የጥናት ርዕስ 12
የሌሎችን ስሜት የምትረዱ ሁኑ
“ሁላችሁም . . . የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ።”—1 ጴጥ. 3:8
መዝሙር 90 እርስ በርስ እንበረታታ
የትምህርቱ ዓላማa
1. በ1 ጴጥሮስ 3:8 መሠረት ስለ እኛ ከሚያስቡና ለስሜታችን ከሚጨነቁ ሰዎች ጋር መሆን የሚያስደስተን ለምንድን ነው?
ስለ እኛ ከሚያስቡና ለስሜታችን ከሚጨነቁ ሰዎች ጋር መሆን ያስደስተናል። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን በእኛ ቦታ በማስቀመጥ ምን እንደሚያሳስበን ወይም ምን እንደሚሰማን ለማስተዋል ይሞክራሉ። አንዳንድ ጊዜ ገና ሳንጠይቃቸው እንኳ ምን ሊያስፈልገን እንደሚችል ተገንዝበው እርዳታ ያደርጉልናል። በእርግጥም ‘ስሜታችንን የሚረዱልንን’b ሰዎች ከልብ እናደንቃለን።—1 ጴጥሮስ 3:8ን አንብብ።
2. ርኅራኄ ማሳየት ተፈታታኝ ሊሆንብን የሚችለው ለምንድን ነው?
2 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም ርኅራኄ ማሳየት ወይም የሌላውን ስሜት መረዳት እንፈልጋለን። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እንዲህ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ለምን? አንዱ ምክንያት ፍጽምና የጎደለን መሆናችን ነው። (ሮም 3:23) በመሆኑም ስለ ራሳችን ብቻ እንድናስብ የሚገፋፋንን ውስጣዊ ዝንባሌ መዋጋት ይኖርብናል። በተጨማሪም አንዳንዶቻችን በአስተዳደጋችን ወይም ከዚህ በፊት ባጋጠመን ነገር ምክንያት ለሌሎች ርኅራኄ ማሳየት ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። ከዚህም በላይ በዙሪያችን ያሉት ሰዎች ዝንባሌ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል። በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ለሌሎች ስሜት ግድ የላቸውም። ከዚህ ይልቅ “ራሳቸውን የሚወዱ” ናቸው። (2 ጢሞ. 3:1, 2) ታዲያ የሌሎችን ስሜት መረዳት ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርጉትን እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት እንድንችል የሚረዳን ምንድን ነው?
3. (ሀ) የሌሎችን ስሜት በመረዳት ረገድ ይበልጥ እየተሻሻልን መሄድ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
3 ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ የተዉትን ምሳሌ የምንከተል ከሆነ የሌሎችን ስሜት በመረዳት ረገድ ይበልጥ እየተሻሻልን መሄድ እንችላለን። ይሖዋ የፍቅር አምላክ ነው፤ ደግሞም ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ትቶልናል። (1 ዮሐ. 4:8) ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። (ዮሐ. 14:9) ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የሰው ልጆች ርኅራኄ ማሳየት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አሳይቷል። በዚህ ርዕስ ውስጥ መጀመሪያ፣ ይሖዋና ኢየሱስ የሌሎችን ስሜት እንደሚረዱ ያሳዩት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። ከዚያም እነሱ የተዉትን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።
የሌሎችን ስሜት በመረዳት ረገድ ይሖዋ የተወው ምሳሌ
4. ኢሳይያስ 63:7-9 ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ስሜት እንደሚያስብ የሚያሳየው እንዴት ነው?
4 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ስሜት እንደሚያስብ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ የጥንቶቹ እስራኤላውያን የተለያዩ ችግሮች በደረሱባቸው ጊዜ ይሖዋ ምን እንደተሰማው እንመልከት። የአምላክ ቃል “በጭንቃቸው ሁሉ እሱ ተጨነቀ” ይላል። (ኢሳይያስ 63:7-9ን አንብብ።) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ይሖዋ፣ በሕዝቡ ላይ የሚፈጸመውን በደል በእሱ ላይ እንደተፈጸመ በደል አድርጎ እንደሚቆጥረው በነቢዩ ዘካርያስ በኩል ተናግሯል። ለአገልጋዮቹ “እናንተን የሚነካ ሁሉ የዓይኔን ብሌን ይነካል” ብሏቸዋል። (ዘካ. 2:8) በእርግጥም ይህ፣ ይሖዋ ለሕዝቡ ያለውን አሳቢነት የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም መግለጫ ነው!
