ምዕራፍ 22
እውነተኛውን ሃይማኖት ለይቶ ማወቅ
1. በመጀመሪያው መቶ ዘመን እውነተኛውን ሃይማኖት የያዙት እነማን ነበሩ?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እውነተኛውን ሃይማኖት የያዙት እነማን እንደነበሩ ምንም ሊያጠራጥር አይችልም። የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ነበሩ። እነዚህ ሁሉ የአንድ ክርስቲያናዊ ድርጅት አባሎች ነበሩ። ዛሬስ ሁኔታው እንዴት ነው? እውነተኛውን ሃይማኖት የያዙት እንዴት ተለይተው ሊታወቁ ይችላሉ?
2. እውነተኛውን ሃይማኖት የያዙት እንዴት ተለይተው ሊታወቁ ይችላሉ?
2 ኢየሱስ እንዴት ለይተን ልናውቃቸው እንደምንችል ሲያብራራ እንዲህ ብሏል:- “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። . . . መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። . . . ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።” (ማቴዎስ 7:16-20) አምላክን በእውነት የሚያመልኩት ሰዎች እንዴት ያሉ መልካም ፍሬዎች ያፈራሉ ብለህ ትጠብቃለህ? በአሁኑ ጊዜ ንግግራቸውና ድርጊታቸው ምን መሆን ይኖርበታል?
የአምላክን ስም መቀደስ
3, 4. (ሀ) ኢየሱስ ባስተማረው ጸሎት ላይ በመጀመሪያ እንድንጠይቅ የጠቀሰው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ የአምላክን ስም የቀደሰው እንዴት ነው?
3 አምላክን በእውነት የሚያመልኩት ሰዎች ኢየሱስ ለተከታዮቹ ካስተማረው ጸሎት ጋር በሚስማማ መንገድ ይመላለሳሉ። ኢየሱስ በዚያ ላይ የጠቀሰው የመጀመሪያው ነገር “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥ ስምህ ይቀደስ” የሚለው ነው። ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ስምህ ቅዱስ ተደርጎ ይያዝ” ይላል። (ማቴዎስ 6:9፣ የኢየሩሳሌም መጽሐፍ ቅዱስ) የአምላክን ስም መቀደስ ወይም ቅዱስ አድርጎ መያዝ ምን ማለት ነው? ኢየሱስ ይህንን ያደረገው እንዴት ነው?
4 ኢየሱስ ይህንን እንዴት እንዳደረገ “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው” በማለት ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ ገልጿል። (ዮሐንስ 17:6) አዎን፣ ኢየሱስ ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ለሌሎች አስታውቋል። በዚህ ስም ከመጠቀም ወደ ኋላ አላለም። ኢየሱስ የአምላክ ስም በምድር ሁሉ ላይ እንዲከበር የአባቱ ዓላማ መሆኑን ያውቅ ነበር። ስለዚህ ያንን ስም በማስታወቅና በመቀደስ በኩል ምሳሌ ትቶልናል። — ዮሐንስ 12:28፤ ኢሳይያስ 12:4, 5
5. (ሀ) የክርስቲያን ጉባኤ ከአምላክ ስም ጋር የተያያዘው እንዴት ነው? (ለ) ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
5 እውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ የመኖሩ ዓላማ ከአምላክ ስም ጋር የተያያዘ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። ሐዋርያው ጴጥሮስ አምላክ “ለስሙ የሚሆንን ወገን ከአሕዛብ ይወስድ ዘንድ” ትኩረቱን ወደ እነርሱ እንዳደረገ ገልጿል። (ሥራ 15:14) ስለዚህ እውነተኞቹ የአምላክ ሕዝቦች ስሙን ቅዱስ አድርገው መያዝና በምድር ሁሉ ላይ ማስታወቅ ይኖርባቸዋል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “[የይሖዋን (አዓት)] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ስለሚል ለመዳን ይህንን ስም ማወቁ እጅግ አስፈላጊ ነው። — ሮሜ 10:13, 14
6. (ሀ) አብያተ ክርስቲያናት በአጠቃላይ የአምላክን ስም ቅዱስ አድርገው ይይዙታልን? (ለ) ለአምላክ ስም የሚመሰክሩ ሰዎች አሉን?
