“ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ”
“[ኢየሱስ] እንዲህ አላቸው፦ ‘. . . እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።’”—ሥራ 1:7, 8
1, 2. (ሀ) ከሁሉ የላቀው የይሖዋ ምሥክር ማን ነው? (ለ) ኢየሱስ የሚለው ስም ትርጉም ምንድን ነው? የአምላክ ልጅ ከስሙ ጋር በሚስማማ መንገድ የኖረው እንዴት ነው?
“የተወለድኩትና ወደ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት እንድመሠክር ነው።” (ዮሐንስ 18:33-37ን አንብብ።) ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሐሳብ የተናገረው በሮማዊው አገረ ገዢ ፊት ለፍርድ ቀርቦ በነበረበት ወቅት ነው። ኢየሱስ ንጉሥ እንደሆነ በዚህ ጊዜ ገልጾ ነበር። ይህ ከሆነ ከዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ በድፍረት ረገድ የተወውን ምሳሌ በማስታወስ “ለጳንጥዮስ ጲላጦስ በይፋ ግሩም ምሥክርነት [እንደሰጠ]” ተናግሯል። (1 ጢሞ. 6:13) በእርግጥም በጥላቻ በተሞላው የሰይጣን ዓለም ውስጥ ‘የታመነና እውነተኛ ምሥክር’ መሆን ትልቅ ድፍረት ይጠይቃል።—ራእይ 3:14
2 ኢየሱስ የአይሁድ ብሔር አባል እንደመሆኑ መጠን ሲወለድ ጀምሮ የይሖዋ ምሥክር ነበር። (ኢሳ. 43:10) ደግሞም ይሖዋ ስለ ስሙ እንዲመሠክሩ ካስነሳቸው ሰዎች ሁሉ የላቀው ምሥክር ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ፣ አምላክ ያወጣለት ስም ያለውን ትርጉም በቁም ነገር ተመልክቶታል። አንድ መልአክ የኢየሱስ አሳዳጊ አባት ለሆነው ለዮሴፍ ማርያም የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ከገለጸለት በኋላ “ወንድ ልጅ ትወልዳለች፣ ስሙንም ኢየሱስ ብለህ ትጠራዋለህ፤ እሱም ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል” ብሎት ነበር። (ማቴ. 1:20, 21 የአ.መ.ት የግርጌ ማስታወሻ) አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን፣ ኢየሱስ የሚለው ስም የመጣው የሹዋ ወይም ኢያሱ ከሚለው የዕብራይስጥ ስም እንደሆነና የመለኮታዊውን ስም ምህጻረ ቃል እንደያዘ ይስማማሉ፤ ኢየሱስ የሚለው ስም ‘ይሖዋ ያድናል’ የሚል ትርጉም አለው። ኢየሱስ ‘ከእስራኤል ቤት የጠፉት በጎች’ ከኃጢአታቸው ንስሐ ገብተው የይሖዋን ሞገስ እንደገና እንዲያገኙ በመርዳት ከስሙ ትርጉም ጋር የሚስማማ ነገር አድርጓል። (ማቴ. 10:6፤ 15:24፤ ሉቃስ 19:10) ይህን ተልእኮ ለመፈጸም ሲልም ስለ አምላክ መንግሥት በቅንዓት መሥክሯል። የወንጌል ጸሐፊው ማርቆስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ኢየሱስ የአምላክን ምሥራች እየሰበከ ወደ ገሊላ ሄደ። ‘የተወሰነው ጊዜ ተፈጽሟል፤ የአምላክ መንግሥት ቀርቧል። ሰዎች ሆይ፣ ንስሐ ግቡ፤ በምሥራቹም እመኑ’ ይል ነበር።” (ማር. 1:14, 15) ኢየሱስ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎችንም በድፍረት አውግዟቸዋል፤ በዚህም ምክንያት በእንጨት ላይ ተሰቅሎ እንዲሞት አደረጉ።—ማር. 11:17, 18፤ 15:1-15
‘የአምላክ ታላቅ ሥራዎች’
3. ኢየሱስ በሞተ በሦስተኛው ቀን ምን ተከናወነ?