5. ይሖዋ መከራ የሚደርስባቸውን አገልጋዮቹን ለመርዳት ሲል እርምጃ እንደወሰደ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
5 ይሖዋ መከራ እየደረሰባቸው ላሉ አገልጋዮቹ ከመራራት ባለፈ እነሱን ለመርዳት ሲል እርምጃ ይወስዳል። ለምሳሌ እስራኤላውያን በግብፅ ባርነት እየማቀቁ በነበሩበት ወቅት ሥቃያቸው የተሰማው ሲሆን ችግራቸውን ለማስወገድ እርምጃ ወስዷል። ይሖዋ ሙሴን እንዲህ ብሎታል፦ “የሕዝቤን መከራ በእርግጥ አይቻለሁ፤ . . . የሚያሰሙትን ጩኸት ሰምቻለሁ፤ እየደረሰባቸው ያለውንም ሥቃይ በሚገባ አውቃለሁ። እኔም ከግብፃውያን እጅ ልታደጋቸው . . . እወርዳለሁ።” (ዘፀ. 3:7, 8) ይሖዋ ሕዝቡ ለሆኑት እስራኤላውያን ስለራራ ከባርነት ነፃ አውጥቷቸዋል። ከብዙ ዘመናት በኋላ ደግሞ እስራኤላውያን በተስፋይቱ ምድር ሳሉ ጠላት ጥቃት ሰንዝሮባቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ምን አደረገ? “በሚጨቁኗቸውና በሚያንገላቷቸው ሰዎች የተነሳ ሲቃትቱ” በማየቱ ‘አዝኗል።’ ለሕዝቡ የነበረው ርኅራኄ አሁንም እነሱን ለመርዳት ሲል እርምጃ እንዲወስድ ማለትም እስራኤላውያንን ከጠላቶቻቸው የሚታደጓቸው መሳፍንት እንዲያስነሳ አድርጎታል።—መሳ. 2:16, 18
6. ይሖዋ አገልጋዮቹ የተሳሳተ አመለካከት በሚይዙበት ጊዜም እንኳ እንደሚያስብላቸው የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
6 ይሖዋ ምንጊዜም ለሕዝቡ ስሜት ያስባል፤ አገልጋዮቹ የተሳሳተ ጎዳና በሚከተሉበት ጊዜም እንኳ ለስሜታቸው እንደሚያስብ አሳይቷል። እስቲ የዮናስን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ይሖዋ በነነዌ ነዋሪዎች ላይ የፍርድ መልእክት እንዲያውጅ ይህን ነቢይ ልኮት ነበር። ነዋሪዎቹ ንስሐ ሲገቡ ግን አምላክ ሊያመጣባቸው ያሰበውን ጥፋት ተወው። ሆኖም ዮናስ በዚህ ውሳኔ አልተደሰተም። ጥፋት እንደሚመጣ የተናገረው ትንቢት ሳይፈጸም በመቅረቱ “እጅግ ተቆጣ።” ይሁንና ይሖዋ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል በትዕግሥት ረድቶታል። (ዮናስ 3:10 እስከ 4:11) ዮናስ በጊዜ ሂደት የይሖዋን እርማት ተቀብሏል፤ ይሖዋም ጠቃሚ ትምህርት የያዘውን ይህን ዘገባ ለማጻፍ ዮናስን ተጠቅሞበታል።—ሮም 15:4c
7. ይሖዋ ሕዝቡን የያዘበትን መንገድ ስንመለከት ስለ ምን ነገር እርግጠኞች እንሆናለን?
