ምዕራፍ 17
ኢየሱስ ምን ባሕርያት አሉት?
ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ የተናገራቸውንም ሆነ ያደረጋቸውን ነገሮች ስንመረምር ወደ እሱም ሆነ ወደ አባቱ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚያደርጉ ባሕርያት እንዳሉት እንገነዘባለን። ኢየሱስን እንድንወደው ከሚያደርጉን ባሕርያቱ መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? እኛስ የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
1. ኢየሱስ አባቱን የሚመስለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
ኢየሱስ በቢሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዓመታት በሰማይ ሲኖር አፍቃሪ የሆነውን አባቱን የማየትና ከእሱ የመማር አጋጣሚ አግኝቷል። በዚህም ምክንያት አስተሳሰቡ፣ ስሜቱና ድርጊቱ ልክ እንደ አባቱ ነው። (ዮሐንስ 5:19ን አንብብ።) እንዲያውም ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያት በሚገባ ከማንጸባረቁ የተነሳ “እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል” ብሎ ሊናገር ችሏል። (ዮሐንስ 14:9) ስለ ኢየሱስ ባሕርያት እየተማርክ በሄድክ መጠን ይሖዋን የበለጠ እያወቅከው ትሄዳለህ። ለምሳሌ ኢየሱስ ለሰዎች ያሳየው ርኅራኄ ይሖዋ ለአንተ ምን ያህል እንደሚያስብልህ ያሳያል።
2. ኢየሱስ ይሖዋን እንደሚወደው ያሳየው እንዴት ነው?
ኢየሱስ “እኔ አብን እንደምወድ ዓለም እንዲያውቅ አብ ባዘዘኝ መሠረት እየሠራሁ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 14:31) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት በአስቸጋሪ ጊዜም ጭምር አባቱን በመታዘዝ ለእሱ ያለውን ጥልቅ ፍቅር አሳይቷል። በተጨማሪም ኢየሱስ ስለ አባቱ ማውራትና ሌሎች ከአባቱ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ መርዳት ያስደስተው ነበር።—ዮሐንስ 14:23
3. ኢየሱስ ሰዎችን እንደሚወድ ያሳየው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ‘በተለይ በሰው ልጆች እጅግ እንደሚደሰት’ ይናገራል። (ምሳሌ 8:31) ሰዎችን በማበረታታትና ራሱን ሳይቆጥብ በመርዳት ፍቅሩን አሳይቷል። የፈጸማቸው ተአምራት ኃይሉን ብቻ ሳይሆን ርኅራኄውንም ያሳያሉ። (ማርቆስ 1:40-42) ለሰዎች ደግነት አሳይቷል፤ እንዲሁም ያለምንም አድልዎ ሁሉንም በእኩል ዓይን ያይ ነበር። የሚናገረው ነገር እሱን ለሚሰሙ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ሁሉ መጽናኛና ተስፋ የሚሰጥ ነበር። ኢየሱስ ለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅር ስላለው ለእነሱ ሲል ለመሠቃየትና ለመሞት ፈቃደኛ ሆኗል። የእሱን ትምህርቶች ለሚከተሉ ሰዎች ደግሞ የተለየ ፍቅር አለው።—ዮሐንስ 15:13, 14ን አንብብ።
ጠለቅ ያለ ጥናት
ስለ ኢየሱስ ባሕርያት በስፋት እንመለከታለን። በተጨማሪም ልክ እንደ እሱ ፍቅርና ልግስና ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንወያያለን።
4. ኢየሱስ አባቱን ይወዳል
ኢየሱስ የተወው ምሳሌ አምላክን እንደምንወደው ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይጠቁመናል። ሉቃስ 6:12ን እንዲሁም ዮሐንስ 15:10ን እና 17:26ን አንብቡ። እያንዳንዱን ጥቅስ አንብባችሁ በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ይሖዋን እንደምንወደው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
5. ኢየሱስ ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች ያዝናል
ኢየሱስ ከራሱ ፍላጎት ይልቅ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ቅድሚያ ይሰጥ ነበር። ደክሞት እያለም እንኳ ጊዜውንና ጉልበቱን ሳይቆጥብ ሰዎችን ረድቷል። ማርቆስ 6:30-44ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
6. ኢየሱስ ለጋስ ነው
ኢየሱስ ብዙ ገንዘብ ባይኖረውም ለሌሎች በልግስና ይሰጥ ነበር፤ እኛንም ለጋስ እንድንሆን አበረታቶናል። የሐዋርያት ሥራ 20:35ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ኢየሱስ በተናገረው መሠረት ደስተኛ ለመሆን ምን ማድረግ አለብን?
ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ብዙ ገንዘብ ባይኖረንም እንኳ ለሌሎች መስጠት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
ይህን ታውቅ ነበር?
መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ ስም ወደ ይሖዋ እንድንጸልይ ያስተምረናል። (ዮሐንስ 16:23, 24ን አንብብ።) በዚህ መንገድ ስንጸልይ ኢየሱስ የይሖዋ ወዳጆች እንድንሆን ለተጫወተው ሚና አድናቆት እንዳለን እናሳያለን።
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “አምላክ በእኛ ላይ የሚደርሰው መከራ አያሳስበውም።”
ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያት ያንጸባርቃል፤ ከዚህ አንጻር እሱ ያደረገው ነገር ይሖዋ የእኛ ሁኔታ እንደሚያሳስበው የሚያሳየው እንዴት ነው?
ማጠቃለያ
ኢየሱስ ይሖዋንና ሰዎችን ይወዳል። ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ ስለሚያንጸባርቅ ስለ እሱ እያወቅክ በሄድክ መጠን ይሖዋን ይበልጥ እያወቅከው ትሄዳለህ።
ክለሳ
የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ይሖዋን እንደምንወደው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ሰዎችን እንደምንወድ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
ከኢየሱስ ባሕርያት መካከል አንተን ይበልጥ የሚማርክህ የትኛው ነው?
ምርምር አድርግ
ኢየሱስን ለመምሰል የሚያስችሉንን አንዳንድ ባሕርያት ተመልከት።
በኢየሱስ ስም መጸለይ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ምን ይመስል እንደነበር የሚጠቁም ፍንጭ ይሰጣል?
ኢየሱስ ለሴቶች ካሳየው ደግነት ምን ትምህርት እናገኛለን?