የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሞት የሁሉ ነገር ፍጻሜ ነው?
ሞት የሁሉ ነገር ፍጻሜ አይደለም!
ቢታንያ ከኢየሩሳሌም ሦስት ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ነበረች። (ዮሐንስ 11:18) ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በዚህች ከተማ ውስጥ አንድ አሳዛኝ ነገር ተከስቶ ነበር። የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ የነበረው አልዓዛር በድንገት በጠና ታሞ ሞተ።
ኢየሱስ ሁኔታውን ሲሰማ ለደቀ መዛሙርቱ አልዓዛር እንደተኛና ሄዶ ሊቀሰቅሰው እንዳሰበ ነገራቸው። (ዮሐንስ 11:11) ሆኖም ደቀ መዛሙርቱ ምን እያላቸው እንዳለ አልተረዱም ነበር፤ ስለሆነም ኢየሱስ “አልዓዛር ሞቷል” ሲል በግልጽ ነገራቸው።—ዮሐንስ 11:14
ኢየሱስ፣ አልዓዛር ከተቀበረ ከአራት ቀናት በኋላ ቢታንያ ደረሰ፤ ከዚያም የሟቹ እህት የሆነችውን ማርታን ሊያጽናናት ሞከረ። ማርታም “አንተ እዚህ ኖረህ ቢሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው። (ዮሐንስ 11:17, 21) ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ። በእኔ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ ቢሞት እንኳ እንደገና ሕያው ይሆናል” አላት።—ዮሐንስ 11:25
“አልዓዛር፣ ና ውጣ!”
ከዚያም የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን በተግባር ለማሳየት አልዓዛር ወደ ተቀበረበት መቃብር ቀረብ ብሎ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” ብሎ ጮኸ። (ዮሐንስ 11:43) በአካባቢው ያሉት ሰዎች ሞቶ የነበረው ሰው ከመቃብር ሲወጣ ሲያዩ እጅግ ተገረሙ።
ከዚያ ቀደም ብሎ ኢየሱስ ቢያንስ ሁለት ሰዎችን ከሞት አስነስቷል። በአንድ ወቅት አንዲትን ወጣት ይኸውም የኢያኢሮስን ሴት ልጅ ከሞት አስነስቷታል። ኢየሱስ ይህችን ልጅ ሊያስነሳት ሲልም እንደተኛች ተናግሮ ነበር።—ሉቃስ 8:52
ኢየሱስ የአልዓዛርንም ሆነ የኢያኢሮስን ሴት ልጅ ሞት አስመልክቶ በተናገረ ጊዜ ሞትን ከእንቅልፍ ጋር እንዳመሳሰለው ልብ በል። ሞት ከእንቅልፍ ጋር መነጻጸሩ በእርግጥም ተገቢ ነው። ለምን? የተኛ ሰው ራሱን አያውቅም፤ በመሆኑም እንቅልፍ ከሕመም ወይም ከሥቃይ ማረፍን የሚያሳይ ተስማሚ ምሳሌ ነው። (መክብብ 9:5፤ “ሞት እንደ ከባድ እንቅልፍ ነው” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) የጥንቶቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሙታን ስላሉበት ሁኔታ ትክክለኛ እውቀት ነበራቸው። ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪልጅን ኤንድ ኤቲክስ እንዲህ ብሏል፦ “የኢየሱስ ተከታዮች እምነታቸውን ጠብቀው ለሞቱ ሰዎች፣ ሞት እንደ እንቅልፍ፣ መቃብር ደግሞ እንደ እረፍት ቦታ . . . እንደሚሆንላቸው ያምኑ ነበር።”a
ሙታን በመቃብር ውስጥ ተኝተው እንደሚገኙና እየተሠቃዩ እንዳልሆነ ማወቃችን ያጽናናናል። እንዲሁም ስንሞት ምን እንደምንሆን መገንዘባችን ከፍርሃት ይገላግለናል።
“ሰው ከሞተ በኋላ ተመልሶ በሕይወት ይኖራል?”
