የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የዮሐንስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
ስለ ክርስቶስ ሕይወትና አገልግሎት የሚገልጸውን ታሪክ በመንፈስ አነሳሽነት ከጻፉት ሰዎች መካከል የመጨረሻው ዮሐንስ ሲሆን ይህ ሰው “ኢየሱስ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር” ተብሎ ተጠርቷል። (ዮሐ. 21:20) በ98 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ የተጻፈው የዮሐንስ ወንጌል በሦስቱ ወንጌሎች ውስጥ የማይገኙ በርካታ ሐሳቦችን ይዟል።
ሐዋርያው ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው አንድ ዓላማ በአእምሮው ይዞ ነበር። የጻፋቸውን ነገሮች አስመልክቶ ሲናገር “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፣ አምናችሁም በስሙ ሕይወት እንዲኖራችሁ ይህ ተጽፎአል” ብሏል። (ዮሐ. 20:31) በእርግጥም ይህ ወንጌል ለእኛ ከፍተኛ ጥቅም አለው።—ዕብ. 4:12
‘እነሆ! የአምላክ በግ’
መጥምቁ ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ሲመጣ አይቶ ‘እነሆ! የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የአምላክ በግ’ በማለት በእርግጠኝነት ተናገረ። (ዮሐ. 1:29) ኢየሱስ እየሰበከ፣ እያስተማረና ተአምራትን እያደረገ በሰማርያ፣ በገሊላ፣ በይሁዳና ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሚገኙ አካባቢዎች ሲጓዝ ‘ብዙ ሰዎች ወደ እሱ ይመጡና በእሱ ያምኑ ነበር።’—ዮሐ. 10:41, 42
ኢየሱስ ከፈጸማቸው በጣም አስደናቂ ተአምራት ውስጥ አንዱ አልዓዛርን ከሞት ማስነሳቱ ነው። ብዙዎች ለአራት ቀናት ሞቶ የነበረ ሰው ሕያው ሆኖ ሲያዩ በኢየሱስ አምነዋል። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ግን ኢየሱስን ለመግደል ተማከሩ። በመሆኑም ኢየሱስ “በምድረ በዳ አጠገብ ወደምትገኝ ኤፍሬም ወደ ተባለች መንደር” ሄደ።—ዮሐ. 11:53, 54
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
1:35, 40—ከእንድርያስ ሌላ ከመጥምቁ ዮሐንስ ጋር የነበረው ደቀ መዝሙር ማን ነው? ጸሐፊው በወንጌሉ ውስጥ መጥምቁ ዮሐንስን ሁልጊዜ “ዮሐንስ” ብሎ የጠራው ሲሆን ስለ ራሱ ሲናገር ግን ስሙን አልጠቀሰም። በመሆኑም ስሙ ያልተጠቀሰው ደቀ መዝሙር ወንጌል ጸሐፊው ዮሐንስ እንደሆነ ግልጽ ነው።
2:20—‘ለመሥራት አርባ ስድስት ዓመት የፈጀው’ ቤተ መቅደስ የትኛው ነው? እዚህ ላይ አይሁዳውያን የይሁዳ ንጉሥ በነበረው በሄሮድስ አማካኝነት እንደገና ስለተገነባው የዘሩባቤል ቤተ መቅደስ መናገራቸው ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ እንዳለው የዚህ ቤተ መቅደስ ግንባታ የተጀመረው ሄሮድስ በነገሠ በ18ኛው ዓመት ወይም በ18/17 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። ቤተ መቅደሱና ሌሎች ዋና ዋና ነገሮች የተገነቡት በስምንት ዓመት ውስጥ ነው። ይሁን እንጂ በቤተ መቅደሱ አቅራቢያ የሚገኙት የሌሎች ሕንፃዎች ግንባታ በ30 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እስከተከበረው የፋሲካ በዓል ድረስ ቀጥሎ ስለነበር አይሁዳውያኑ ሥራው 46 ዓመት እንደፈጀ ገልጸዋል።
