የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ አባላት ምሥራቹን ሰሙ
ጊዜው 59 ዓ.ም. ነው። በርካታ እስረኞች በጉዞ በዛሉ ወታደሮች ታጅበው ፖርታ ካፔና በሚባለው በር በኩል ወደ ሮም ገቡ። በፓላታይን ኮረብታ ላይ የሚገኘው የንጉሠ ነገሥት ኔሮ ቤተ መንግሥት በንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ ይጠበቃል፤ የዚህ ክብር ዘብ አባላት የሆኑት ወታደሮች ሰይፍ የሚታጠቁ ሲሆን በሥራ ላይ በሚሆኑበት ጊዜ የሚለብሱት ልብስ ሰይፉን ይሸፍነዋል።a መቶ አለቃ ዩልዮስ እስረኞቹን አሰልፎ የሮምን አደባባይ በማቋረጥ ወደ ቪሚናል ኮረብታ አቀና። በጉዟቸው ወቅት፣ ለሮማውያን አማልክት የተሠሩ ብዙ መሠዊያዎች በቆሙበት መናፈሻ እንዲሁም ወታደራዊ ትርዒቶች በሚካሄዱበትና ወታደራዊ ሥልጠና በሚሰጥበት ቦታ ያልፋሉ።
ከእነዚህ እስረኞች አንዱ ሐዋርያው ጳውሎስ ነበር። እዚህ ከመድረሳቸው ከጥቂት ወራት በፊት ጳውሎስ የተሳፈረበት መርከብ ኃይለኛ ማዕበል በገጠመው ወቅት አንድ የአምላክ መልአክ ተገልጦለት “ቄሳር ፊት መቅረብ ይገባሃል” ብሎት ነበር። (ሥራ 27:24) ታዲያ ጳውሎስ በቄሣር ፊት ይቀርብ ይሆን? ጳውሎስ የሮምን ግዛት ዋና ከተማ ሲመለከት ጌታ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም በአንቶኒያ ግንብ ውስጥ ሳለ የነገረው ነገር በአእምሮው ሳያቃጭል አልቀረም፤ ኢየሱስ “አይዞህ፣ አትፍራ! ምክንያቱም በኢየሩሳሌም ስለ እኔ የተሟላ ምሥክርነት እንደሰጠህ ሁሉ በሮምም ልትመሠክርልኝ ይገባል” ብሎት ነበር።—ሥራ 23:10, 11
ጳውሎስ ካስትራ ፕሪቶሪያ የሚባለው ትልቅ ምሽግ ጋ ሲደርስ ቆም ብሎ ቦታውን ሳይቃኝ አልቀረም፤ ይህ ምሽግ በቀይ ጡቦች የተሠሩ ረጃጅም ግድግዳዎችና ማማዎች እንዲሁም በግድግዳዎቹ ዙሪያ ሰገነቶች አሉት። በዚህ ምሽግ ውስጥ የንጉሠ ነገሥቱ ጠባቂ የሆኑት የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ አባላት እንዲሁም የከተማዋ ፖሊሶች ይኖራሉ። የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ 12 ብርጌዶችb እንዲሁም በርካታ የከተማዋ ፖሊሶችና ፈረሰኞችም የሚኖሩት በካስትራ ፕሪቶሪያ ውስጥ በመሆኑ በዚህ ምሽግ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ነበሩ። ካስትራ ፕሪቶሪያ ንጉሠ ነገሥቱ ምን ያህል ከፍተኛ ኃይል እንዳለው የሚጠቁም ነበር። ከተለያዩ ግዛቶች የሚመጡ እስረኞችን ጉዳይ የሚመለከተው የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ በመሆኑ እስረኞቹን እየመራ ወደ ሮም ያመጣቸው የዚህ ዘብ አባል የሆነው ዩልዮስ ነው። ዩልዮስ ወራት ከፈጀ አደገኛ ጉዞ በኋላ፣ ወደ ሮም ከሚያስገቡት አራት ዋና ዋና በሮች በአንዱ በኩል እስረኞቹን ይዞ ወደ ከተማዋ ዘለቀ።—ሥራ 27:1-3, 43, 44
ሐዋርያው “ያለምንም እንቅፋት” ሰበከ
