126ኛው የጊልያድ ምረቃ
ስኬታማ ሚስዮናዊ መሆን የሚቻልበት መንገድ
ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል ውስጥ በሚደረገው ልዩ ዝግጅት ላይ ለመካፈል የተሰበሰቡት ሰዎች የፕሮግራሙን መጀመር በጉጉት እየተጠባበቁ ነው። ቅዳሜ፣ መጋቢት 14, 2009 የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ126ኛው ክፍል የምረቃ ፕሮግራም ተካሂዶ ነበር። ተመራቂዎቹ የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንዲሰብኩ ወደ 22 አገራት ይላካሉ።—ማቴዎስ 24:14
እነዚህ ተማሪዎች ውጤታማ ክርስቲያን ሚስዮናውያን እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ለአምስት ወራት የቆየ ጥልቀት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ተከታትለዋል። የሚመረቁበት ይህ ዕለት ውጤታማ ሚስዮናዊ ለመሆን የሚረዳቸውን ጥበብ ያዘለ ምክር አንድ ላይ ሆነው የሚያዳምጡበት የመጨረሻው አጋጣሚ ነው።
የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር ሆኖ ያገለገለውና የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም አንቶኒ ሞሪስ፣ የጊልያድ ትምህርት ቤት ሚስዮናውያንን ማሠልጠን የጀመረው በ1943 እንደሆነ ተናገረ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተመረቁት ሚስዮናውያን በዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ ብዙ ውጤት እንዲገኝ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
ጸሐፍትና ፈሪሳውያን የኢየሱስን ሐዋርያት “መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ” እንደሆኑ በመቁጠር ዝቅ አድርገው ቢመለከቷቸውም እነዚህ ተቃዋሚዎች ሐዋርያቱ በድፍረት ሲናገሩ ሲመለከቱ ከኢየሱስ ጋር በመሆናቸው የተገኘ ውጤት እንደሆነ ለመገንዘብ መገደዳቸውን ተናጋሪው አብራርቷል። (የሐዋርያት ሥራ 4:13 የ1954 ትርጉም) ተማሪዎቹ የወሰዱት ሥልጠና በድፍረት እንዲናገሩ ያስችላቸዋል።
“አምላክ አያዳላም” የሚል ጭብጥ ያለውን ንግግር ያቀረበው ደግሞ በበላይ አካሉ ሥር ያለውን የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ በመርዳት ላይ የሚገኘው ወንድም ሮበርት ሲራንኮ ነው። ወንድም ሲራንኮ ተማሪዎቹ ተመድበው በሚሄዱበት ቦታ የተለየ ባሕልና ልማድ ያላቸው ሰዎች እንደሚያጋጥሟቸው ተናገረ። ሆኖም ተማሪዎቹ የይሖዋን ዓይነት አስተሳሰብ ካዳበሩ ለእነዚህ ሰዎች መስበክ ምንም አያስቸግራቸውም። የሐዋርያት ሥራ 10:34 እንደሚናገረው ‘አምላክ አያዳላም።’ በእሱ ዘንድ ሁሉም ሰው ተቀባይነት አለው። (የሐዋርያት ሥራ 10:35) ወንድም ሲራንኮ በመቀጠል እንዲህ ብሏል፦ “የአምላክን ዓይነት አስተሳሰብ የምታዳብሩና በተመደባችሁበት ቦታ የሚገኙ ሰዎች በሙሉ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳላቸው አድርጋችሁ የምትመለከቱ ከሆነ የእሱ ሚስዮናዊ ሆናችሁ በምታከናውኑት አገልግሎት ውጤታማ መሆናችሁ አይቀርም።”
“ውጤታማ ለመሆን የሚያስፈልጋችሁን ነገር አግኝታችኋል”
