የአንባብያን ጥያቄዎች
ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን የገባው በዑር ነው ወይስ በካራን?
ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን እንዳደረገ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የምናገኘው በዘፍጥረት 12:1-3 ላይ ሲሆን ጥቅሱም እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም አብራምን አለው:- ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፣ . . . የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ።”a ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ይህን ቃል ኪዳን የገባው አብርሃም ገና በዑር ሳለ ሲሆን ካራን በነበረበት ጊዜ ይህንኑ ቃል ኪዳን በድጋሚ ነግሮት መሆን አለበት።
አብርሃም ወደ ከነዓን እንዲሄድ ይሖዋ እንዳዘዘው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው እስጢፋኖስ ተናግሯል። በሳንሄድሪን ፊት ቀርቦ እንዲህ አለ:- “የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በካራን ሳይቀመጥ ገና በሁለት ወንዝ መካከል ሳለ ታየና:- ከአገርህና ከዘመዶችህም ወጥተህ ወደማሳይህ ወደ ማንኛውም ምድር ና አለው።” (ሥራ 7:2, 3፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አብርሃም ትውልዱ ዑር ሲሆን፣ እስጢፋኖስም እንዳመለከተው ወደ ከነዓን እንዲሄድ ለመጀመሪያው ጊዜ ትእዛዝ የተሰጠው እዚያ እያለ ነው። (ዘፍጥረት 15:7፤ ነህምያ 9:7) እስጢፋኖስ፣ አምላክ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን ስለመግባቱ ምንም የጠቀሰው ነገር የለም፤ ሆኖም በዘፍጥረት 12:1-3 ላይ የሰፈረው ቃል ኪዳን ወደ ከነዓን እንዲሄድ ከተሰጠው ትእዛዝ ጋር የተያያዘ ነው። ስለዚህ ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን የገባው በዑር ነው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው።
ይሁን እንጂ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ዘገባ በጥንቃቄ ማንበቡ ይሖዋ በከነዓን ቃል ኪዳኑንና የቃል ኪዳኑን የተለያዩ ዘርፎች በድጋሚና በስፋት እንደተናገረ ሁሉ በካራንም ለአብርሃም ቃል ኪዳኑን እንደደገመለት ይጠቁማል። (ዘፍጥረት 15:5፤ 17:1-5፤ 18:18፤ 22:16-18) ዘፍጥረት 11:31, 32 የአብርሃም አባት ታራ ከአብርሃም፣ ከሣራ እና ከሎጥ ጋር ሆኖ ወደ ዑር መሄዱን ይገልጻል። ካራን ከደረሱ በኋላ ታራ እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ እዚያው ተቀምጠዋል። አብርሃም በዛ ያለ ሃብት ለማካበት የሚያስችል ረዘም ያለ ጊዜ በካራን ተቀምጧል። (ዘፍጥረት 12:5) እንዲሁም በሆነ ጊዜ ላይ የአብርሃም ወንድም ናኮርም ወደዚያው ሄዷል።
መጽሐፍ ቅዱስ የታራን ሞት ከዘገበ በኋላ ይሖዋ ለአብርሃም የተናገራቸውን ቃላት በመግለጽ “አብራምም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 12:4) ከዚህም የተነሣ ዘፍጥረት 11:31–12:4 ይሖዋ በዘፍጥረት 12:1-3 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን ቃላት ለአብርሃም የተናገረው ታራ ከሞተ በኋላ ነው የሚል መልእክት ያስተላልፋል። እንደዚያ ከሆነ አብርሃም ካራንን ለቅቆ የወጣውና ይሖዋ ወዳመለከተው ምድር የሄደው ከብዙ ዓመት በፊት ዑር እያለ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰጠው እንዲሁም በዚህ ጊዜ በተነገረው ትእዛዝ መሠረት ነው።
ዘፍጥረት 12:1 እንደሚገልጸው ይሖዋ አብርሃምን “ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ” ብሎታል። በአንድ ወቅት የአብርሃም ‘አገር’ እንዲሁም የአባቱ “ቤት” ዑር ነበር። ይሁን እንጂ የአብርሃም አባት ቤተሰቡን ይዞ ወደ ካራን የሄደ ሲሆን አብርሃምም ያንን ምድር አገሩ እንደሆነ ተናግሯል። በከነዓን ብዙ ዓመት ከኖረ በኋላ ሎሌው ለይስሐቅ ሚስት እንዲፈልግ ‘ወደ አገሩና ወደ ተወላጆቹ’ በላከው ጊዜ ሎሌው “ወደ ናኮር ከተማ” (ወደ ካራን ወይም በአቅራቢያው ወደሚገኝ አንድ ቦታ) ሄዷል። (ዘፍጥረት 24:4, 10) እዚያም ሰፊ በሆነው በናኮር ቤተሰብ ማለትም በአብርሃም ዘመዶች መካከል ርብቃን አገኘ።—ዘፍጥረት 22:20-24፤ 24:15, 24, 29፤ 27:42, 43
እስጢፋኖስ በሳንሄድሪን ፊት በሰጠው ንግግር ላይ “አባቱ ከሞተ በኋላ እናንተ ዛሬ ወደምትኖሩባት ወደዚች አገር አወጣው” በማለት ስለ አብርሃም ተናግሯል። (ሥራ 7:4) ይህም ይሖዋ በካራን አብርሃምን አነጋግሮት እንደነበረ ያመለክታል። ይሖዋ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን ሥራ ላይ የዋለው አብርሃም ወደ ከነዓን በሄደ ጊዜ ስለሆነ በዘፍጥረት 12:1-3 ላይ በሠፈረው መሠረት በዚህ ጊዜ ይሖዋ ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ደግሞ ተናግሯል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው። ስለዚህ ሁሉንም ማስረጃዎች መመርመራችን ይሖዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን የገባው በዑር ሲሆን ይህንንም ቃል ኪዳን በካራን በድጋሚ አጽንቶታል ወደሚለው መደምደሚያ ያደርሰናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አብርሃም የ99 ዓመት ሰው ሆኖ በከነዓን ይኖር በነበረበት ጊዜ ይሖዋ የአብራምን ስም አብርሃም ብሎ ለውጦታል።—ዘፍጥረት 17:1, 5