3 ይሁን እንጂ አስደናቂ ነገር ተፈጠረ! ኢየሱስ በጭካኔ በተገደለ በሦስተኛው ቀን ይሖዋ ከሞት አስነሳው፤ የተነሳውም ሰው ሆኖ ሳይሆን የማይሞት መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ ነው። (1 ጴጥ. 3:18) ጌታ ኢየሱስ ሰብዓዊ አካል ለብሶ በመገለጥ ከሞት መነሳቱን ለደቀ መዛሙርቱ አረጋግጦላቸዋል። ከሞት በተነሳበት ቀን፣ ለተለያዩ ደቀ መዛሙርቱ ቢያንስ አምስት ጊዜ ተገልጧል።—ማቴ. 28:8-10፤ ሉቃስ 24:13-16, 30-36፤ ዮሐ. 20:11-18
4. ኢየሱስ ከሞት በተነሳበት ቀን የትኛውን ስብሰባ አድርጎ ነበር? ለደቀ መዛሙርቱስ ምን ኃላፊነት እንዳለባቸው ነገራቸው?
4 ኢየሱስ ለአምስተኛ ጊዜ የተገለጠው ለሐዋርያቱና አብረዋቸው ለነበሩ ሌሎች ሰዎች ነው። በዚያ የማይረሳ ወቅት፣ ለተከታዮቹ የአምላክን ቃል አስተምሯቸዋል ማለት ይቻላል። “የቅዱሳን መጻሕፍትን ትርጉም መረዳት እንዲችሉ አእምሯቸውን ከፈተላቸው።” በመሆኑም በአምላክ ጠላቶች እጅ እንደሚገደልና በተአምር እንደሚነሳ ቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድመው ተናግረው እንደነበር ተገነዘቡ። ኢየሱስ ከሞት በተነሳበት ቀን ከተከታዮቹ ጋር ያደረገው ይህ ስብሰባ ሲያበቃ፣ ምን ኃላፊነት እንዳለባቸው በግልጽ ነገራቸው። እንዲህ አላቸው፦ “[በስሜም] የኃጢአት ይቅርታ የሚያስገኝ ንስሐ ለሕዝቦች ሁሉ ይሰበካል፤ ከኢየሩሳሌምም አንስቶ ለእነዚህ ነገሮች ምሥክሮች ትሆናላችሁ።”—ሉቃስ 24:44-48
5, 6. (ሀ) ኢየሱስ “ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ያለው ለምንድን ነው? (ለ) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከይሖዋ ዓላማ ጋር በተያያዘ ማወጅ ያለባቸው አዲስ ነገር ምንድን ነው?
5 በመሆኑም ከ40 ቀናት በኋላ ይኸውም ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ በተገለጠላቸው ወቅት ሐዋርያቱ እሱ የሰጣቸውን ቀላል ሆኖም ትልቅ መልእክት ያዘለ ትእዛዝ ለመረዳት እንዳልተቸገሩ ግልጽ ነው፤ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በኢየሩሳሌምም ሆነ በመላው ይሁዳ፣ በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።” (ሥራ 1:8) ኢየሱስ፣ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚሆኑ ከመናገር ይልቅ “ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ያለው ለምንድን ነው? እርግጥ፣ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚሆኑ መናገር ይችል ነበር፤ ሆኖም ይህን ሐሳብ የተናገረው ቀድሞውኑም የይሖዋ ምሥክሮች ለሆኑት እስራኤላውያን ነው።
6 ከዚህ በኋላ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከይሖዋ ዓላማ ጋር በተያያዘ አዲስ ነገር ሊያውጁ ነው፤ ይህ መልእክት እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት እንዲሁም ከጊዜ በኋላ ከባቢሎን ምርኮ ነፃ መውጣታቸውን ከሚገልጸው መልእክት እጅግ የላቀ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ከሁሉ ከከፋው ባርነት ይኸውም ከኃጢአትና ከሞት ለመላቀቅ የሚያስችል መሠረት አስገኝቷል። በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት አዲስ የተቀቡት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” ለሰዎች ያወጁ ሲሆን ብዙዎቹም መልእክቱን ተቀብለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ንስሐ ከመግባታቸውም ሌላ መዳን ለማግኘት ይሖዋ ያዘጋጀው መንገድ ኢየሱስ መሆኑን አምነዋል፤ በዚህ ወቅት ኢየሱስ በሰማይ በአባቱ ቀኝ ሆኖ የስሙ ትርጉም የበለጠ ፍጻሜ ሲያገኝ ተመልክቷል።—ሥራ 2:5, 11, 37-41
‘በብዙዎች ምትክ የተሰጠ ቤዛ’
7. በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት የተከናወኑት ነገሮች ምን ያረጋግጣሉ?