“አንዳንድ ሰዎች ግመል አስቀያሚ እንስሳ እንደሆነ ይሰማቸዋል፤ ይሁንና የግመልን ያህል በረሃን መቋቋም የሚችል እንስሳ የለም” በማለት ንግግሩን የጀመረው የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ሳሙኤል ኸርድ ነበር። በተመሳሳይም አዲሶቹ ሚስዮናውያን በተመደቡበት ቦታ ውጤታማ ለመሆን እንዲችሉ የሚያስፈልጋቸውን ነገር አግኝተዋል። በዚህ ረገድ አምስት ነገሮች ይረዷቸዋል፦
1. ይሖዋን መውደድ። (ማቴዎስ 22:37, 38) ተማሪዎቹ ይሖዋን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረጉ ቀድሞውንም ቢሆን አሳይተዋል።
2. የተከማቸ የአምላክ ቃል እውቀት። ግመል ሻኛው ውስጥ በሚገኘው ስብ ውስጥ ምግብ ያከማቻል። ይሁንና አንድ ግመል የተከማቸ ምግብ አለኝ ብሎ ምግብ ሲያገኝ ከመብላት ወደኋላ አይልም። ሚስዮናውያኑም በተመሳሳይ በጊልያድ ትምህርት ቤት በተማሩት ነገር ላይ ብቻ ረክተው መኖር የለባቸውም፤ ከዚህ ይልቅ ዕለት ዕለት መንፈሳዊነታቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል።
3. ሰዎችን መውደድ። (ማቴዎስ 22:39) ተማሪዎቹ ለሰዎች ርኅራኄ ያሳያሉ።
4. የፈቃደኝነት መንፈስ። (መዝሙር 110:3) አንድ ሚስዮናዊ በሚዝልበት ጊዜ ይሖዋ ጉልበት ይጨምርለታል።—ኢሳይያስ 40:29
5. የወጣትነት ጉልበት። ግመል አንድን ሰው ተሸክሞ በረሃን እንደሚያቋርጥ ሁሉ አንድ ሚስዮናዊም በመንፈሳዊ ችግር ላይ የወደቀን ክርስቲያን “መሸከም” ያስፈልገው ይሆናል። ይህ ደግሞ ከፍተኛ ጉልበት ይጠይቃል፤ ያም ሆኖ ሚስዮናውያኑ የወጣትነት ጉልበት አላቸው።
የፕሮግራሙ ሌሎች ገጽታዎች
የጊልያድ ትምህርት ቤት መምህር የሆነው ወንድም ማይክል በርኔት፣ ያዕቆብ ለግብፁ ፈርዖን በስጦታ መልክ ከላካቸው ምርጥ ነገሮች መካከል ለውዝ እንደሚገኝበት ተናገረ። (ዘፍጥረት 43:11) በአንዲት ትንሽ ዘለላ ላይ ካሉ ለውዞች ጠቃሚ የሆኑ ብዙ ንጥረ ነገሮችን ማግኘት ይቻላል። ተማሪዎቹ በትምህርት ቤቱ ቆይታቸው ምሳሌያዊ የሆኑ በርካታ የለውዝ ፍሬዎችን መብላት ችለዋል። ከቀሰሟቸው ትምህርቶች መካከል በይሖዋ አምላክ ዝግጅቶች ረክቶ መኖርና አዲሱን የምድብ ቦታቸውን መውደድ ያለውን አስፈላጊነት በተመለከተ የተማሩት ትምህርት ይገኝበታል።
የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆነው ወንድም ማርክ ኑሜር የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ጥቅም በሚሰጥ ጥበብ የተሞላ እንደሆነ ገለጸ። (ኢዮብ 28:18) ከዚህ ጥበብ ጥቅም ለማግኘት ከፈለግን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ያነበብነውን ነገር በተግባር ማዋል አለብን። ተማሪዎቹ የሚስዮናዊነት አገልግሎታቸውን እንደሚጠብቁት ሆኖ ካላገኙት ሐዋርያው ጳውሎስን ማሰባቸው ሊጠቅማቸው ይችላል። ጳውሎስ፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመደቡት በትውልድ ቦታው ለዘጠኝ ዓመት አገልግሏል። ጳውሎስ “የተመረጠ ዕቃ” መሆኑን ሰበብ አድርጎ እሱ ደስ ባለው ቦታ ማገልገል እንደሚፈልግ ከመናገር ይልቅ በተመደበበት ቦታ ሁሉ በትጋት አገልግሏል። (የሐዋርያት ሥራ 9:15, 28-30) የይሖዋን ምርጫ መቀበል ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። የይሖዋን ምርጫ ሳያንገራግሩ ከተቀበሉት ሰዎች መካከል ዮናታን ይገኝበታል። ዮናታን፣ ይሖዋ ለንግሥና የመረጠው ዳዊትን እንደሆነ ሲገነዘብ እሱን በደስታ ከመደገፍ ወደኋላ አላለም።