7 ይሖዋ ሕዝቡን የያዘበትን መንገድ ስንመለከት አምላክ ለአገልጋዮቹ ርኅራኄ እንዳለው እርግጠኞች እንሆናለን። እያንዳንዳችን እየደረሰብን ያለውን ሥቃይና መከራ ይገነዘባል። ይሖዋ “የሰውን ልብ በሚገባ [ያውቃል]።” (2 ዜና 6:30) የውስጥ ሐሳባችንን፣ ስሜታችንንና ያለብንን የአቅም ገደብ ይረዳል። ደግሞም ‘ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ፈተና እንዲደርስብን አይፈቅድም።’ (1 ቆሮ. 10:13) ይህ ማረጋገጫ ምንኛ የሚያጽናና ነው!
የሌሎችን ስሜት በመረዳት ረገድ ኢየሱስ የተወው ምሳሌ
8-10. ኢየሱስ ለሌሎች አሳቢነት እንዲያሳይ ያነሳሱት የትኞቹ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ?
8 ኢየሱስ ሰው ሆኖ ምድር ላይ ይኖር በነበረበት ጊዜ ለሌሎች ልባዊ አሳቢነት አሳይቷል። እንዲህ ያለ አሳቢነት እንዲያሳይ ያነሳሱት ቢያንስ ሦስት ምክንያቶች ናቸው። አንደኛ፣ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ኢየሱስ በሰማይ ያለውን አባቱን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። ኢየሱስ ልክ እንደ አባቱ ሰዎችን ይወድ ነበር። ከአባቱ ጋር አብሮ በተሳተፈባቸው የፍጥረት ሥራዎች ሁሉ ደስተኛ የነበረ ቢሆንም “በተለይ . . . በሰው ልጆች እጅግ [ይደሰት] ነበር።” (ምሳሌ 8:31) ፍቅር፣ ኢየሱስን ለሌሎች ስሜት እንዲያስብ አነሳስቶታል።
9 ሁለተኛ፣ ልክ እንደ ይሖዋ ኢየሱስም ልብን የማንበብ ችሎታ አለው። የሰዎችን ውስጣዊ ዝንባሌና ስሜት ማወቅ ይችላል። (ማቴ. 9:4፤ ዮሐ. 13:10, 11) በመሆኑም ልባቸው የተሰበረ ሰዎችን ሲያይ በአሳቢነት ተነሳስቶ ያጽናናቸው ነበር።—ኢሳ. 61:1, 2፤ ሉቃስ 4:17-21
10 ሦስተኛ፣ ሰዎች ከሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች መካከል አንዳንዶቹ ኢየሱስንም አጋጥመውታል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ያደገው በድሃ ቤተሰብ ውስጥ እንደሆነ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። አሳዳጊ አባቱ ከሆነው ከዮሴፍ ጋር ይሠራ ስለነበር የጉልበት ሥራ ምን ያህል አድካሚ እንደሆነ ያውቃል። (ማቴ. 13:55፤ ማር. 6:3) ዮሴፍ የሞተው ኢየሱስ አገልግሎቱን ከመጀመሩ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ሳይሆን አይቀርም። በመሆኑም ኢየሱስ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለውን ሥቃይ በገዛ ሕይወቱ ተመልክቷል ማለት እንችላለን። በተጨማሪም ኢየሱስ ከእሱ የተለየ ሃይማኖታዊ አመለካከት ባለው ቤተሰብ ውስጥ መኖር ምን ሊመስል እንደሚችል ያውቃል። (ዮሐ. 7:5) ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ያጋጠሙት እነዚህና ሌሎች ሁኔታዎች ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዲያውቅና ስሜታቸውን እንዲረዳ አስችለውታል።
11. ኢየሱስ ለሌሎች ያለው አሳቢነት በግልጽ የታየው በተለይ በየትኛው አጋጣሚ ነው? አብራራ። (ሽፋኑን ተመልከት።)