6 ታዲያ በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ስም ቅዱስ አድርገው የሚይዙትና በመላው ምድር ላይ የሚያስታውቁት እነማን ናቸው? አብያተ ክርስቲያናት በአጠቃላይ ይሖዋ በሚለው ስም ከመጠቀም ይቆጠባሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው ውስጥ አውጥተውታል። ይሁን እንጂ ከጎረቤቶችህ ጋር ስትነጋገር ብዙውን ጊዜ በስሙ ብትጠቀም ይኸውም ይሖዋ እያልክ ብትጠራ ከየትኛው ድርጅት ጋር የሚመድቡህ ይመስልሃል? በዚህ ረገድ የኢየሱስን አርዓያ በትክክል የሚከተል አንድ ሕዝብ ብቻ አለ። የሕይወታቸው ዋና ዓላማ ልክ እንደ ኢየሱስ አምላክን ማገልገልና ለስሙ ምስክርነት መስጠት ነው። በዚህም ምክንያት “የይሖዋ ምስክሮች” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ስም ይዘዋል። — ኢሳይያስ 43:10-12
የአምላክን መንግሥት ማወጅ
7. ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት አስፈላጊነት ያሳየው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ ባስተማረው ጸሎት ላይ የአምላክን መንግሥት አስፈላጊነትም ጭምር አሳይቷል። ሰዎች “መንግሥትህ ትምጣ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:10) ኢየሱስ መንግሥቱ ለሰው ዘር ችግሮች ብቸኛ መፍትሔ እንደሆነች ደግሞ ደጋግሞ ገልጿል። እርሱና ሐዋርያቱ ስለዚች መንግሥት “ከመንደር ወደ መንደር” እና “ከቤት ወደ ቤት” እየሄዱ ለሰዎች በመስበክ ይህንን ቁም ነገር አጥብቀው ገልጸዋል። (ሉቃስ 8:1፤ ሥራ 5:42፤ 20:20) የስብከታቸውና የትምህርታቸው ዋና መልእክት የአምላክ መንግሥት ነበረች።
8. ኢየሱስ በእነዚህ “የመጨረሻ ቀኖች” የእውነተኛ ተከታዮቹ ዋና መልእክት ምን እንደሚሆን ያሳየው እንዴት ነው?
8 ዛሬስ እንዴት ነው? እውነተኛው የአምላክ ክርስቲያናዊ ድርጅት ዋና ትምህርቱ ምንድን ነው? ስለ እነዚህ “የመጨረሻ ቀኖች” ትንቢት ሲናገር ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:14) ስለዚህ ዛሬም የአምላክ ሕዝቦች ዋና መልእክት መንግሥቲቱ መሆን አለባት።
9. በዛሬው ጊዜ የመንግሥቱን መልእክት የሚሰብኩት የትኞቹ ሰዎች ናቸው?
9 እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው:- አንድ ሰው በርህን አንኳኩቶ ለሰው ዘር እውነተኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት ስለመሆኗ ቢናገር ይህንን ሰው ከየትኛው ድርጅት ጋር ትመድበዋለህ? ከይሖዋ ምስክሮች ሌላ ስለ አምላክ መንግሥት ያነጋገሩህ ሰዎች አሉን? እንዲያውም ስለ እርስዋ ምንነት የሚያውቁት በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው! ስለ አምላክ መንግሥትም ምንም አይናገሩም። ሆኖም ያች መንግሥት ዓለምን የሚያናውጥ ዜና ናት። ነቢዩ ዳንኤል ይህች መንግሥት ‘ሌሎቹን መንግሥታት በሙሉ እንደምትፈጭና ብቻዋን ምድርን እንደምትገዛ’ አስቀድሞ ተናግሯል። — ዳንኤል 2:44
ለአምላክ ቃል አክብሮት ማሳየት
10. ኢየሱስ ለአምላክ ቃል አክብሮት ያሳየው እንዴት ነው?
10 እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉት ሰዎች ተለይተው የሚታወቁበት ሌላው መንገድ ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው ዝንባሌ ነው። ኢየሱስ ምን ጊዜም ለአምላክ ቃል አክብሮት አሳይቷል። በአንዳንድ ነገሮች ላይ የመጨረሻው ባለሥልጣን በማድረግ ብዙ ጊዜ ጠቅሶታል። (ማቴዎስ 4:4, 7, 10፤ 19:4-6) በተጨማሪም ኢየሱስ ከትምህርቶቹ ጋር ተስማምቶ በመኖር ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለውን አክብሮት አሳይቷል። መጽሐፍ ቅዱስን በፍጹም አቃልሎ አያውቅም። ከዚህ ይልቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማ ትምህርት ያላስተማሩትንና የራሳቸውን የግል አሳብ በማስቀደም የትምህርቶቹን ኃይል ለማዳከም የሞከሩትን አውግዟቸዋል። — ማርቆስ 7:9-13
11. አብያተ ክርስቲያናት ብዙውን ጊዜ ለአምላክ ቃል እንዴት ያለ ዝንባሌ ያሳያሉ?