“የአምላክ አገልጋዮች በድፍረት ይናገራሉ” የሚለው ክፍል ሲቀርብ ተማሪዎቹ በኮርሱ ወቅት በመስክ አገልግሎት ያገኟቸውን ተሞክሮዎች በሠርቶ ማሳያ መልክ አቀረቡ። አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማግኘት ችለው ነበር። ቀጣዩ ንግግር “የይሖዋ ድርጅት ያዘጋጃችኋል” በሚለው ርዕስ ላይ የተመሠረተ ሲሆን ለረጅም ዓመታት ሚስዮናዊ ሆነው ለቆዩ ሦስት ወንድሞች ቃለ ምልልስ ተደርጎላቸዋል። ሦስቱም ወንድሞች ከአምላክ ድርጅት ጋር መተባበር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ያገኙትን ሥልጠና ገልጸዋል።
‘ደስተኛ ሚስዮናውያን ሁኑ’
ቀጥሎም የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጌሪት ሎሽ “ደስተኛ ሚስዮናውያን ሁኑ” በሚል ርዕስ የፕሮግራሙን ዋነኛ ንግግር አቀረበ። ወንድም ሎሽ “አዝናኝ” እንደሆኑ ተደርገው የሚቆጠሩ ብዙ እንቅስቃሴዎች እውነተኛ ደስታ እንደማያስገኙ ተናገረ። (ምሳሌ 14:13፤ መክብብ 2:10, 11) የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ዘላቂ ደስታ ያስገኛል፤ ሆኖም የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ለምሳሌ የጊልያድ ኮርስ ከባድ ነበር፤ ይሁን እንጂ ከፍተኛ እርካታ አስገኝቷል።
እውነተኛ ክርስቲያኖች ደስተኛ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ በርካታ ነገሮች አሉ። ደስተኛ የሆነውን አምላክ ያመልካሉ። (መዝሙር 33:12፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:11) በአሁኑ ወቅት በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ እየኖሩ ነው፤ በቅርቡ ደግሞ ምድር ወደ ገነትነት እንደምትለወጥ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ተስፋ ተገንዝበዋል። የሕይወት ዓላማ ይሖዋን ማገልገልና እሱን ማወደስ እንደሆነ ተረድተዋል። ከዚህም በላይ ይሖዋና ኢየሱስ እንደሚወዷቸው ያውቃሉ።
ተናጋሪው “ባላችሁ ነገር ረክታችሁ የምትኖሩ ከሆነ ደስተኛ ሚስዮናውያን ትሆናላችሁ” በማለት አክሎ ተናግሯል። ለደስታ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው ሌላው ነገር ደግሞ ሰዎችን መውደድና በሌሎች መወደድ ነው። ስለዚህ ሌሎች ሰዎች የሚሠሩትን ስህተት ከማጋነን ይልቅ ችላ ብላችሁ እለፉ። ለሌሎች መልካም አድርጉ፣ ደካሞችን ደግፉ እንዲሁም ያሏችሁን ጥሩ ተሞክሮዎች ለሌሎች አካፍሉ። (መዝሙር 41:1, 2፤ የሐዋርያት ሥራ 20:35) አንድ ሰው በስብከቱ ሥራ ራሱን ማስጠመዱ ደስታ ያስገኝለታል።—ሉቃስ 11:28
ወንድም ሎሽ “ደስተኛ ሚስዮናውያን በመሆን ወደፊት ግፉ፤ በመጠኑ መዝናናት የሚያስፈልጋችሁ ቢሆንም በዋነኝነት ማተኮር ያለባችሁ ደስተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን በማወደሱና በርካታ ሰዎች ደስተኛ እንዲሆኑ በመርዳቱ ሥራ ላይ ነው” በማለት ንግግሩን ደምድሟል።