7 በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት የተከናወኑት ነገሮች ይሖዋ የኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ያለውን ዋጋ የኃጢአት ማስተሰረያ ወይም መሸፈኛ አድርጎ እንደተቀበለው ያሳያሉ። (ዕብ. 9:11, 12, 24) ኢየሱስ እንደተናገረው ወደ ምድር የመጣው “ለማገልገልና በብዙዎች ምትክ ነፍሱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት እንጂ እንዲገለገል አይደለም።” (ማቴ. 20:28) ከኢየሱስ ቤዛ የሚጠቀሙት “ብዙዎች” ንስሐ የገቡ አይሁዳውያን ብቻ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ ፈቃድ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ” ነው፤ ምክንያቱም ቤዛው የሚያስወግደው “የዓለምን ኃጢአት” ነው!—1 ጢሞ. 2:4-6፤ ዮሐ. 1:29
8. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የምሥክርነቱን ሥራ ምን ያህል በስፋት ማከናወን ችለው ነበር? እንዲህ ማድረግ የቻሉትስ እንዴት ነው?
8 ጥንት የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስለ እሱ መመሥከራቸውን ለመቀጠል የሚያስችል ድፍረት ነበራቸው? አዎ፣ ሆኖም ይህን ድፍረት ያገኙት በራሳቸው አቅም አይደለም። ኃያል የሆነው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ መመሥከራቸውን እንዲቀጥሉ አነሳስቷቸዋል፤ እንዲሁም ኃይል ሰጥቷቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 5:30-32ን አንብብ።) በ33 ዓ.ም. የጴንጤቆስጤ በዓል ከተከበረ ከ27 ዓመታት በኋላ ‘የምሥራቹ እውነት’ “ከሰማይ በታች ባለ ፍጥረት ሁሉ መካከል” ለሚገኙ አይሁድና አሕዛብ “ተሰብኳል” ተብሎ ነበር።—ቆላ. 1:5, 23
9. አስቀድሞ በተነገረው መሠረት እውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ ምን አጋጠመው?
9 የሚያሳዝነው ግን ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የሐሰት ትምህርቶች ወደ እውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ ሰርገው ገቡ። (ሥራ 20:29, 30፤ 2 ጴጥ. 2:2, 3፤ ይሁዳ 3, 4) ኢየሱስ እንደተናገረው “ክፉ” የሆነው ሰይጣን የሚያስፋፋው እንዲህ ያለው ክህደት እስከዚህ “ሥርዓት መደምደሚያ” ድረስ እየጨመረ በመሄድ እውነተኛውን ክርስትና ሸፈነው። (ማቴ. 13:37-43) ከዚያም ይሖዋ፣ ኢየሱስን በአምላክ መንግሥት ላይ ንጉሥ አድርጎ ሾመው። ክርስቶስ የነገሠው ጥቅምት 1914 ሲሆን የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀኖች’ የጀመሩት በዚህ ጊዜ ነው።—2 ጢሞ. 3:1
10. (ሀ) በዘመናችን ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለ የትኛው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጊዜ አስቀድመው ተናግረዋል? (ለ) ጥቅምት 1914 ምን ተከናወነ? ይህን እንዴት እናውቃለን?
