ከኢየሱስ ተአምራት የሚገኙ ትምህርቶች
“በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፣. . . ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት፦ የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው።” ይህ አጋጣሚ ኢየሱስ ላደረገው የመጀመሪያ ተአምር መንገድ ከፈተ።—ዮሐንስ 2:1–3
እንዲህ ያለው ችግር በጣም ቀላልና የኢየሱስን ትኩረት የማይሻ ጉዳይ አልነበረምን? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ፦ “በምሥራቁ ዓለም እንግዳ ተቀባይነት ከባድ ግምት የሚሰጠው ተግባር ነበር . . . ልባዊ የሆነ እንግዳ ተቀባይነት በተለይ በሰርግ ግብዣ ላይ ድል ያለ ድግስ ማድረግን ይጠይቃል። በሰርግ ድግሱ ላይ [እጅ አጥሮ] ከነበረ ቤተሰቡና ወጣት ባልና ሚስቱ መቼም ቢሆን ሃፍረቱን አይረሱትም።”
በዚህም ምክንያት ኢየሱስ እርምጃ ወሰደ። “አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው” ተመለከተ። በአይሁዶች ዘንድ ከምግብ በፊት መታጠብ የተለመደ ሥርዓት ሲሆን በዚያ ለተገኙት ሁሉ የሚበቃ ብዛት ያለው ውኃ ያስፈልግ ነበር። ኢየሱስ “ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው” በማለት አስተናጋጆቹን አዘዛቸው። ኢየሱስ “የግብዣው ኃላፊ” ባይሆንም በቀጥታና በሥልጣን ይናገር ነበር። ታሪኩ “የግብዣው ኃላፊ ውኃውን ሲቀምሰው [ውኃው] ወደ ወይን ጠጅ ተለውጦ ነበር” ብሎ ይናገራል።—ዮሐንስ 2:6–9 አዓት፤ ማርቆስ 7:3
እንደ ሠርግ ያለ የተለመደ ነገር ኢየሱስ የመጀመሪያ ተአምር የሚፈጽምበት አጋጣሚ መሆኑ እንግዳ ቢመስልም የተፈጸመው ነገር ስለ ኢየሱስ ብዙ ይገልጻል። እርሱ ነጠላ ሰው የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት የነጠላነትን ጠቃሚ ጎኖች ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተወያይቶባቸዋል። (ማቴዎስ 19:12) በሌላ አንጻር በሠርግ ድግስ ላይ መገኘቱ ፀረ–ጋብቻ እንዳልነበረ ያሳያል። የጋብቻን ዝግጅት የሚደግፍ ሚዛናዊ ሰው የነበረ ሲሆን ጋብቻን በአምላክ ዓይን ክቡር እንደሆነ ነገር አድርጎ ተመልክቶታል።—ከዕብራውያን 13:4 ጋር አወዳድር።
በተጨማሪም ኢየሱስ የቤተ ክርስቲያን ሠዓሊዎች ከጊዜ በኋላ እንደሰየሙት ራሱን የሚጎዳ ባሕታዊ አልነበረም። ከሰዎች ጋር አብሮ በመሆኑ እንደተደሰተ ምንም አያጠያይቅም፤ እንዲሁም በሕብረት መሆንን አላወገዘም። (ከሉቃስ 5:29 ጋር አወዳድር።) የፈጸማቸው ተግባራት ለተከታዮቹ ምሳሌ ሆነዋል። ጻድቅ መሆን ማለት ደስታ ቢስነት ይመስል ሳያስፈልግ ኮስታራ መሆን ወይም ፊትን የሐምሌ ደመና ማስመሰል