ጥሩ እንቅልፍ ተኝቶ ማደር አስደሳች ቢሆንም እንኳ ለዘላለም አሸልቦ መቅረት የሚፈልግ ማን ይኖራል? በመቃብር ውስጥ ተኝተው ያሉት ሙታን ልክ እንደ አልዓዛርና እንደ ኢያኢሮስ ሴት ልጅ ዳግም ሕያው እንደሚሆኑ ተስፋ ማድረግ እንችላለን?
ኢዮብ ሊሞት እንደተቃረበ አድርጎ ባሰበ ጊዜ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ “ሰው ከሞተ በኋላ ተመልሶ በሕይወት ይኖራል?” የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር።—ኢዮብ 14:14
ኢዮብ ሁሉን ቻይ ወደሆነው አምላክ ሲጸልይ “ትጠራኛለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ የእጅህንም ሥራ ትናፍቃለህ” ብሏል። (ኢዮብ 14:15) ኢዮብ፣ ይሖዋ ታማኝ የሆነውን አገልጋዩን ከሞት የሚያስነሳበትን ቀን በናፍቆት እንደሚጠባበቅ እርግጠኛ ነበር። ኢዮብ እንዲህ ብሎ መናገሩ የማይፈጸም ነገር እየተመኘ እንዳለ የሚያሳይ ነው? በፍጹም።
ኢየሱስ ሙታንን ማስነሳቱ አምላክ ሞትን ድል ለማድረግ የሚያስችል ኃይል እንደሰጠው በግልጽ ያሳያል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ ‘የሞትን ቁልፍ’ እንደያዘ ይናገራል። (ራእይ 1:18) ስለሆነም ኢየሱስ የአልዓዛር መቃብር ተዘግቶበት የነበረውን ድንጋይ እንዲያነሱት እንዳዘዘ ሁሉ የመቃብርንም በሮች ይከፍታል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ ተስፋ ደጋግሞ ይናገራል። አንድ መልአክ ለነቢዩ ዳንኤል ‘አንተ ታርፋለህ ሆኖም በቀኖቹ መጨረሻ ተነሥተህ የተመደበልህን ርስት ትቀበላለህ’ የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶታል። (ዳንኤል 12:13) ኢየሱስ በትንሣኤ ተስፋ የማያምኑትን የአይሁድ መሪዎች ማለትም ሰዱቃውያንን “እናንተ ቅዱሳን መጻሕፍትንም ሆነ የአምላክን ኃይል ስለማታውቁ ትሳሳታላችሁ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 22:23, 29) ሐዋርያው ጳውሎስ “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል።—የሐዋርያት ሥራ 24:15
ሙታን የሚነሱት መቼ ነው?
ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት የሚነሱት መቼ ነው? መልአኩ ጻድቅ ሰው ለነበረው ለዳንኤል “በቀኖቹ መጨረሻ” እንደሚነሳ ነግሮታል። በተመሳሳይም ማርታ ወንድሟ አልዓዛር “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ” እምነት እንዳላት ገልጻለች።—ዮሐንስ 11:24
መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ‘የመጨረሻ ቀናት’ ከክርስቶስ መንግሥት አገዛዝ ጋር ያያይዛቸዋል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[ክርስቶስ፣] አምላክ ጠላቶችን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግለት ድረስ ንጉሥ ሆኖ ሊገዛ ይገባዋልና። የመጨረሻው ጠላት የሆነው ሞት ይደመሰሳል።” (1 ቆሮንቶስ 15:25, 26) የአምላክ መንግሥት እንዲመጣና ፈቃዱ በምድር ላይ እንዲፈጸም ከምንጸልይባቸው ዋነኛ ምክንያቶች መካከል አንዱ ይህ ነው።b
ኢዮብ እንደተናገረው አምላክ የሞቱ ሰዎችን ማስነሳት ይፈልጋል። ይህ ቀን ሲደርስ ሞት በእርግጥ ይደመሰሳል። ከዚያ በኋላ ‘ሞት የሁሉ ነገር ፍጻሜ ነው?’ የሚል ጥያቄ የሚያነሳ ሰው አይኖርም።
a “ሰምተሪ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የመጣው “የመኝታ ስፍራ” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል ነው።
b ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ተመልከት። ይህ መጽሐፍ www.jw.org/am በተባለው ድረ ገጽ ላይም ይገኛል።