5:14—አንድ ሰው የሚታመመው በሠራው ኃጢአት ምክንያት ነው? ሁልጊዜ እንደዚያ ነው ማለት አይቻልም። ኢየሱስ የፈወሰው ግለሰብ ለ38 ዓመት የታመመው በወረሰው አለፍጽምና ምክንያት ነው። (ዮሐ. 5:1-9) እዚህ ላይ ኢየሱስ፣ ሰውየው ምሕረት ስለተደረገለት ከዚያ በኋላ መዳን የሚገኝበትን መንገድ መከተልና ሆነ ብሎ ኃጢአት ከመሥራት መቆጠብ እንዳለበት መናገሩ ነበር። አለበለዚያ ከበሽታው የከፋ ነገር ይደርስበታል። ግለሰቡ ሆነ ብሎ ኃጢአት ከሠራ ይቅር የማይባል ኃጢአት ይሆንበታል፤ ይህ ደግሞ ትንሣኤ የሌለው ሞት ያስከትልበታል።—ማቴ. 12:31, 32፤ ሉቃስ 12:10፤ ዕብ. 10:26, 27
5:24, 25—‘ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገሩት’ እነማን ናቸው? ኢየሱስ በአንድ ወቅት በመንፈሳዊ ሙታን ስለነበሩ ሆኖም ቃሉን ከሰሙ በኋላ በእሱ አምነው በኃጢአት ጎዳና መመላለሳቸውን ስለተዉ ሰዎች መናገሩ ነበር። እነዚህ ሰዎች ከሞት ኩነኔ ነፃ ስለወጡ እንዲሁም በአምላክ ላይ ባላቸው እምነት ምክንያት የዘላለም ሕይወት ተስፋ ስለተዘረጋላቸው ‘ከሞት ወደ ሕይወት ተሻግረዋል’ ሊባል ይችላል።—1 ጴጥ. 4:3-6
5:26፤ 6:53—‘በራሱ ሕይወት አለው’ ሲባል ምን ማለት ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ ሕይወት አለው ሲባል ከአምላክ ሁለት ልዩ ችሎታዎች ተሰጥተውታል ማለት ነው። አንደኛው፣ ሰዎች በይሖዋ ፊት ተቀባይነት እንዲኖራቸው የማድረግ ችሎታ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሞቱ ሰዎችን ከሞት አስነስቶ ሕይወት የመስጠት ኃይል ነው። የኢየሱስ ተከታዮች ‘በራሳቸው ሕይወት አላቸው’ ሲባል ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ ማለት ነው። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይህን ሕይወት የሚያገኙት ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ ሲሄዱ ነው። ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ታማኝ ሰዎች ደግሞ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት እንዳበቃ የሚኖረውን ፈተና ሲያልፉ ነው።—1 ቆሮ. 15:52, 53፤ ራእይ 20:5, 7-10
6:64—ኢየሱስ የአስቆሮቱ ይሁዳን ከመረጠበት ጊዜ አንስቶ አሳልፎ እንደሚሰጠው ያውቅ ነበር? አያውቅም ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ በ32 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “ከእናንተ አንዱ ዲያብሎስ ነው” ብሏቸው ነበር። ኢየሱስ በወቅቱ የአስቆሮቱ ይሁዳ መጥፎ አካሄድ መጀመሩን ሳያስተውል አልቀረም።—ዮሐ. 6:66-71
ምን ትምህርት እናገኛለን?