ወንድም አንቶኒ ሞሪስ ከተለያዩ አገሮች የተላኩ ሰላምታዎችን ካነበበ በኋላ ለተማሪዎቹ ዲፕሎማቸውን ሰጣቸው። ከዚያም የ126ኛው ክፍል ተወካይ ተማሪዎቹ ለበላይ አካሉ የጻፉትን ደብዳቤ አነበበ። ደብዳቤው ተማሪዎቹ በጊልያድ ትምህርት ቤት በመካፈላቸው የተሰማቸውን አድናቆት የሚገልጽ ነው።
የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር በንግግሩ መደምደሚያ ላይ፣ አካልን አንድ የሚያደርጉት ‘መገጣጠሚያዎችና ጅማቶች’ “ታማኝና ልባም ባሪያ” የይሖዋን ሕዝቦች ለመመገብና ለመምራት ከሚጠቀምባቸው መንገዶችና ዝግጅቶች ጋር እንደሚመሳሰሉ ተናግሯል። (ቆላስይስ 2:18, 19፤ ማቴዎስ 24:45) የጊልያድ ተመራቂዎች አምላክ ከሾማቸው ተወካዮቹ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚተባበሩ ከሆነ አገልግሎታቸውን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም ይችላሉ።—2 ጢሞቴዎስ 4:5
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ
ተማሪዎቹ የተውጣጡባቸው አገሮች ብዛት፦ 6
የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት፦ 22
የተማሪዎቹ ብዛት፦ 56
ባልና ሚስት፦ 28
አማካይ ዕድሜ፦ 32.8
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ፦ 17.9
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ፦ 13.5
ተማሪዎቹ የተመደቡባቸው አገሮች
ተማሪዎቹ የተመደቡባቸው አገሮች፦ ሆንዱራስ፣ ላይቤሪያ፣ ማዳጋስካር፣ ሞዛምቢክ፣ ሩማንያ፣ ሴራ ሊዮን፣ ቡልጋሪያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ቤኒን፣ ቦሊቪያ፣ ቶጎ፣ ኒካራጓ፣ ኡጋንዳ፣ ካሜሮን፣ ኬንያ፣ ኮስታ ሪካ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና፣ ጓቲማላ፣ ፓራጓይ፣ ፓናማ እና ፔሩ።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ126ኛው ክፍል ተመራቂዎች
ለእያንዳንዱ ረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።
(1) ካትሪን ክሪኮፍ፣ ክሪስቲን ኒከልዝ፣ ያሬሊ ጉስማን፣ ሃይዲ ኮይል፣ ኦንግሊ ቤከር፣ አንቶኔላ ዴ ሲሞኔ (2) ኤዝሃ ማንሳናሬስ፣ ኤሊስ ቡቬኤ፣ ጆዲን ፔደል፣ ሄዘል ማሶን፣ ጄርለን ብራስ (3) ጄኒ ሊ፣ አና ፎርቴ፣ ታንየ ቡሼ፣ አኒከ ማርሽ፣ ሶፊ ሌተን፣ መሼል ግለቨር (4) ሃሊ ካምባክ፣ ትዋና ጆንስ፣ ኤድሪአ ፌሬረ፣ ጃነስ ሞራሌስ፣ ስቴፋኒ ቺከስ፣ ቢአትሪክ ዴቨስ፣ ኤለና ዶርመነን (5) ባራየን ዶርመነን፣ ጄረሚ ኒከልዝ፣ ቲፈኒ ፓቾ፣ ሉቺአነ ቲትመስ፣ ኤሪክ ቡቬኤ፣ አንዲ ክሪኮፍ (6) ጋይ ሌተን፣ አንቶኒ ፓቾ፣ ቤተኒ ቫን ካምፔን፣ አርቱሮ ማንሳናሬስ፣ ኦተም ሪቫርድ፣ ዮንግ ሊ፣ ሉከስ ቲትመስ (7) ማርክ ቡሼ፣ ኬቨን ኮይል፣ ቼሰሪ ማርሽ፣ ጆሹዋ ጉስማን፣ ዊል ጆንስ፣ ጆኤል ካምባክ (8) አዳም ግለቨር፣ ጆርጅ ፌሬረ፣ ኤሊአት ማሶን፣ ዳንዬሌ ፎርቴ፣ ናታኒየል ዴቨስ፣ ኦስካር ቺከስ፣ ዮአን ሪቫርድ (9) ዳን ብራስ፣ ዳን ቫን ካምፔን፣ አቤል ሞራሌስ፤ ሚኬሌ ዴ ሲሞኔ፣ ማርኮ ቤከር፣ ድዌን ፔደል