የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ይቅር ማለትና መርሳት የሚቻለው እንዴት ነው?
“በደላቸውን ይቅር እልላቸዋለሁ፤ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስባቸውም።”— ኤርምያስ 31:34 የ1980 ትርጉም
እነዚህ በነቢዩ ኤርምያስ የተመዘገቡ ቃላት የይሖዋ ምህረት ስላለው አስደናቂ ገጽታ ይገልጻሉ። ይሖዋ አንድን በደል ይቅር ካለ ይረሳዋል። (ኢሳይያስ 43:25) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ በነጻ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም እንዲሁ አድርጉ” ይላል። (ቆላስይስ 3:13 አዓት ) ስለዚህ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የይሖዋን ይቅር ባይነት መኮረጅ ይኖርብናል።
ይሁን እንጂ አንዳንድ አስፈላጊ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ካለ ጨርሶ አያስታውሰውም ማለት ነውን? እኛስ ይቅር ስንል ፈጽሞ ማስታወስ በማንችልበት ሁኔታ መሆን አለበት ማለት ነውን? ፈጽሞ ለማስታወስ እስከማንችልበት ደረጃ ካልደረስን ይቅርታ አላደረግንም ማለት ነውን?
ይሖዋ ይቅር የሚለው እንዴት ነው?
ይቅርታ ማድረግ ማለት ቂም አለመያዝ ማለት ነው። ይሖዋ ይቅር ሲል ሙሉ በሙሉ ይምራል።a መዝሙራዊው ዳዊት እንደሚከተለው ብሏል:- “[ይሖዋ] ሁልጊዜም አይቀስፍም፣ ለዘ ላለምም አይቆጣም። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል።”— መዝሙር 103:9, 12, 13
በተጨማሪም የአምላክ ይቅርታ ፍጹም መሆኑ በሥራ 3:19 ላይ ተገልጿል:- “ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም” ይላል። “ይደመሰስ ዘንድ” የሚለው ሐረግ “መጥረግ፣ ማጥፋት” የሚል ትርጉም ካለው (ኤክሳሌይፎ) ከሚለው ከአንድ ግሪክኛ ግሥ የተገኘ ነው። (ራእይ 7:17፤ 21:4 ተመልከት።) ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ቲዎሎጂ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “ይህ ግሥ እዚህ ላይና ምናልባትም በሌሎች ቦታዎች ላይ የሚያስተላልፈው ሐሳብ በአንድ ከሰም በተሠራ ጽላት ላይ ለመፃፍ ቀደም ሲል በጽላቱ ላይ ተጽፎ የነበረውን ጽሑፍ መደምሰስንና መጥረግን የሚያመለክት ነው።” ከኃጢአታችን ንስሐ ስንገባ ይሖዋ ቀድሞ የነበረንን መዝገብ አጽድቶ ንጹሕ ያደርገዋል። ታዲያ ይህ ማለት ኃጢአታችንን ፈጽሞ አያስታውስም ማለት ነውን? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ አንድ ምሳሌ እንመልከት።
ንጉሥ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ከፈጸመ በኋላ ኃጢአቱን ሰውሮ ለማስቀረት ሲል ባልዋን ባስገደለ ጊዜ ይሖዋ ዳዊትን እንዲገሥጽ ነቢዩ ናታንን ላከው። (2 ሳሙኤል 11:1–17፤ 12:1–12) ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ዳዊት ከልቡ ተፀፀተ፣ ይሖዋም ይቅር አለው። (2 ሳሙኤል 12:13፤ መዝሙር 32:1–5) ታዲያ ይሖዋ የዳዊትን ኃጢአት ረስቷልን? በፍጹም አልረሳም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የሆኑት ጋድና ናታን ዳዊት ከመሞቱ ጥቂት ዓመታት ቀደም ብለው (1040 ከዘአበ ገደማ ተጽፎ ባለቀው) በ2 ሳሙኤል መጽሐፍ ውስጥ ታሪኩን በዝርዝር መዝግበዋል።
ስለዚህ ዳዊት የሠራቸውን ኃጢአቶች የሚዘክረው ዘገባም ሆነ ንስሃ መግባቱንና በዚህም ምክንያት ይሖዋ ይቅር እንዳለው የሚገልጸው ታሪክ ለመጽሐፍ ቅዱስ አንባብያን ጥቅም ሲባል እስከ ዛሬ ድረስ ተጠብቆ ቆይቷል። (ሮሜ 15:4፤ 1 ቆሮንቶስ 10:11) እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ‘የይሖዋ ቃል ለዘላለም ስለሚኖር’ የዳዊት ኃጢአት ፈጽሞ አይረሳም።— 1 ጴጥሮስ 1:25
ታዲያ ከልብ ከተጸጸትን ይሖዋ ኃጢአታችንን ፈጽሞ ይደመስስልናል ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? “በደላቸውን ይቅር እልላቸዋለሁ፤ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስባቸውም” የሚለውን የይሖዋ ቃል የምንረዳው እንዴት ነው?— ኤርምያስ 31:34 የ1980 ትርጉም፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
ይሖዋ የሚረሳው እንዴት ነው?
‘ማስታወስ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ግስ (ዛካር) የቀድሞውን ነገር ማስታወስን ብቻ አያመለክትም። ቲኦሎጂካል ወርድቡክ ኦቭ ዘ ኦልድ ቴስታመንት በሚለው መሠረት “መጥቀስ፣ ማሳወቅ፣ መድገም፣ መግለጫ መስጠት፣ ማሰብ፣ መክሰስ፣ መናዘዝ” የሚል ትርጉሞች ሊኖሩት ይችላል። ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ አቭ ዘ ኦልድ ቴስታመንት እንዲህ በማለት ተጨማሪ ሐሳብ ሰጥቷል:- “እንዲያውም [ዛካር] ብዙውን ጊዜ አንድን እርምጃ የሚያመለክት ቃል፤ ወይም ደግሞ አንድን እርምጃ ከሚገልጹ ግሶች ጋር ተያይዞ ይሠራበታል።” ስለዚህ ይሖዋ ከእርሱ ስለ ራቁት ሕዝቦች ‘በደላቸውን አስታውሳለሁ’ ብሎ ሲናገር ንስሐ ባለመግባታቸው ምክንያት እርምጃ እወስድባቸዋለሁ ማለቱ ነበር። (ኤርምያስ 14:10 የ1980 ትርጉም) በተቃራኒው ደግሞ ይሖዋ “ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስባቸውም” ሲል አንድ ጊዜ ኃጢአታችንን ይቅር ካለ በኋላ እንደገና አስታውሶ እንደማይከሰን፣ እንደማያወግዘንና እንደማይቀጣን ማረጋገጡ ነው።
ይሖዋ እንዴት ይቅር እንደሚልና እንደሚረሳ በነቢዩ ሕዝቅኤል በኩል ገልጿል:- “ኃጢአተኛውም ካደረጋት ኃጢአት ሁሉ ቢመለስ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቅ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። የበደለው በደል ሁሉ አይታሰብበትም፤ በሠራው ጽድቅ በሕይወት ይኖራል።” (ሕዝቅኤል 18:21, 22 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን፤ 33:14–16) አዎን፣ ይሖዋ አንድን ንስሐ የገባ ኃጢአተኛ ይቅር ሲል ኃጢአቱን ፈጽሞ ይደመስስለታል። ወደፊት ቀደም ሲል የሠራውን ኃጢአት አስታውሶ ስለማይቀጣው በደሉን ይረሳዋል።— ሮሜ 4:7, 8
ፍጹማን ባለመሆናችን እንደ ይሖዋ ፍጹም በሆነ መንገድ ይቅር ለማለት አንችልም። የይሖዋ ሐሳቦችና መንገዶች ከእኛ በጣም ከፍ ያሉ ናቸው። (ኢሳይያስ 55:8, 9) ታዲያ ሌሎች ሲበድሉን ይቅር እንድንልና እንድንረሳ የሚጠበቅብን እስከምን ድረስ ነው?
ይቅር ለማለትና ለመርሳት የምንችልበት መንገድ
ኤፌሶን 4:32 “እርስ በርሳችሁ በነጻ ይቅር ተባባሉ” በማለት ይመክራል። የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ የሆኑት ደብልዩ ኢ ቫይን እንዳሉት “በነጻ ይቅር ማለት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (ካሪዞማይ) “አለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ሞገስ ማሳየት” የሚል ትርጉም አለው። ቀላል የሆነ በደል ሲፈጸምብን ይቅር ለማለት አይከብደን ይሆናል። እኛም ፍጹማን አለመሆናችንን ማሰባችን የሌሎችን ስህተት እንድናልፍ ያስችለናል። (ቆላስይስ 3:13) ይቅር ስንል የነበረንን ቅያሜ ፈጽሞ እናስወግዳለን። ከበደለን ሰው ጋር የነበረን ዝምድናም ተቋርጦ አይቀርም። ከጊዜ በኋላ የተፈጸመብን አነስተኛ በደል ፈጽሞ ይረሳናል።
ይሁን እንጂ በጣም የጎዳን ከበድ ያለ በደል ቢፈጸምብንስ? አስገድዶ እንደ መድፈር፣ እንደ ግድያ ሙከራና በቤተዘመዶች መካከል እንደተደረገ ሩካቤ ሥጋ ያለ ከባድ ኃጢአት ከሆነ ይቅር ከማለት በፊት በርካታ ነገሮችን ማገናዘብ ያስፈልጋል። በተለይ በደለኛው ሰው ኃጢአቱን ካላመነ ወይም ካልተጸጸተና ይቅርታ ካልጠየቀ ይቅር ለማለት አይቻልም።b (ምሳሌ 28:13) ይሖዋ ራሱ አንገተ ደንዳና የሆኑና ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር አይልም። (ዕብራውያን 6:4–6፤ 10:26) የተፈጸመብን በደል ስሜታችንን በጣም አቁስሎት ከሆነ የሆነውን ነገር ከአእምሮአችን ሙሉ በሙሉ ለማውጣት አንችል ይሆናል። ቢሆንም በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ “የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም” በሚለው ተስፋ ልንጽናና እንችላለን። (ኢሳይያስ 65:17፤ ራእይ 21:4) በዚያ ጊዜ የምናስታውሰው ማንኛውም ነገር አሁን እንደሚሰማን ያለ የስሜት መቁሰል እንዲሰማን የሚያደርግ አይ ሆንም።
ይቅር ከማለታችን በፊት ራሳችን ቅድሚያ ወስደን የበደለንን ሰው ማነጋገርና ችግሩን መፍታት የሚያስፈልገን ጊዜም ሊኖር ይችላል። (ኤፌሶን 4:26) እንዲህ በማድረግ ማንኛውንም አለመግባባት ማስወገድ፣ ይቅር መባባልና ምህረት ማድረግ ይቻላል። መርሳትስ? የተደረገውን ነገር ፈጽሞ ከአእምሮአችን ለማጥፋት ባንችልም በበደለን ሰው ላይ ቂም ስለማንይዝ ወይም ነገሩን በሌላ ጊዜ ስለማናነሳበት ረስተነዋል ማለት ይቻላል። የበደለንን ሰው አናርቀውም ወይም አናማውም። ቢሆንም ዝምድናችን ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ በርካታ ጊዜ ሊያስፈልገው ይችላል። የሚኖረንም ቅርርብ የቀድሞውን ያህል ላይሆን ይችላል።