እንዳልሆነ ኢየሱስ በራሱ አሳይቷል። ከዚህ ይልቅ ከጊዜ በኋላ ክርስቲያኖች “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ” ተብለው ታዘዋል። (ፊልጵስዩስ 4:4) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ለመዝናኛ ተገቢውን ገደብ በማበጀት ጥንቃቄ ያደርጋሉ። በአምላክ አገልግሎት የሚደሰቱ ቢሆኑም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል አልፎ አልፎ ከባልንጀሮቻቸው ጋር እርስ በርስ ተገናኝተው የሚደሰቱበትን ጊዜ ያመቻቻሉ።
በተጨማሪም ኢየሱስ አንጀቱ እንደተላወሰ ተመልከት። ተአምር እንዲፈጽም የሚያስገድደው ሁኔታ አልነበረም። ይህንን በተመለከተ መፈጸም የነበረበት ትንቢት አልነበረም። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ስሜቱ የተነሳሳው በእናቱ አሳቢነትና አዲሶቹ ጎጆ ወጪዎች በተጋረጠባቸው መጥፎ ችግር ምክንያት ነው። ለስሜታቸው አስቧል፤ እንዲሁም ከሚደርስባቸው ሀፍረት ሊገላግላቸው ፈልጓል። ሌላው ቀርቶ ክርስቶስ ለዕለት ተዕለት ችግሮችህ እንኳ ልባዊ የሆነ አሳቢነት ማሳየቱ ያለህን እምነት አይገነባውምን?—ከዕብራውያን 4:14–16 ጋር አወዳድር።
እያንዳንዱ ጋን ‘ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ውኃ ለመያዝ ይችል ስለነበር’ ኢየሱስ በተአምር የለወጠው የወይን ጠጅ ምናልባትም 390 ሊትር (105 ጋሎን) የሚያክል ላቅ ያለ መጠን ነበረው! (ዮሐንስ 2:6) ይህ ሁሉ ለምን አስፈለገ? ኢየሱስ አምላክ የከለከለውን ሰካራምነት እያበረታታ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። (ኤፌሶን 5:18) ከዚህ ይልቅ የአምላክ ዓይነት ለጋስነት እያሳየ ነበር። ወይን መደበኛ መጠጥ ስለነበረ የተረፈው ለሌላ ጊዜ ሊያገለግል ይችል ነበር።—ከማቴዎስ 14:14–20፤ 15:32–37 ጋር አወዳድር።
የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የኢየሱስን የለጋስነት ምሳሌ ኮርጀዋል። (ከሥራ 4:34, 35 ጋር አወዳድር።) እንዲሁም በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች ልክ እንደዚሁ ‘ሰጪ እንዲሆኑ’ ተበረታተዋል። (ሉቃስ 6:38) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ያደረገው የመጀመሪያ ተአምር ትንቢታዊ ቁም ነገርም አለው። አምላክ በልግስና “የሰባ ግብዣ፣ ያረጀ የወይን ጠጅ” የሚያዘጋጅበትንና ረሃብን ሙሉ በሙሉ የሚያስወግድበትን የወደፊቱን ጊዜ ያመለክታል።—ኢሳይያስ 25:6
ነገር ግን አካላዊ ፈውስን በተመለከተ ኢየሱስ የፈጸማቸው አያሌ ተአምራትስ? ከእነርሱ ምን ልንማር እንችላለን?