10 በዘመናችን ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጥቅምት 1914 ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጊዜ እንደሆነ አስቀድመው ተናግረው ነበር። ይህን ያሉት ዳንኤል ስለ አንድ ትልቅ ዛፍ የተናገረውን ትንቢት መሠረት በማድረግ ነው፤ ዛፉ ከተቆረጠ ‘ከሰባት ዓመታት’ ወይም ዘመናት በኋላ ተመልሶ ያድጋል። (ዳን. 4:16) ኢየሱስ ስለ መገኘቱና ‘ስለዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ በተናገረው ትንቢት ላይ እነዚህን ሰባት ዘመናት “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” በማለት ጠርቷቸዋል። ልዩ ከሆነው ዓመት ይኸውም ከ1914 ወዲህ ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ ‘እንደተገኘ’ የሚጠቁመው “ምልክት” ሁሉም ሰው ሊያስተውለው በሚችል ሁኔታ በግልጽ እየታየ ነው። (ማቴ. 24:3, 7, 14፤ ሉቃስ 21:24) በመሆኑም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፣ ለሰዎች ከምናውጃቸው ‘የአምላክ ታላቅ ሥራዎች’ አንዱ ይሖዋ ኢየሱስን በአምላክ መንግሥት ላይ ንጉሥ አድርጎ መሾሙ ነው።
11, 12. (ሀ) አዲስ የተሾመው ንጉሥ ከ1919 አንስቶ ምን ማድረግ ጀመረ? (ለ) ከ1930ዎቹ አጋማሽ ወዲህ ምን መካሄድ ጀመረ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
11 አዲስ የተሾመው ንጉሥ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙም ሳይቆይ ቅቡዓን ተከታዮቹን ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ ነፃ ማውጣት ጀመረ። (ራእይ 18:2, 4) አንደኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ ይኸውም በ1919፣ ይሖዋ ለመዳን ስላደረገው ዝግጅትና መንግሥቱ መቋቋሙን ስለሚገልጸው ምሥራች በመላው ዓለም ምሥክርነት መስጠት የሚያስችል አጋጣሚ ተከፈተ። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው በመመሥከራቸው የክርስቶስ ተባባሪ ገዢዎች የሚሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ቅቡዓን ተሰበሰቡ።
12 ከ1930ዎቹ አጋማሽ በኋላ ደግሞ ክርስቶስ ከተለያዩ ብሔራት የሚውጣጡትን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” መሰብሰብ እንደጀመረ ግልጽ ሆነ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት እነዚህ ሰዎች የክርስቶስ “ሌሎች በጎች” አባላት ናቸው። የዚህ እጅግ ብዙ ሕዝብ አባላትም ከቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚያገኙትን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ የኢየሱስን የድፍረት ምሳሌ ተከትለው፣ መዳን ያገኙት ከአምላክና ከክርስቶስ እንደሆነ በይፋ ያውጃሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች በዚህ የምሥክርነት ሥራ ስለሚጸኑና በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ስላላቸው የሰይጣን ዓለም ‘በታላቁ መከራ’ ሲጠፋ በሕይወት ይተርፋሉ።—ዮሐ. 10:16፤ ራእይ 7:9, 10, 14
‘ምሥራቹን ለመናገር እንደምንም ብሎ ድፍረት ማግኘት’
13. የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ምን ለማድረግ ቆርጠናል? እንደሚሳካልን እርግጠኞች የምንሆነውስ ለምንድን ነው?
13 እኛም ይሖዋ አምላክ ስላከናወናቸው ‘ታላቅ ሥራዎች’ እንዲሁም ወደፊት ለማከናወን ቃል ስለገባቸው ነገሮች ምሥክርነት የመስጠት መብታችንን ከፍ አድርገን መመልከታችንን እንቀጥል። እርግጥ እንዲህ ያለ ምሥክርነት መስጠት ቀላል የማይሆንባቸው ጊዜያት አሉ። አብዛኞቹ ወንድሞቻችን በሚያገለግሉባቸው ክልሎች ውስጥ ፌዘኛና ለመልእክቱ ግድ የለሽ የሆኑ ሰዎች ያጋጥሟቸዋል፤ አሊያም ስደት ይደርስባቸዋል። ይሁንና እኛም ሐዋርያው ጳውሎስና የሥራ አጋሮቹ እንዳደረጉት ማድረግ እንችላለን። ጳውሎስ “የአምላክን ምሥራች በከፍተኛ ትግል ለእናንተ ለመናገር በአምላካችን እርዳታ እንደምንም ብለን . . . ድፍረት [አገኘን]” ብሏል። (1 ተሰ. 2:2) እንግዲያው ፈጽሞ ተስፋ አንቁረጥ። ከዚህ ይልቅ ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን የገባነውን ቃል የሰይጣን ሥርዓት ሙሉ በሙሉ እስከሚጠፋበት ጊዜ ድረስ ጠብቀን ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (ኢሳ. 6:11) ይህን በራሳችን ኃይል ማድረግ አንችልም፤ በመሆኑም የጥንቶቹን ክርስቲያኖች ምሳሌ በመከተል ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነውን] ኃይል” እንዲሰጠን መጸለይ ይኖርብናል።—2 ቆሮንቶስ 4:1, 7ን አንብብ፤ ሉቃስ 11:13
14, 15. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች እንዴት ይታዩ ነበር? ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ እነሱ ምን ብሏል? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናችን ስደት ቢደርስብን ምን ሊሰማን ይገባል?