ጳውሎስ በጉዞ ላይ እያለ፣ የተሳፈሩበት መርከብ ቢሰበርም ሁሉም በሕይወት እንደሚተርፉ በራእይ ተመልክቶ ነበር። ከዚህም ሌላ ጳውሎስ አንድ መርዘኛ እባብ ቢነድፈውም ምንም ጉዳት አልደረሰበትም። በሚሊጢን ደሴት ላይ ደግሞ የታመሙ ሰዎችን በመፈወሱ የአካባቢው ሕዝብ አምላክ እንደሆነ መናገር ጀምረው ነበር። ስለ እነዚህ ነገሮች የሚገልጸው ወሬ በአጉል እምነት በተተበተቡት የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ አባላት ዘንድ ተናፍሶ መሆን አለበት።
የሮም ወንድሞች ጳውሎስን ለማግኘት “እስከ አፍዩስ የገበያ ስፍራና ሦስት ማደሪያ እስከሚባለው ቦታ ድረስ” መጥተው ነበር። (ሥራ 28:15) ታዲያ ጳውሎስ እስረኛ እንደመሆኑ መጠን ሮም ከደረሰ በኋላ ምሥራቹን መስበክ የሚችለው እንዴት ነው? (ሮም 1:14, 15) እስረኞች የሚቀርቡት የክብር ዘቡ ኃላፊ ጋ እንደሆነ አንዳንዶች ይገምታሉ። ይህ ከሆነ ጳውሎስ የቀረበው የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ ኃላፊ የሆነው አፍራኒዩስ ቡሮስ ዘንድ መሆን አለበት፤ ይህ ሰው ከንጉሠ ነገሥቱ ቀጥሎ ከፍተኛ ሥልጣን ሳይኖረው አይቀርም።c ያም ሆነ ይህ፣ ጳውሎስ እንዲጠበቅ የተደረገው በአንድ የመቶ አለቃ ሳይሆን የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ አባል በሆነ ተራ ወታደር ነበር። ከዚህም ሌላ የራሱን ቤት እንዲከራይ የተፈቀደለት ሲሆን ሊጠይቁት የሚመጡትን እየተቀበለ “ያለምንም እንቅፋት” መስበክ ይችል ነበር።—ሥራ 28:16, 30, 31
ጳውሎስ ለትንሹም ሆነ ለትልቁ ይሰብክ ነበር
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኔሮ ፊት ከመቅረቡ በፊት ቡሮስ ሳያነጋግረው አልቀረም፤ ቡሮስ ይህን ያደረገው በቤተ መንግሥት አሊያም ካስትራ ፕሪቶሪያ በተባለው ምሽግ ውስጥ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ “ለትንሹም ሆነ ለትልቁ [ለመመሥከር]” ያገኘው ይህ ልዩ አጋጣሚ እንዲያመልጠው አልፈቀደም። (ሥራ 26:19-23) ቡሮስ ጳውሎስን አስመልክቶ የደረሰበት መደምደሚያ ምንም ይሁን ምን፣ ሐዋርያው በክብር ዘቡ ምሽግ ውስጥ እንዲታሰር አላደረገም።d
ጳውሎስ የተከራየው ቤት “የአይሁዳውያንን ታላላቅ ሰዎች” እና “ወደ መኖሪያ ስፍራው [የሚመጡ]” ሌሎች ብዙ ሰዎችን ለመቀበልና ለእነዚህ ሰዎች ለመመሥከር የሚበቃ ነበር። በተጨማሪም ጳውሎስን የሚጠብቁት የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ አባል የሆኑ ወታደሮች ትተውት መሄድ ስለማይችሉ ሐዋርያው “ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ” ስለ አምላክ መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ለአይሁዳውያን “የተሟላ ምሥክርነት [ሲሰጥ]” ይሰሙ ነበር።—ሥራ 28:17, 23