2:4:- ኢየሱስ የተጠመቀና የተቀባ የአምላክ ልጅ እንደመሆኑ መጠን መመሪያ መቀበል ያለበት በሰማይ ከሚኖረው አባቱ መሆኑን ለማርያም መጠቆሙ ነበር። ኢየሱስ ገና አገልግሎቱን መጀመሩ ቢሆንም እንኳ መሥዋዕት ሆኖ መሞቱን ጨምሮ የተሰጠውን ሥራ የሚያከናውንበትን ጊዜ በሚገባ ያውቅ ነበር። እንደ ማርያም ያሉ ቅርብ የቤተሰቡ አባላት እንኳ መለኮታዊውን ፈቃድ ሲያከናውን ጣልቃ እንዲገቡበት አልፈቀደም። እኛም ይሖዋን ስናገለግል ተመሳሳይ አቋም ሊኖረን ይገባል።
3:1-9:- የአይሁድ አለቃ ከነበረው ከኒቆዲሞስ ሁለት ነገሮችን እንማራለን። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኒቆዲሞስ የአንድን አናጢ ልጅ ከአምላክ የተላከ መምህር እንደሆነ አድርጎ በመቀበል ትሑት፣ አስተዋይና መንፈሳዊ ነገር እንደሚያስፈልገው የሚገነዘብ ሰው መሆኑን አሳይቷል። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ትሑት መሆን ያስፈልጋቸዋል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኒቆዲሞስ ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ የእሱ ደቀ መዝሙር አልነበረም። ለዚህ ምክንያቱ የሰው ፍርሃት፣ በሳንሄድሪን የነበረውን ሥልጣን ላለማጣት የነበረው ፍላጎት አሊያም ለሀብት የነበረው ፍቅር ሊሆን ይችላል። እኛም ከዚህ እንደምንማረው፣ እንዲህ ያሉት ነገሮች ‘የራሳችንን የመከራ እንጨት ተሸክመን ኢየሱስን ያለማቋረጥ ከመከተል’ ወደኋላ እንድንል ሊያደርጉን አይገባም።—ሉቃስ 9:23 NW
4:23, 24:- አምልኮታችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጸው እውነት ጋር መስማማትና መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠውን አመራር መከተል አለብን።
6:27:- “ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር ምግብ” መሥራት ሲባል መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ማለት ነው። ይህን ስናደርግ ደስታ እናገኛለን።—ማቴ. 5:3
6:44:- ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ያስብልናል። ምሥራቹ ለእያንዳንዳችን እንዲደርሰን በማድረግ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንድናስተውልና ተግባራዊ እንድናደርግ በመርዳት ወደ ልጁ ይስበናል።
11:33-36:- ስሜትን አውጥቶ መግለጽ የድክመት ምልክት አይደለም።
‘እሱን መከተላችሁን ቀጥሉ’
በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የፋሲካ በዓል ሲቃረብ ኢየሱስ ወደ ቢታንያ ተመልሶ መጣ። ኒሳን 9 ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። ኒሳን 10 በድጋሚ ወደ ቤተ መቅደስ መጣ። ኢየሱስ የአባቱ ስም እንዲከበር ላቀረበው ጸሎት ከሰማይ “አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ” የሚል መልስ አገኘ።—ዮሐ. 12:28
የፋሲካን እራት እየበሉ ሳለ ኢየሱስ ለተከታዮቹ የመሰነባበቻ ምክር ሰጣቸው፤ ከዚያም ጸለየላቸው። ኢየሱስ ከተያዘ፣ ለፍርድ ከቀረበና ከተሰቀለ በኋላ ከሞት ተነሳ።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
14:2—ኢየሱስ ለታማኝ ተከታዮቹ ‘ስፍራ የሚያዘጋጅላቸው’ እንዴት ነው? ይህ ሁኔታ ኢየሱስ የደሙን ዋጋ በአምላክ ፊት አቅርቦ አዲሱ ቃል ኪዳን የጸና እንዲሆን ማድረጉን ያመለክታል። ከዚህም በላይ ክርስቶስ ንጉሣዊ ሥልጣኑን መቀበሉንም ይጨምራል፤ ከዚያም ቅቡዓን ተከታዮቹ በሰማይ ለመኖር ትንሣኤ የሚያገኙበት ጊዜ ይጀምራል።—1 ተሰ. 4:14-17፤ ዕብ. 9:12, 24-28፤ 1 ጴጥ. 1:19፤ ራእይ 11:15