በሰንበት መልካም ማድረግ
“ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ።” ኢየሱስ እነዚህን ቃላት የተናገረው ለ38 ዓመታት ታሞ ለነበረ አንድ ሰው ነው። የወንጌሉ ዘገባ በመቀጠል “ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ” ይላል። የሚያስገርመው በዚህ የሁኔታዎች መለወጥ የተደሰቱት ሁሉም ሰዎች አልነበሩም። “በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር” በማለት ታሪኩ ይናገራል።—ዮሐንስ 5:1–9, 16
ሰንበት ለሁሉም የዕረፍትና የመደሰቻ ቀን እንዲሆን ታቅዶ ነበር። (ዘጸአት 20:8–11) በኢየሱስ ዘመን ግን በሰው ሠራሽ ሕግጋት የተወሳሰበ ሸክም ሆኖ ነበር። አልፍሬድ ኢደርሻይም የተባሉት ምሁር በታልሙድ መጽሐፍ ላይ ስላለው የተንዛዙ የሰንበት ሕግ ክፍሎች እንዲህ በማለት ጽፈዋል “ብዙ ጉዳዮች ጠቃሚ የሆነ ሃይማኖታዊ ትርጉም እንዳላቸው ተደርገው ከልብ ተብራርተዋል፤ ጤናማ የማሰብ ችሎታ ያለው አንድ ሰው ከቁብ የማይቆጥረው ጉዳይም በቁም ነገር ታስቦበታል።” (ዘ ላይፍ ኤንድ ታይምስ ኦቭ ጂሰስ ዘ መሳያ) ረቢዎች የአይሁድን መላ የሕይወት ዘርፍ የሚቆጣጠሩ ከንቱ ለሆኑና በየጊዜው ለሚለዋወጡት ሕግጋት የሕይወትና ሞት ያህል ከፍተኛ ግምት ይሰጧቸዋል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሕግጋት ለሰው ስሜት ምንም ግድ የላቸውም። አንድ የሰንበት ሕግ እንዲህ ሲል ያዛል “ሕንፃ በአንድ ሰው ላይ ቢወድቅና ሰውዬው ውስጡ አለ ወይስ የለም፣ በሕይወት አለ ወይስ ሞቷል፣ አሕዛብ ነው ወይስ እስራኤላዊ የሚል ጥርጣሬ ካለ ፍርስራሹን ከላዩ ላይ ሊያነሱለት ይችላሉ። በሕይወት ካገኙት በላዩ ላይ የቀረውንም ሊያነሱለት ይችላሉ ከሞተ ግን ትተውት ይሂዱ”—ትራክቴት ዮማ 8:7 ዘ ሚሽና፣ በሃርበርት ዳንቤ የተተረጎመ።
ኢየሱስ እንደነዚህ ያሉትን የማያፈናፍኑ ልዩነቶች ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶችን እንዴት ተመለከታቸው? በሰንበት ቀን በመፈወሱ በተተቸ ጊዜ “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 5:17) ኢየሱስ ራሱን ለማበልጸግ ተቀጥሮ የሚሠራ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የአምላክን ፍቃድ ይፈጽም ነበር። ልክ ሌዋውያን በሰንበት ቀን ቅዱስ አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ እንደተፈቀደላቸው ሁሉ እርሱም መሲሕ እንደመሆኑ መጠን አምላክ የሰጠውን ሥራ የአምለክን ሕግ ሳይጥስ በትክክል መፈጸም ይችላል።—ማቴዎስ 12:5
በተጨማሪም ኢየሱስ በዕለተ ሰንበት የፈጸመው ፈውስ የአይሁድ ጻፎችና ፈሪሳውያን ድርቅ ያሉና ሚዛናዊ አስተሳሰብ የሌላቸው ‘እጅግ ጻድቆች’ እንደሆኑ አጋልጧል። (መክብብ 7:16) መልካም ተግባራት በተወሰኑ የሳምንቱ ቀናት ብቻ እንዲከናወኑ የአምላክ ፈቃድ እንዳልነበረ ወይም ደግሞ አምላክ ሰንበት የማያፈናፍን ጥቅም አልባ ሥርዓት እንዲሆን እንዳላቀደ የተረጋገጠ ነው። ኢየሱስ በማርቆስ 2:27 ላይ “ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም” ብሏል። ኢየሱስ ፍርደ ገምድል ሕግጋትን ሳይሆን ሰዎችን ይወድ ነበር።
በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም ከመጠን በላይ ጥብቅ ባይሆኑ ወይም በሕግ ላይ ድርቅ ያለ አመለካከት ባይኖራቸው ጥሩ ነው። በጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ላይ ያሉ በሌሎች ላይ ከመጠን ያለፉ ሰው ሠራሽ ሕጎችንና ደንቦችን ከመጫን ይቆጠባሉ። በተጨማሪም የኢየሱስ ምሳሌ መልካም ለማድረግ አጋጣሚዎችን እንድንፈልግ ያበረታታናል። ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለሰዎች የሚያካፍለው መደበኛ በሆነ መንገድ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ሲካፈል ወይም መድረክ ላይ ወጥቶ ንግግር ሲሰጥ ብቻ እንደሆነ አድርጎ ፈጽሞ ማሰብ የለበትም። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደተናገረው ክርስቲያኖች ‘በእነርሱ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋቸው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጁ’ መሆን አለባችው። (1 ጴጥሮስ 3:15፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) መልካም ማድረግ የጊዜ ገደብ የለውም።
ስለ ርኅራኄ የተሰጠ ትምህርት
ሌላው ዝነኛ ተአምር በሉቃስ 7:11–17 ላይ የተመዘገበው ነው። ታሪኩ እንደሚገልጽልን ኢየሱስ “ናይን ወደምትባል ወደ አንዲት ከተማ ሄደ፣ ደቀ መዛሙርቱም ብዙ ሕዝብም ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ።” ከዘመናዊቷ የዓረብ መንደር ከናይን ደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ መካነ መቃብሮችን እስከ ዛሬ ድረስ መመልከት ይቻላል። “ወደ ከተማይቱ በር በቀረበ ጊዜ” ጩኸት የሞላበት አንድ ሁኔታ አጋጠመው። “እነሆ፣ የሞተ ሰው ተሸክመው አወጡ፤ እርሱም ለእናቱ አንድ ልጅ ነበረ፣ እርስዋም መበለት ነበረች፣ ብዙም የከተማ ሕዝብ ከእርስዋ ጋር አብረው ነበሩ።” ኤች ቢ ትሪስትራም ጥንት ከነበረው “የቀብር ሥርዓት ምንም አልተለወጠም” በማለት አስታውቀዋል፤ አክለውም “በአስለቃሽ ሴቶች እየተመራች ከቃሬዛው ፊት ፊት የምትሄድ ሴት አይቻለሁ። እጆቻቸውን ያወናጭፋሉ፣ በሐዘን እየተወራጩ ጸጉራቸውን ይነጫሉ፤ እንዲሁም የሟቹን ስም ጮክ ብለው ይጠራሉ።”—ኢስተርን ካስተምስ ኢን ባይብል ላንድስ
እንዲህ ባለው በጩኸት በተሞላ ትርምስ ውስጥ በፊቷ ላይ መሪር ሐዘን የሚታይባት አንዲት ሐዘንተኛ መበለት ትራመዳለች። ባሏን አስቀድማ አጥታ ስለነበር ደራሲው ኸርበርት ሎክየር እንዳሉት ልጅዋን “በስተርጅናዋ የሚጦራትና ከብቸኝነቷ የሚያጽናናት የቤቱ አለኝታና ምሰሶ” አድርጋ ትመለከተው ነበር። “አንድያ ልጅዋን በማጣቷ የቀራት የመጨረሻ አለኝታዋ ጠፍቶ ነበር።” (ኦል ዘ ሚራክል ኦቭ ዘ ባይብል) ኢየሱስ ያሳየው ስሜት ምን ነበር? ልብ የሚነኩት የሉቃስ ቃላት “ጌታም ባያት ጊዜ አዘነላትና፦ አታልቅሽ አላት” በማለት ይገልጻሉ። “አዘነላትና” የሚለው አገላለጽ ቃል በቃል “አንጀት” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው። ይህም “ከውስጣዊ ስሜቱ ተነሳሳ” ማለት ነው። (ቫይንስ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ወርድስ) አዎን፣ ኢየሱስ ከውስጡ ተፈንቅሎ ነበር።
