የምታፈቅሯቸውን በሞት የተለዩአችሁን ሰዎች እንደገና ታገኙአቸው ይሆን?
ጆን እናቱ ስትሞት ገና ዘጠኝ ዓመቱ ነበር። ከጊዜ በኋላ አስከሬኑ ዘመድ ወዳጅ እየመጣ እንዲሰናበተው በተቀመጠበት አዳራሽ ውስጥ የተከናወነውን ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሥዕል ሳልኩላትና ሁላችንንም በመንግሥተ ሰማያት እንድትጠብቀን የሚጠይቅ አጭር ማስታወሻ ጻፍኩላት። በሬሳ ሳጥኑ ውስጥ ከእርሷ ጋር እንዲያስቀምጠው ለአባባ ሰጠሁት። የሞተች ቢሆንም እንኳ ከእኔ ያ የመጨረሻ መልእክት መላኩ ያስደስተኛል።”—አንድ ወላጅ ሲሞት የሚሰማን ስሜት በሚል በጂል ክሬሜንትስ የተጻፈ
ጆን እናቱን በጣም ይወዳት እንደነበረ ምንም አያጠራጥርም። ጥሩ ጥሩ ባሕርያቶቿን ከዘረዘረ በኋላ እንዲህ አለ፦ “መጥፎ ጎኖቿን ማስታወስ ስላልፈለግሁ ብቻ ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ስለእርሷ አንድም መጥፎ ነገር ማሰብ አልችልም። በሕይወቴ ሁሉ ካየኋቸው ቆንጆ ሴቶች እሷን የሚተካከላት የለም።”
ልክ እንደ ጆን ሁሉ ብዙዎች በሞት የተለዩአቸውን ሰዎች እንደሚያፈቅሯቸው የሚገልጹባቸው ትዝታዎች አሏቸው። እነርሱን እንደገና የማግኘት ስሜታዊ ፍላጎት እንዳላቸውም ያምናሉ። የ26 ዓመት ልጅዋ በካንሰር በሽታ የሞተባት ኢድትዝ እንዲህ ብላለች፦ “ልጄ የሆነ ቦታ ይኖራል ብዬ ማመን እፈልጋለሁ፤ ቦታው የት እንደሆነ ግን አላውቅም። እንደገና አየው ይሆን? እንጃ፤ ግን ተስፋ አደርጋለሁ።”
አፍቃሪው የሰው ልጆች ፈጣሪ ይህ የሰው ልጆች ተፈጥሮአዊ ፍላጎት እንደሚሰማው አያጠራጥርም። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሚያፈቅሯቸው በሞት የተለዩአቸው ሰዎች ጋር እንደገና የሚገናኙበት ጊዜ እንደሚመጣ ቃል የገባው ለዚህ ነው። የአምላክ ቃል በቅርቡ ስለሚፈጸመው ስለዚህ የሙታን ትንሣኤ ተስፋ የሚገልጹ ብዙ ጥቅሶችን ይዟል።—ኢሳይያስ 26:19፤ ዳንኤል 12:2, 13፤ ሆሴዕ 13:14፤ ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 20:12, 13
ሰማያዊ ትንሣኤ የሚያገኙት እነማን ናቸው?
