ምዕራፍ 104
አይሁዳውያን የአምላክን ድምፅ ሰምተው ያምኑ ይሆን?
ብዙዎች የአምላክን ድምፅ ሰሙ
ለፍርድ መሠረት የሚሆነው ነገር
ሰኞ፣ ኒሳን 10 ገና አልተገባደደም፤ ኢየሱስ አሁንም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲሆን የሚሞትበት ጊዜ እየቀረበ መሆኑን ተናገረ። በአምላክ ስም ላይ የሚደርሰው ነቀፋ ስላሳሰበው “አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው” አለ። በዚህ ጊዜ “ስሜን አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ” የሚል ታላቅ ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።—ዮሐንስ 12:27, 28
በቦታው ቆሞ የነበረው ሕዝብ ግራ ተጋባ። አንዳንዶች የተሰማው ድምፅ ነጎድጓድ እንደሆነ አሰቡ። ሌሎች ደግሞ “መልአክ አናገረው” አሉ። (ዮሐንስ 12:29) ይሁንና የተናገረው ይሖዋ ነው! ደግሞም ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ ሰዎች የአምላክን ድምፅ ሲሰሙ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ከሦስት ዓመት ተኩል በፊት ኢየሱስ በተጠመቀበት ጊዜ አምላክ “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ ስለ ኢየሱስ ሲናገር መጥምቁ ዮሐንስ ሰምቶ ነበር። ከዚያም በ32 ዓ.ም. የፋሲካ በዓል ከተከበረ በኋላ ኢየሱስ በያዕቆብ፣ በዮሐንስና በጴጥሮስ ፊት ተአምራዊ በሆነ መንገድ ተለወጠ። እነዚህ ሦስት ሰዎች፣ አምላክ “በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት” ብሎ ሲናገር አዳምጠዋል። (ማቴዎስ 3:17፤ 17:5) አሁን ለሦስተኛ ጊዜ ይሖዋ፣ ብዙዎች ሊሰሙ በሚችሉበት መንገድ ተናገረ!
ኢየሱስ “ይህ ድምፅ የተሰማው ለእኔ ሳይሆን ለእናንተ ሲባል ነው” አለ። (ዮሐንስ 12:30) የአምላክ ድምፅ መሰማቱ፣ ኢየሱስ በእርግጥም የአምላክ ልጅና አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ መሆኑን ያረጋግጣል።
ኢየሱስ በታማኝነት ያሳለፈው ሕይወት የሰው ልጆች እንዴት መኖር እንዳለባቸው አርዓያ ከመሆኑም ሌላ የዚህ ዓለም ገዢ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ መጥፋት እንደሚገባው የሚያረጋግጥ ነው። ኢየሱስ “ይህ ዓለም የሚፈረድበት ጊዜ አሁን ነው፤ የዚህ ዓለም ገዢ አሁን ይባረራል” አለ። እየቀረበ ያለው የኢየሱስ ሞት፣ ድል እንጂ ሽንፈት አይደለም። እንዴት? ኢየሱስ “እኔ ግን ከምድር ወደ ላይ ከፍ ከተደረግኩ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ወደ ራሴ እስባለሁ” በማለት የተናገረው ሐሳብ መልሱን ይሰጠናል። (ዮሐንስ 12:31, 32) ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ በመሞት ሌሎችን ወደ ራሱ ይስባል፤ በሌላ አባባል የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ መንገድ ይከፍትላቸዋል።
ኢየሱስ ‘ወደ ላይ ከፍ እንደሚደረግ’ ሲናገር ሕዝቡ እንዲህ አሉ፦ “ክርስቶስ ለዘላለም እንደሚኖር ከሕጉ ሰምተናል። ታዲያ አንተ የሰው ልጅ ከፍ ማለት አለበት እንዴት ትላለህ? ይህ የሰው ልጅ ማን ነው?” (ዮሐንስ 12:34) አብዛኞቹ ሰዎች የራሱን የአምላክን ድምፅ መስማትን ጨምሮ ብዙ ማስረጃዎችን የተመለከቱ ቢሆንም ኢየሱስ እውነተኛው የሰው ልጅ ማለትም ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መሆኑን አላመኑም።
ኢየሱስ ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ አሁንም “እኔ . . . ብርሃን ነኝ” በማለት ተናገረ። (ዮሐንስ 8:12፤ 9:5) ከዚያም ሕዝቡን እንዲህ ሲል አሳሰባቸው፦ “ብርሃኑ ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ይቆያል። ጨለማ እንዳይውጣችሁ ብርሃኑ እያለላችሁ በብርሃን ሂዱ፤ . . . የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃኑ እያለላችሁ በብርሃኑ እመኑ።” (ዮሐንስ 12:35, 36) ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ አካባቢውን ለቆ ሄደ፤ ምክንያቱም የሚሞተው ኒሳን 10 አይደለም። ‘ወደ ላይ ከፍ የሚደረገው’ ወይም በእንጨት ላይ የሚቸነከረው ኒሳን 14 በፋሲካ በዓል ላይ ነው።—ገላትያ 3:13
ኢየሱስ ያከናወነውን አገልግሎት መለስ ብለን ስንመለከት አይሁዶች በእሱ አለማመናቸው አስቀድሞ የተነገረው ትንቢት እንዲፈጸም እንዳደረገ ግልጽ ይሆንልናል። ሕዝቡ ተመልሰው እንዳይፈወሱ፣ ዓይናቸው እንደሚታወርና ልባቸው እንደሚደነድን ኢሳይያስ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 6:10፤ ዮሐንስ 12:40) በእርግጥም አብዛኞቹ አይሁዳውያን፣ ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት አዳኛቸውና የሕይወት መንገድ መሆኑን የሚያሳየውን ማስረጃ ለመቀበል አሻፈረን ብለዋል።
ኒቆዲሞስ፣ የአርማትያሱ ዮሴፍና ሌሎች በርካታ ገዢዎች በኢየሱስ ‘አምነዋል።’ ሆኖም እነዚህ ሰዎች እምነት እንዳላቸው ያሳዩ ይሆን? ወይስ ከምኩራብ እንዳይባረሩ በመፍራት ወይም ‘ከሰው የሚገኘውን ክብር በመውደድ’ እምነታቸውን ከመግለጽ ወደኋላ ይላሉ?—ዮሐንስ 12:42, 43
ኢየሱስ በእሱ ማመን ምንን እንደሚጨምር ሲገልጽ “በእኔ የሚያምን ሁሉ በእኔ ብቻ ሳይሆን በላከኝም ጭምር ያምናል፤ እኔን የሚያይ ሁሉ የላከኝንም ያያል” አለ። ኢየሱስ የአምላክን መመሪያ በመከተል የሚያውጀው እውነት በጣም አስፈላጊ በመሆኑ እንዲህ አለ፦ “እኔን የሚንቀውንና ቃሌን የማይቀበለውን ሁሉ የሚፈርድበት አለ። በመጨረሻው ቀን የሚፈርድበት የተናገርኩት ቃል ነው።”—ዮሐንስ 12:44, 45, 48
ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ደመደመ፦ “እኔ የተናገርኩት በራሴ ተነሳስቼ አይደለምና፤ ከዚህ ይልቅ ምን እንደምልና ምን እንደምናገር ያዘዘኝ የላከኝ አብ ራሱ ነው። ደግሞም የእሱ ትእዛዝ የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝ አውቃለሁ።” (ዮሐንስ 12:49, 50) ኢየሱስ በቅርቡ፣ በእሱ ለሚያምኑ ሁሉ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ እንደሚሰጥ ያውቃል።—ሮም 5:8, 9