ዶርቃ
[የሜዳ ፍየል]።
በኢዮጴ ጉባኤ የነበረችና ለችግረኛ መበለቶች ከውስጥ የሚለበሱ ልብሶችንና መደረቢያዎችን እየሠሩ መስጠትን ጨምሮ “መልካም በማድረግና ምጽዋት በመስጠት የምትታወቅ” ክርስቲያን ሴት ነበረች። (ሥራ 9:36, 39) “ዶርቃ” የሚለው ስም በአረማይክ “ጣቢታ” ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ሲሆን የሁለቱም ትርጉም “የሜዳ ፍየል” ማለት ነው። ምናልባትም ዶርቃ በሁለቱም ስሞች ትጠራ ይሆናል፤ ምክንያቱም ለአይሁዳውያን፣ በተለይም እንደ ኢዮጴ በመሰለ የባሕር ወደብ ላይ ከአሕዛብ ጋር ተቀላቅለው ለሚኖሩ አይሁዳውያን በዕብራይስጥና በግሪክኛ ወይም በላቲንኛ ስም መጠራት የተለመደ ነበር። አሊያም ደግሞ ሉቃስ ለአሕዛብ አንባቢያን ሲል ስሟን ወደ አረማይክ ተርጉሞት ይሆናል። በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ደቀ መዝሙር” የሚለው ቃል ለአንስታይ ፆታ ተሠርቶበት የምናገኘው ለዶርቃ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች በሙሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ስለሆኑ ዶርቃ በጉባኤ ውስጥ የተለየ ሥልጣን እንደነበራት ያመለክታል ማለት አይደለም። (ማቴ 28:19, 20) በ36 ዓ.ም. ስትሞት፣ መበለቶች (በደግነት ብዙ ነገር ያደረገችላቸው መበለቶች ሊሆኑ ይችላሉ) በጣም እንዳለቀሱላት ቢጠቀስም ባለቤቷ እንዳዘነ የሚገልጽ ነገር አለመኖሩ ዶርቃ በዚያን ጊዜ ያላገባች እንደነበረች ይጠቁማል።
በኢዮጴ የነበሩት ደቀ መዛሙርት አስከሬኗን ለቀብር ካዘጋጁ በኋላ ጴጥሮስ ከኢዮጴ በስተ ደቡብ ምሥራቅ 18 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው በልዳ እንዳለ ሲሰሙ እንዲመጣ መልእክት ላኩበት። እነዚህ ክርስቲያኖች ጴጥሮስ ልዳ ውስጥ ኤንያስ የተባለውን ሽባ ሰው መፈወሱን እንደሰሙ ምንም ጥርጥር የለውም፤ በመሆኑም ይህ ሐዋርያ ዶርቃንም ከሞት ሊያስነሳት ይችላል ብለው አስበው ይሆናል። አሊያም ጴጥሮስ እንዲመጣ የላኩበት እንዲሁ እንዲያጽናናቸው ፈልገው ሊሆን ይችላል።—ሥራ 9:32-38
ኢየሱስ የኢያኢሮስን ሴት ልጅ ባስነሳበት ጊዜ እንዳደረገው ሁሉ (ማር 5:38-41፤ ሉቃስ 8:51-55) ጴጥሮስም ሁሉንም ሰው ከክፍሉ ካስወጣ በኋላ ጸለየ፤ ከዚያም “ጣቢታ፣ ተነሺ” አለ። ዶርቃም ዓይኖቿን ገለጠችና ቀና ብላ ተቀመጠች፤ ከዚያም የጴጥሮስን እጅ ይዛ ተነሳች። ከኢየሱስ ሐዋርያት አንዱ የሞተ ሰው ሲያስነሳ ይህ የመጀመሪያው ሲሆን ይህም በኢዮጴ ብዙዎች አማኞች እንዲሆኑ አድርጓል።—ሥራ 9:39-42