11 የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በዚህ ረገድ ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ አንጻር ሲታዩ ሁኔታቸው እንዴት ነው? ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ አክብሮት አላቸውን? በአሁኑ ጊዜ ብዙ ቄሶች አዳም ወደ ኃጢአት ስለመውደቁ፣ በኖኅ ዘመን ስለደረሰው የጥፋት ውኃ፣ ስለ ዮናስና እርሱን ስለዋጠው ዓሣ እንዲሁም ስለሌሎቹ የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች አያምኑባቸውም። በተጨማሪም ሰው በአምላክ በቀጥታ ተፈጥሮ ሳይሆን በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው ብለው ይናገራሉ። ታዲያ እንደዚህ ሲያደርጉ ሰዎች ለአምላክ ቃል አክብሮት እንዲያድርባቸው ማበረታታቸው ነውን? እንዲሁም አንዳንድ የቤተክርስቲያን መሪዎች ከጋብቻ ውጭ የሚደረጉ የጾታ ግንኙነቶች ስሕተት አይደሉም ወይም ግብረሶዶም ወይም ከአንድ በላይ ማግባት ትክክል ሊሆን ይችላል ብለው ይከራከራሉ። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መመሪያቸው አድርገው እንዲጠቀሙበት ሰዎችን እያበረታቱ ነው ትላለህን? በእርግጥ የአምላክን ልጅና የሐዋርያቱን ምሳሌ መከተላቸው እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። — ማቴዎስ 15:18, 19፤ ሮሜ 1:24-27
12. (ሀ) ብዙ ሰዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስን የሚይዙ ሰዎች ጭምር፣ አምልኮታቸው ለምን አምላክን አያስደስትም? (ለ) ሆነ ብለው ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጥሩ አቋም ይዘው ከቀጠሉ ምን ብለን መደምደም ይገባናል?
12 መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው እንዲያውም የሚያጠኑት አንዳንድ የቤተክርስቲያን አባሎች አሉ። ሆኖም አኗኗራቸው እርሱን እንደማይከተሉት ያሳያል። እንደነዚህ ስላሉት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፥ ዳሩ ግን . . . በሥራቸው ይክዱታል።” (ቲቶ 1:16፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:5) ቁማር የሚጫወቱ፥ የሚሰክሩ ወይም ሌሎች ኃጢአቶችን የሚፈጽሙ የቤተክርስቲያን አባሎች በቤተክርስቲያናቸው ውስጥ ጥሩ አቋም እንዳላቸው ተደርገው እንዲቀጥሉ ከተፈቀደላቸው ይህ ምን ያሳያል? ሃይማኖታዊ ድርጅታቸው በአምላክ ተቀባይነት እንደሌለው የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው። — 1 ቆሮንቶስ 5:11-13
13. አንድ ሰው ቤተክርስቲያኑ የሚያስተምራቸው ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይስማሙ ሆነው ካገኛቸው ምን ከባድ ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል?