በቤተ መንግሥቱ ውስጥ የሚመደቡት የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ አባላት በየቀኑ በስምንተኛው ሰዓት ላይ ይቀያየሩ ነበር። ጳውሎስን የሚጠብቁት ዘቦችም ፈረቃቸውን ጠብቀው ይቀያየራሉ። ሐዋርያው በእስር በቆየባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ ይጠብቁት የነበሩት ወታደሮች ወደ ኤፌሶን፣ ፊልጵስዩስ፣ ቆላስይስ እና ዕብራውያን ክርስቲያኖች የሚላክ ደብዳቤ በቃሉ እየተናገረ ሲያስጽፍ ሰምተውታል፤ እንዲሁም ፊልሞን ለሚባል አንድ ክርስቲያን ራሱ ደብዳቤ ሲጽፍ ተመልክተዋል። ጳውሎስ በእስር ላይ እያለ ያገኘውን አናሲሞስ የተባለ ከጌታው የኮበለለ ባሪያ ረድቶት ነበር፤ ስለዚህ ባሪያ ሲናገር “በእስር ላይ እያለሁ እንደ አባት የሆንኩለት” ያለ ሲሆን አናሲሞስን ወደ ጌታው መልሶ ልኮታል። (ፊል. 10) ጳውሎስ የሚጠብቁትን ወታደሮችም አነጋግሯቸው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። (1 ቆሮ. 9:22) ሐዋርያው እያንዳንዱ የጦር ትጥቅ ምን ጥቅም እንዳለው ወታደሮቹን ጠይቋቸው እንደሚሆን ማሰብ እንችላለን፤ ጳውሎስ መንፈሳዊውን የጦር ትጥቅ አስመልክቶ የሰጠውን ምሳሌ የጻፈው በዚህ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ሊሆን ይችላል።—ኤፌ. 6:13-17
‘የአምላክን ቃል ያለ ፍርሃት መናገር’
የጳውሎስ መታሰር በንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ ሁሉና በሌሎች ዘንድ ምሥራቹ “ይበልጥ እንዲስፋፋ” ምክንያት ሆኗል። (ፊልጵ. 1:12, 13) በካስትራ ፕሪቶሪያ ውስጥ የሚኖሩት ወታደሮች በመላው የሮም ግዛት ካሉ ሰዎች እንዲሁም ከንጉሠ ነገሥቱና ሰፊ ከሆነው ንጉሣዊ ቤተሰብ ጋር መገናኘት ይችሉ ነበር። ንጉሣዊው ቤተሰብ፣ የንጉሡን ቤተሰብ አባላት እንዲሁም አገልጋዮችንና ባሮችን ያቀፈ ሲሆን ከእነሱም መካከል አንዳንዶቹ ክርስቲያኖች ሆነዋል። (ፊልጵ. 4:22) ጳውሎስ በድፍረት ምሥክርነት በመስጠቱ በሮም የነበሩት ወንድሞች “የአምላክን ቃል ያለ ፍርሃት ለመናገር” ድፍረት አግኝተዋል።—ፊልጵ. 1:14
እኛም ቃሉን “አመቺ በሆነ ወቅትም ሆነ በአስቸጋሪ ወቅት” ስንሰብክ ጳውሎስ በሮም ከሰጠው ምሥክርነት ብርታት ማግኘት እንችላለን። (2 ጢሞ. 4:2) አንዳንዶቻችን እንክብካቤ በሚሰጥባቸው ተቋማት ወይም ሆስፒታል ውስጥ በመሆናችን ከቤት መውጣት በማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ልንሆን እንችላለን፤ አሊያም ደግሞ በእምነታችን ምክንያት ታስረን ይሆናል። ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ በተለያየ ምክንያት እኛ ጋ ለሚመጡ ሰዎች ለምሳሌ ቤታችን መጥተው እንክብካቤ ለሚያደርጉልን ወይም የተለያዩ አገልግሎቶች ለሚሰጡን ሰዎች መስበክ እንችል ይሆናል። በእያንዳንዱ አጋጣሚ በድፍረት የምንመሰክር ከሆነ ‘የአምላክ ቃል ሊታሰር እንደማይችል’ በራሳችን ሕይወት ማየት እንችላለን።—2 ጢሞ. 2:8, 9
a “የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ በኔሮ ዘመን” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
b አንድ የሮማውያን ብርጌድ እስከ 1,000 የሚደርሱ ወታደሮችን የያዘ ነበር።
c “ሴክስተስ አፍራኒዩስ ቡሮስ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።