11 ኢየሱስ ለሌሎች ያለው አሳቢነት በተለይ ተአምር በሚፈጽምበት ወቅት በግልጽ ይታይ ነበር። ኢየሱስ ተአምር ይፈጽም የነበረው እንደዚያ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት ስለተሰማው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ መከራ እየደረሰባቸው ላሉት ሰዎች ‘በጣም ስላዘነላቸው’ ነው። (ማቴ. 20:29-34፤ ማር. 1:40-42) ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ መስማት የተሳነውን ሰው ለብቻው ለይቶ በመውሰድ ሲፈውሰው አሊያም የመበለቷን አንድያ ልጅ ከሞት ሲያስነሳ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። (ማር. 7:32-35፤ ሉቃስ 7:12-15) ኢየሱስ ለእነዚህ ሰዎች ያዘነላቸው ከመሆኑም ሌላ ሊረዳቸው ፈልጎ ነበር።
12. ዮሐንስ 11:32-35 ኢየሱስ የማርታንና የማርያምን ስሜት እንደተረዳ የሚያሳየው እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ የማርታንና የማርያምን ስሜት ተረድቶላቸዋል። በወንድማቸው በአልዓዛር ሞት እንዳዘኑ ሲመለከት ‘እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐንስ 11:32-35ን አንብብ።) ኢየሱስ ያለቀሰው የቅርብ ጓደኛው ስለተለየው ብቻ አልነበረም። ምክንያቱም አልዓዛርን ከሞት ሊያስነሳው እንደሆነ ያውቃል። ኢየሱስ ያለቀሰው ወዳጆቹ ምን ያህል ሐዘን እንደደረሰባቸው ስለተረዳና በዚህም ምክንያት ስሜቱ በጥልቅ ስለተነካ ነው።
13. ኢየሱስ የሌሎችን ስሜት እንደሚረዳ ማወቃችን የሚያበረታታን ለምንድን ነው?
13 ኢየሱስ የሌሎችን ስሜት እንደሚረዳ ማወቃችን በጣም ይጠቅመናል። እርግጥ እኛ እንደ እሱ ፍጹም አይደለንም። ሆኖም ሌሎችን የያዘበትን መንገድ ማሰባችን እሱን እንድንወደው ያደርገናል። (1 ጴጥ. 1:8) በአሁኑ ጊዜ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ እየገዛ መሆኑን ማወቃችን ያበረታታናል። በቅርቡ ደግሞ መከራን ሁሉ ያስወግዳል። ኢየሱስም በአንድ ወቅት ሰው ሆኖ ይኖር ስለነበር የሰይጣን አገዛዝ በሰው ልጆች ላይ ያስከተለውን ሥቃይ ለማስወገድ ከማንም የተሻለ ብቃት አለው። በእርግጥም “በድካማችን ሊራራልን” የሚችል ገዢ ያለን በመሆኑ በጣም ደስተኞች ነን።—ዕብ. 2:17, 18፤ 4:15, 16
ይሖዋና ኢየሱስ የተዉትን ምሳሌ ተከተሉ
14. በኤፌሶን 5:1, 2 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋና ኢየሱስ የተዉትን ምሳሌ ስንመረምር ምን ለማድረግ እንነሳሳለን?
14 ይሖዋና ኢየሱስ የተዉትን ምሳሌ መመርመራችን የሰዎችን ስሜት ለመረዳት ይበልጥ ጥረት እንድናደርግ ያነሳሳናል። (ኤፌሶን 5:1, 2ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ እንደ እነሱ ልብን የማንበብ ችሎታ የለንም። ያም ቢሆን ሌሎች ምን እንደሚሰማቸውና ምን እንደሚያስፈልጋቸው ለመገንዘብ ጥረት ማድረግ እንችላለን። (2 ቆሮ. 11:29) በዙሪያችን ያለው ራስ ወዳድ የሆነ ዓለም፣ ተጽዕኖ እንዲያሳድርብን አንፈቅድም፤ በመሆኑም ‘ስለ ራሳችን ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት እንሰጣለን።’—ፊልጵ. 2:4
15. የሌሎችን ስሜት ለመረዳት ጥረት ማድረግ ያለባቸው በተለይ እነማን ናቸው?