13 በውስጣቸው የሚገኙትን ጥቅሶች እየተመለከትክ ከዚህ በፊት ያሉትን የዚህ መጽሐፍ ምዕራፎች በደንብ አስበህባቸው ከሆነ የአምላክን ቃል መሠረታዊ ትምህርቶች አውቀሃል። ሆኖም አንተ የምትሰበሰብበት ሃይማኖታዊ ድርጅት የሚያስተምራቸው ትምህርቶች ከአምላክ ቃል ትምህርቶች ጋር የማይስማሙ ቢሆኑስ? እንደዚያ ከሆነ ከባድ ችግር አለብህ ማለት ነው። ችግሩም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኝነት መቀበል አለዚያም እርሱን አልቀበልም ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ የማይደግፋቸውን ትምህርቶች ለመከተል ውሳኔ ማድረጉ ነው። እርግጥ ነው የምታደርገው ነገር ሁሉ የራስህ ውሳኔ መሆን ይኖርበታል። ሆኖም ነገሮችን በጥንቃቄ ማመዛዘን ይኖርብሃል። ይህ የሆነበት ምክንያት የምታደርገው ውሳኔ ከአምላክ ጋር ያለህን አቋምና በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር ተስፋህን ስለሚነካብህ ነው።
ከዓለም ተለይቶ መኖር
14. (ሀ) የእውነተኛ ሃይማኖት ሌላው መለያ ምልክት ምንድን ነው? (ለ) እውነተኛ አምላኪዎች ይህንን ብቃት ማሟላታቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
14 ሆኖም የእውነተኛው ሃይማኖት ተከታዮች ተለይተው የሚታወቁበት ሌላው ምልክት ኢየሱስ እንደተናገረው ‘የዓለም ክፍል አለመሆናቸው ነው።’ (ዮሐንስ 17:14) ይህም ሲባል እውነተኛ አምላኪዎች ምግባረ ብልሹ ከሆነው ዓለምና ከጉዳዮቹ ገለል ይላሉ ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የፖለቲካ ገዥ ለመሆን እምቢ ብሏል። (ዮሐንስ 6:15) መጽሐፍ ቅዱስ የዓለም ገዥ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው ብሎ መናገሩን ካስታወስክ ከዓለም ገለል ማለቱ ለምን ያን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ልትገነዘብ ትችላለህ። (ዮሐንስ 12:31፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4) መጽሐፍ ቅዱስ “እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኗል” ሲል የተናገረው ቃል ጉዳዩ ከበድ ተደርጎ መታየት እንዳለበት ተጨማሪ ማስረጃ ይሆናል። — ያዕቆብ 4:4
15. (ሀ) አንተ የምታውቃቸው አብያተ ክርስቲያናት በእርግጥ ‘ከዚህ ዓለም የተለዩ’ ናቸውን? (ለ) ይህንን ብቃት የሚያሟላ ሃይማኖት ታውቃለህን?
15 በአካባቢህ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ይህንን ጉዳይ ከልብ እንደሚቀበሉት ማስረጃዎቹ ያሳያሉን? ቄሶቹና የጉባኤዎቹ አባላት በእርግጥ ‘ከዓለም የተለዩ’ ናቸውን? ወይስ በዓለም ብሔራዊ ስሜት፥ በፖለቲካና በመደብ ትግሎች በጥልቅ ተጠላልፈዋል? አብያተ ክርስቲያናት የሚያደርጓቸው ነገሮች በሰፊው የታወቁ ስለሆኑ እነዚህ ጥያቄዎች ለመመለስ ከባድ አይደሉም። በሌላም በኩል የይሖዋ ምስክሮች የሚያደርጓቸውን ነገሮች መመርመሩ ቀላል ነው። ይህንን በማድረግህም እነርሱ በእርግጥም ከዓለም፣ ከፖለቲካዊ ጉዳዮቹና ከስስት፣ ከብልግና፣ ከአመፀኝነት መንገዶቹ በመለየት በኩል የክርስቶስንና የመጀመሪያ ተከታዮቹን ምሳሌ እንደሚከተሉ ለማወቅ ትችላለህ። — 1 ዮሐንስ 2:15-17
በመካከላቸው የሚኖር ፍቅር
16. እውነተኞቹ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ተለይተው ሊታወቁ የሚችሉበት አንዱ ትልቅ መንገድ ምንድን ነው?
16 የክርስቶስ እውነተኛ ደቀመዛሙርት ተለይተው የሚታወቁበት ከሁሉ የበለጠው መንገድ በመካከላቸው ያለው ፍቅር ነው። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀመዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35) አንተ የምታውቃቸው ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የዚህ ዓይነት ፍቅር አላቸውን? ለምሳሌ የሚኖሩበት አገር ከሌላ አገር ጋር በሚዋጋበት ጊዜ ምን ያደርጋሉ?
17. እርስ በርስ ስለመዋደድ የተሰጠውን ትእዛዝ በመፈጸም ረገድ ሃይማኖታዊ ድርጅቶችና አባሎቻቸው ያላቸው ሁኔታ እንዴት ነው?