የምወዳት እናቴ በሰማይ ትጠብቀኛለች የሚለውን የጆንን ተስፋ እስቲ እንመልከት። አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ብዙዎች ይህ ተስፋ ወይም እምነት አላቸው። እንዲህ ዓይነቶቹን አመለካከቶች ለመደገፍ ቄሶችና አንዳንድ የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኞች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በተሳሳተ መንገድ እየጠቀሱ ይጠቀሙባቸዋል።
ለምሳሌ ያህል የሟች ቤተሰቦችን በመርዳት ልዩ ባለሙያ የሆኑ ዶክተር ኩብለር ሮስ የተባሉ አንዲት ሴት ኦን ችልድረን ኤንድ ዴዝ (ልጆችና ሞት) በተባለ መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “መሞት ማለት ያረጀ ኮታችንን ልንጥለው እንደምንችል ሁሉ አካላችንንም ከላያችን ላይ ማስወገድ ማለት ነው። ወይም ከአንድ ክፍል ወጥቶ ወደሌላ ክፍል መሄድ ማለት ነው። መክብብ 12:7 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ ‘አፈርም ወደነበረበት ወደ ምድር ይመለሳል መንፈስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ይመለሳል።’ ኢየሱስ ‘ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁ’ ብሏል። በመስቀል ላይ ለነበረው ሌባ ደግሞ ‘ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ’ ብሎታል።”
ከላይ ባሉት ጥቅሶች መሠረት በሞት የተለዩን የምናፈቅራቸው ሰዎች በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ ሕያዋን ሆነው በሰማይ እየተጠባበቁን ነው ማለት ነውን? ከመክብብ 12:7 ጀምረን ጥቅሶቹን እስቲ ይበልጥ ጠለቅ ብለን እንመርምራቸው። እነዚህን ቃላት የጻፈው ጠቢቡ ሰው በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ ቀደም ሲል ካሰፈረው ሐሳብ ጋር የሚጋጭ ነጥብ ለመጻፍ እንደማያስብ የታወቀ ነው። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም።” (መክብብ 9:5) በጥቅሉ ስለ ሰው ዘሮች ሞት በአጠቃላይ እየተናገረ ነበር። አምላክ የለም የሚሉ ደፋሮችና በዓመፅ ድርጊት የተጨማለቁ ወንጀለኞች በሙሉ ሲሞቱ ወደ አምላክ ይመለሳሉ ብሎ ማመኑ ምክንያታዊ ነውን? በፍጹም አይደለም። እንዲያውም ራሳችንን ጥሩ ወይም መጥፎ አድርገን አየንም አላየን አንዳችንም ብንሆን ወደ አምላክ እንመለሳለን ሊባልልን አይችልም። አንዳችንም ብንሆን ከዚህ በፊት ከአምላክ ጋር በሰማይ ሳንኖር እንዴት ወደ እርሱ እንመለሳለን ሊባልልን ይችላል?
ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊው አንድ ሰው ሲሞት ‘መንፈሱ ወደ እግዚአብሔር ትመለሳለች’ ሲል ምን ማለቱ ነበር? “መንፈስ” ተብሎ የተተረጎመውን የዕብራይስጥ ቃል ሲጠቀም አንድን ሰው ከሌላው ሰው ስለሚለይ ልዩ ስለሆነ ነገር መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይኸው በመንፈስ አነሣሽነት የጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ በመክብብ 3:19 [አዓት] ላይ ሰውና እንስሳት “ሁሉም አንድ መንፈስ አላቸው” በማለት ይገልጻል። “መንፈስ” የሰዎችንና የእንስሳትን አካል የሚገነባ በሴሎች ውስጥ የሚገኝ የሕይወት ኃይል ነው ማለቱ እንደነበረ ግልጽ ነው። ይህን መንፈስ በቀጥታ ከአምላክ አልተቀበልንም። ስንፀነስና በኋላም