19:11—ኢየሱስ አሳልፎ ስለሰጠው ሰው ለጲላጦስ ሲናገር የአስቆሮቱ ይሁዳን መጥቀሱ ነበር? ኢየሱስ ይህን የተናገረው ይሁዳን ወይም ሌላን ግለሰብ በአእምሮው ይዞ ሳይሆን በእሱ መገደል ተጠያቂ የነበሩትን ሁሉ ለማመልከት ሳይሆን አይቀርም። ይህ ደግሞ ይሁዳን፣ ‘የካህናት አለቆችንና የአይሁድ ሸንጎን’ አልፎ ተርፎም በርባን እንዲፈታ ሲወተውት የነበረውን ‘ሕዝብ’ ይጨምራል።—ማቴ. 26:59-65፤ 27:1, 2, 20-22
20:17—ኢየሱስ መግደላዊት ማርያምን አትንኪኝ ያላት ለምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ “መንካት” ተብሎ የሚተረጎመው ግሪክኛ ግስ “ሙጭጭ አድርጎ መያዝ፣ ማቀፍ፣ አጥብቆ መያዝ፣ መጨበጥ እና ማገድ” የሚል ትርጉምም አለው። ኢየሱስ ከእሷ ከተለየ በኋላ ሌሎች ሴቶች ‘እግሩን እንዲይዙት’ መፍቀዱ መግደላዊት ማርያም ጨርሶ እንዳትነካው እንዳልከለከላት ያስገነዝበናል። (ማቴ. 28:9) ማርያም ኢየሱስን ሙጭጭ አድርጋ የያዘችው ወደ ሰማይ እንደሚያርግና ዳግመኛ እንደማታየው ስለተሰማት ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሚያርግበት ጊዜ ገና እንደሆነ ለማስረዳት ሲል እንዳትይዘው ከዚያ ይልቅ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሄዳ ከሞት መነሳቱን እንድትነግራቸው መጠየቁ ነበር።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
12:36:- “የብርሃን ልጆች” ወይም ብርሃን አብሪዎች ለመሆን የአምላክ ቃል የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት ሊኖረን ይገባል። ያገኘነውን እውቀት ደግሞ ሌሎች ከመንፈሳዊ ጨለማ ወጥተው አምላክ ወደሚሰጠው ብርሃን እንዲመጡ ለመርዳት ልንጠቀምበት ይገባል።
14:6:- በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ካልሆነ በስተቀር በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት አንችልም። ወደ ይሖዋ መቅረብ የምንችለው በኢየሱስ ካመንና የእሱን ምሳሌ ከተከተልን ብቻ ነው።—1 ጴጥ. 2:21
14:15, 21, 23, 24፤ 15:10:- መለኮታዊውን ፈቃድ በታዛዥነት መፈጸማችን ከአምላክና ከልጁ ፍቅር እንዳንወጣ ይረዳናል።—1 ዮሐ. 5:3
14:26፤ 16:13:- የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ የሚያስተምረን ከመሆኑም ሌላ ቀደም ሲል የምናውቃቸውን ነገሮች ያስታውሰናል። በተጨማሪም መንፈሳዊ እውነቶችን ይገልጥልናል። ይህ ደግሞ በእውቀት፣ በጥበብና በማስተዋል እንድናድግ እንዲሁም የማመዛዘንና የማሰብ ችሎታችን እንዲሰፋ ይረዳናል። በመሆኑም መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠን ለይተን በመጥቀስ በጸሎት መጽናት ይኖርብናል።—ሉቃስ 11:5-13
21:15, 19:- ኢየሱስ፣ ጴጥሮስን “ከእነዚህ” ማለትም ፊት ለፊታቸው ከነበሩት ዓሦች አስበልጦ ይወደው እንደሆነ ጠይቆታል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ዓሣ ከማጥመድ ሥራው ይልቅ እሱን ሙሉ በሙሉ መከተሉ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ጠበቅ አድርጎ ገልጾለታል። በወንጌሎች ውስጥ የሰፈረውን ሐሳብ ከመረመርን በኋላ ትኩረታችንን ሊስብ ከሚችል ከማንኛውም ነገር አስበልጠን ኢየሱስን ለመውደድ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። አዎን፣ በሙሉ ልባችን እሱን መከተላችንን እንቀጥል።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከኒቆዲሞስ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?