15 በተለይም የጉባኤ ሽማግሌዎች የሌሎችን ስሜት ለመረዳት ጥረት ማድረግ አለባቸው። በአደራ የተሰጧቸውን በጎች የሚይዙበት መንገድ በአምላክ ዘንድ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ያውቃሉ። (ዕብ. 13:17) ሽማግሌዎች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን መርዳት እንዲችሉ የሌሎችን ስሜት የሚረዱ መሆን ይኖርባቸዋል። ታዲያ ሽማግሌዎች ይህን ባሕርይ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
16. አሳቢ የሆነ ሽማግሌ ምን ያደርጋል? ይህስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
16 አሳቢ የሆነ ሽማግሌ ከክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ጊዜ ያሳልፋል። ጥያቄዎችን ይጠይቃቸዋል፤ ከዚያም የሚሰጡትን መልስ በትኩረትና በትዕግሥት ያዳምጣል። በተለይ ደግሞ ውድ ከሆኑት በጎች መካከል አንዱ የልቡን አውጥቶ መናገር ቢፈልግም ስሜቱን እንዴት እንደሚገልጽ ግራ በሚጋባበት ጊዜ እንዲህ ማድረግ አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 20:5) አንድ ሽማግሌ ጊዜውን በልግስና የሚሰጥ ከሆነ ወንድሞቹ ይበልጥ እምነት ይጥሉበታል፣ ከእሱ ጋር ያላቸው ወዳጅነት ይጠናከራል እንዲሁም ለእሱ ያላቸው ፍቅር ይጨምራል።—ሥራ 20:37
17. በርካታ ወንድሞችና እህቶች ከጉባኤ ሽማግሌዎች ባሕርይ ውስጥ ከፍ አድርገው የሚመለከቱት የትኛውን ባሕርይ እንደሆነ ተናግረዋል? ምሳሌ ስጥ።
17 በርካታ ወንድሞችና እህቶች እንደተናገሩት አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ካሉት ባሕርያት ሁሉ ከፍ አድርገው የሚመለከቱት የሌሎችን ስሜት የሚረዳ መሆኑን ነው። ለምን? አደሌድ የተባለች እህት “ስሜታችሁን እንደሚረዱላችሁ ስለምታውቁ እነሱን ማናገር ቀላል ይሆንላችኋል” በማለት ተናግራለች። አክላም “በምታነጋግሯቸው ወቅት ምላሽ የሚሰጡበት መንገድ ስሜታችሁን እንደሚረዱላችሁ በግልጽ ያሳያል” ብላለች። አንድ ወንድም ደግሞ ርኅራኄ ላሳየው ሽማግሌ ያለውን አድናቆት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ያጋጠመኝን ነገር ለአንድ ሽማግሌ ስነግረው ዓይኖቹ እንባ አቀረሩ። ይህ ሁኔታ ፈጽሞ ከአእምሮዬ አይጠፋም።”—ሮም 12:15
18. የሌሎችን ስሜት እንደምንረዳ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
18 እርግጥ የሌሎችን ስሜት እንደሚረዱ ማሳየት ያለባቸው ሽማግሌዎች ብቻ አይደሉም። ሁላችንም ይህን ባሕርይ ማዳበር ይኖርብናል። እንዴት? የቤተሰባችሁ አባላት ወይም የእምነት ባልንጀሮቻችሁ ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመረዳት ጥረት አድርጉ። በጉባኤያችሁ ውስጥ ላሉ ወጣቶች እንዲሁም የታመሙ፣ በዕድሜ የገፉና የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ያጡ ወንድሞች አሳቢነት አሳዩ። ስላሉበት ሁኔታ ጠይቋቸው። ሐሳባቸውን ሲገልጹ በትኩረት አዳምጧቸው። ያለባቸውን ችግር በደንብ እንደምትረዱላቸው እንዲሰማቸው አድርጉ። አቅማችሁ በፈቀደ መጠን እነሱን ለመርዳት ዝግጁ እንደሆናችሁ ግለጹላቸው። እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ እውነተኛ ፍቅር እንዳላችሁ በተግባር ታሳያላችሁ።—1 ዮሐ. 3:18
19. ሌሎችን ለመርዳት ስንሞክር አቀራረባችንን እንደ ሰዎቹ ሁኔታ መቀያየር ያለብን ለምንድን ነው?