ስንወለድ ከሰብዓዊ ወላጆቻችን የወረስነው ነገር ነው። ከዚህም በተጨማሪ አንድ ሰው ሲሞት ይህ መንፈስ ቃል በቃል ሕዋውን አቋርጦ ወደ አምላክ አይመለስም። ‘መንፈስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ይመለሳል’ የሚለው አባባል ምሳሌያዊ አነጋገር ነው። የአንድ የሞተ ሰው የወደፊት ሕይወት ተስፋ በአምላክ እጅ ላይ ወድቋል ማለት ነው። በዝክሩ ውስጥ ማንን እንደሚያስቀምጥና በኋላም እንደሚያስነሣ የሚወስነው ራሱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በመዝሙር 104:29, 30 ላይ እንዴት ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳይ ራሳችሁ ተመልከቱት።
ይሖዋ አምላክ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የክርስቶስ ታማኝ ተከታዮች ማለትም 144,000 ብቻ ሰማያዊ ትንሣኤ አግኝተው የእርሱ መንፈሳውያን ልጆች በመሆን ሕይወት እንዲያገኙ ዓላማው ነው። (ራእይ 14:1, 3) እነዚህ ሰዎች በምድር ላይ የሚኖሩት የሰው ልጆች በረከት እንዲያገኙ ከክርስቶስ ጋር ሆነው አንድ ሰማያዊ መንግሥት ያቋቁማሉ።
ስለዚህ ነገር ለመስማት የመጀመሪያዎቹ የሆኑት የኢየሱስ ታማኝ ሐዋርያት ነበሩ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “በአባቴ ዘንድ ብዙ መኖሪያ አለ፤ አለበለዚያ ግን ‘የምትኖሩበትን ስፍራ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ’ ባላልኋችሁም ነበር። ሂጄ ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እንድትኖሩ እንደገና መጥቼ እወስዳችኋለሁ።” (ዮሐንስ 14:2, 3 የ1980 ትርጉም) እነዚህ ሐዋርያትና ሌሎች የጥንት ክርስቲያኖች ሞቱ፤ ምንም የማይሰሙ በድን ሆነውም ኢየሱስ መጥቶ በማስነሣት የሰማያዊ ሕይወት ሽልማት እስኪሰጣቸው ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው። ስለ መጀመሪያው ሰማዕት ክርስቲያን ስለ እስጢፋኖስ “አንቀላፋ” የሚል ቃል የምናነበው በዚህ ምክንያት ነው።—ሥራ 7:60፤ 1 ተሰሎንቄ 4:13
ምድራዊ ሕይወት አግኝቶ ከሞት መነሣት
ይሁን እንጂ ኢየሱስ በአጠገቡ ለሞተው ወንጀለኛ ስለሰጠው ተስፋ ምን ለማለት ይቻላል? በዚያ ወቅት ይኖሩ እንደነበሩት እንደ ብዙዎቹ አይሁዳውያን ሁሉ ይህ ሰው አምላክ በምድር ላይ ለአይሁድ ሕዝብ መንግሥትን የሚያቋቁምና ሰላምንና ደህንነትን መልሶ የሚያመጣ አንድ መሲሕ ይልካል የሚል እምነት ነበረው። (1 ነገሥት 4:20–25ን ከሉቃስ 19:11፤ 24:21 እና ከሥራ 1:6 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በላይ ንጉሥ እንዲሆን በአምላክ የተመረጠው ሰው ኢየሱስ መሆኑን እንዳመነ ክፉ አድራጊው ገልጿል። ሆኖም ኢየሱስ ሞት ተፈርዶበት በተሰቀለበት በዚያ ሰዓት ይህ ሊሆን የማይችል ነገር መስሎ ነበር። ኢየሱስ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎ ቃል በመግባት ማረጋገጫ የሰጠው ለዚህ ነበር።—ሉቃስ 23:42, 43 አዓት