በዚህ ወቅት የራሱ የኢየሱስ እናት መበለት እንደነበረች የታወቀ ሲሆን፤ የሚወዱት ሰው ከአጠገብ ሲለይ የሚኖረው ሐዘን ምን ያህል እንደሆነ ከአሳዳጊ አባቱ ዮሴፍ ሞት ሳያውቅ አይቀርም። (ከዮሐንስ 19:25–27 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ መበለቲቷ ደጅ መጥናት አላስፈለጋትም። ምንም እንኳ በሙሴ ሕግ ላይ አስክሬን የሚነካ ርኩስ ይሆናል ቢባልም “ቀርቦም ቃሬዛውን ነካ።” (ዘኁልቁ 19:11) ኢየሱስ በተአምራዊ ኃይሉ አማካኝነት ሁሉንም የርኩሰት መነሾዎች ማስወገድ ይችላል። “አለውም፦ አንተ ጎበዝ፣ እልሃለው፣ ተነሣ። የሞተውም ቀና ብሎ ተቀመጠ ሊናገርም ጀመረ፣ ለእናቱም ሰጣት።”
ስለ ርኅራኄ የሚገልጽ እንዴት ያለ ስሜት የሚነካ ትምህርት ነው! ክርስቲያኖች በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀኖች’ የሚታዩትን ፍቅር አልባ የሆኑ ቀዝቃዛ ዝንባሌዎች አይኮርጁም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) ከዚህ ይልቅ 1 ጴጥሮስ 3:8 “በመጨረሻም ወንድሞች ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፣ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፣ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ ርኅሩኆችና [“ከአንጀት የምትራሩ” አዓት] ትሑታን ሁኑ” በማለት አጥብቆ ይመክራል። አንድ የምናውቀው ሰው ሲሞት ወይም በጠና ሲታመም የሞተውን ልናስነሳ ወይም የታመመውን ልንፈውስ አንችልም። ይሁን እንጂ አብረናቸው በመሆንና በማልቀስ በቀላሉ ተግባራዊ የሆነ እርዳታና ማጽናኛ ልንሰጣቸው እንችላለን።—ሮሜ 12:15
በተጨማሪም ይህ በኢየሱስ የተፈጸመ አስደናቂ ትንሣኤ “በመቃብር [“በመታሰቢያ መቃብር” አዓት] ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት” ጊዜ እንደሚመጣ ያመለክታል። (ዮሐንስ 5:28, 29) የሚወዱት ሰው በሞት የተለያቸው በመላው ዓለም ያሉ ሰዎች በሞት የተለዩ እናቶች፣ አባቶች፣ ልጆችና ጓደኞች ከመቃብር በሚመለሱበት ጊዜ የኢየሱስን ርኅራኄ በግለሰብ ደረጃ ይቀምሳሉ!
ተአምራቱ የሚያስተላልፉት ትምህርት
የኢየሱስ ተአምራት አስደናቂ ኃይልን ለማሳየት ብቻ የተደረጉ አለመሆናቸው ግልጽ ነው። ‘አምላክን እንዲያከብሩ’ ለታዘዙ ክርስቲያኖች ምሳሌ በመተው አምላክን ክብር አጎናጽፈዋል። (ሮሜ 15:6) መልካም ማድረግን፣ ለጋስነትን፣ ርኅራኄን ማሳየትን አበረታተዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ውስጥ ለሚፈጸሙት አስገራሚ ሥራዎች ሠርቶ ማሳያ ሆነው ያገለግላሉ።
ኢየሱስ ምድር በነበረበት ጊዜ አስገራሚ ሥራዎቹን የፈጸመው በተወሰነ አካባቢ ነው። (ማቴዎስ 15:24) ንጉሥ ሆኖ ክብር ሲቀዳጅ ግዛቱ ምድር ዓቀፍ እስከመሆን ይሰፋል! (መዝሙር 72:8) ኢየሱስ ምድር በነበረበት ጊዜ ተአምራዊ ፈውሱን ተቀብለው ከሞት የተነሱ ሰዎች ከጊዜ በኋላ ሞተዋል። በሰማያዊ ንግሥናው ሥር ኃጢአትና ሞት ጭራሹኑ መጥፋታቸው ለዘላለም ሕይወት መንገድ ይከፍታል። (ሮሜ 6:23፤ ራእይ 21:3, 4) አዎን፣ የኢየሱስ ተአምራት በመምጣት ላይ ያለውን ክብራማ ጊዜ ይጠቁማሉ። የይሖዋ ምሥክሮች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህ ጊዜ በሚፈጸመው እውን ተስፋ ተካፋይ እንዲሆኑ እየረዱ ነው። ያ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ ኢየሱስ ክርስቶስ በፈጸማቸው ተአምራት አማካኝነት በቅርቡ ስለሚመጣው ጊዜ የሚያሳይ እንዴት ያለ አስደናቂ ቅምሻ ነው!
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ለወጠ