17 ብዙውን ጊዜ ምን እንደሚደረግ ታውቃለህ። የዓለማዊ ሰዎችን ትእዛዝ በመከተል የልዩ ልዩ ሃይማኖቶች አባል የሆኑ ሰዎች ወደ ጦር ሜዳ ሄደው በሌላ አገር ያሉትን የእምነት መሰሎቻቸውን ገድለዋል። በዚህም መንገድ ካቶሊኮች ካቶሊኮችን፣ ፕሮቴስታንቶች ፕሮቴስታንቶችን፣ እስላሞች እስላሞችን ገድለዋል። እንደዚህ ያለው መንገድ ከአምላክ ቃል ጋር የሚስማማና በእርግጥም የአምላክን መንፈስ የሚያሳይ ይመስልሃልን? — 1 ዮሐንስ 3:10-12
18. የይሖዋ ምስክሮች እርስ በርስ ፍቅር በማሳየት በኩል ያላቸው ሁኔታ እንዴት ነው?
18 የይሖዋ ምስክሮች በዚህ መለኪያ ማለትም እርስ በርስ ፍቅር በማሳየት በኩል ሲለኩ ሁኔታቸው እንዴት ሆኖ ይገኛል? የዓለማዊ ሃይማኖቶችን መንገድ አይከተሉም። በጦር ሜዳ ላይ የእምነት ወንድሞቻቸውን አይገድሉም። ከሌላ ብሔር፣ ጎሣ ወይም ዘር የሆነውን ወንድማቸውን እየጠሉ “አምላክን እወዳለሁ” በማለት ውሸተኞች ሆነው አልተገኙም። (1 ዮሐንስ 4:20, 21) ነገር ግን በሌሎች መንገዶችም ጭምር ፍቅር ያሳያሉ። እንዴት? ከጎረቤቶቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነትና ሌሎች ስለ አምላክ እንዲማሩ ለመርዳት በሚያደርጓቸው ፍቅራዊ ጥረቶች ነው። — ገላትያ 6:10
አንድ እውነተኛ ሃይማኖት
19. አንድ እውነተኛ ሃይማኖት ብቻ አለ ብሎ መናገሩ ምክንያታዊና ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆነው ለምንድን ነው?
19 አንድ እውነተኛ ሃይማኖት ብቻ መኖር አለበት ቢባል ነገሩ ምክንያታዊ ነው። ይህም እውነተኛው አምላክ “የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም” ከሚለው ሐቅ ጋር የሚስማማ ነው። (1 ቆሮንቶስ 14:33) መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ እምነት” ብቻ እንዳለ ይገልጻል። (ኤፌሶን 4:5) ታዲያ በዛሬው ጊዜ የእውነተኛ አምላኪዎች ድርጅት የሆኑት እነማን ናቸው?
20. (ሀ) በማስረጃዎቹ መሠረት ይህ መጽሐፍ በዛሬው ጊዜ እውነተኛ አምላኪዎች እነማን መሆናቸውን ያመለክታል? (ለ) አንተስ ይህንን ታምንበታለህን? (ሐ) ከይሖዋ ምስክሮች ጋር በደንብ ለመተዋወቅ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው?
20 የይሖዋ ምስክሮች ናቸው ብለን ለመናገር ምንም አናመነታም። አንተም ይህ ነገር እውነት መሆኑን እንድታረጋግጥ ከእነርሱ ጋር በበለጠ እድትተዋወቅ እንጋብዝሃለን። ይህንን ለማድረግ የሚያስችለው ከሁሉ የተሻለው መንገድ የይሖዋ ምስክሮች በመንግሥት አዳራሽ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ነው። እውነተኛውን ሃይማኖት መከተሉ በአሁኑ ጊዜ ታላቅ ደስታ እንደሚያመጣ ወደፊት ደግሞ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት መንገድ እንደሚከፍት መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያሳይ በእርግጥም እንደዚህ ያለውን ምርምር ማድረግህ ተገቢ ነው። (ዘዳግም 30:19, 20) ይህንን እንድታደርግ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልሃለን። ለምን አሁንኑ ሁኔታውን አትመረምረውም?
[በገጽ 185 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለአንድ ሰው ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ ብትነግረው የየትኛው ሃይማኖት አባል እንደሆንህ አድርጎ ያስባል?
[በገጽ 186 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አንድ ሰው የአምላክን ቃል በሕይወቱ የማይሠራበት ከሆነ ለቃሉ አክብሮት አለው ሊባል ይቻላልን?
[በገጽ 188, 189 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ፖለቲካዊ መሪ ለመሆን እምቢ ብሏል
[በገጽ 190 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በይሖዋ ምስክሮች ስብሰባዎች ላይ እንድትገኝ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልሃለን