‘ነገር ሁሉ የሚታደስበት ዘመን’ ቀርቧል!
ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ጥቂት ቀደም ብሎ የተወሰኑ ታማኝ ደቀ መዛሙርቱ “ጌታ ሆይ፣ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን?” በማለት ጠይቀውት ነበር። ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄያቸው የሰጠው መልስ መንግሥቱ ከመምጣቱ በፊት የተወሰነ ጊዜ እንደሚያልፍ ያመለክታል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ተከታዮቹ የሚሠሩት ታላቅ ሥራ ይኖራቸዋል። “በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ” የኢየሱስ ምሥክሮች መሆን ነበረባቸው።—ሥራ 1:6-8
ይህንን ሥራ በጥቂት ቀናት፣ ሳምንታት ወይም ወራት ውስጥ ሠርቶ መጨረስ አይቻልም። ቢሆንም ደቀ መዛሙርቱ ወዲያውኑ መስበክ ጀመሩ። ያም ሆኖ ግን መንግሥቱ ስለሚመለስበት ጊዜ ለማወቅ የነበራቸው ፍላጎት አልጠፋም። ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህንን አስመልክቶ በኢየሩሳሌም ተሰብስቦ ለነበረው ብዙ ሕዝብ የሚከተለውን ተናግሯል:- “ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፣ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም። እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገረው፣ ነገር ሁሉ እስከሚታደስበት ዘመን ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ ይገባልና።”—ሥራ 3:19-21፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
ይህ ‘ነገር ሁሉ የሚታደስበት ዘመን’ የሚመጣው በይሖዋ “የመጽናናት ዘመን” ውስጥ ነው። ነገር ሁሉ እንደሚታደስ አስቀድሞ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን የሚያገኘው በሁለት መልኩ ነው። አንዱ አስደሳች በሆነው መንፈሳዊ ተሐድሶ አማካኝነት ሲሆን ይህም በዛሬው ጊዜ በመከናወን ላይ ይገኛል። ሁለተኛው ደግሞ ይህን ተሐድሶ ተከትሎ በሚቋቋመው ምድራዊ ገነት ወቅት ፍጻሜውን ያገኛል።
ነገር ሁሉ የሚታደስበት ዘመን ጀመረ
ሐዋርያው ጴጥሮስ በኢየሩሳሌም ለተሰበሰበው ብዙ ሕዝብ እንደተናገረው ሰማይ ኢየሱስን ‘ተቀብሎታል።’ ይህ ሁኔታ ኢየሱስ በ1914 በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ በመገኘት በአምላክ የተሾመ ንጉሥ ሆኖ መግዛት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ ቀጥሏል። ጴጥሮስ አስቀድሞ እንደተናገረው በ1914 በአምላክ ዓላማ ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው ኢየሱስ የድርሻውን እንዲያከናውን በመፍቀድ ይሖዋ ልጁን ‘ልኳል’ ሊባል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ሁኔታውን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል:- “[የአምላክ ሰማያዊ ድርጅት] አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ [በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራውን የአምላክ መንግሥት] ወለደች።”—ራእይ 12:5
ሆኖም ብሔራት ለክርስቶስ አገዛዝ ራሳቸውን በፈቃደኝነት የማስገዛት ፍላጎት ፈጽሞ አልነበራቸውም። እንዲያውም በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በመባል በሚታወቁት ታማኝ የኢየሱስ ምድራዊ ተገዥዎች ላይ የቃላት ጥቃት ሰንዝረው ነበር። ይሁን እንጂ ምሥክሮቹ ልክ እንደ ቀድሞዎቹ ሐዋርያት ያላንዳች ማመንታት ስለ ‘ኢየሱስ ምስክርነት’ የመስጠቱን ሥራ ተያያዙት። (ራእይ 12:17) እነዚህ ቅን ክርስቲያኖች የሚሠሩት ሥራ በየአገሩ ተቃውሞ ይገጥመው ጀመር። በ1918 ብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኀበር ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሠሩ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የሐሰት ክስ ተመስርቶባቸው ችሎት ፊት ከመቅረባቸውም በላይ ፍትህ በጎደለው መንገድ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲታሰሩ ተበይኖባቸው ነበር። ስለዚህም ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ’ የሚከናወነው ዘመናዊው የምሥክርነት ሥራ ለተወሰነ ጊዜ ያህል የተቋረጠ መስሎ ነበር።—ራእይ 11:7-10
ይሁን እንጂ በ1919 እስር ላይ የነበሩት የዋናው መሥሪያ ቤት አባላት ከእስር ከመፈታታቸውም በላይ ከቀረበባቸው የሐሰት ክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ ሆኑ። እነዚህ ወንድሞች ጊዜ ሳያጠፉ መንፈሳዊ ተሐድሶ የማካሄዱን ሥራ ተያያዙት። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የይሖዋ ሕዝቦች ታይቶ የማያውቅ መንፈሳዊ ብልጽግና አግኝተዋል።
አሕዛብ ሁሉ ክርስቶስ ተከታዮቹ እንዲያደርጉት ያዘዘውን ነገር እንዲጠብቁ ለማስተማር መጠነ ሰፊ ዘመቻ ተካሂዷል። (ማቴዎስ 28:20) ቀድሞ የእንስሳ ዓይነት ባህርይ ያሳዩ የነበሩ ሰዎች አሁን አመለካከታቸውን ለውጠው ማየት እንዴት መንፈስን ያድሳል! እንዲህ ያሉት ሰዎች እንደ “ንዴት፣” “ስድብ” እንዲሁም “የሚያሳፍር ንግግር” የመሳሰሉትን ባሕርያት እንዲያንጸባርቁ ተጽእኖ ያደረገባቸውን አሮጌ ሰው አውልቀው በመጣል “የፈጠረውንም ምሳሌ [አምላክን] እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው” ለብሰዋል። ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት አሁንም እንኳ በመንፈሳዊ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን እያገኙ ነው:- “ተኩላ [ቀድሞ የተኩላ ዓይነት ባሕርይ የነበረው ሰው] ከበግ ጠቦት [የየዋህነት ባሕርይ ከሚያሳይ ሰው] ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ።”—ቆላስይስ 3:8-10፤ ኢሳይያስ 11:6, 9
ሌላ ተሐድሶ የሚከናወንበት ጊዜ ቀርቧል!
በዛሬው ጊዜ መንፈሳዊ ገነት ካስገኘው ተሐድሶ በተጨማሪ ምድራችን ቃል በቃል ወደ ገነትነት የምትለወጥበት ጊዜ በጣም ቀርቧል። ይሖዋ አዳምና ሔዋን የተባሉትን የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን በኤደን የአትክልት ስፍራ ባስቀመጣቸው ወቅት የምድር ጥቂቱ ክፍል ገነት ነበር። (ዘፍጥረት 1:29-31) ገነት ተመልሶ ይቋቋማል ብለን መናገር የምንችለው ለዚህ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ከመሆኑ በፊት ምድር አምላክን ከማያስከብሩ የሐሰት ሃይማኖቶች ሙሉ በሙሉ መጽዳት ያለባት ሲሆን ይህንን የማጽዳት እርምጃ የሚወስዱት ደግሞ የዚህ ዓለም ፖለቲካዊ ኃይላት ይሆናሉ። (ራእይ 17:15-18) ከዚያ በኋላ የፖለቲካውና የንግዱ ክፍል እስከ ደጋፊዎቹ ይደመሰሳል። በመጨረሻም የቀሩት የአምላክ ተቃዋሚዎች ማለትም ሰይጣንና አጋንንቱ የተሐድሶው ሥራ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለአንድ ሺህ ዓመት ይታሰራሉ። በዚያን ጊዜ “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፣ በረሀውም ሐሤት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል።” (ኢሳይያስ 35:1) ምድር ሁሉ ጸጥታ የሰፈነባት ትሆናለች። (ኢሳይያስ 14:7) እንዲያውም በሚልዮን የሚቆጠሩ የሞቱ ሰዎች ሳይቀሩ ትንሣኤ አግኝተው በምድር ላይ ይኖራሉ። ሁሉም ሰው ቤዛዊ መሥዋዕቱ ከሚያስገኘው ተሐድሶ ተጠቃሚ ይሆናል። (ራእይ 20:12-15፤ 22:1, 2) ያን ጊዜ በምድር ላይ ዕውር፣ ደንቆሮ ወይም አንካሳ የሆኑ ሰዎች አይኖሩም። “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም።” (ኢሳይያስ 33:24) የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ካበቃ በኋላ ሰይጣንና አጋንንቱ ለአጭር ጊዜ ከእስራታቸው ይፈቱና አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ እንዴት ፍጻሜውን እንዳገኘ ይመለከታሉ። ከዚያም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይደመሰሳሉ።—ራእይ 20:1-3
የሺው ዓመት ምድራዊ ተሐድሶ ሲያበቃ “እስትንፋስ ያለው ሁሉ” ይሖዋን ያመሰግናል። ይህም ለዘላለም የሚቀጥል ይሆናል። (መዝሙር 150:6) አንተስ በእነርሱ መካከል ትገኝ ይሆን? መገኘት ትችላለህ።