ነገሩን በምሳሌ እንመልከት:- በጣም ምስጢር የሆነ ነገር ለምታምነው ወዳጅህ ተናግረሃል እንበል። ይህ ወዳጅህ ምስጢርህን ለሌላ ሰው በመናገሩ በጣም አፍረሃል ወይም ተጎድተሃል። ወደ እርሱ ትሄድና ታነጋግረዋለህ። በጣም ያዝንና ይቅርታ ይጠይቅሃል። ከልቡ በመፀፀቱ ይቅር ለማለት ከልብህ ትገፋፋለህ። የሆነውን ነገር በቀላሉ ትረሳለህን? አትረሳ ይሆናል። ሌላ ጊዜ ለእርሱ ምስጢር የሆነ ነገር ላለመናገር እንደምትጠነቀቅም የታወቀ ነው። ቢሆንም ይቅር ትለዋለህ። ጉዳዩን እየደጋገምክ አታነሳበትም። ቂም አትይዝበትም ወይም አታማውም። የቀድሞውን ያህል ባትቀርበውም በክርስቲያን ወንድምነቱ ትወደዋለህ።— ከምሳሌ 20:19 ጋር አወዳድር።
ነገሩን እልባት ላይ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት አድርገህም እንኳ የበደለህ ሰው ስህተት መሥራቱን አምኖ ይቅርታ ባይጠይቅስ? ቅያሜህን በመርሳት ይቅር ትለዋለህን? ሌሎችን ይቅር ማለት ያደረጉትን ነገር አቃልሎ መመልከት ወይም መሸፋፈን ማለት አይደለም። ቂም ከባድ ሸክም ነው። ሐሳባችንን በሙሉ ሊቆጣጠረው ከመቻሉም በላይ ሰላም ያሳጣናል። ይቅርታ እንድንጠየቅ መጠበቅ ተጨማሪ ብስጭት ከማስከተል ሌላ የሚፈይድልን ነገር አይኖርም። ያስቀየመን ሰው ስሜታችንን እንዲቆጣጠር ፈቀድንለት ማለት ነው። ስለዚህ ሌሎችን ለእነርሱ ብለን ብቻ ሳይሆን የተለመደውን ሕይወታችንን በተረጋጋ መንፈስ ለመቀጠል እንድንችል ለራሳችን ጭምር ብለን ይቅር ማለት ያስፈልገናል።
ሌሎችን ይቅር ማለት ሁልጊዜ ቀላል አይሆንም። ልባዊ የሆነ ንስሐ ከኖረ ግን የይሖዋን የይቅር ባይነት ምሳሌ ለመከተል ጥረት ልናደርግ እንችላለን። ይሖዋ ንስሐ የገቡ በደለኞችን ይቅር ሲል ምንም ዓይነት ቂም አይዝባቸውም። ኃጢአታቸውን ፈጽሞ ስለሚደመስስላቸው ይረሳዋል። የሠሩትን ኃጢአት ወደፊት አያስብባቸውም። እኛም ብንሆን የበደለን ሰው ሲጸጸት ቅያሜያችንን ለማስወገድ መጣር ይኖርብናል። ይሁን እንጂ ይቅር ለማለት የማንገደድባቸው ጊዜያት ሊኖሩ ይችላሉ። ከልክ ያለፈ ጭካኔ ወይም ግፍ የተፈጸመበት ሰው ያልተፀፀተውን ግፈኛ ይቅር ለማለት አይገደድም። (ከመዝሙር 139:21, 22 ጋር አወዳድር።) በአብዛኞቹ ሁኔታዎች ግን ሌሎች ሰዎች ሲበድሉን ቅያሜያችንን በማስወገድ ይቅር ልንል እንችላለን፤ እንዲሁም ጉዳዩን ዳግመኛ ባለማንሳት በደሉን ልንረሳ እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በታኅሣሥ 8, 1993 የእንግሊዝኛ ንቁ! እትም ገጽ 18–19 ላይ የወጣውን “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት፣ የአምላክ ይቅርታ ምን ያህል የተሟላ ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል ጥራዝ 1 ገጽ 862 “ክርስቲያኖች በጥላቻ ተነሳስተውና ሆነ ብለው የሚበድሏቸውን እንዲሁም የንስሐ መንፈስ የማያሳዩትን ሰዎች ይቅር እንዲሉ አይገደዱም። እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች የአምላክ ጠላት ይሆናሉ” ይላል።— በኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዮሴፍና ወንድሞቹ