ምዕራፍ 102
ንጉሡ በውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ
ማቴዎስ 21:1-11, 14-17 ማርቆስ 11:1-11 ሉቃስ 19:29-44 ዮሐንስ 12:12-19
ኢየሱስ እንደ ድል አድራጊ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ
ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ ተነገረ
በሚቀጥለው ቀን ማለትም እሁድ፣ ኒሳን 9 ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ከቢታንያ ወጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም አቀና። በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ወደምትገኘው ቤተፋጌ ሲቃረቡ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ አላቸው፦
“ወደዚያ ወደምታዩት መንደር ሂዱ፤ እዚያ እንደደረሳችሁም አንዲት የታሰረች አህያ ከነውርንጭላዋ ታገኛላችሁ። ፈታችሁ ወደ እኔ አምጧቸው። ማንም ሰው ቢጠይቃችሁ ‘ጌታ ይፈልጋቸዋል’ በሉት። በዚህ ጊዜ ወዲያውኑ ይልካቸዋል።”—ማቴዎስ 21:2, 3
ደቀ መዛሙርቱ፣ ኢየሱስ የሰጣቸው መመሪያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጋር የተያያዘ መሆኑን አላስተዋሉም። በኋላ ላይ ግን የዘካርያስ ትንቢት እየተፈጸመ መሆኑን ተገነዘቡ። ዘካርያስ፣ አምላክ ተስፋ የሰጠበት ንጉሥ ‘ትሑት እንደሆነና በአህያ፣ በአህያዪቱ ልጅ፣ በውርንጭላ ላይ ተቀምጦ’ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚመጣ ተናግሮ ነበር።—ዘካርያስ 9:9
ደቀ መዛሙርቱ፣ ቤተፋጌ ገብተው ውርንጭላውንና እናቱን ሲወስዱ በዚያ ቆመው ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ “ውርንጭላውን የምትፈቱት ለምንድን ነው?” አሏቸው። (ማርቆስ 11:5) ሆኖም እንስሳቱን የሚወስዱት ለጌታ እንደሆነ ሲነግሯቸው ፈቀዱላቸው። ደቀ መዛሙርቱ መደረቢያቸውን በአህያዋና በውርንጭላዋ ላይ አነጠፉ፤ ኢየሱስ ግን በውርንጭላው ላይ ተቀመጠ።
ኢየሱስ በውርንጭላው ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ በዙሪያው ያለው ሕዝብ እየጨመረ መጣ። ብዙ ሰዎች መደረቢያቸውን በመንገዱ ላይ አነጠፉ። ሌሎቹ ደግሞ “በመንገድ ዳር ካሉት ዛፎች ቅርንጫፎች እየቆረጡ አነጠፉ።” ድምፃቸውን ከፍ አድርገውም “እንድታድነው እንለምንሃለን! በይሖዋ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! የሚመጣው የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከ ነው!” አሉ። (ማርቆስ 11:8-10) በሕዝቡ መካከል ያሉ አንዳንድ ፈሪሳውያን ይህን ሲሰሙ ተበሳጩ። ኢየሱስን “መምህር፣ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው እንጂ” አሉት። ኢየሱስም “እላችኋለሁ፣ እነዚህ ዝም ቢሉ እንኳ ድንጋዮች ይጮኻሉ” በማለት መለሰ።—ሉቃስ 19:39, 40
ኢየሱስ፣ ወደ ኢየሩሳሌም በተቃረበ ጊዜ ከተማዋን አይቶ አለቀሰላት፤ እንዲህም አለ፦ “አንቺ፣ አዎ አንቺ ራስሽ፣ ሰላም የሚያስገኙልሽን ነገሮች ምነው ዛሬ በተረዳሽ ኖሮ፤ አሁን ግን ከዓይኖችሽ ተሰውረዋል።” ኢየሩሳሌም ለመታዘዝ አሻፈረኝ ያለችው ሆን ብላ በመሆኑ ቅጣት ይጠብቃታል። ኢየሱስ የሚከተለውን ትንቢት ተናገረ፦ “ጠላቶችሽ በሾለ እንጨት በዙሪያሽ ቅጥር ቀጥረው አንቺን የሚከቡበትና ከሁሉም አቅጣጫ የሚያስጨንቁበት ጊዜ ይመጣል። አንቺንና በውስጥሽ የሚኖሩትን ልጆችሽን ፈጥፍጠው ከአፈር ይደባልቃሉ፤ በአንቺ ውስጥም ሳያፈርሱ እንደተነባበረ የሚተዉት ድንጋይ አይኖርም።” (ሉቃስ 19:42-44) ኢየሱስ በተናገረው መሠረት ኢየሩሳሌም በ70 ዓ.ም. ጥፋት መጣባት።
ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ “‘ይህ ሰው ማን ነው?’ በማለት መላዋ ከተማ ታወከች።” በዚያ ያሉ ሰዎችም “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው!” አሉ። (ማቴዎስ 21:10, 11) ከሕዝቡ መካከል ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሳው የተመለከቱት፣ ስለዚህ ተአምር ለሌሎች መናገር ጀመሩ። ፈሪሳውያኑም ምንም ማድረግ ባለመቻላቸው ምሬታቸውን ገለጹ። እርስ በርሳቸው “ዓለሙ ሁሉ ግልብጥ ብሎ ተከትሎታል” ተባባሉ።—ዮሐንስ 12:18, 19
ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ሁልጊዜ እንደሚያደርገው አሁንም በቤተ መቅደሱ ለማስተማር ሄደ። በዚያም ዓይነ ስውሮችንና አንካሶችን ፈወሰ። የካህናት አለቆችና ጸሐፍት፣ ኢየሱስ እያደረገ ያለውን ሲመለከቱና በቤተ መቅደሱ ውስጥ “የዳዊትን ልጅ እንድታድነው እንለምንሃለን!” እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ሲሰሙ ተቆጡ። የሃይማኖት መሪዎቹ “እነዚህ የሚሉትን ትሰማለህ?” በማለት ኢየሱስን ጠየቁት። እሱም “‘ከልጆችና ከሕፃናት አፍ ምስጋና አዘጋጀህ’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁም?” አላቸው።—ማቴዎስ 21:15, 16
ኢየሱስ ዞር ብሎ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ተመለከተ። ቀኑ እየመሸ በመሆኑ ከሐዋርያቱ ጋር ሆኖ ከዚያ ወጣ። ኒሳን 10 ከመጀመሩ በፊት እንደገና ወደ ቢታንያ ተጓዘ፤ እሁድ ያደረው እዚያ ነው።