“ዛሬ” ከሚለው ቃል በፊት ነጠላ ሰረዝ ያስገቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የኢየሱስን ቃላት ለመረዳት ለሚፈልጉት ሰዎች ችግር ፈጥረውባቸዋል። ኢየሱስ በዚያ ቀን ወደ የትኛውም ገነት አልሄደም። ከዚህ ይልቅ አምላክ እስካስነሳው ጊዜ ድረስ ለሦስት ቀናት በሞት በድን ሆኖ ቆይቶ ነበር። ኢየሱስ ከተነሣና ወደ ሰማይ ካረገም በኋላ እንኳን በአባቱ ቀኝ ሆኖ በሰው ዘሮች ላይ ንጉሥ በመሆን የሚገዛበት ጊዜ እስኪደርስ መጠበቅ ነበረበት። (ዕብራውያን 10:12, 13) በቅርቡ የኢየሱስ መንግሥታዊ አገዛዝ ለሰው ዘሮች እፎይታን ታመጣለች፤ መላዋን ምድርም ወደ ገነትነት ትለውጣለች። (ሉቃስ 21:10, 11, 25–31) ከዚያ በኋላ ያንን ወንጀለኛ በምድር ላይ እንዲኖር ከሞት በማስነሣት የገባውን ቃል ይፈጽማል። ይህ ሰው የአኗኗር ዘይቤውን ከአምላክ የጽድቅ ሕግጋት ጋር ለማስማማት እንዲችል የሚያስፈልጉትን ነገሮች ጨምሮ ፍላጎቶቹን ሁሉ በማሟላት ስለሚረዳው ኢየሱስ ከሰውዬው ጋር ይሆናል ማለት ይቻላል።
ብዙዎች የሚያገኙት ትንሣኤ
ንስሐ እንደገባው እንደዚያ ወንጀለኛ ሁሉ የአብዛኛዎቹ ሰዎች ትንሣኤ የሚከናወነው በዚህ ምድር ላይ ነው። ይህም አምላክ ሰውን ሲፈጥር ከነበረው ዓላማ ጋር ይስማማል። አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት በገነት የአትክልት ሥፍራ አስቀመጣቸውና ምድርን እንዲገዟት ነገራቸው። ለአምላክ ታዛዥ ሆነው ቢቀጥሉ ኖሮ እርጅናም ሆነ ሞት አይደርስባቸውም ነበር። አምላክ በወሰነው ጊዜ ምድር በጠቅላላ በአዳምና በፍጹማን ዘሮቹ ትሞላ ነበር፤ ዓለም አቀፋዊ ገነትም ያደርጓት ነበር።—ዘፍጥረት 1:28፤ 2:8, 9
ይሁን እንጂ አዳምና ሔዋን በፈቃዳቸው ኃጢአት በመሥራታቸው በራሳቸውና ከእነሱ በኋላ በሚመጡት ዘሮቻቸው ላይ ሞትን አመጡ። (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:17–19) መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአት በአንድ ሰው [በአዳም] ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” ሲል የሚገልጸው በዚህ ምክንያት ነው።—ሮሜ 5:12
በዘር ከሚተላለፈው ኃጢአት ነጻ ሆኖ የተወለደ አንድ ሰው ብቻ ነበር። ይህ ሰው ሕይወቱ ከሰማይ ወደ አይሁዳዊቷ ድንግል ማርያም ማህፀን የተዛወረው የአምላክ ፍጹም ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበት ሰው ሆኖ ቀጥሏል፤ ሞትም የሚገባው አልነበረም። ስለዚህ ‘ስለ ዓለም ኃጢአት ሲል’ መሞቱ ቤዛዊ ዋጋ አለው። (ዮሐንስ 1:29፤ ማቴዎስ 20:28) ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል” ብሎ ሊናገር የቻለው ለዚህ ነው።—ዮሐንስ 11:25
እንግዲያው ከምታፈቅሯቸው በሞት ከተለዩአችሁ ሰዎች ጋር እንደገና ለመገናኘት ተስፋ ልታደርጉ ትችላላችሁ። ይሁን እንጂ ይህን ተስፋ ለመጨበጥ ኢየሱስን አንደ አዳኛችሁ በመመልከት በእርሱ ላይ እምነት ማሳደርና በአምላክ እንደ ተሾመ ንጉሥ አድርጋችሁ በማየት ለእርሱ መታዘዝ ይኖርባችኋል። በቅርቡ የአምላክ መንግሥት ክፋትን ሁሉ ከምድር ገጽ ጠራርጋ ታጠፋለች። ለዚህች መንግሥት አልገዛ ያሉት ሰዎች በሙሉ ይደመሰሳሉ። የአምላክ መንግሥት ተገዥዎች ግን ከጥፋቱ ተርፈው ይህችን ምድር ወደ ገነትነት በመለወጡ ሥራ ይጠመዳሉ።—መዝሙር 37:10, 11፤ ራእይ 21:3–5
ከዚያ በኋላ ትንሣኤ የሚጀምርበት አስደናቂ ጊዜ ከተፍ ይላል። የሞቱ ሰዎችን ሁለት እጃችሁን ዘርግታችሁ እንደገና ለመቀበል በዚያ ቦታ ትገኛላችሁን? ይህ አሁን በምታደርጉት ነገር ላይ ሙሉ በሙሉ የተመካ ነው። በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ለምትመራው የይሖዋ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ራሳቸውን የሚያስገዙ ሁሉ አስደሳች በረከቶች ከፊታቸው ይጠብቋቸዋል።