሲጠመቅ ሌላም የተፈጸመ ነገር አለ። ቅዱሳን መጻሕፍት ‘ሰማያት እንደተከፈቱለት’ ይገልጻሉ። ይህ ምን ማለት ነው? ኢየሱስ ሲጠመቅ፣ ሰው ከመሆኑ በፊት በሰማይ ያሳለፈውን ሕይወት ማስታወስ እንደቻለ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት አምላክ በሰማይ ያስተማረውን እውነት ጨምሮ የይሖዋ መንፈሳዊ ልጅ ሆኖ ያሳለፈውን ሕይወት ማስታወስ ቻለ።
ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ሲጠመቅ ከሰማይ አንድ ድምፅ “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” አለ። (ማቴዎስ 3:17) ይህ የማን ድምፅ ነው? ኢየሱስ እዚያው ከዮሐንስ ጋር ስለሆነ ድምፁ የእሱ ሊሆን አይችልም። የተሰማው ድምፅ የአምላክ ነው። ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደምንችለው ኢየሱስ የይሖዋ ልጅ እንጂ እሱ ራሱ ይሖዋ አምላክ አይደለም።
እንደ መጀመሪያው ሰው እንደ አዳም ሁሉ ኢየሱስም የአምላክ ሰብዓዊ ልጅ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ደቀ መዝሙሩ ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ጥምቀት ከገለጸ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ኢየሱስ ሥራውን ሲጀምር 30 ዓመት ገደማ ሆኖት ነበር፤ ሕዝቡም የዮሴፍ ልጅ እንደሆነ አድርገው ያስቡ ነበር፤ ዮሴፍ የሄሊ ልጅ፣ . . . የዳዊት ልጅ፣ . . . የአብርሃም ልጅ፣ . . . የኖኅ ልጅ፣ . . . የአዳም ልጅ፣ . . . የአምላክ ልጅ።”—ሉቃስ 3:23-38
አዳም ሰው የሆነ “የአምላክ ልጅ” እንደነበረ ሁሉ ኢየሱስም ሰው የሆነ የአምላክ ልጅ ነበር። ኢየሱስ ሲጠመቅ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ በመሆን ከአምላክ ጋር አዲስ ዝምድና መሥርቷል። በመሆኑም ኢየሱስ መለኮታዊውን ትምህርት ማስተማርም ሆነ የሕይወትን መንገድ ማሳየት ይችላል። አሁን የጀመረው ጎዳና፣ ኃጢአተኛ ለሆኑት የሰው ልጆች ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ መስጠትን ይጠይቅበታል።