14 በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ክርስቲያኖች እንደሆኑ ቢናገሩም “አምላክን . . . በሥራቸው ይክዱታል፤ ምክንያቱም አስጸያፊና የማይታዘዙ እንዲሁም ለማንኛውም ዓይነት መልካም ሥራ የማይበቁ ናቸው።” (ቲቶ 1:16) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች በወቅቱ በነበሩት ብዙ ሰዎች ዘንድ ይጠሉ እንደነበረ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ለክርስቶስ ስም ስትሉ ብትነቀፉ ደስተኞች ናችሁ፤ ምክንያቱም . . . የአምላክ መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋል” በማለት የጻፈው ለዚህ ነው።—1 ጴጥ. 4:14
15 በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ሐሳብ በዛሬው ጊዜ ላሉ የይሖዋ ምሥክሮች ይሠራል? እንዴታ! ምክንያቱም እኛም ክርስቶስ ንጉሥ መሆኑን እንመሠክራለን። ከዚህ አንጻር፣ በይሖዋ ስም በመጠራታችን የተነሳ መጠላት ‘ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስንል ከመነቀፍ’ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን “እኔ በአባቴ ስም መጣሁ፤ እናንተ ግን አልተቀበላችሁኝም” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 5:43) እንግዲያው በሚቀጥለው ጊዜ በአገልግሎት ላይ ተቃውሞ ሲያጋጥምህ አትፍራ። እንዲህ ያለው ስደት የአምላክ ሞገስ እንዳለህና መንፈሱ ‘በአንተ ላይ እንዳረፈ’ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።
16, 17. (ሀ) በብዙ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች ምን ያጋጥማቸዋል? (ለ) ምን ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል?
16 በሌላ በኩል ደግሞ በብዙ የዓለም ክፍሎች ከፍተኛ እድገት እየተገኘ እንደሆነም መዘንጋት አይኖርብንም። በተደጋጋሚ በተሸፈኑ ክልሎች ውስጥም እንኳ የምንሰብከውን አስደሳች የመዳን መልእክት ለማዳመጥ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች እየተገኙ ነው። ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግና ከተቻለም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፤ በዚህ መንገድ፣ እድገት እንዲያደርጉ ብሎም ራሳቸውን ወስነው እንዲጠመቁ እንረዳቸዋለን። አንተም በደቡብ አፍሪካ እንደሚኖሩትና ከ60 ለሚበልጡ ዓመታት በምሥክርነቱ ሥራ በቅንዓት እንደተካፈሉት እንደ እህት ሳሪ ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ ብለዋል፦ “የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ከሆነው ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና ለመመሥረት ስላስቻለኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ፤ እንዲሁም የአምላክን ታላቅ ስም ማሳወቅ በጣም ያስደስተኛል።” እህት ሳሪና ባለቤታቸው ወንድም ማርቲነስ፣ ሦስት ልጆቻቸውን ጨምሮ ብዙ ሰዎች የይሖዋ አምላኪዎች እንዲሆኑ ረድተዋል። እህት ሳሪ እንዲህ ብለዋል፦ “ከዚህ የበለጠ እርካታ የሚያስገኝ ሌላ ሥራ የለም፤ ይሖዋም በዚህ ሕይወት አድን ሥራ መሳተፋችንን ለመቀጠል የሚያስፈልገንን ኃይል በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ለሁላችንም ይሰጠናል።”
17 የተጠመቅን ክርስቲያኖችም ሆንን እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ እየጣርን ያለን፣ የዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ አባል የመሆን መብት በማግኘታችን አመስጋኝ ልንሆን ይገባል። እንግዲያው ርኩስ ከሆነው የሰይጣን ዓለም ርቀህ ለመኖር ምንጊዜም ጥረት እያደረግህ የተሟላ ምሥክርነት መስጠትህን ቀጥል። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ በታላቅ ስሙ የመጠራት መብት ለሰጠንና አፍቃሪ ለሆነው የሰማዩ አባታችን ክብር ታመጣለህ።