19 ሌሎችን ለመርዳት ስንሞክር አቀራረባችንን እንደ ሰዎቹ ሁኔታ መቀያየር አለብን። ለምን? ምክንያቱም ሰዎች ላጋጠማቸው ችግር ምላሽ የሚሰጡበት መንገድ የተለያየ ነው። አንዳንዶች ማውራት ይፈልጋሉ፤ ሌሎች ደግሞ ስለ ችግራቸው ማውራት አይፈልጉም። በመሆኑም እርዳታ መስጠት ብንፈልግም የግል ጉዳያቸውን የሚያውጣጡ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ መቆጠብ ይኖርብናል። (1 ተሰ. 4:11) በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች የሚሰማቸውን አውጥተው ቢናገሩም፣ እነሱ በተናገሩት ሐሳብ የማንስማማበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ሆኖም ይህ የእነሱ ስሜት እንደሆነ ልናስታውስ ይገባል። እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ሥር፣ ለመስማት የፈጠንንና ለመናገር የዘገየን መሆን እንፈልጋለን።—ማቴ. 7:1፤ ያዕ. 1:19
20. በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?
20 የሌሎችን ስሜት እንደምንረዳ ማሳየት ያለብን በጉባኤ ውስጥ ብቻ አይደለም፤ ይህን ግሩም ባሕርይ በአገልግሎታችን ላይም ማንጸባረቅ እንፈልጋለን። ሰዎችን ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ስንካፈል የሌሎችን ስሜት እንደምንረዳ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በቀጣዩ ርዕስ ላይ የዚህን ጥያቄ መልስ እንመረምራለን።
መዝሙር 130 ይቅር ባይ ሁኑ
a ይሖዋ እና ኢየሱስ ለሌሎች ስሜት ከልብ ያስባሉ። ይህ ርዕስ እነሱ ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት እንደምናገኝ ያብራራል። በተጨማሪም የሌሎችን ስሜት መረዳት ያለብን ለምን እንደሆነና ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።
b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ “የሌላውን ስሜት [መረዳት]” ማለት ሌሎች ምን ሊሰማቸው እንደሚችል ለማስተዋል በመሞከር የእነሱን ስሜት መጋራት ማለት ነው። (ሮም 12:15) በዚህ ርዕስ ውስጥ “የሌላውን ስሜት [መረዳት]” እና “አሳቢነት ማሳየት” የሚሉት አገላለጾች ተመሳሳይ ትርጉም ለማስተላለፍ ተሠርቶባቸዋል።
c ይሖዋ ስሜታቸው ለተደቆሰ ታማኝ አገልጋዮቹም ርኅራኄ እንዳለው አሳይቷል። ስለ ሐና (1 ሳሙ. 1:10-20)፣ ስለ ኤልያስ (1 ነገ. 19:1-18) እና ስለ ኤቤድሜሌክ (ኤር. 38:7-13፤ 39:15-18) የሚናገሩትን ዘገባዎች እንደ ምሳሌ መመልከት ይቻላል።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ በስብሰባ አዳራሾቻችን ውስጥ የምናደርጋቸው ስብሰባዎች ለሌሎች ያለንን ፍቅር የምናሳይበት ሰፊ አጋጣሚ ይሰጡናል። በሥዕሉ ላይ (1) አንድ ሽማግሌ፣ አስፋፊ የሆነን አንድ ትንሽ ልጅና እናቱን በደግነት ሲያነጋግራቸው፣ (2) አንድ አባትና ሴት ልጁ አንዲት አረጋዊ እህትን ወደ መኪና ይዘዋቸው ሲሄዱ፣ (3) ሁለት ሽማግሌዎች እርዳታ ማግኘት የምትፈልግን አንዲት እህት በጥሞና ሲያዳምጧት ይታያል።